ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ካበቃ በኋላ የእንግሊዝ መንግስት በጦርነቱ አደጋ የደረሰባቸው ወታደሮችን ለመንከባከብ እንዲቻል ማዕከል ይቋቋም ዘንድ ለአንድ የአእምሮ ሃኪም ጥሪ አቀረበ።በደቡብ ምስራቃዊቷ እንግሊዝ በምትገኝ አንዲት ከተማም ይህ የአካል ጉዳተኞች ማገገሚያና የመንከባከቢያ ማዕከል እ.አ.አ 1944 ተቋቋመ።ይህንን ኃላፊነት የወሰደው ዕውቁ የአእምሮ ህክምና ባለሙያ ዶክተር ሉድዊግ ጉትማን አብዛኛዎቹ ወታደሮች የአከርካሪ ጉዳት የደረሰባቸውና መንቀሳቀስ የማይችሉ ቢሆኑም ከህክምናው ጎን ለጎን ስፖርት የተሻለ እገዛ ሊያደርግላቸው እንደሚችል ጽኑ እምነት ነበረው።
በተለይ አካላዊ ጥንካሬ እና በራስ የመተማመን አቅማቸውን እንደሚያጎለብት በታመነበት መሰረትም ጥቂት የእንግሊዝ አካል ጉዳተኛ ወታደሮች በማዕከሉ ስፖርታዊ ውድድር ማካሄድ ጀመሩ።ታሪካዊ ግጥምጥሞሽ ሆኖም ለንደን እ.አ.አ የ1948ቱን ኦሊምፒክ በምትከፍትበት ዕለት በማዕከሉ የሚገኙ ታካሚዎች ‹‹የዊልቸር ተጠቃሚዎች ስፖርታዊ ውድድር›› ሲሉ በሰየሙት ውድድር የእርስ በእርስ ፉክክር ያካሂዱ ነበር። በጊዜ ሂደትም ይህ ውድድር በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲካሄድ ለማድረግ እንቅስቃሴ ሲጀመርም ዶክተር ጉትማን የውድድሩ መጠሪያ ‹‹ፓራፕልጂክ›› እንዲሰኝ በማድረግ አሁን ያለበትን የስያሜ ቅርጽ ለማስያዝ ችለዋል።አንዳንዶችም ከኦሊምፒክ ጎን ለጎን የሚካሄድ በመሆኑ ‹‹ፓራለል ጌምስ›› ሲሉ ይጠሩት ነበር።
እ.አ.አ ከ1952 ጀምሮ ዓመታዊ ውድድር ለመሆን ሲበቃ 130 የሚሆኑ አካል ጉዳተኛ ስፖርተኞችም ከመላው ዓለም ይሳተፉ ነበር።ይህ ውድድር ይበልጥ ትኩረት እያገኘ ለመምጣት የቻለውም በዓለም አቀፍ ደረጃ በተከሰተው የፖሊዮ ወረርሽኝ የአካል ጉዳተኞች ቁጥር በመጨመሩም ነው።የፓራሊምፒክ አባት ተብለው የሚጠሩት ዶክተር ጉትማን ጥረታቸው ሰምሮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና ሲያገኙ፤ ለተቀደሰው ሃሳባቸውም በዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ እንዲሁም ከአካል ጉዳተኞች የስፖርት ውድድር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።እአአ 1960 በተካሄደው የሮም ኦሊምፒክ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ እንደ ታላቁ የኦሊምፒክ ውድድር ሁሉ በተቀናጀ ሁኔታ የአካል ጉዳተኞች ስፖርታዊ ውድድሮችም መካሄድ እንዳለባቸው በመታመኑ እንዲሁም በአካል ጉዳተኞች በተቋቋሙ ማህበራት ጥያቄ በመቅረቡ ፓራሊምፒክ ጌምስ ተሰኘ።
መነሻውን በእንግሊዝ ያደረገው የዊልቸር ተጠቃሚዎች ስፖርታዊ ውድድር በዓለም አቀፍ ደረጃ ራሱን የቻለ ማህበር ሲሆን፤ ሌሎች የጉዳት ዓይነቶችም በየራሳቸው መንገድ ማህበራትን አቋቁመዋል።እአአ 1980 ጀምሮም በህክምና ባለሙያዎች እገዛ የአካል ጉዳት አይነቶች ተለይተው ውድድር የሚካሄድባቸው ምድቦችን ለማዘጋጀት ተችሏል።ይህም ተመሳሳይ ጉዳት ያለባቸው አትሌቶች ባላቸው የመንቀሳቀስ አቅም እና ችሎታ የሰውነት ክፍል እንቅስቃሴ ወይም የጡንቻ ክፍሎች ቅልጥፍና እና ጥምረት የእንቅስቃሴን ስፋት በማየት መፈጸም እንዲችሉ ያደርጋቸዋል።
ሁሉን የጉዳት አይነቶች የሚያጠቃልለውና (የተፈጥሮም ሆነ ሰው ሰራሽ) በየአራት ዓመቱ ከኦሊምፒክ ማግስት የሚካሄደው የፓራሊምፒክ ውድድርም እአአ 1988 ደቡብ ኮሪያ አዘጋጅ በነበረችበት የሴኡል ኦሊምፒክ ጠቅላላ ጉባኤ፤ ዓለም አቀፍ የፓራሊምፒክ ኮሚቴ ተቋቁሞ በራሱ እንዲመራ ለማድረግ ተችሏል።በጥቂቶች የተጀመረው ይህ ውድድርም አሁን ላይ ከኦሊምፒክ እኩል በርካታ ሃገራት በሺዎች በሚቆጠሩ ስፖርተኞች የሚወከሉበት ደማቅ ውድድር ለመሆን በቅቷል።ይህም ብቻ ሳይሆን እንደበጋው ሁሉ የክረምት ፓራሊምፒክ ውድድር የሚካሄድበትም ነው።
ቁጥራዊ ንጽጽሩን ለመመልከት ያህልም የመጀመሪያው ውድድር በተካሄደበት የ1960ው ፓራሊምፒክ ከ23 ሃገራት የተወጣጡ 400 አትሌቶች ብቻ ነበሩ ተሳታፊዎቹ።ከዓመታት በኋላ በተካሄደው እአአ 2012ቱ የለንደን ኦሊምፒክ 100 ሃገራት በሺዎች የሚቆጠሩ
አትሌቶች ተካፋይ የሆኑበት ነበር።በበጋው ፓራሊምፒክ 22 የስፖርት ዓይነቶች ውድድር የሚካሄድባቸው ሲሆን፤ በክረምቱ ፓራሊምፒክ ደግሞ 5 ስፖርታዊ ውድድሮች ይደረጋሉ።በዚህ ወቅት እየተካሄደ ባለው የቶኪዮ ፓራሊምፒክም ኢትዮጵያን ጨምሮ 163 ሃገራት 4ሺ537 አትሌቶችን በ22 ስፖርቶች እያወዳደረ ይገኛል።ከ1960-2016ቱ የሪዮ ፓራሊምፒክ ድረስም አሜሪካ 2ሺ175 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ ቀዳሚዋ ሃገር ስትሆን፤
1ሺ789 ሜዳሊያዎች ያሏት እንግሊዝና 1ሺ443 ሜዳሊያዎችን የሰበሰበችው ጀርመን ሁለተኛ እና ሶስተኛ ናቸው።ቻይና፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ ፈረንሳይ፣ ሆላንድ፣ ስዊድን እና ፖላንድ ደግሞ እስከ አስር ባለው ደረጃ የተቀመጡ ሃገራት ናቸው፡፡
በዚህ የፓራሊምፒክ ውድድር ልዩነት በማስመዝገብ በተለይ አንድ ስም የምንጉዜም ተጠቃሽ ነው።ብቻዋን በርካታ ሜዳሊያዎችን በማጥለቅ በክብር የደመቀችው
ይህቺ አትሌት ትሪቺያ ዞርን ትባላለች።ዞርን አሜሪካዊት ዋናተኛ ስትሆን በተፈጥሮ የአይነ ስውርነት ጉዳት አለባት።በ7 ፓራሊምፒኮች (እአአ1984፣ 1988፣ 1992፣ 1996፣ 2000 እና 2004 በተካሄዱት ፓራሊምፒኮች) ላይ ሃገሯን የወከለችው ዞርን ብቻዋን ባስቆጠረቻቸው ሜዳሊያዎች ብዛት በርካታ ሃገራትን ቀድማ መቀመጥ የምትችል ስፖርተኛ ናት።
ወደር ያልተገኘላት ልበ ብሩኋ ዋናተኛ 41 የወርቅ፣ 9የብር እና 5ነሃስ በጥቅሉ 55 ሜዳሊያዎች አሏት።ይህም ለሃገሯ በበርካታ ስፖርተኞች ሊመዘገብ የሚችል የሜዳሊያ ቁጥር ሲሆን፤ በደረጃ ሰንጠረዡ ሃገሯ ልዩነት እንድታመጣ ከፍተኛ ሚና ያለው መሆኑ እሙን ነው።ዞርን እንደ ሃገር በሜዳሊያ ሰንጠረዡ ብትቀመጥ ከሩሲያ እኩል 41ኛ ላይ መቀመጥ ትችላለች።
በእርግጥም በተፈጥሮም ሆነ በአደጋ ለአካል ጉዳት የተጋለጡ ሰዎች ስፖርት ከፍተኛ ጠቀሜታ አለው።የመጀመሪያው ነገር ሰዎች በጉዳታቸው ምክንያት ማከናወን የማይችሏቸው ጉዳዮች መኖራቸውን እንዳያስቡ ያደርጋቸዋል።እንደ ሌሎች ጉዳዮች ሁሉ በስፖርታዊ እንቅስቃሴዎች በመሳተፍ አካላዊ ጤናቸውን ለመጠበቅ እንዲሁም ሰውነታቸውን ለማዝናናት ከስፖርት የሚገኘውን አካላዊና አእምሯዊ ጥቅምን ያተርፋሉ።ስፖርተኛ በመሆን ህይወታቸውን የሚመሩበት መንገድም ያለ ሲሆን፤ ወዳጆችን ለማፍራትና ከሰዎች ጋር ለመግባባትም ስፖርት አይነተኛ አማራጭ ነው።ስፖርት አስቀድሞ ጤናን እና አካልን ከጉዳት ለመጠበቅ የሚያግዝ መሳሪያ ከመሆኑም ባለፈ ከጉዳት ለማገገምም በጤና ባለሙያዎች እንደ መፍትሄ ይወሰዳል።በመሆኑም አካል ጉዳት ያለባቸው ሰዎች በስፖርት የጉዳት መጠናቸውን የመቀነስ አጋጣሚውን መፍጠር ይችላሉ።ስፖርት በራስ የመተማመን አቅምን በማጎልበትና በራስ የመተማመን ኃይልን በማላበስ ረገድም ተወዳዳሪ የሌለው ነው።
በፓራሊምፒክ ውድድሮች የበላይነቱን የያዙት አውሮፓዊያን ያደጉ ሃገራት ሲሆኑ፤ በአንጻሩ አፍሪካ ተሳትፎዋ የነሰ አህጉር ናት።መቀመጫውን በአንጎላ ያደረገው የአፍሪካ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ በስሩ 48 አባል ሃገራት አሉት።በሜዳሊያ የደረጃ ሰንጠረዡ ለመመልከት እንደሚቻለው ከሆነም ግብጽ በአህጉር አቀፍ ደረጃ የበላይ ስትሆን 157 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብ 30ኛ ላይ ትገኛለች።ቱኒዚያ፣ ናይጄሪያ፣ አሌጄሪያ፣ ኬንያ እና ሞሮኮ ደግሞ ተከታዮቹ ሃገራት ናቸው።ኢትዮጵያ በበኩሏ ከኳታር ጋር በእኩል የሜዳሊያ ብዛት በደረጃ ሰንጠረዡ 106ኛ ላይ ትገኛለች።ሃገሪቷ ይህንን ውጤት ያገኘችውም ባስመዘገበችው 2 የብር ሜዳሊያዎች ነው።
የአካል ጉዳተኞች ስፖርት ወደ ኢትዮጵያ በስፋት መቸ እንደተጀመረ ባይታወቅም፤ የአካል ጉዳተኞች ስፖርት ማህበር እንዲቋቋም በር የከፈተው ግን የማራቶኑ ጀግና ሻምበል አበበ ቢቂላ መሆኑን የኢፌዴሪ ስፖርት ኮሚሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል። ሻምበል አበበ ቢቂላ በ1961 ዓም በአጋጠመው የመኪና አዳጋ ምክንያት የአካል ጉዳት ከደረሰበት በኃላ እአአ በ1971 ዓለም አቀፉ ስቶክ ማድብልስ ጨዋታ ፌዴሬሽን ባዘጋጀው የአካል ጉዳተኞች ስፖርት ውድድር በመሳተፍ ውጤት አስመዝግቧል።ወደ ሃገሩ ከተመለሰ በኃላም የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ስፖርት ማህበር በ1964 ዓም ሊቋቋም ችሏል ።
ማህበሩ በሂደትም ስለ አካል ጉዳተኞች ስፖርት ምንነት እና ጠቀሜታ ለህብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲያስጨብጥ እና ስፖርቱን የበለጠ በሀገሪቷ እንዲያስፋፋ ታስቦ በ1989 ዓም የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኞች ስፖርት ፌዴሬሽን በሚል እንደገና ተደራጀ። በመቀጠልም በ1994 ዓም የኢትዮጵያ ፖራሊምፒክ ኮሚቴ የሚለውን ስያሜ በመያዝ እስካሁን አካል ጉዳተኛው ማህበረሰብ በስፖርት ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲሆን እየሰራ ይገኛል። በተለይም የአካል ጉዳተኛው ማህበረሰብ በስፖርት በመሳተፍ ጤንነቱን እንዲጠብቅ ግንዛቤ ከመፍጠር ባሻገር የተሻለ ብቃት ያላቸውን አካል ጉዳተኞች በመለየት እና ተገቢውን ስልጠና እንዲያገኙ በማድረግ በአህጉር እና ዓለም አቀፍ ውድድሮች በመሳተፍ ውጤታማ እንዲሆኑ እየሰራ እንደሚገኝም በመረጃው ተመላክቷል።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2013