የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ) የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታቸውን ዛሬ ምሽት 4፡00 ሰአት ለማድረግ አክራ ይገኛሉ፡፡ በኳታር አስተናጋጅነት ለሚካሄደው የ2022 ዓለም ዋንጫ ተሳታፊ ለመሆን የማጣሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉት ዋልያዎቹ ከቀናት በፊት ወደ ጋና ያመሩ ሲሆን፤ 15ሺ ተመልካቾችን የመያዝ አቅም ባለው ኬፕ ኮስት ስታዲየም ከጋና ብሄራዊ ቡድን ጋር (ጥቁር ከዋክብቱ) ጋር የሚፋለሙ ይሆናል፡፡
የዓለም አገራት በቀጣዩ ዓመት በሚካሄደው የእግር ኳሱ ትልቅ መድረክ ተካፋይ ለመሆን የሚያስችላቸውን የማጣሪያ ጨዋታዎች እያደረጉ ይገኛሉ፡፡ አፍሪካን ወክለው በመድረኩ የሚካፈሉ ብሄራዊ ቡድኖች የማጣሪያ ጨዋታዎች በሳምንቱ የተጀመሩ ሲሆን፤ በምድብ ስድስት (ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምቧቡዌ) ዛሬ ሁለት ጨዋታዎችን ያካሂዳሉ። በጨዋታው ኢትዮጵያ ከጋና ሲገናኙ፤ ደቡብ አፍሪካ እና ዚምቧቡዌም ይጫወታሉ፡፡
ምዕራብ አፍሪካዊቷ አገር ጋና ምስራቅ አፍሪካዊቷን ኢትዮጵያ በሜዳዋ ኬፕ ኮስት ስታዲየም ታስተናግዳለች። የጥቁር ከዋክብቱ አሰልጣኝ ቻርለስ አክኖር አስቀድመው ለተጫዋቾቻቸው ጥሪ ያደረጉ ሲሆን፤ አሁን 32 ተጫዋቾች በካምፕ እንደሚገኙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ በተለያዩ የአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ ተጫዋቾችም አገራቸው ለሚኖራት የማጣሪያ ጨዋታዎች ቡድኑን መቀላቀላቸው ታውቋል። ይሁን እንጂ ከእነዚህ መካከል የአርሰናሉ ተጫዋች ቶማስ ፓርቴ፣ የአያክሱ ሞሃመድ ኩዱስ እና በስሎቫኪያ ሊግ የሚጫወተው ቤንሰን አናንግ በጉዳት ምክንያት በዛሬው ጨዋታ ላይ አይሰለፉም፡፡
የጋና ብሄራዊ ቡድን በፊፋ የደረጃ ሰንጠረዥ 52ኛ ላይ የተቀመጠ ሲሆን፤ በአፍሪካ የወቅቱ 7ኛው ምርጥ ቡድን ነው፡፡ ይህም በአህጉር አቀፍ ደረጃ የተሻለ የእግር ኳስ ብቃት ካላቸው አገራት መካከል እንዲመደብ ያደርገዋል፡፡ የቡድኑ ተጫዋቾች የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግን ጨምሮ በአውሮፓ ሊጎች የሚጫወቱ መሆናቸው ከቡድን ከጥራት አንጻር የተሻለ የአሸናፊነት ግምት አሰጥቷቸዋል፡፡ በጥቁር ከዋክብቱ ስብስብ ጥቂት ቁልፍ ተጫዋቾች ያልተካተቱ ቢሆንም የመጀመሪያውን ጨዋታ በሜዳው እንደማስተናገዳቸው የፈለጉትን ውጤት ከሜዳ ይዘው ለመውጣት ከባድ እንደማይሆንባቸው ተገምቷል፡፡
በአሰልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመሩት ዋሊያዎቹ በበኩላቸው በተሻለ መነሳሳትና የአሸናፊነት ስሜት ወደ ጋና ተጉዘዋል፡፡ በቡድኑ ውስጥ ተካተው ወደ ጋና የተጓዙት 23 ተጫዋቾችም፣ በግብ ጠባቂዎች በኩል ተክለማርያም ሻንቆ፣ ጀማል ጣሰው እና ፋሲል ገብረሚካኤል ናቸው፡፡ ተከላካዮች ደግሞ አስራት ቱንጆ፣ ሱሌማን ሀሚድ፣ ረመዳን የሱፍ፣ ደስታ ዮሀንስ፣ ያሬድ ባዬ፣ አስቻለው ታመነ፣ ምኞት ደበበ እንዲሁም መናፍ አወል ናቸው፡፡ አማካዮች አማኑኤል ዮሀንስ፣ ለግብጽ ክለብ የሚጫወተው ሽመልስ በቀለ፣ ይሁን እንደሻው፣ ጋቶች ፓኖም፣ መሱድ መሀመድ፣ ታፈሰ ሰለሞን እና ሽመክት ጉግሳ ናቸው፡፡ አጥቂዎች አቡበከር ናስር፣ አማኑኤል ገ/ሚካኤል፣ ጌታነህ ከበደ፣ አቤል ያለው እና ቸርነት ጉግሳ መሆናቸው ታውቋል፡፡ ሁሉም ተጫዋቾች በመልካም ጤንነት ላይ የሚገኙና ልምምዳቸውን በማድረግ ላይ የሚገኙ መሆኑንም ፌዴሬሽኑ በድረገጹ አስነብቧል፡፡
28 ተጫዋቾችን በማሰባሰብ ከሳምንታት በፊት ወደ ልምምድ የገቡት የዋልያዎቹ አለቃ ውበቱ አባተ በአዳማ አበበ ቢቂላ ስታዲየም እንዲሁም በአዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ሜዳዎች ዝግጅት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ቡድኑ ከአካል ብቃት ልምምድ ባሻገር ጨዋታዎችን በተንቀሳቃሽ ምስል በመመልከትና ውይይት በማድረግም ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡ ጨዋታውን በሚመለከት ጋዜጣዊ መግለጫ በተሰጠበት ወቅትም የቡድኑ ዋና አሰልጣኝ ውበቱ አባተ የቡድኑ ዝግጅት ትኩረት ያደረገው በአካል ብቃት፣ በስነልቦና እና ታክቲክ መሆኑን ገልጸዋል።
ይህ ወቅት የአገር ውስጥ ውድድሮች የማይካሄዱበት በመሆኑ ምክንያት ለእነዚህ ጨዋታዎች አስፈላጊ የሆኑ ዝግጅቶችን በማድረግ ላይ እንደነበሩ የጠቀሱት አሰልጣኝ ውበቱ፤ በተለይ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ከሴራሊዮን እና ከዩጋንዳ ብሄራዊ ቡድኖች ጋር ማድረጋቸው ስብስባቸውን በደንብ ለማየት እንዳስቻላቸው አስረድተዋል። ቡድኑ ለዛሬው ጨዋታው እንዲረዳው ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎችን ሲያደርግ ከሴራሊዮን ብሄራዊ ቡድን ጋር በተገናኘበት ጨዋታ ያለ ምንም ግብ ተለያይቷል፡፡ ቀጣዩን የወዳጅነት ጨዋታ ከዩጋንዳ አቻው ጋር አድርጎም፤ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፍ አቋሙን መገምገም ችሏል፡፡
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለአምስት ጊዜያት የተገናኙ ሲሆን ጥቋቁር ከዋክብቱ የበላይነቱን ይዘዋል፡፡ ለአራት ጊዜያት ሽንፈትን የቀመሱት ዋሊያዎቹ በበኩላቸው አንድ ጊዜ አሸናፊ ለመሆን ችለዋል፡፡ ዋሊያዎቹ ወደ አዲስ አበባ የመመለስ ጉዟቸውን ነገ የሚያደርጉ መሆኑን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ድረገጽ የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ቡድኑ ቀጣዩን የማጣሪያ ጨዋታም ከቀናት በኋላ ጳጉሜን 3/2013 ዓ.ም በባህር ዳር ኢንተርናሽናል ስታዲየም ከዚምቧቡዌ ብሄራዊ ጋር የሚያደርግ ይሆናል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28/2013