ጦርነት አስገዳጅ ካልሆነ በስተቀር አጥፊ እንደሆነ ለማንም የተሰወረ አይደለም ። በሰው እና በንብረት ላይ የሚያደርሰው ጉዳትም እንደ የጦርነቱ ባህሪ የሚሰላ ይሆናል ። ለዚህም በቀደሙት ዘመናት በሰው ልጆች ታሪክ ውስጥ ጥቁር ስፍራ አስቀምጠው የሄዱ በዓለማችን በተለያዩ ወቅቶች እና ስፍራዎች የተካሄዱ ጦርነቶች ያስከተሉትን ሰብአዊና ቁሳዊ ውድመት ማሰብ በቂ ነው።
ስም የተሰጣቸው የአንደኛው እና የሁለተኛው የዓለም ጦርነቶች አነሳሳቸው ትንሽ የሚመስሉ ክስተቶችን መሰረት አድርገው ቢሆንም ያስከፈሉት ዋጋ ግን ለማሰብ የሚከብድ እንደሆነ የታሪክ ድርሳናት ከፍ ባሉ የሰቆቃ ቃላት ከትበው ያስቀመጡት ነው ።
ከጦርነቶቹ በስተጀርባ የነበሩ የአስተሳሰብ መሰረቶችም ከፍ ያለ ራስ ወዳድነት እና የስነ ልቦና መዛነፍ ያለባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች የተዛባ አስተሳሰብ እንደሆነ የዓለም ታሪክ ያስረዳል።
ጦርነቶቹ የትኛውንም አይነት የአስተሳሰብ መሰረት ላይ ቢዋቀሩ ፣ የቱንም ያህል ዋጋ አስከፍለው ዓላማቸውን ያሳኩ በሚመስል ቁመና ላይ ቢታዩም የሰው ልጅ ከጦርነቶች ያተረፈው አንዳች ነገር የለም ። ወደ ፊትም የሰው ልጅ ውጤቱ ሞትና ውድመት ከሆነው ጦርነት ያተርፋል ተብሎ አይገመትም።
በተለይም የሰው ልጅ ከትናንት ጥፋቶቹ ተምሮ ስለ ሰላም አንድ አይነት ዜማ እያዜመ ባለበት በአሁኑ ወቅት አለመግባባቶችን በውይይትና በድርድር ከመፍታት ባለፈ ወደ ጦርነት የሚገባበት መንገድ ጤነኛና ዘመኑን የሚመጥን ነው ለማለት የሚያስደፍር አይደለም።
ሀገራችን ኢትዮጵያም በረጅም ዘመን ታሪኳ ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፋለች ።በእነዚህ ዘመን ውስጥ በከፍታዎችም በዝቅታዎችም የተገለጠችባቸው ሰፊ ታሪኮች አሏት ። ብዙ ለሉአላዊነት የተደረጉ የተጋድሎና የነጻነት ታሪክ ባለቤት እንደመሆኗ ሁሉ ካለመደማመጥ እና ከሴረኞች ሴራም የተነሳ የብዙ የእርስ በእርስ ጦርነቶችና የግጭቶች ታሪክ ባለቤት ሆናለች።
ከአብዛኞቹ የእርስ በርስ ጦርነቶችና የግጭት ታሪኮቻችን ውስጥ አንዳንዶቹ ከዘመኑ የፖለቲካ አስተሳሰብ ጋር የሚቆራኙ ፤ ሌሎቹ ደግሞ በግለሰቦችና በቡድኖች የስነ ልቦና መዛነፍ የተፈጠሩ ናቸው ። በእነዚህም ውስጥ የታሪካዊ ጠላቶቻችን እጆች በአንድም ይሁን በሌላው የግጭቶች አባባሽ አቅም ሆነው የተስተዋሉባቸው ናቸው።
በተለይም ከ1960 ዎቹ በሀገሪቱ የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ለሀገሪቱ ትልቅ ተስፋ የመሰነቃቸውን ያህል ካለመደማመጥ፣ ከራስ ወዳድነት እና ከግለሰቦች እና ቡድኖች የስነ ልቦና መዛነፎች የተነሳ የግጭቶች እና የጦርነቶች ምክንያት ሆነው ሀገርና ህዝብን ያስከፈሉት ዋጋ ከፍ ያለ ነው ።
ጎራ ከፍሎ ልዩነትን በማስፋት ላይ የተመሰረተው የዚህ ዘመን ሀገራዊ የፖለቲካ አስተሳሰብ ለውይይት እና ለድርድር ቦታ ካለመስጠቱም በላይ ልዩነቶችን በኃይል የመጨፍለቅን አካሄድ መምረጡ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሆኖ የህዝባችንን የአዲስ ቀን ተስፋዎች በልቷል ።
የኃይል አማራጭን መሰረት ያደረገው ሀገራዊ የፖለቲካ አስተሳሰቡ አንድም ሀገሪቱ የተለያዩ የፖለቲካ አማራጮች እንዳይኖራት፤ ዜጎችም አማራጮችን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ባህል እንዳይገነቡ ትልቅ ተግዳሮት ሆኗል ። ከዚህም በላይ በሀገሪቱ የፖለቲካ ባህል ውስጥ ኃይል እልፋና ኦሜጋ እንዲሆን አድርጓል።
ከዚህም የተነሳ ሕዝብ አልፈልግህም በቃኸኝ ያለውና በህዝባዊ ትግል በብዙ መስዋእትነት ከስልጣን የተባረረ ቡድን የስልጣን ተስፋውን በኃይል እውን ለማድረግ ባልተገባ መንገድ እንዲንቀሳቀስ ትምክህት ፈጥሮለታል ። ይህ መሰረቱ የተበላሸ አሮጌ የፖለቲካ አስተሳሰብ በየትኛውም መመዘኛ ሀገርን እና ህዝብን ሊታደግ የሚችል አይደለም ።
ለዚህም አሸባሪው ህወሓት እያደረገ ያለውን ማየት ተገቢ ነው ። ይህ ቡድን ከውልደቱ ጀምሮ የጠመንጃ አፈሙዝ በሚተፋው ጥይት አቅም ላይ የተመሰረተ የፖለቲካ ስትራቴጂ ነድፎ በነጻነት ትግል ስም በብዙ ንጹሀን ደም ወደ ስልጣን የመጣ ነው ።
ቡድኑ በስልጣን በነበረባቸውም 27 ዓመታት የአስተሳሰብ መሰረቱ ቀድሞውኑም ጤነኛ ስላልነበር ለሀገር ይቅርና ታገልኩለት ለሚለው የትግራይ ህዝብ የፈየደው አንዳችም ነገር የለም ።ለመላው ህዝባችን የመከራና የስቃይ ምንጭ በመሆን ነው የስልጣን ዘመኑን የጨረሰው ።
ስለ ነጻነት ብዙ ዋጋ የከፈለው የትግራይ ህዝብ ሳይቀር በነጻነት ትግል ስም በቡድኑ በከፋ ባርነት ውስጥ እንዲኖር ሆኗል። ህዝቡ አማራጭ የፖለቲካ አስተሳሰብ እንዳይኖረው በማድረግ የማሰብ ነጻነቱን ጭምር በግልጽና በተለያዩ የስጋት ትርክቶች ነጥቆት ዘመኑን በማይመጥንና ያልተገባ አስገዳጅ ህይወት ውስጥ እንዲያሳልፍ አስገድዶታል ።
ከዚህም በከፋ ሁኔታ ጦርነት ባህላዊ ጨዋታችን ነው በሚል የክፉዎችና የጨካኞች የገለማ ትርክት የትግራይ ወጣቶች ከዛም አልፎ እናቶችና አዛውንቶች ሳይቀር እራሱ በጫረው የእብሪት ጦርነት ውስጥ በመማገድ ለስልጣን ተስፋው ሕይወት ለመዝራት እየተንቀሳቀስ ይገኛል ።በዚህ የቡድኑ ከንቱ ተስፋ ከመኖር ተፋትቶ እያለቀ ያለውን የትግራይ ወገናችንን ቤቱ ይቁጠረው ።
የትግራይ ህዝብ ትናንትም ሆነ ዛሬ አሸባሪው ህወሓት በተለያየ ስም ካካሄዳቸው፤ ዛሬም እያካሄደ ካለው የእብሪት ጦርነት እንደ ህዝብ ያተረፈውም ሆነ ሊያተርፍ የሚችለው አንዳች ነገር የለም ፤ አይኖርም ። ይኖራል ብሎ ማሰብ ከትናንት ተጨባጭ ተሞክሮ ለመማር ፈቃደኛ አለመሆን ፣ ለእራስና ለመጪ ትውልዶች ደንታ ቢስ መሆን ነው ።
ይህን ደግሞ የትግራይ ህዝብ የቀደሙት አባቶቹ ስነልቦናዊ መሰረት የሚፈቅደው አይደለም ። ለዘመናት ጠብቆ ያቆያቸውን ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቶቹን የሚያጠለሹ ፤ ማህበረሰባዊ ስብእናውንም አደጋ ውስጥ የሚከት ተግዳሮት ነው ።
ይህንን ተግዳሮት አሸንፎ ለመውጣት ደግሞ የትግራይ ህዝብ እንደ ህዝብ ቆም ብሎ ማሰብና ወደ ቀልቡ መመለስ ይጠበቅበታል።ይህን ማድረግ ሲችል እንደቀደሙት ዘመናት ለራሱም ለሀገርም ባለውለታ ይሆናል ።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 24/2013 ዓ.ም