የአሸባሪው ህወሓት መሪዎች ለረጅም ዓመታት በስርቆት፣ በሌብነትና በዝርፍያ የኖሩበት ዘመን በማብቃቱ አገር ለማፍረስ ትልልቅና በክፋት የተሞሉ ሴራዎችን ሲፈጽሙና ሲያስፈጽሙ ኖረዋል። ሲያደርጉ የነበረው አፍራሽ እንቅስቃሴ አልበቃ ብሏቸው አገሩን ከጠላት በመጠበቅ ላይ የነበረውን የአገር መከላከያ ከጀርባው አጥቅተው በተወሰዳባቸው የህግ ማስከበር ዘመቻ ከመቃብር ሊገቡ ግድ ብሏቸዋል። ይሁንና ለዘመናት በሰሩት ግፍ ዘመናቸው ማብቃቱ ስላልተገለጸላቸው አፈር ልሰው ለመነሳት በማሰብ በዓለም ታሪክ የክፋት ጥግ የሆነውን የናዚ ጀርመንን መሰሪ አካሄድና አሰራር በመከተል ለተግባራዊነቱ ከምን ጊዜ በበለጠ እንቅልፍ አጥተው ተግተው እየሰሩ ይገኛሉ።
ናዚ በጀርመን የፖለቲካ የበላይነቱን ለማረጋገጥ በጀርመናውያን ዘንድ የአይሁድን ጠላትነት እንዳስተጋባ ሁሉ ያለ ጠላት መኖር የማይችሉት የአሸባሪው ህወሓት መሪዎችም በተመሳሳይ በዋናነት የአማራን ህዝብ በመቀጠል የፌዴራል መንግስትንና ኤርትራን በጥምር ጠላትነት ፈርጀው የትግራይ ህዝብ የመከበብና የመገፋት ስሜት እንዲሰማው በማድረግ ለእኩይ ዓላማቸው ለማሰለፍ እንቅልፍ አጥተው እየባዘኑ ነው።
አሸባሪው ህወሓት የሚጠላትን ሀገር ‘’ኢትዮጵያን’’ ለ27 ዓመታት በኢፍትሃዊነት፣ በዘረፋና ግፍ ሲገዛ ከኖረ በኋላ በመላ ኢትዮጵያውያን ወድ መስዋዕትነት ከስልጣኑ ተባሮ በመቀሌ እንዲመሽግ ተገዷል። ቆሞ ቀሩና ካለፈው ስህተቱ የማይማረው ግፈኛው ህወሓት መቀሌ ከመሸገ በኋላም አሻፈረኝ በማለት የስልጣን ጥማቱን ለማርካት ሀገርን በመክዳት ባልተጠበቀ ሁኔታ በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ አስነዋሪ ጥቃት በመፈፀም በበርካታ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ላይ አሰቃቂ እና ኢ-ሰብዓዊ ሁኔታ የጅምላ ግድያ ፈጽሟል።
በከፍተኛ መስዋዕትነት አገራቸውን በታማኝነት ያገለግሉ የነበሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ከጀርባ ወግቶም የእናት ጡት ነካሽነቱን አረጋግጧል። በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ከፈጸመው ጥቃት ባለፈም በማይካድራ፣ ሁመራ፣ አጋምሳ ወዘተ ንጹሃንን በገፍ ጨፈጭፏል፤ አቃጥሏል፣ አፈናቅሏል፤ ሀብት ንብረታቸውን አውድሞ ለስቃይ ዳርጓል፡፡
የሽብር ቡድኑ ዋነኛ ዓላማ ኢትጵያውያንን በመከፋፈል አገር ማፍረስና በህዝብ ላይ የጥላቻ ሂሳብ ማወራረድ ነው። ይሄን ሃሳቡን በተግባር ላይ እያዋለው እንደሚገኝም በቅርቡ በአፋርና አማራ ክልል በህዝብ ላይ በፈጸመው ግፍ ተረጋግጧል። ለትግራይ ህጻናት የተላከን አልሚ ምግብ ለሆዳም አባላቱ ያለምንም እፍረት ያደለው ይህ የጥፋት ኃይል በአማራ ክልል ከአንድ ቤት አስከ አምስት የሚደርሱ ንጹሃን ዜጎችን ከባድ መሳሪያ ተኩሶ በመግደል የአረመኔያዊነቱን ልክ አሳይተቷል። በአፋር ክልልም ህጻናትን ሳይቀር ያለምንም ጥፋታቸው በግፍ በመጨፍጨፍ የህዘብ ጠላትነቱን በይፋ አሳይቷል።
ለእምነትና ለእምነት ተቋማት ደንታ የሌለው ይህ የሽብር ኃይል የእምነት ተቋማትን በምሽግነትና በካምፕነት በመጠቀም ከዚህም አልፎ አቅዶና አስቦ በከባድ መሳሪያ ደብድቦ በማፍረስ ታሪክ ይቅር የማይለው በደል በማድረስ ላይ ይገኛል። ለዚህም በትግራይ ክልል በህግ ማስከበር ዘመቻ ወቅት የሰራው አፍራሽ ተግባርና ከሰሞኑ በጨጨሆ መድሃኔኣለም ቤተክርስቲያን ላይ ያደረሰው ጥፋት ጥቂቶቹ ማሳያዎች ናቸው። የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎቹ ምዕመናንን ገድለዋል። ቅዳሴ ላይ የነበሩ የደብር አገልጋዮችንም አቁስለው ለከፋ ጉዳት አጋልጧቸዋል።
ህዝብን እንደ ህዝብ ፈርጆ ለጥፋት የሚንቀሳቀሰው ይህ የጥፋት ኃይል ከአማራ ህዝብ ላይ የማወራርደው ሂሳብ አለኝ ብሎ በአደባባይ በመፎከር የግድያና የዘረፋ እቅድ አውጥቶ አስፈጽሟል፡፡ የሚችለውን ዘርፏል፤ የማይችለውን አውድሟል፡ ፡ ቡሃቃ ተሸክሞ ሄዷል፤ ሽሮና በርበሬ ገልብጦ ወስዷል፡፡ ሴቶችን ደፍሯል፤ ወጣቶችን ገድሏል፡፡ አረመኔያዊ ባህሪውን እንስሳትንና የእርሻ ማሳን ጭምር በመጨፍጨፍና በማውደም አሳይቷል።
የነገ አገር ተረካቢ የሆኑ የትግራይ ለጋ ህጻናትን ያለስልጠና በጦርነት በመማገድ ዘር የማጥፋት ተግባር ፈጽሟል። ትምህርት ቤት ተከፍቷልና ኑ በማለት ተማሪዎችን በመጥራትና አፍሶ ለእሳት በመዳረግም የአረመኔነቱን ጫፍ በአደባባይ አሳይቷል። እርዳታ ለማድረስ ወደትግራይ የተጓዙ መኪኖች ተመልሰው የእርዳታ ቁሳቁስ እንዳያቀርቡ በማገት በድሆች ጉሮሮ ላይ በመቆመር ላይ ይገኛል። በአማራና በአፋር ክልሎች የአርዳታ መጋዘኖችን በመዝረፍም ሥርዓት አልበኝነቱ ልክ እንደሌለው አስመስክሯል።
በዚህ ሁኔታ ውስጥ በጣም የሚያሳዝነው ነገር ይህ አሸባሪ ኃይል ይህንን ሁሉ ግፍ በንጹሃን ኢትዮጵያውያን ላይ ሲፈጽምና ሥርዓት አልበኝነቱ ጣራ ሲነካ የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪና ጠበቃ ነን ባይ አገሮች ደፈር ብለው ሲያወግዙ አለመታየታቸው። ከዚህ ይልቅ ይህን ሁሉ ግፍና ጥፋት እንዳላየ ሲያልፉ ብሎም በስመ አርዳታ ይህ ኃይል አፈር ልሶ እንዲነሳ ሲሞክሩ ተስተውሏል።
ይሁን እንጂ ከሰሞኑ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ካንትሪ ዳይሬክተር ለኢቢሲ በሰጡት መረጃ አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል የእርዳታ ቁሳቁሶችን መዝረፉን በይፋ ተናግረዋል። ይህንንም መረጃ በዓለም ላይ ያሉ ታዋቂ መገናኛ ብዙሃን በሰበር ዜናነት አሰተጋብተውታል። “አካፋን አካፋ” ብሎ የመሰየሙ ይህ ጅምር አጥፊን አደብ ለማስገዛት የራሱ የሆነ በጎ አስተዋጽኦ ይኖረዋልና ይህን ዓይነቱ ተግባር ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባዋል!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 27/2013