የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሰሞኑን ‹‹ሰላምና ደህንነት በአፍሪካ (Peace and Security in Africa)›› በሚል አጀንዳ ‹‹ስለኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ›› ለመምከር ተሰብስቦ ነበር:: አምስት የማይገሰስ ስልጣን ባላቸው ባለፀጋ አገራት የሚዘወረውና ‹‹ዓለም አቀፍ ሰላምና ደህንነትን የማስፈን ኃላፊነት አለብኝ›› የሚለው ምክር ቤቱ ለስብሰባ የተቀመጠው የኢትዮጵያ ሰላምና አንድነት እንዲሁም የኢትዮጵያውያን ደህንነት አስጨንቆት አልነበረም:: ይልቁንም የኢትዮጵያን አንድነት አደጋ ላይ የጣለውንና ሕዝብን ከአደጋ በሚጠብቅ የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ፈፅሞ ታሪክ የማይዘነጋው ክህደት የፈፀመውን፣ ህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህ.ወ.ሓ.ት) የተባለውን ቡድን በሰብዓዊ ድጋፍ ስም ከወደቀበት ለማንሳት የቡድኑ ‹‹ወዳጅ›› በሆኑት በአሜሪካና አጋሮቿ የተጠራ ስብሰባ ነበር:: ስብሰባው እንዲደረግ የጠየቀችው አየርላንድ ናት::
የፀጥታው ምክር ቤት ‹‹በትግራይ ጉዳይ›› ሲሰበሰብ የሰሞኑ ለስምንተኛ ጊዜ መሆኑ ነው:: ምክር ቤቱ በአንድ አገር ጉዳይ ላይ እንዲህ በተደጋጋሚ የተሰበሰበበት ሌላ አጋጣሚ ይኖር ይሆን? የህ.ወ.ሓ.ት ወዳጅ የሆኑት አሜሪካና አየርላንድ በስብሰባው ላይ እንደተለመደው ‹‹ … የኢትዮጵያ መንግሥት ወደ ትግራይ ክልል እርዳታ እንዳይገባ እያደረገ ነው … ብዙ ሕዝብ በሞት አፋፍ ላይ ይገኛል …›› የሚሉ ውንጀላዎችን አሰምተዋል::
[በነገራችን ላይ የአቶ መለስ ዜናዊ አድናቂና ወዳጅ የሆነው (በ2015 ዓ.ም ‹‹The Real Politics of the Horn of Africa ፡ Money, War and the Business of Power›› በሚል ርዕስ ያሳተመውን መጽሐፉን ‹‹መታሰቢያነቱ ለአቶ መለስ ዜናዊ ይሁንልኝ›› ያለው)፤ በዘመነ ህ.ወ.ሓ.ት/ኢ.ሕ.አ.ዴ.ግ የአራት ኪሎ ደንበኞች ከነበሩና ህ.ወ.ሓ.ት ከማዕከል ፖለቲካ በመባረሩ ምክንያት ካኮረፉ የውጭ ሰዎች መካከል አንዱ የሆነው፤ ከህ.ወ.ሓ.ት ባለስልጣናት ጋር የቅርብ ግንኙነት ያለው፤ ‹‹የመለስ ዜናዊ ፋውንዴሽን›› ሃሳብ አመንጪው፤ በኢትዮጵያ ላይ መጠነ ሰፊ የሀሰት ውንጀላዎችን እያቀረበ የሚገኘው … አሌክስ ዲ ዎል አየርላንድ በምክር ቤቱ በኩል በኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ እንደትፈጥር ሲወተውት ከርሟል]
ሕንድ ጦርነቱ በህ.ወ.ሓ.ት አማካኝነት ወደ አማራና አፋር ክልሎች እንደተዛመተና ይህም በሰላማዊ ሰዎች ላይ የሚደርሰውን የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዲሁም ህፃናትን በተዋጊነት የማሰማራት ከባድ ችግር ማስከተሉን ገልፃለች።
በምክር ቤቱ የአገሪቱ ተወካይ አምባሳደር ቲሩሙትሪ በሰኔ ወር የኢትዮጵያ መንግሥት የወሰደው የተናጠል ተኩስ አቁም እርምጃ የተፈጠረውን የሰብአዊ ቀውስ ለማሻሻል ወሳኝ እርምጃ እንደነበር አስታውሰው፤ የተኩስ አቁሙ በህ.ወ.ሓ.ት በኩል ተቀባይነት ሳያገኝ በመቅረቱ ጦርነቱ ወደ ሌሎች አካባቢዎች ተስፋፍቶ የሚደርሰው ጉዳት መጨመሩን ጠቅሰዋል።
ተወካዩ ጨምረውም መንግሥት ችግሩን ለመቅረፍ ከተባበሩት መንግሥታት ተቋማትና ከሌሎች የሰብአዊ እርዳታ አጋሮች ጋር እየሰራ መሆኑን በመግለጽ ባደረገው ጥረትም የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት እየተሻሻለ መሆኑንና ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል። በዚህም ኢትዮጵያ ለምታደርገው ጥረት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አስፈላጊው ድጋፍ ሊደረግላት እንደሚገባና በተለይ የተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ ሕብረት ችግሩን ለመፍታት ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባቸው አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ችግር መፍትሔ ለማምጣት መፍትሄው በኢትዮጵያ በእራሷ የሚመራና በሕገ መንግሥቷ ማዕቀፍ ውስጥ መከናወን እንዳለበት በመግለጽ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ለማስፈን መተማመን፣ እርቅና ውይይት መኖር እንዳለበትም አመልክተዋል። አገራቸው ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ነጻነት፣ ሉዓላዊነትና የግዛት መከበር ያላትን ቁርጠኝነትም ገልጸዋል።
ቻይና በትግራይና በሌሎችም ቦታዎች ሰብአዊ እርዳታ የሚሰጡ ድርጅቶች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እንዲያከብሩና የተባበሩት መንግሥታት መርህን እንዲከተሉ በአፅንዖት አሳስባለች። የኢትዮጵያ መንግሥት ችግሩን ለመፍታት የወሰደውን እርምጃ እንደምትደግፍ ገልፃ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን መንግሥት በመደገፍ ለዘላቂ ሰላም እና ብሔራዊ እርቅ እንዲቆም ጠይቃለች። በአማራ እና በአፋር ክልሎች እርዳታ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ እንደሆነ በመግለፅ ሁሉም አካሎች ሰብአዊ እርዳታ እንዲዳረስ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አሳስባለች።
‹‹በሰብአዊ እርዳታ ስም የውጪ ጣልቃ ገብነት መኖር የለበትም። የአፍሪካ ችግር በአፍሪካውያን ይፈታ:: ኢትዮጵያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦች ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጻረሩ እና ችግሩን ከመፍታት ይልቅ የሚያባብሱ ናቸው›› በማለት በተወካዯ በኩል ተናግራለች።
የውጭ ድጋፍ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት እና የፖለቲካ ነጻነት በጠበቀ መልኩ መሰጠት እንዳለበት ያስረዳችው ደግሞ ሩስያ ናት:: በስብሰባው ላይ የአገራቸውን አቋም ያስረዱት አና ኢቭስቲግኒቫ፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ውይይት እንደሚያስፈልግና ይህም በኢትዮጵያውያን መሪነት መካሄድ እንዳለበት ገልጸዋል። ወደ ትግራይ እርዳታ ለመላክ በሰመራ የተቋቋመው መተላለፊያ ተገቢውን አገልግሎት ይሰጣል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
‹‹በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ሰብአዊ ሁኔታ ከፖለቲካ ጉዳይ መነጠል ያስፈልጋል። በትግራይ በሚደረገው ሰብአዊ እርዳታ መድልዎ መኖርም የለበትም። አማራ፣ ኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎችም ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል” ሲሉ ለምክር ቤቱ የሩሲያን አቋም አስታውቀዋል።
ከዚህ በተጨማሪም የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት አገሪቱን በአንድነት ወደ ሰላም የመውሰድ አቅም እንዳለው ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ላይ የተጣሉ ማዕቀቦችን አውግዘው፤ የፀጥታው ምክር ቤት አባላት ምክረ ሐሳብ መካተት እንዳለበት አሳስበዋል።
[ባለፈው ሳምንት የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማርያ ዛካሮቫ የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የተከሰተውን ግጭት ለማስቆም ለወሰዳቸው የመፍትሄ እርምጃዎች ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እውቅና እንዲሰጥ ጥሪ ማቅረባቸው የሚታወስ ነው:: ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ‹‹የአንዳንድ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን መርዛማ ዘገባዎች ትኩረት የሚያሻው ጉዳይ ነው:: በአንዳንድ ጋዜጠኞች የሚሰጡ ኃላፊነት የጎደላቸው ሃሳቦች ግጭቱን ለማስቆም በጎ አስተዋፅዖ የሌላቸው፣ ችግሩን የሚያባብሱና ሁለቱም ወገኖች ስምምነት ላይ እንዳይደርሱ መሰናክል የሚሆኑ ናቸው›› በማለት የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንን ወገንተኛ አዘጋገብ በቸልታ ሊታይ እንደማይገባ ተናግረው ነበር::]
አፍሪካዊቷ ኬንያ በበኩሏ በስብሰባው ላይ ሀብታም አገራት ለሰብአዊ እርዳታ በቂ ገንዘብ እንዲያቀርቡ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲሰጡ፣ በኢትዮጵያ ምጣኔ ሀብት ላይ ድቀትን ሊያስከትል ከሚችል ማንኛውንም የተናጠል ማዕቀብ ከመጣል እንዲቆጠቡ እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት ሰላም በማምጣት በኩል የሚጠበቅበትን እንዲወጣ ጠይቃለች።
በተባበሩት መንግሥታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ ለምክር ቤቱ ባደረጉት ንግግር ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥት ሰላም ለማስፈን የወሰነውን የተናጠል ተኩስ አቁም ህ.ወ.ሓ.ት እንዲቀበል ጫና መደረግ አለበት›› ብለዋል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አክብሮ በገንቢ መንገድ ብቻ አገሪቱን ማገዝ እንደሚገባው ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ሰላም እንዲወርድ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በህ.ወ.ሓ.ት ላይ ጫና እንዲያደርግም አሳስበዋል።
መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ያወጀው ሰብአዊ እርዳታ ወደ ትግራይ እንዲደርስና ለክልሉ ሕዝብ ሰላም ለመስጠት ቢሆንም፤ ህ.ወ.ሓ.ት ጦርነቱን ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች አስፋፍቶ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው እንደተፈናቀሉ ለምክር ቤቱ ተናግረዋል።
‹‹ህ.ወ.ሓ.ት የሰብአዊ እርዳታ እንዳይደርስ አድርጓል›› ብለው የተናገሩት አምባሳደር ታዬ፤ ቡድኑ በአገሪቱ አለመረጋጋት እንደፈጠረና መንግሥትም ሰላም ለማስፈን ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሆነ አስረድተዋል። የምክር ቤቱን ውይይት አስመልክተውም ጉዳዩን ማግነን እና ፖለቲካዊ ቅርጽ መስጠት የኢትዮጵያን መንግሥት ውሳኔ እንደማይለውጥ አስታውቀዋል።
በስብሰባው ላይ የተንፀባረቁት አብዛኞቹ አቋሞች ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ ሊጥል ነው ብለው የቋመጡ አፍቃሪ ህወሓቶችን እንዳበሳጩ ግልጽ ነው:: የሕግ ማስከበር ስራው ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ ብዙዎቹ ዓለም አቀፍ (የውጭ) መገናኛ ብዙኃን ስለጉዳዩ የሚያሰራጩት ዘገባ በእውነተኛ መረጃ ላይ ያልተመሰረተ፣ ነባራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ ያላስገባና ተገቢ ያልሆነ ነው:: ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ዓለም አቀፍ ተቋማትም ስለጉዳዩ ያላቸው ግንዛቤ ከእውነታው በእጅጉ የራቀ ሆኖ ታዝበናል::
አሜሪካና አጋሮቿ ፖለቲካዊ ትርፋቸውን አስልተው ከህ.ወ.ሓ.ት ጎን መቆማቸው ብዙም የሚያስገርም እንዳልሆነ ይታወቃል:: ይህ ፖለቲካዊ ትርፍን ያገናዘበ እሳቤ ኢትዮጵያን ለከፍተኛ ዲፕሎማሲያዊ ጫና ዳርጓታል:: የውሸት መረጃዎች እውነተኛ ተደርገው ተቆጥረው አገሪቱ ከገጽታ ግንባታ ጀምሮ በሌሎች ዘርፈ ብዙ መስኮች ቀላል የማይባሉ ኪሳራዎችን እንድታስተናግድ ተገዳለች::
ቀደም ባሉት ሳምንታት እንደጠቀስኩት፣ ይህ የውሸት መረጃን የማሰራጨትና የተሳሳተ ግንዛቤን የመያዝ ችግር የተፈጠረው በመንግሥት ድክመት እና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና ተቋማት እንዲሁም በመንግሥታት ዓላማና የግል ፍላጎት ምክንያት ነው:: ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና ተቋማት የራሳቸው ዓላማ አላቸው:: እነዚህ አካላት በሌሎች አገራት የሚፈጠሩ ክስተቶችን የሚመለከቱትና ብያኔ የሚሰጡት ከራሳቸው ጥቅም አንፃር ነው:: ኢትዮጵያ ውስጥ የተፈጠረውን ሁኔታም የሚመዝኑት ዓላማቸውንና ጥቅማቸውን መሰረት አድርገው ነው:: ምዕራባውያን አገራትም ሆኑ ለመንግሥታቱ ቅርብ የሆኑት መገናኛ ብዙኃን ሰብዓዊነት፣ እውነት፣ የጋዜጠኝነት መርህ … የሚባሉትን ነገሮች ፈፅሞ አያውቋቸውም:: ለእነዚህ አካላት ሰብዓዊነት፣ እውነት፣ የጋዜጠኝነት መርህ … ማለት የተቋማቸውና የመንግሥቶቻቸው ጥቅምና አቋም እንጂ በመርህ የሚነገሩት የጽንሰ ሃሳቦቹ ትክክለኛ ትርጉም አይደለም::
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዲፕሎማሲው መስክ እየተመዘገቡ ያሉ አንዳንድ ስኬቶች ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ (የህ.ወ.ሓ.ት አጋሮችን አይጨምርም) ስለሕግ ማስከበር ዘመቻው የያዘውን የተሳሳተ ግንዛቤ በማስተካከል ረገድ አስተዋፅዖ ይኖራቸዋል::
በእርግጥ መንግሥት ያለውን አቅም ሁሉ ተጠቅሞ ስለሕግ ማስከበር ዘመቻውና ስለህ.ወ.ሓ.ት ወንጀለኛነት ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስረዳት ጥረት ቢያደርግም የህ.ወ.ሓ.ት አጋሮች እውነትን ማወቅና ለሰብዓዊነት መጨነቅ ጉዳያቸው ስላልሆነ እውነቱን ለመቀበል አይፈልጉም:: እነርሱ ባይፈልጉም በዲፕሎማሲውና በሕዝብ ግንኙነት ስራዎች ረገድ ጠንክሮ በመገኘት እውነትን ማስረዳት ከኢትዮጵያ ዜጎችና መንግሥት የሚጠበቅ ተግባር በመሆኑ ይህ ተግባር ለአፍታም ቢሆን ችላ ሊባል አይገባም፤አይችልምም!
[በነገራችን ላይ አሜሪካና አጋሮቿ ህ.ወ.ሓ.ትን ከወደቀበት ለማንሳት የሚሯሯጡት ‹‹ለትግራይ ሕዝብ አዝነው›› የሚመስለው ካለ በእጅጉ ተሸውዷል:: አሜሪካ አፍጋኒስታንን፣ ሊቢያን፣ የመንን፣ ሶሪያንና ኢራቅን በመውረር አገራቱን የዜጎቻቸው ሲኦል ያደረገችው የአፍጋናውያን በታሊባን መጨቆን፣ የሊቢያውያን በጋዳፊ አገዛዝ ነፃነት ማጣት፣ የየመናውያን በአብደላ ዳሌህ መረገጥ፣ የሶሪያውያን በአሳድ መማረርና የኢራቃውያን በሳዳም መከፋት አሳስቧት እንዳልሆነ ዛሬ አገር አልባ ሆነው የሚሰቃዩት የእነዚያ አገራት ዜጎች ብቻ ሳይሆኑ ወራሪዎቹ እነጆርጅ ቡሽ፣ ባራክ ኦባማ፣ ሳማንታ ፓወርና ጓዶቻቸውም ያውቃሉ:: ጉዳዩ ሌላ ነው … ነገሩ ‹‹ብሔራዊ ጥቅምን ማስጠበቅ›› የሚባል አጀንዳ ነው!]
የሕግ ማስከበር እንቅስቃሴውን በተመለከተ የውሸት መረጃን የማሰራጨትና የተሳሳተ ግንዛቤን የመያዝ ችግር የተፈጠረው በመንግሥት ድክመት እና በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃንና ተቋማት እንዲሁም በመንግሥታት ዓላማና የግል ፍላጎት ምክንያት ነው:: መንግሥት ስለጉዳዩ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በግልፅ ከማሳወቅ አንፃር የሰራው ስራ በቂ የሚባል አልነበረም (በእርግጥ መንግሥት ሁሉንም ኃላፊነት ብቻውን ሊወጣ አይችልም፤ አይገባምም:: በተለይ እንዲህ ዓይነት ጠንካራ የዘመቻና የቅስቀሳ ስራ በሚፈልጉ ተግባራት ላይ የምሁራን፣ የተቋማት በአጠቃላይ የዜጎች ተሳትፎ እጅግ አስፈላጊ ነው)::
ሕግ የማስከበሩ እንቅስቃሴ ብዙ የሴራ ትንታኔዎችን የሚጋብዝና ነገሩ የአፍሪካ ቀንድ ጉዳይ ስለሆነ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙኃንን ሴራ ከግምት ውስጥ ያስገባ ጠንካራ የመረጃ ዝግጅትና ጥንቃቄን የሚፈልግ ተግባር እንደሆነ ከዚህ ቀደም ጠቅሻለሁ:: የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን መረን የለቀቀ ፀረ-ኢትዮጵያ ዘመቻ ከመንግሥት ጥረት ባሻገር የምሁራንንና የዲያስፖራውን ኅብረተሰብ ጨምሮ የመላ ዜጎችን ተሳትፎና ንቅናቄ የሚፈልግ ጉዳይ መሆኑን በድጋሚ ማሳሰብም ተገቢ ይሆናል::
በአጠቃላይ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በዲፕሎማሲው መስክ እየተመዘገቡ ያሉ አንዳንድ ስኬቶችን በማጠንከር ዲፕሎማሲው ይበልጥ እንዲያሸንፍ ሁለገብና ዘርፈ ብዙ ጥረት ማድረግ ይገባል::
አንተነህ ቸሬ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 24/2013 ዓ.ም