
ሁሉም ሰው የአደጋ ጊዜ ተጠሪ አለው፡፡መታወቂያ ላይ ይስፈርም አይስፈር ሁሉም ሰው ችግር ውስጥ ሲገባ ቀድሞ እንዲደርስለት የሚጠብቀው አንድ ሀይል አለ፡፡ አንዳንዶች እናቶቻቸውን ፤ አንዳንዶች አባቶቻቸውን ፤ አንዳንዶች እህት ወይም ወንድሞቻችውን ፤ አንዳንዶች የልብ ጓደኞቻቸውን ፤ አንዳንዶች ከአማልከቱ ወይም ከመላእክቱ አንዱን ሊጠቅሱ ይችላሉ፡፡ ብቻ ሁሉም ለክፉ ቀን የሚደርስለትን ወገን አዘጋጅቷል፡፡
የአደጋ ጊዜ ተጠሪ ያለው ግን ሰው ብቻ አይደለም፡፡ የሽብር ቡድኖችም የአደጋ ጊዜ ተጠሪ አላቸው፡፡ ምሳሌ ካላችሁ ደግሞ የህወሓትን የአደጋ ጊዜ ተጠሪዎች ማየት እንችላለን፡፡ ህወሓት ማንነቷን የሚገልጽ መታወቂያ አላት፡፡ እዚያ መታወቂያ ላይ ብዙ የአደጋ ጊዜ ተጠሪዎች አሏት፡፡
የአደጋ ጊዜ ተጠሪ ተብለው የተቀመጡት ደግሞ ብዙ ናቸው፡፡ዋነኛዋ የአደጋ ጊዜ ተጠሪ አሜሪካ ናት፡ ፡ከዚያ የአውሮፓ ህብረት አለ፡፡ከዚያ የአለም ጤና ድርጅት ነው፡፡ከዚያ የአለም ባንክ እና አይ ኤም ኤፍ አሉ፡፡ከዚያ የእርዳታ ድርጅቶች አሉ፡፡ከዚያ እነ ሲ ኤን ኤን እና ቢቢሲ አሉ፡፡ከዚያ ደግሞ እነ ማርቲን ፕላውት አሉ፡፡
እንግዲህ ይሄ ሁሉ የአደጋ ጊዜ ተጠሪ ሀይሎች ስብስብ ዋነኛ ስራቸው ልጃቸው እና ተንከባክበው ያሳደጉት ሀይል ጭንቅ ሲይዘው ከተፍ ብሎ መድረስ እና ግሉኮስ መሰካት ነው፡፡እዩአቸው እስኪ እነዚህ ሀይሎች ጩሀታቸው መች መች ደመቅ እንደሚል፡፡ ልክ ህወሓት ከባድ ቡጢ ስትቀምስ ፤ ማፍግፈግ ሲጀምር ፤ መንሸራተት ሲኖር ያኔ ኡኡታው ይጀምራል፡፡ሁሉም ከያሉበት እንደየአቅማቸው የሆነ ነገር ይዘው ለህወሓት ለመድረስ ይከንፋሉ፡፡
ጩሀቱ እነ ርብርቡ ብዙ አይነት መልክ አለው፡፡ ለምሳሌ የአሜሪካኖቹን ጩከት እንዴት መሰላችሁ…ልክ ህወሓት ዱላ ሲበዛበት ብድግ ይሉና “ችግሩ በድርድር እንጂ በጦርነት መፍትሄ አይገኝለትም” ይላሉ፡፡ማዘናጊያ ነገር ናት፡፡ዱላውን ቀነስ አርጉለት ፤ አትጉዱብን ነው ነገሩ፡፡
በውነቱ ይህን ምክር የሚለግሱ አሜሪካውያን ባይሆኑ ደስ ይል ነበር፡፡ምክንያቱም በጦርነት ሰላም አይመጣም የሚሉት አሜሪካውያን በአፍጋኒስታን መፍትሄ ለማምጣት 20 አመታት ጦርነት ያደረጉ ናቸው፡ ፡በሊቢያ ፤ በሶሪያ ፤ በየመን ፤ ወዘተ…በጦርነት መፍትሄ ለማምጣት ሲጥሩ የኖሩ እና እየኖሩ ያሉ ሰዎች እኛን በየት መንገድ ሰላም ማምጣት እንደሚገባን ሊመክሩን አይገባቸውም፡፡
በአለም ግዙፍ የሆነውን ጦር የገነቡ ፤ ኒውክለር የታጠቁ እና በየቀኑ አዳዲስ የጦር መሳሪያ ሲፈበርኩ የሚውሉ ሀገራት ጦርነት መፍትሄ አይደለም ሲሉ ከመሳቅ ውጭ ምን ይደረጋል፡፡ ለማንኛውም ጦርነት መፍትሄ አይደለም ማለት በቻይንኛው ህወሓትን አትግደሉብን ማለት ነው፡፡
ሌላኛው የአደጋ ጊዜ ድምጽ “የእርዳታ እህል ማስገባት አልቻልንም” የሚል ነው፡፡ይሔም ህወሓት ወደ መቃብሩ ሲቃረብ ግሉኮስ ለመሰካት የሚደረግ ጥረት ነው፡፡ቢቻል ህወሓት ሲዳከም በእርዳታ ስም መሳሪያ አቅብሎ ማዳን ነው አላማው፡፡ካልሆነም መንግስትን በዚህ በኩል ወጥሮ ትኩረቱን ከህወሓት ላይ እንዲያነሳ ማድረግ ነው፡፡እሱም ካልሆነ አሁን እንደሚያደርጉት በእርዳታ እህል ስም ለሚያጣጥረው የጁንታው ሰራዊት ሀይል ሰጪ ምግብ ማቅረብ ነው፡፡ታዲያ አደጋ ጊዜ ተጠሪ ከዚህ በላይ ማን አለ ::
ሌላኞቹ የህወሓት የአደጋ ጊዜ ተጠሪ እነ ሲ ኤን ኤን እና ቢቢሲ ናቸው፡፡እነዚህ ደግሞ ልክ ህወሀሓት ህመም ሲጸናባት በአንድ ጊዜ ከደምሳሽነት ወደ የጄኖሳይድ ተጠቂነት የሚያዞሯት ናቸው፡፡ህወሓት ወደ አማራ እና አፋር ክልል ስትዘምት እና ንጹህን ገበሬዎችን ስትጨፈጭፍ ህወሓት ንጹሀንን ጎዳች ሳይሆን “ጦርነቱ ከትግራይም አልፎ ወደ ሌሎች ክልሎች እየተስፋፋ ነው” ብለው አድበስብሰው ያልፉታል፡፡ልክ ህወሓት ዱላ ሲበዛባት ግን የትግራይ ህዝብ በጦርነቱ ስለደረሰበት ጉዳት ከህወሓት ሰዎች አፍ የሰሙትን ይዘው የጄኖሳይድ ልቅሶአቸውን ማለቃቀስ ይጀምራሉ፡፡
እነ ተመድ ደግሞ አሉ፡፡ነገሩ ከረር ሲል አስቸኳይ ስብሰባ በመጥረት እና በመግለጫ ላይ መግለጫ በማውጣት የአደጋ ጊዜ ተጠሪነታቸውን የሚገልጹ፡ ፡ህወሓት ማጣጣር ስትጀምር ከጸጥታው ምክር ቤት አባላት አንዳቸው ብቅ ይሉና አስቸኳይ ስብሰባ ይጠራሉ፡፡ሁሉም በየፊናቸው መግለጫ ያወጣሉ፡፡ ንግግሮች ይዘጋጃሉ፡፡ህወሓት ምን ያህል እንደተጎዳች እና መንግስት ምን ያህል እንደበደለ በአደባባይ ይለፈፋል፡፡ አላማው መንግስትን ጫና ውስጥ ለመክተት እና ትንሽ መተንፈሻ ቀዳዳ ለህወሓት ለመስጠት ነው፡፡እነዚህኞቹ በስብሰባ አዳራሽ የህወሓትን የአደጋ ጊዜ ጥሪ ለመመለስ ሲሯሯጡ ሌሎቹ ባለስልጣናት ደግሞ በትዊተር ብቅ ይሉና “አይዞሽ በርታ በይ እንዳትሞቺ” እያሉ ህወሓትን ያባብላሉ፡፡
የሆኑ ተቋማት ደግሞ አሉ፡፡የሆነ አይነት የኢትዮጵያን መንግስትን የሚከስስ እና የሚያጣጥል ሪፖርት አዘጋጅተው የሚጠብቁ፡፡የእነዚህ ተቋማት ስራም እንዲሁ ልክ ህወሓት ኮማ ውስጥ ስትገባ ሪፖርታቸውን ይዞ ብቅ ማለት እና ማዳን ነው፡፡
ጁንታው እየተዳከመ መሆኑን ሲያውቁ ሪፖርቱን ይፋ ያደርጉታል፡፡ጫጫታ ይፈጠራል፡፡መንግስት ህግ ማስከበሩን ትቶ ለነሱ መልስ በመስጠት ይጠመዳል፡፡ በዚህ ቅጽበት ከገደል አፋፍ ደርሳ የነበረችው ህወሓት ማገገሚያ እድሜ ታገኛለች፡፡
አሁን ላይ እነዚህ የአደጋ ጊዜ ተጠሪዎች ተቀናጅተው እየሰሩ ነው፡፡እነ አለም ባንክ እና አሜሪካ በኢኮኖሚው ዘርፍ ሀገሪቱን ለማሽመድመድ እየተጉ ነው ፡፡አሜሪካ እና የአውሮፓ ህብረት ዲፕሎማሲያዊ ጫናውን አጠንክረው ይዘዋል፡፡እነ ሲ ኤን ኤን እና ቢቢሲ በይፋ የፕሮፓጋንዳ ትግሉን አጡፈውታል፡፡የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተለያዩ ኤጀንሲዎች ትጥቅ እና ስንቅ በማቅረብ ጁንታውን ለመደገፍ የሚያደርጉት ግብግብ ተበራክቷል፡፡ እነ ሳማንታ ፓወር እና አንቶኒ ብሊንከን ነገሩን ግላዊ ጉዳያቸው አድርገው በትዊተር እንኳ አላረፉም፡፡ የሁሉም ርብርብ አላማው አንድ ነው፡ ፡ላለፉት 46 አመታት ተንከባክበው ያሳደጉት እና አሁን ለ27 አመታት ቀጥ ለጥ ብሎ የታዘዛቸውን ልጅ ነፍስ ማዳን ነው፡፡
ህወሓትም ወደዚህ አደገኛ ጨዋታ ሲገባ የአደጋ ጊዜ ተጠሪዎቼ እነሱ ናቸው ብሎ ተማምኖ ነው፡፡እነሱም አላሳፈሩትም፤ በጭንቅ ሰአቱ ሊደርሱለት እየሞከሩ ነው፡፡ነገር ግን እስካሁን እለተ ሞቱን ቢያራዝሙለትም መዳንን አላስገኙለትም፡፡ ምክንያቱ ኢትዮጵያውያን ይህን በሽታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመገላገል የቆረጡ በመሆናቸው ነው፡፡
አቤል ገ/ኪዳን
አዲስ ዘመን ነሐሴ 25/2013