በኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን አስተባባሪነት ኃብረተሰቡ ለጀግናው የአገር መከላከያ ሠራዊት ደጀን መሆኑን ለማረጋገጥ ከነሐሴ 9/2013 ዓ.ም ጀምሮ ከፌዴራል ጀምሮ እስከ ታችኛው የአስተዳደር መዋቅር የስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች እና የገቢ መሰብሰቢያ ፕሮግራሞች እየተሄዱ ይገኛሉ። ይህም በቀጣይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ስፖርት ኮሚሽን ከትናንት በስቲያ በፅህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አሳውቋል።
መግለጫውን የሰጡት የኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር አቶ ዱቤ ጅሎ፣ ስፖርት ህብረተሰቡን አንድ በማድረግ፣ ሰላምን በማስፈን ፣ ልማትን ለማስቀጠል እና ግጭትን ለመፍታት ትልቅ አቅም እንዳለው ተናግረዋል። በዚህም መሠረት እንደ ስፖርት ሴክተር የአገራችንን መከላከያ ሠራዊት ለማበረታታትና ለመደገፍ የስፖርት ቤተሰቡ በከፍተኛ አመራሩ አማካኝነት በተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ ላይ እንደሚገኝ ምክትል ኮሚሽነሩ አስረድተዋል። ከመደበኛ የስፖርት ልማት ስራዎችም ጎን ለጎን የአገር መከላከያን ለመደገፍ የተጀመሩ የህብረተሰብ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው መልእክት አስተላልፈዋል።
ኢፌዲሪ ስፖርት ኮሚሽን የስፖርት ማህበረሰብ ተሳትፎ ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ በቀለ በበኩላቸው፣ እንደ ስፖርት ሴክተር የአገር መከላከያ ሰራዊትን ለማበረታታትና ለመደገፍ ‹‹እኔም ለአገሬ ወታደር ነኝ›› በሚል መርህ በሰባት ክልሎችና በሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች ሰፊ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን እየተካሄዱ እንደሚገኙ ገልፀው፣ እስከ አሁን በተደረጉ እንቅስቃሴዎች በአጠቃላይ 479,596 ከሚሆኑ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች 7648 ዩኒት ደም እና 13,095,000 ብር የገንዘብ ድጋፍ መሰብሰቡን ተናግረዋል፡፡
ለአገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ የሚደረጉ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ነሐሴ 30/2013 ዓ.ም ሁሉም የፌዴራል መስሪያ ቤቶች በደም ልገሣ፣ በጤና እና አካል ብቃት እንቅስቃሴዎች እንዲሁም በተለያዩ መረሃ ግብሮች “የማህበረሰብ ስፖርት ልዩ ቀን” በሚል መርህ እንደሚካሄዱም አቶ ተስፋዬ ገልፀዋል፡፡
“እኔም ለአገሬ ወታደር ነኝ” በሚል መሪ ቃል የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሮች በተለያዩ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ነሐሴ 23/12/2013 ዓ.ም መካሄዳቸው ይታወሳል። “ኢትዮጵያን ለማዳን እዘምታለሁ፣ እኔም ለአገሬ ወታደር ነኝ” በሚል መሪ ቃል በሱማሌ ክልላዊ መንግስት የተካሄደው የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር አንዱ ሲሆን፣ በዕለቱ የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ፣ እንዲሁም ምክትል ቢሮ ኃላፊ እና የክልሉ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት በስፍራው ተገኝተው ውድድሩን አስጀምረዋል።
የክልሉ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡመርዚያድ ኢብራሒም “ለጀግናው መከላከያ ሠራዊት ያላችሁን ክብር እና አጋርነት ለመግለፅ በተዘጋጀው የሩጫ ውድድር ላይ የተሳተፋችሁ ሁሉ ምስጋና ይገባችኋል፤ እንዲሁም ጀግናው መከላከያ ሠራዊታችንን ለመደገፍ ያሳያችሁት ቁርጠኝነት የሽብር ቡድኑ ተጠራርጎ እስኪወገድ ድረስ መቀጠል አለበት” በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል። ከውድድሩ ጎን ለጎን የደም ልገሳ ፕሮግራምም ተካሂዷል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽንም በእለቱ ከሁሉም የማርሻል አርት ስፖርት ማህበራትና ማርሻል አርት ጥምረት ጋር በመተባበር በስፖርቱ ማህበረሰብ የአገር መከላከያ ሰራዊትን የማበረታታት እና የመደገፍ ንቅናቄ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም አካሂዷል። በመርሃግብሩ ላይ የተገኙት የኢፌድሪ ሰላም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ፣ የስፖርቱ ማህበረሰብም ስፖርትን በመጠቀም ከፍተኛ የንቅናቄ ስራ በመስራት ከመከላከያ ጎን መቆሙን በማድነቅ ሁሉም በያለበት ከመከላከያ ጎን በመቆም ደጀንነቱን እንዲያሳይ ጥሪ አቅርበዋል ። በመርሀ ግብሩ ላይ የተሳተፉ የከተማ የውሹ ፣ የካራቴ እና የወርልድ ቴኳንዶ የስፖርት አደረጃጀቶች የተለያዩ ስፖርታዊ ትዕይንቶችን አሳይተዋል፡፡
በተመሳሳይ የአገር መከላከያ ሰራዊትን ለመደገፍ በሰበታ ከተማ የማህበረሰብ ስፖርት እንቅስቃሴ ተካሂዷል። በኦሮሚያ ስፖርት ኮሚሽን እና በሰበታ ከተማ አስተዳደር ስፖርት ኮሚሽን አስተባባሪነት “የአገራችንን ስም፣ዝና እና ክብር ለማስጠበቅ ከመከላከያ ስራዊት ጎን ዘብ እንቆማለን” በሚል መሪ ቃል ዓለምገና ፋጂ አደባባይ የተለያዩ ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ፤ በመርሃግብሩ ላይ የባህል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር የስፖርት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀብታሙ ሲሳይን ጨምሮ፤ የኦሮሚያ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ነስር ሁሴን ፣ የሰበታ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ብርሃኑ በቀለ እና ሌሎች የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል ። በተካሄደው የማህበረሰብ የስፖርት እንቅስቃሴ ላይ አትሌቶች፣ የሰበታ ከተማ ነዋሪዎች እና ወጣቶች የእግር ጉዞ፣ የደም ልገሳ እና የማስ ስፖርት እንቅስቃሴ ያደረጉ ሲሆን፤ በሁሉም ፆታ ከተለያዩ የአትሌቲክስ ክለቦች የተወጣጡ አትሌቶች የአምስት ኪሎ ሜትር የጎዳና ሩጫ በማድረግ “ለመከላከያ ሠራዊት ክብር እንቆማለን” በማለት ድጋፋቸውን በአንድነት ገልፀዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 26/2013