ኢትዮጵያ የራሷን ሉኣላዊነት ጠብቃ ከመኖሯም ባሻገር ለሌሎች ጭቁን ህዝቦችም የነጻነት ተምሳሌት ሆና የዘለቀች ሀገር ነች። ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሀገራት በቅኝ አገዛዝ ጨለማ ውስጥ በነበሩበት ዘመን ጭቆናንና ኢፍትሃዊነትን ታግላ ያሸነፈችና የነጻነት ተምሳሌት የሆነች ብቸኛዋ አፍሪካዊ ቀንዲል ናት።
ኢትዮጵያ ኢፍትሃዊነትን ከታገለችባቸውና ታግላም በአሸናፊነት ከተወጣችባቸው መድረኮች የአድዋ ድል አንዱና ዋነኛው ነው። የአድዋ ድል በጥቁር ህዝቦች ታሪክ ውስጥ ኢፍትሃዊነትን ታግሎ ማሸነፍ እንደሚቻልም ምሳሌ የሆነ የተጋድሎ ታሪክ ነው። የዛሬ 124 ዓመት ኢትዮጵያውያን በአልበገርም ባይነት ያሳዩት ተጋድሎም ጥቁር ህዝቦች ጭቆናንና ኢፍትሃዊነትን ታግለው ማሸነፍ እንደሚችሉ ህያው ምስክር ሆኖ የቆመ ሀውልት ከመሆኑም ባሻገር በአራቱም የዓለም አቅጣጫ የሚገኙ ህዝቦችም ለጭቆና እንዳይንበረከኩ የቃል ኪዳን ሰነድ ሆኖ ያገለገለና እያገለገለም የሚገኝ ነው። የአድዋ ድል የፓን አፍሪካኒዝምን አስተሳሰብ እንዲወለድ በማድረግ አፍሪካውያን ለነጻነታቸው በጋራ እንዲታገሉ መሰረት የጣለ ነው።
ከአንድ መቶ ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው የፓንአፍሪካኒዝም ጽንሰ ሃሳብ፣ በአፍሪካውያን መካከል የሚቀሰቀሱ የእርስ በርስ ግጭቶችን፣ የአስተዳደር ችግሮችንና የማንነት ቀውሶችን ለመፍታት እንደ መሣሪያ ለመጠቀም ያለመ ነው። ይህንን ሃሳብ የበለጠ ለማጠናከርና እየተዘነጋ የሚመስለውን የፓን አፍሪካኒዝምን ንቅናቄ መሬት እንዲረግጥ ለማስቻል የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2063 ቀርጿል።
አጀንዳ 2063 የፓን አፍሪካኒዝም ማጠናከርያ መድረክ ሲሆን ቀጠናዊ ትስስርን በማጠናከር አፍሪካ ሀገሮች የሚገጥሟቸውን ችግሮች በጋራ ታግለው እንዲያሸንፉ ትኩረት አድርጎ የሚሰራ መድረክ ነው። ፓን አፍሪካኒዝምም ሆነ አጀንዳ 2063 ለአፍሪካውያን በታሰበው መልኩ ውጤት እንዲያመጡና የአፍሪካ ሀገራትም መርሃቸው እንዲያደርጓቸው ኢትዮጵያ ከጥንስሱ ጀምሮ ስትዋደቅ ቆይታለች። ዛሬም በግንባር ቀደምትነት በመዋደቅ ላይ ነች።
አፍሪካ ከምዕራባውያን ጥገኝነት እንድትላቀቅና የራሷ ነፃ የሆነ አህጉራዊ ርዕዮተ ዓለምና የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንድትከተል ቀደምት አፍሪካዊ አባቶች የተሟገቱ ቢሆንም ዛሬ የእነዚህን ፓን አፍሪካኒስት አባቶች ተጋድሎ የሚያረክስና ከ1960ዎቹ በፊት ወደ ነበረው የቅኝ ተገዢነት አስተሳሰብ የሚመልስ ተግባር በምዕራባውያን እየተቀነቀነ ነው። በትግል የተገኘውን ነጻነት በሀገራት የውስጥ ጉዳይ እጃቸውን በማስገባት የተሸነፈውን የቅኝ አገዛዝ አስተሳሰብና ድርጊት ዳግም በአፍሪካ ላይ ለመጫን ጥረት እያደረጉ ነው። ለዚህ አንዱ ማሳያ ደግሞ በኢትዮጵያ ላይ እያደረጉት ያለው ጫናና ጣልቃ ገብነት ነው።
ለ27 ዓመታት ኢትዮጵያን በጨካኝ መዳፉ ውስጥ አስገብቶ አረመኔያዊ ድርጊቱን ሲፈጽምና የተለያዩ ምዝበራዎችን ሲያካሂድ የኖረውና በህዝብ ተቃውሞ ስልጣኑን ያጣውን አሸባሪውን ህወሓት ከህዝብ ፍላጎት ውጪ ወደ ስልጣን ለመመለስ የዴሞክራሲና የሰብአዊ መብት ጠበቃ ነን ባይ አንዳንድ አገራት የተለያዩ ደባዎች በኢትዮጵያ ላይ በመፈጸም ላይ ይገኛሉ። ስልጣን ላይ በቆየባቸው 27 ዓመታት የኢትዮጵያን ሉዓላዊን በሚጻረር መልኩ የእነዚህኑ አገራት ፍላጎት ሲያስፈጽምና በእጅ አዙር የሀገሪቱ ሀብትን ሲያስመዘብር የኖረውን አሸባሪ ቡድን ከገባበት መቃብር ውስጥ ለማውጣት ብዙ ጥረት ተደርጓል።
እነዚሁ አገራትና በእነሱ የሚመሩት የእርዳታ ድርጅቶችና ሚዲያዎች በተቀናጀ መልኩ አሸባሪውን ህውሓትን በመደገፍና ኢትዮጵያ መንግስትን ባልሰራው ስራ በመውቀስ የኢትዮጵያን የህዝቦቿን ስም በማጠልሸት ላይ ተጠምደው ቆይተዋል። አሸባሪው ቡድን የእርዳታ እህል ወደ ትግራይ እንዳይደርስ የሚፈጥረውን መሰናክል እያዩ እንዳላዩ በመሆንና ይባሱንም ችግሩ ወደ ኢትዮጵያ መንግስት በማላከክ በሰብአዊ ጥሰት ለመክሰስ ዳር ዳር ሲሉ ታይተዋል። አሸባሪ ቡድኑ የትግራይ ህዝብን በሰብአዊ ጋሻነት በመያዝ የሚፈጽማቸውን ግፍና በደሎች ባላየና ባልሰማ በማለፍ ቡድኑን የነጻነት ታጋይ ሲያደርጉት ቆይተዋል። ይባስ ብሎም የአሸባሪ ቡድኑን አስጸያፊ ተግባራት ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በመስጠት በጸጥታው ምክር ቤት በተደጋጋሚ ክስ ቢመሰርቱም የያዙት ውሸት ጠልፎ ጥሏቸዋል።
ገና ከጅምሩ የለውጥ መንግስቱ በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራና በሉዓላዊነቱ ላይ የማይደራደር መሆኑንም በመረዳታቸው እነዚሁ ጣልቃ ገብ አገራት በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ፊታቸውን አዙረዋል። ይባሱኑም 50 ሚሊዮን የሚጠጋ ህዝብ ወጥቶ የመረጠውን መንግስት ዕውቅና ለመስጠት ሲተናነቃቸው ታይቷል።
እነዚህ አገራት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ እጃቸውን አስገብተው ኢትዮጵያን ለማተራመስ ከሚያደርጉት እኩይ ሴራ ጎን ለጎን በራሷ አንጡራ ህብት የምትሰራውን ህዳሴ ግድብ ለማደናቀፍ ብዙ ርቀት ተጉዘዋል። ለመጀመሪያ ጊዜም የልማትን ጉዳይ በጸጥታው ምክር ቤት እንዲታይ በማድረግ ሀገሪቱን ለማንበርከክ ብዙ ርቅት ተጉዘዋል። ተላኪዎቻቸውን ግብጽና ሱዳንን ጋሻ በማድረግ ተጽእኗቸውን ለማስፋት ሞክረዋል። ሆኖም በሉዓላዊነቱ የማይደራደረው የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በየመድረኩ አሳፍሮ መልሷቸዋል።
ስለዚህም ኢትዮጵያ እያደረገችው ያለው ትግል ለራሷ ብቻ ሳይሆን ነጻነትን ለሚሹ የአፍሪካ ሀገራት ጭምር መሆኑ ታውቆ ስለፓአፍሪካኒዝም ይመለከታናል የሚሉና በሰው ልጅ ነጻነትና እኩልነት የሚያምኑ ሁሉ ሊቀላቀሉት የሚገባ ትግል ነው!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 28/2013