አሸባሪው ህወሓት በስልጣን በቆየባቸው 27 ዓመታት በሀገር ላይ ታሪክ የማይዘነጋው አስከፊና አሳፋሪ ተግባራቶችን ፈጽሟል። ከእዚህም አንዱ የትምህርት ሥርዓቱን ለማዳከም የወሰዳቸው የተለያዩ እርምጃዎች ተጠቃሽ ናቸው።
የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት በሞራልና በስነምግባር ያልተቃኘ እንዲሆን፣ ብቁ ዜጎችን ማፍራት የማይችልና ሀገር ወዳድ ዜጋ እንዳይፈጠር የሰራው ስራ የሚዘነጋ አይደለም። ከትምህርት ሥርዓቱ ጋር ተያይዞ ሲያደርጋቸው የነበሩ ነገሮች የህወሓትን የከፋፋይነት እና ሀገር የማፍረስ መሰረታዊ ባህሪውን ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ ናቸው።
አሁንም እየሰራ ያለው የሀገርን ኢኮኖሚ ማዳከም ፣ ህዝብን ከህዝብ፣ አንዱን ሃይማኖት ከሌላው ጋር እንዲጋጭ ማድረግ፣ ህዝብን ማፈናቀል፣ ህጻናትን ለጦርነት መማገድ፣ የህዝብ አገልግሎት መስጫ መሠረተ ልማቶችን ፤ የህክምናና የትምህርት ተቋማት ማውደም እንዲሁም ሌሎች የመንግሥትና የግል ንብረቶች ላይ ዘረፋና ውድመት መፈጸም የዚህ አሸባሪ ድርጅት መገለጫ ባህሪዎች ናቸው ።
እንዲሁም በሥነምግባር የታነጹ፣ በእውቀት የበለጸጉ ዜጎች እንዳይወጡ ማድረግ ፣ የሀሰት ትርክቶችን መፈብረክ ፣እውነተኛ ታሪኮችን ማዳፈን ከመሰረታዊ ባህሪያቶቹ መካከል የሚጠቀሱ ናቸው። ዜጎች የሀገራቸውን እውነተኛ ታሪክ እንዳያውቁ የታሪክ ተመራማሪዎችም ታሪክን እንዳያኖሩ የታሪክ አዋቂዎችን ደብዛ በማጥፋት፣ የታሪክ ትምህርቶችን ከማዛባት አልፎ ትምህርቱም በዩኒቨርሲቲ ውስጥ እንዳይሰጥ ሲያደርግ ቆይቷል። የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት እንዲዳከምና ብዝሀነትን ያከበረ ኢትዮጵያዊ አንድነት እንዳይጎለብት ከፋፋይ የሆነ የትምህርት ሥርዓት በሀገሪቱ እንዲተገበር ሰርቷል። ይሄም ሀገራዊ አንድነት እንዳይጠናከር፣ በትምህርታቸው ብቁ የሆኑና በማንነታቸው የሚኮሩ ዜጎች እንዳይኖሩ የማድረጊያ የሴራ መንገዱ ነበር ።
አሁንም ባለፉት አስር ወራት ጦርነት ከቀሰቀሰ በኋላ እያደረገ ያለው ሀገሪቱን በተለያየ መልኩ ማዳከም ነው። ጸረ ሰላ የሆነው ይህ አሸባሪ በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ከሰባት ሺህ በላይ ትምህርት ቤቶች ሙሉ በሙሉና አንዳንዶች ደግሞ በከፊል አውድሟል። ትምህርት ቤቶችን ማውደም ብቻ ሳይሆን የተማሪዎችን የትምህርት ማስረጃዎች እና ሌሎች ሰነዶችን ጭምር አጥፍቷል።
የትምህርት መሳሪያዎችን ሰባብሮ አበላሽቷል። በቅርቡ በአማራና በአፋር ክልሎች ያደረገውም ይሄንኑ ነው። በአንድ ወር ብቻ በአፋር ክልል 88 ሺህ ተማሪዎች ይማሩባቸው የነበሩ 455 ትምህርት ቤቶች ፤ በአማራ ክልል ደግሞ 140 ትምህርት ቤቶችና ሁለት የመምህራን ማሰልጠኛና ኮሌጆች ሙሉ በሙሉና በከፊል ውድመት አድርሶባቸዋል።
በተመሳሳይ በትግራይ ክልል ከአንድ ነጥብ አራት ሚሊዮን በላይ ተማሪዎችንና ከ48 ሺህ በላይ መምህራን ከትምህርት ሥርዓት ውጪ አድርጓል። የሰላም መንገድ ፈጽሞ የማይዋጠው ይህ አሸባሪ ድርጅት በአማራና የአፋር ክልሎች ባስፋፋው ጦርነት በትምህርት ተቋማት ላይ ያደረሰው ውድመት እጅግ ከፍተኛ መሆኑን የትምህርት ሚኒስቴር አስታውቋል።
መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ወስኖ ትግራይን ለቆ ሲወጣ አሸባሪው ህወሓት በዋና ዋና ከተሞች ላይ ትምህርት ለማስጀመር በሚል ሁሉም ተማሪ ትምህርት ቤት እንዲገኝ ቅስቀሳ አድርጎ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤታቸው ሲሄዱ ለአብዛኞቹ ህፃናት የቀረበላቸው ትምህርት ሳይሆን ያለዕድሜያቸው ለጦርነት መመልመል ነበር። ሳይወዱ በግድ ተመልምለው እና ታፍሰው በለጋ ዕድሜያቸው በጦርነት ተማግደዋል። በጥይት አሩር አረዋል ። ትምህርት ቤቶችም በጦር ሰፈርነት እንዲውሉ ሆነዋል።
አሸባሪው ህወሓት አሁን የትምህርት ተቋማትን ሲያወድም፣ ሲዘርፍ ሰነዶችን ሲያቃጥልና ሲያጠፋ መመልከት አዲስ ቢመስልም ይሄ ባህሪው የነበረና ከውልደቱ ጋር አብሮ አድጎ የመጣ የክፋቱ መገለጫ ነው። በእውቀቱ የበቁ ዜጎች እንዳይወጡ፣ የትምህርት ሥርዓቱም እንዳይጠናከር ማዳከም የኖረበት መሰረታዊ ባህሪው ነበርና፣ ስለሆነም የአሁኑ እኩይ ተግባሩ ለትምህርት ተቋማትና ለሀገር ሀብት ያለውን የተጣመመ አስተሳሰብ በድጋሚ ያረጋገጠበትና ድብቁን ባህሪውን ያጋለጠበት ስራው ነው።
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ህፃናትን ከትምህርት ውጪ ማድረግ ፣ ዕድሜያቸው ያልደረሱ ህጻናትን ለጦርነት ማሰለፍ የሀገሪቱም ሆነ የዓለም አቀፍ ህጎችንና መርሆችን የሚጻረር ተግባር ቢሆንም አሸባሪወ ህወሓት ግን በዚሁ እብሪቱ ቀጥሏል ።
በህግ የማይመራ፣ ላወጣው ህግ እንኳን የማይገዛ ለጥፋትና ሽብር ብቻ የቆመ መሆኑን በተደጋገሚ በሚፈጽማቸው የጥፋት እጆቹ፣ በሚያራግባቸው ሀሰተኛ ትርክቶቹና ሴራዎቹ አስመስክሯል። ይሄ የጥፋት ኃይል አሁን በትምህርት ተቋማት ላይ የሚያደርሰው ውድመት ቀደም ሲልም ከፋፋይ የትምህርት ሥርዓት በመከተል፣ ብዝሃነትን በማዳከም፤ ኢትዮጵያ አንድነቷ የተጠበቀ ጠንካራ ሀገር እንዳትሆን ፣ ሀገር ወዳድ ዜጋ እንዳይፈጠር ሲሰራበት የነበረው መሰረታዊ ባህሪው ቀጣይ ክፍል ነውና መላ ኢትዮጵያውያን ይህን ጸረ ህዝብ አሸባሪ ከአገሪቱ ለመንቀል የጀመሩትን ዘመቻ በተባበረ ክንድ በድል ሊደመድሙት ይገባል!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 26/2013