ኢትዮጵያ በታላቁ መድረክ ኦሊምፒክ በተለይም በረጅም ርቀት ውድድሮች ገናና ስምና ዝና ከገነባች ወዲህ ሕዝብን ያስቆጣ ውጤትና አሳፋሪ ስህተት እንዳለፈው ቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ተፈጥሮ አያውቅም። ውጤቱ የተበላሸው ስህተቶቹም የተሰሩት በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት እንጂ በኢትዮጵያውያን አትሌቶች አቅም ማነስ እንዳልሆነ በብዙ ማሳያዎች መሞገት ይቻላል።
የተፈጠረው ነገር ሁሉ ከእውቀትና ልምድ ማነስ ሳይሆን አንዱ ባንዱ ላይ ነጥብ ለማስቆጠር ሆን ተብሎ በእልህ በተሰሩ ሴራዎች ስለመሆኑ ሁለቱ ተቋማት ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከኦሊምፒኩ መልስ በተናጠል የሰጧቸው ጋዜጣዊ መግለጫዎች ምስክር ናቸው። የኢትዮጵያ ሕዝብም ለውጤቱ መጥፋትና ለተሰሩት ስህተቶች ከአገር ክብርና ጥቅም የበለጠ ግለሰቦች ለራሳቸው አጀንዳ ሲሽቀዳደሙ የተፈጠረ ስለመሆኑ በቂ ግንዛቤ እንዳገኘ ግልፅ ነው።
የተፈጠረው ሁሉ ተፈጥሮ፣ የጠፋው ሁሉ ጠፍቶ የነገው የአገሪቱ ስፖርት በተለይም ኦሊምፒክና አትሌቲክስን በተመለከተ አሳሳቢ ጉዳዮች ተዳፍነው እንዳይቀሩ የብዙዎች ስጋት ነው። በቀጣይ ዓመታት ስፖርቱን የሚመሩት ሰዎች ለተፈጠሩት ችግሮች ሁሉ ተጠያቂ የሆኑ ግለሰቦች መሆናቸው ጉዳዩን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል። ሁለቱ ተቋማት በተፈጠሩት ችግሮች ዙሪያ የሰጧቸው የተናጠል መግለጫዎች ሃሳባቸው በአብዛኛው አሉባልታ የሚመስል ዋናውን ጉዳይ ያልነካና ለወደፊትም መፍትሄ የሚያመጣ ሆኖ አልተገኘም።
በኦሊምፒክ ኮሚቴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያልጠሩ አለመግባባቶች አሁንም እንደደፈረሱ ናቸው። ይህ ያልተፈታ ግጭት እንዳለ አሁንም በመግለጫ ጋጋታ እንደቀጠለ ነው። በሁለቱ መግለጫዎች ብቻም ጉዳዩ ይደመደማል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ አንዱ አንዱ ላይ ጣት ከመቀሰር የዘለለ ለስፖርቱ የወደፊት እጣ ፋንታ አንዳች ጥቅምና ተስፋ ያላመላከቱ የሁለቱ ተቋማት መግለጫዎች የበለጠ ነገሮች እንዲከሩ ማድረግ እንጂ ሁሉም ባጠፋው ልክ እንዲጠየቅ የማድረግ ምንም ምልክት የታየባቸው እንዳልሆኑ መረዳት ይቻላል፡፡
አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለኦሊምፒክ ኮሚቴ የመልስ ምት በሰጠበት የሐሙሱ የስካይ ላይት ሆቴል መግለጫ ከዚህ በኋላ ከኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር ምንም አይነት ግንኙነት እንደማይኖረው በይፋ አሳውቋል። በእርግጥ ለስፖርቱ ሰላም ሲባልም መንግስት አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
በኦሊምፒኩ ከተሰሩ ስህተቶች መካከል ግለሰቦችን የሚያስጠይቁ ጉዳዮች ቢኖሩም ሁለቱም ተቋማት ግለሰቦችን ከመከላከልና ተጠያቂ እንዳይሆኑ ከመታገል የዘለለ ፍላጎት እንደሌላቸው በግልፅ አሳይተዋል። ሁለቱም ተቋማት ጣት ከመጠቋቆም የዘለለ በኦሊምፒኩ ትልልቅ ችግር የፈጠሩ ጉዳዮችን አፍረጥርጠው በማውጣት መጠየቅ ያለበት እንዲጠየቅ ለመድፈር አልፈለጉም። በኦሊምፒኩ የተፈጠሩ እንደ የዓለም አትሌቲክስ ገበያ፣ የማኔጀሮችና ወኪሎች ፈላጭ ቆራጭነት ያሉ በርካታ ችግሮች ባለፈው ኦሊምፒክ ብቻ ሳይሆን በወደፊቱም የአገሪቱ ስፖርት ቀጣይ እጣ ፋንታ ላይ ትልቅ አደጋ እንዳንዣበበ አመላካች ቢሆኑም በሚገባ ሊነኩ አልተፈለገም።
የተፈጠሩት እነዚህ ችግሮች በሙሉ በሁለቱ ተቋማት ጣት የመቀሳሰር መግለጫ ብቻ ሊታለፉ ነው? ሁለቱስ ተቋማትና አመራሮቻቸው እንዳለፉት ዓመታት እንደተቃቃሩ ሊዘልቁ ነው? ወይንስ እንደለመዱት መገናኛ ብዙሃን ጠርተው ለይምሰል ታርቀናል ካሉ በኋላ ከተሰበሰቡበት አዳራሽ እንኳን ሳይወጡ ሽኩቻቸውን ሊጀምሩ ነው? ምላሽ ያላገኙ የበርካቶች ጥያቄዎች ናቸው። የተፈጠሩ ችግሮችን ሁሉ አንድ በአንድ መርምሮ የሚጠየቀው ተጠይቆ ወጥ የሆነ አቅጣጫ የሚያስቀምጥ እስከሌለ ድረስ ነገም የአገሪቱ የኦሊምፒክ እጣ ፋንታ ‹‹አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመልሱ›› እንደሚባለው እንደሚሆን መገመት ከባድ አይደለም፡፡
የፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ከሦስት ዓመታት ያነሰ ጊዜ ይቀረዋል። ፓሪስም ሌሎች የዓለም አገራትም ከቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ማግስት ለቀጣዩ ታላቅ የስፖርት መድረክ ሽር ጉዳቸውን የሚጀምሩት ዛሬ እንጂ ነገ አይደለም። የኢትዮጵያን ኦሊምፒክና አትሌቲክስ የሚመሩት ግለሰቦችም በጠቅላላ ጉባኤ ተመርጠው የአገልግሎት ዘመናቸው የሚጠናቀቀው ከፓሪሱ ኦሊምፒክ በኋላ ነው። ሁለቱ ተቋማትና አመራሮች በዚህ አይነት ውጥንቅጡ የወጣ ሽኩቻ ውስጥ ገብተው ነገም ፓሪስ ላይ ተመሳሳይ ነገር ተፈጥሮ ከማለቃቀስ ከወዲሁ ጉዳያቸውን መልክ ማስያዝ ለነገ የማይባል የቤት ስራ ነው።
የአገሪቱን ስፖርት በበላይነት የሚመሩት የመንግስት አካላት የሆኑት የኢፌድሪ ባህልና ቱሪዝም እንዲሁም ስፖርት ኮሚሽን በቶኪዮ የተፈጠሩ ችግሮችን በስፍራው ሆነው እየተመለከቱ ዝምታን በመምረጣቸው ነገሮች ፈር እንደሳቱ ኦሊምፒክ ኮሚቴም አትሌቲክስ ፌዴሬሽንም በመግለጫቸው ማስቀመጣቸው ይታወቃል። ዛሬ ግን ይሄ ዝምታቸው ‹መንግስት በስፖርቱ ጣልቃ አይገባም› በሚል ሰበብ ሳይሰበር መታለፍ የለበትም። አገርን በዓለም አቀፍ የስፖርት መድረኮች ላለማስቀጣትና ላለማሳገድ ያለው ስጋት ግልፅ ቢሆንም የአገሪቱ ስፖርት ከዚህ የበለጠ ኪሳራ እንዲደርስበት መፍቀድም ተገቢ አይሆንም። ነገሩ ‹‹ካልደፈረሰ አይጠራም›› ነውና ሁኔታዎችን በብልሃት አጢኖ የአገሪቱን ስፖርት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ፈር ማስያዝ ተገቢ ነው፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 24/2013 ዓ.ም