አዳማ:- የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽንባለፉት ስድስት ወራት ከፕሮጀክት ማኔጅመንት፣ ከኮንስትራክሽን መሳርያዎችና ማሽነሪዎች እንዲሁም ሌሎች አገልግሎቶች ከ600 ሚሊየን ብር በላይ ገቢ ማግኘቱ ተገለፀ፡፡
ኮርፖሬሽኑ የ2011 በጀት አመት የመጀመርያ ስድስት ወራት አፈጻፀሙን በአዳማ ከተማ ካኔት ሆቴል በገመገመበት ወቅት ዋና ስራ አስፈፃሚው ኢንጂነር ሀይለመስቀል ተፈራ እንዳሉት ኮርፖሬሽኑ በግማሽ አመት አፈፃፀሙ ከፕሮጀክት ማኔጅመንት ማእከል 69.6 ሚሊዮን ብር ለማስከባት አቅዶ ከ90.8 ሚሊዮን በላይ፣ ከኮንስትራክሽን መሳሪያዎች እና ማሺነሪዎች ማኔጅመንት እንዲሁም ለውጭ ደንበኞች መሳሪያ በማከራየት 496.48 ሚሊዮን፣ ለውጭ ደንበኞች ከተሰጠ የጥገና አገልግሎት 2.46 ሚሊዮን ብር፤ የካይዘን አሰራርን ተግባራዊ በማድረግ ከ33.9 ሚሊዮን ብር በላይ በመስገባት ከእቅድ በላይ ውጤት ያስመዘገበ ሲሆን ለ1930 ዜጎችም የስራ እድል አስገኝቷል።
ዋና ስራ አስፈፃሚው እንደገለፁት ኮርፖሬሽኑ ይህን ያከናውን እንጂ በርካታ ውስንነቶችና ክፍተቶች ተስተውለውበታል። በተለያዩ ውጫዊና ውስጣዊ ችግሮች ምክንያትም እቅዱን ሙሉ ለሙሉ ተግባራዊ ማድረግ አልቻለም ያሉት ሀላፊው እነዚህ ክፍተቶች ተሞልተው ውጤታማ እንደሚሆን ያላቸውን እምነት ገልፃዋል።
ኮርፖሬሽኑ በአጠቃላይ በስድስት ወሩ ያሳየው አፈጻፀም አነስተኛ መሆኑንም የአፈጻፀም ግምገማ ሪፖርቱ ያመላክታል፡፡ በዚህም መሰረት በስድስት ወራት ውስጥ ከ4.26 ቢሊዮን ብር በላይ ለመሰብሰብ ታቅዶ 1.78 ቢሊዮን፣ ከ934.63 ሚሊዮን ብር ያልተጣራ ትርፍ ለማስገባት ታቅዶ 469.58 ሚሊዮን፤ 75.72 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመገንባት አቅዶ 40.56 ኪሎ ሜትር፣ 5ሺህ 699.73 ኪሎ ሜትር መንገድ ለመጠገን አቅዶ 2ሺህ 170.99 ኪሎ ሜትር መፈጸሙንና የትራንስፖርት መሰረተ-ልማት አፈፃፀም 38.35 በመቶ፤ የውሀ መሰረተ-ልማት ዘርፍ አፈፃፀም 30.18 በመቶ፣ የህንፃ ኮንስትራክሽን ዘርፍ 69.56 በመቶ፣ የህንፃ ግንባታ 23.80 በመቶ መሆኑንም አመልክቷል።
ለእቅዱ አፈፃፀም ማነስ የተለያዩ ችግሮች የተዘረዘሩ ሲሆን የግብአት አቅርቦት እጥረት፣ የዲዛይን በወቅቱ አለመቅረብ፣ የፕሮጀክት ባለቤቶች በወቅቱ ውል አለመፈረም፣ የገንዘሰብ እጥረት፣ ከውሀ ስራዎች ጋር በተያያዘ የውሀ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር ያለበትን እዳ አለመክፈል፣ የወሰን ማስከበር ችግር፣ የካሳ ክፍያ አለመፈፀም ዋና ዋናዎቹ መሆናቸውን ከተሰራጨው ሰነድ መረዳት ተችሏል።
ለውጡ በየደረጃው በሙሉ እምነትና ፅናት ባለመያዙ ከማእከል እስከ ፕሮጀክት አፈፃፀሙ ድረስ ተግዳሮቶች የሚስተዋሉበት ነው የሚሉት ዋና ስራ አስፈፃሚው መድረኩ ችግሮችን ለይቶና በያንዳንዱ ጉዳይ ላይ በጥልቀት ተወያይቶ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን እንደሚያስቀምጥና ኮርፖሬሽኑም በሚቀጥለው የእቅድ አፈፃፀም ሁሉም ዘርፎች በመረባረበ የአመቱን እቅድ አፈፃፀም ሙሉ ለሙሉ እንደሚያሳካ ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2011
ግርማ መንግሥቴ