ልጆቼ እንዴት ናችሁ። ሁሉ ሰላም ነው? ክረምት ሲመጣ ከሆያ ሆዬ ቀጥሎ የሚከበረው በኣል አሸንዲዬ፤ አሸንዳ፤ ሻደይ፤ ሶለል ይባላል። ይህ በኣል ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? አሸንዲዬ፡ አሸንዳ፡ ሻደይ፡ ሶለል በመባል የሚጠራው የቄጠማ ቅጠል የሚመስል የለመለመ የሳር ዓይነት ነው፡፡
ይህ በዓል ምንጩ ሃይማኖታዊ (የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ) ሆኖ ከፆመ ፍልሰታ መውጫ እስከ ነሃሴ 21 ቀን ድረስ በታላቅ ድምቀት የሚከበር ሲሆን እንደየ አካባቢው የተለያዩ ስያሜዎች አሉት፡፡ በወሎ ያሉት የዋግ ኽምራ ሰቆጣዎች ሻደይ፣ ላስታ ላሊበላዎች አሸንድዬ፣ ቆቦና አካባቢዋ ሶለል፣ የአክሱም ነዋሪዎች ዓይነ ዋሪ እያሉ ሲጠሩት፤ ትግራይና አካባቢዋ ደግሞ አሸንዳ እያሉ ይጠሩታል፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ እምነት ሰለዚህ በኣል አንዲህ የሚል አሳቤ አላት። የአዳም ከገነት መባረር ለማስታወስ ልጃገረዶች ተሰባስበው አሸንዳ የሚባለውን ቅጠል ማገልደማቸው አዳምና ሄዋን ኃጢአትን ሰርተው ልብስ የሆናቸው ፀጋ እግዚአብሔር ሲርቃቸው እርስ በርሳቸው ሲተያዩ ራቁታቸውን መሆናቸውን አውቀው ኃፍረተ ሥጋቸውን በቅጠል ሸፍነው ነበር፡ ፡ ስለሆነም በዚህ በዓል ይህን ለማስረዳት አሸንዳ ቅጠልን ያገለድማሉ፡፡
ሌላው በኖኅ ዘመን የነበረውን የጥፋት ውኃን የሚያስታወስ ነው። በፃድቁ በኖህ ዘመን ኖህ ከነቤተሰቦቹና እንዲሁም በኖህ የተመረጡት ከእያንዳንዳቸው አንድ ተባዕትና እንስት እንስሳት በስተቀር በኃጢአት ምክንያት ፍጥረት ሁሉ ከላይ በሚዘንብና ከታች በሚፈልቅ ንፍር ውሃ አልቀዋል፡፡ ኖህና ቤተሰቦቹ እንዲሁም ተመርጠው የነበሩት እንስሳትም በመርከቧ ውስጥ ስለነበሩ በእግዚአብሔር ጥበብ ተርፈዋል፡፡ ውሃውም መጉደሉን ለማረጋገጥ መጀመሪያ ኖህ ቁራን ላከው፡፡ ቁራው ግን የሞተውን እየበላ በዛው ወጥቶ ቀረ፡፡
ዛሬ ተልኮ ወጥቶ በዛው የውሃ ሽታ የሆነን ሰው የቁራ መልእክተኛ የምንለው ከዚህ የመጣ ነው፡፡ ሗላ ግን ኖህ እርግብን ውሃው መጉደሉን አይታ እንድትመጣ ሲልካት የተላከችበትን ተልዕኮ ፈፅማ የጥፋት ውሃ ጎድሏል ስትል
የለመለመ የወይራ ቅጠል ይዛ ተመልሳለች፡፡ ስለሆነም በዚህ በዓል የለመለመ ቅጠል መያዛቸው ከእንግዲህ ወዲህ እግዚአብሔር ሕዝቡን በንፍር ውሃ ላያጠፋ ቃል ገብቷል፡፡ ወቅቱም ዝናብ እየቀነሰ ባህር እየጎደለ ስለሆነ የጥፋት ውሃ ጎድሎ አበባ የሚታይበት ፍሬው የሚናፈቅበት የደስታ ጊዜ መሆኑን ሲያበስሩ ነው፡፡
ሌሎች ሃይማኖታዊ ትርጓሜዎች ቢኖሩትም በይበልጥ ግን የልጃገረዶች የነፃነት በኣል በመሆንይታወቃል። በተለያዩ የጭፈራ አይነቶች የሚደምቀው ይህ ባህላዊ በኣል ለሀገራችን ተጨማሪ መስህብም ነው።
ክረምቱ አልቆ ወደ አዲሱ ዘመን እየተቃረብን ስለሆነ ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ተዘጋጁ እሺ። መልካም ጊዜ ይሁንላችሁ።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2013