በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ውጤት ያስመዘገቡ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ከትናንት በስቲያ ምሽት በሸራተን አዲስ እውቅናና ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። መርሃግብሩን ያዘጋጀውና ሽልማቱን ያበረከተው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውጤት ላስመዘገቡ አትሌቶች ከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት ቢያበረክትም በኦሊምፒኩ ተሳትፈው ውጤት ያልቀናቸው ነገር ግን የዲፕሎማ ውጤት ከማስመዝገብ ጀምሮ በተለያዩ ውድድሮች ትልቅ ተጋድሎ አድርገው ታሪክ የሰሩ አትሌቶችን ዘንግቷል። በወርልድ ቴኳንዶ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈውና የዲፕሎማ ውጤት ያስመዘገበው እንደ ሰለሞን ቱፋ የመሳሰሉ አትሌቶች እንዲሁም በተለያዩ ርቀቶች ተሳትፈው አዲስ ታሪክና የዲፕሎማ ውጤት ያስመዘገቡ ኮከቦች በይፋ ሊበረታቱ ሲገባቸው በሽልማትና በእውቅና መርሃግብሩ በዝምታ ታልፈዋል። የአለማችን ታላቁ የስፖርት መድረክ የሆነው ኦሊምፒክ ከውጤት ባሻገር ተሳትፎ በራሱ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው መሆኑን ደጋግሞ የሚናገረው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሽልማትና እውቅና ሲሆን ቃሉን ማጠፉ ያልተጠበቀ ሆኗል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በኦሊምፒኩ ዘገባ መገናኛ ብዙሃንን መርጦ እንደተጓዘው ሁሉ በሽልማትና እውቅና መርሃግብሩም የተወሰኑ የተመረጡ መገናኛ ብዙሃን ብቻ በደብዳቤ ጠርቷል። እንደ ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ያሉ ታላላቅና አንጋፋ የሕዝብ መገናኛ ብዙሃን ኦሊምፒኩን ከቅድመ ውድድር ጀምሮ በተለያዩ ቋንቋዎችና የሕትመት ውጤቶች በስፋት ሲዘግቡ የቆዩ ቢሆንም በሽልማት መርሃግብሩ ሳይጋበዙ ቀርተዋል።
የሽልማትና የእውቅና መርሃግብሩ ብዙዎችን ቅር ያሰኘ የተለያየ ስህተት የተፈፀመበት ቢሆንም ውጤት ላስመዘገቡ አትሌቶች የተበረከተው የገንዘብ ሽልማት ከፍተኛና የአትሌቶቹን ልፋት የሚመጥን ነበር። በዚህም መሰረት በኦሊምፒኩ ብቸኛውን የወርቅ ሜዳሊያ በወንዶች አስር ሺ ሜትር ያስመዘገበው አትሌት ሰለሞን ባረጋ ሁለት ነጥብ ሁለት ሚሊየን ብር ሽልማት ተበርክቶለታል። በተመሳሳይ ብቸኛውን የብር ሜዳሊያ በሶስት ሺ ሜትር መሰናክል ያስመዘገበው አትሌት ለሜቻ ግርማ የአንድ ነጥብ አምስት ሚሊየን ብር ሽልማት ተበርክቶለታል። በአምስትና አስር ሺ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ያስመዘገቡት አትሌት ለተሰንበት ግደይና ጉዳፍ ፀጋይ እያንዳንዳቸው የአንድ ነጥብ ሁለት መቶ ሃያ አምስት ሺ ብር ተሸላሚ ሆነዋል።
የወርቅ ሜዳሊያ እንዲመዘገብ ምክንያት የሆኑ አሰልጣኞች አምስት መቶ ሺ ብር፣ ለብር ሜዳሊያ አራት መቶ ሃምሳ ሺ ብር፣ ለነሐስ ሜዳሊያ አራት መቶ ሃያ አምስት ሺ ብር ተበርክቶላቸዋል። በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ በእግር ኳስ ዳኝነት የተሳተፈው ኢንተርናሽናል ዋና ዳኛ ባምላክ ተሰማ የሽልማት ፕሮግራሙ አካል በመሆን የሃምሳ ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶለታል። ለመጀመሪያው የኦሊምፒክ አንጋፋ ብስክሌተኛ ገረመው ደንቦባም መቶ ሺ ብር ተበርክቷል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ካበረከተው የገንዘብ ሽልማት በተጨማሪ ሚድሮክ ኢትዮጵያ ለውጤታማ አትሌቶችና አሰልጣኞች የተለያየ መጠን ያለው የገንዘብ ሽልማት አበርክቷል። በዚህም ወርቅ ያስመዘገበው አትሌት ሰለሞን ባረጋ አንድ ሚሊየን ብር፣ ብር ያስመዘገበው ለሜቻ ግርማ ስድስት መቶ ሺ ብር፣ ነሐስ ያስመዘገቡት ጉዳፍ ፀጋይና ለተሰንበት ግደይ እያንዳዳቸው ሶስት መቶ ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል። ሚድሮክ ኢትዮጵያ ለዋና አሰልጣኞች ሃምሳ ሺ ብርና ለምክትል አሰልጣኞች ሃያ አምስት ሺ ብር ማበርከቱም ታውቋል።
‹‹በቶኪዮ ኦሊምፒክ በምንፈልገው ልክ ውጤቱ ባይመጣም የአትሌት ሰለሞን ባረጋ ወርቅ፣ የአትሌት ለሜቻ ግርማ ብርና የአትሌት ጉዳፍ ጸጋይና የአትሌት ለተሰንበት ግደይ ነሀስ ባይኖር ዛሬ ባልተሰበሰብን ነበር›› በማለት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት በደገፈው ልክና አቅም የተጠበቀውን ውጤት ባለመመዝገቡ ህዝብን ይቅርታ የሚጠይቁት በተሰበረ ልብ እንደሆነም ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል:: ‹‹የተመዘገበው ውጤት ህዝባችን በጠበቀው ልክ መንግስት በደከመው ልክ ባለመሆኑ ብናዝንም በቶኪዮ 2020 ከስረናል ብለን ግን አናምንም›› ሲሉም አክለዋል።
ለተመዘገበው ድልና ለተገኘው ድጋፍ የሚድሮክ ኢትዮጵያ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ጀማል አህመድ፣ ሼህ መሃመድ አሊ አላሙዲንና በርካታ ባለድርሻ አካላትን ያመሰገኑት ፕሬዚዳንቱ፤ ከዚህ ቀደም በዚህ ደረጃ ኦሊምፒክን የደገፈና ያገዘ መንግስት እንደሌለ ተናግረዋል። በተለይ ለስምንት ተከታታይ ወራት ልምምድ ሲሰራ ‹‹ለህዝባችን የምንሰስተው ነገር የለም›› በሚል ሙሉ ድጋፍ ሰጥተዋል ያሏቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድን አመስግነዋል።
የኦሊምፒክ ልኡካን ቡድኑ በቦሌ ኤርፖርት ደብዛዛ አቀባበል ላይ የተከፉት ውጤታማ አትሌቶች እንዳልተረሱና ጀግንነታቸው የሚታወስ መሆኑን ለማሳየት የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንቱና የቀድሞ የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ርስቱ ይርዳው እውቅናና ለሰጡት ሽልማትም ምስጋና ተችሯቸዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 27/2013