አዲስ አበባ፡- የላብራቶሪ ማሽኖችንና ኬሚካሎቻቸውን ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት የተደረገው አዲስ የግዢ ስምምነት በሆስፒታሎች ይታይ የነበረውን የተቆራረጠ የላቦራቶሪ አገልግሎት በመፍታት የተሻለ አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል የመድኃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
የኤጀንሲው የህዝብ ግንኙነትና ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር ወይዘሮ አድናን በሬ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለፁት፣ ቀደም ሲል ወደ ሀገር ውስጥ ሲገቡ የነበሩ የላቦራቶሪ ማሽኖች የተለያየ ብራንድ ያላቸውና ኬሚካሎቻቸውም የየራሳቸውን ብራንድ የሚፈልጉ ነበሩ፡፡
የላብራቶሪ ማሽኖቹን ለመግዛት ጨረታዎች ሲወጡ የማሽኖቹ አቅራቢዎች ስለሚቀያየሩና የማሽኖቹ ኬሚካሎች አቅርቦት ስለሚቆራረጥ የላቦራቶሪ አገልግሎቶችን በሆስፒታሎች በሚፈለገው ልክ መስጠት እንደማይቻል ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
አብዛኛዎቹ የላቦራቶሪ ኬሚካሎች የመጠቀሚያ ጊዜ አጭር መሆኑን ገልጸው፣ የግዢ ስርዓቱም የተጓተተ መሆኑም ለላቦራቶሪ አገልግሎት አሰጣጡ ተጨማሪ እንቅፋት ሆኖ መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሯ ገለፃ፤ የላቦራቶሪ አገልግሎት መቆራረጥን በዘላቂነት ለመፍታት በፍሬም ዎርክ አግሪመንት /framework agreement/ ከሦስት የአውሮፓና የአሜሪካ ኩባንያዎች ጋር የላብራቶሪ ማሽን ግዢ ስምምነት ተደርጓል፡፡ ለሦስት ዓመት በሚቆየው ስምምነት ኩባንያዎቹ የላብራቶሪ ማሽኖችን በነፃ ሲያቀርቡ ኤጀንሲው ደግሞ ለኬሚካሎቹ ግዢ ክፍያ እንደሚፈፅም ገልጸዋል፡፡ይህም ከላብራቶሪ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የሚከሰቱ ችግሮችን በዘላቂነት ይፈታል ተብሎ ይታሰባል ብለዋል፡፡
የላብራቶሪ ማሳሪያዎቹ በነፃ የሚገቡ ከመሆናቸው አኳያ ቀደም ሲል ለማሽኖቹ የሚወጣውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ወጪ እንደሚቀንስ የጠቀሱት ዳይሬክተሯ፤ በተለይም የኩባንያዎቹ ውስን መሆን ለላብራቶሪ ማሽኖቹ የሚያስፈልጉ ኬሚካሎችን ሳይቆራረጥ ለማቅረብ እንደሚያስችል ገልጸዋል፡፡ ለኬሚካል ግዢ የሚያስፈልገውን ወጪም በእጅጉ እንደሚቀነስ ተናግረው፣ የላብራቶሪ ማሽኖቹ ሲበላሹ የጥገና ስራዎችን የሚያከናውኑት እነዚሁ ኩባንያዎች መሆናቸውም ለጥገና ይወጣ የነበረውን ወጪ ለመቀነስ እንደሚያስችል አስታውቀዋል፡፡
በዚህ የግዢ ስምምነት መሰረት ለተለያዩ የደም ምርመራዎች የሚያገለግሉ መሳሪያዎች / hematology instrument/፣ የስኳር ህመም መመርመሪያ መሳሪያዎች /glucose meteres/ እና ልዩ ልዩ የኬሚስትሪ ማሽኖች /Chemistry Machines/ ወደ ሀገር ውስጥ እንደሚገቡ ዳይሬክተሯ አመልክተው፣ማሽኖቹ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች በሚገኙ ሆስፒታሎች ውስጥ አገልግሎት እንደሚሰጡም ጠቁመዋል፡፡
አዲስ ዘመን የካቲት 18/2011
አስናቀ ፀጋዬ