አዲስ አበባ፡- በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሚገኙት የሥነዜጋና የሥነምግባር ክበባት ተማሪዎች በሥነምግባር የታነፁ የማድረግ ሚናቸውን እየተወጡ አለመሆኑ ተገለፀ፡፡
የፌዴራል የሥነምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሥነዜጋና የሥነምግባር ክበባት በተመለከተ ያደረገውን ዳሰሳዊ ጥናት ሰሞኑን ለርዕሳነ መምህራንና መምህራን አቅርቦ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
በውይይቱ ላይ የፌዴራል የሥነምግባና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አየልኝ ሙሉዓለም እንደተናገሩት፣ ህፃናትና ወጣቶች በሥነምግባር የታነፁ እንዲሆኑ ትምህርት ቤቶች ዋነኛ ስፍራዎች ሲሆኑ፣ የሥነ ዜጋ የሥነምግባር ክበባት ደግሞ ለዚህ ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው፡፡
በአገሪቱ በወጣቱ አካባቢ የሥነምግባር ጉድለቶች እየተስተዋሉ እንደሚገኙ የጠቀሱት አቶ አየልኝ፤ ለዚህም በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙት የሥነዜጋና የሥነምግባር ክበባት በተጠናከረ መንገድ ሥራቸውን ባለማከናወናቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡
በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙት የሥነዜጋና የሥነምግባር ክበባት በባህሪ ግንባታ ላይ ተፅዕኖ ከማሳረፍ ባሻገር የአገር ግንባታ ላይ ከፍተኛ ሚና እንዳላቸውም አስረድተዋል፡፡ በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ የሥነዜጋና የሥነምግባር ክበባትን ማጠናከር ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራት እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡
የአዲስ አበባ የሥነምግባርና የፀረ ሙስና ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ ከፍያለ፤ «በመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሥነዜጋና ሥነምግባር ክበባት ያሉበት ደረጃ» የሚል ዳሰሳዊ ጥናት ያቀረቡ ሲሆን፣ በዳሰሳቸውም በመንግሥት ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሥነዜጋና የሥነምግባር ክበባት ቢኖሩም ተማሪውን በሥነምግባር ማነፅ ላይ ችግሮች እንዳሉበት አካተዋል፡፡
ጥናት በተደረገባቸው ሦስት ክፍለ ከተሞች ማለትም አራዳ፣ቂርቆስና ቦሌ ክፍለከተሞች ውስጥ የሚገኙ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የሥነዜጋና የሥነምግባር ክበባት እንደሚገኙ በመጥቀስ፤ ክበባቱ ግን በተማሪዎች ሥነምግባር ለውጥ ላይ ተፅዕኖ ማሳደር እንዳልቻሉ በጥናት መታየቱን ተናግረዋል፡፡
የሥነዜጋና የሥነምግባር ትምህርት መምህራን ክበባቱን በማጠናከር በኩል ያሉባቸውን ክፍተቶች በመሙላት ረገድ ጥረት እንደሚፈልግም ገልፀዋል፡፡ በቀጣይ የሥነዜጋና የሥነምግባር ክበባትን በማጠናከር ተማሪዎች ትምህርት ቤት ሲወጡ በሥነምግባር የታነፁ እንዲሆኑ ለማድረግ የጋራ ሥራ እንደሚያስፈልግም አቶ ተስፋዬ አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2011
መርድ ክፍሉ