ክሊኒካል ሳይኮሎጅስት መአዛ መንክር ካላቸው እውቀት ላይ ለወላጆች የሚጠቅሙ ስነልቦናዊና ስነባህሪያዊ እሳቤዎችን እያነሱ በዚህ አምዳችን በተከታታይ ሲያካፍሉን ቆይተዋል። ለዛሬ ደግሞ ልጆች ከመልክና ገፅታቸው ጋር በተያያዘ በራሳቸው የሚተማመኑ እንዲሆኑ ከወላጆች ምን ማድረግ እንደሚጠበቅ፣ መደረግ ስለሚኖርበት ጥንቃቄ ይመክሩናል። መልካም ንባብ።
ወይዘሮ መአዛ ለዚህ ፅሁፍ መነሻ የሆናቸውን ገጠመኝ ሲያስታውሱ የስነልቦና ህክምና እርዳታ እንዲደረግላት የመጣች አንድ ወጣት የነገረቻቸውን ግለ ታሪክ ያነሳሉ፡፡
“ተማሪ ነኝ። እስከ 9ኛ ክፍል በጣም ደስተኛና ትምህርቴን በአግባቡ የምከታተል ነበርኩ። ከሆነ ጊዜ በኋላ ግን ትኩረቴ ተቀየረ። መስታወት ፊት ደጋግሜ ሳይ ውዬ ባድር አልጠግብም። መልኬ አስጠሊታና በተለይ ግንባሬ በጣም ወጣ ያለ ሆኖ ይታየኛል፤ በጣም እጨነቃለሁ። አንዳንዴ ከቤተሰቦቼ ጋር ወጣ ስንል ሰው ሁሉ እኔን ያየኛል። ምክንያቱ ደግሞ ግንባሬ የተለዬ ስለሆነ ነው። እንደዚህ መጨነቅ ከጀመርኩ ሁለት አመት ሊሆነኝ ነው። ሰው አጠገቤ ሆኖ ከማውራት ይልቅ በሀሳብ ጭልጥ እላለሁ። እንዲያውም ባል የማገባ አይመስለኝም። ምክንያቱም ግንባራምን ማን ይፈልጋል? የሚል ስሜት ፈጥሮብኛል፡፡” እንዳለቻቸው ያስታውሳሉ።
ከዚህ በመነሳት ወ/ሮ መዓዛ እንዲህ በማለት ምክራቸውን ይለግሳሉ። ከልክ ያለፈ ሰውነት/መልክ ተኮር ጭንቀት (body dysmorphic disorder) የአእምሮ ህመም ነው። እንደዚህ አይነት የአእምሮ ህመም ያለባቸው ሰዎች ራሳቸውን ከላይ በተቀመጠው መንገድ የሚገልፁና በሴቶችም ሆነ በወንዶች ላይ የሚከሰት ችግር ነው። ከ50 ሰው በአንድ ሰው ላይ ችግሩ ሊታይ ይችላል። ችግሩም ከ12 አመት ጀምሮ ባለው እድሜ መታየት የሚጀምርና ህክምና ካልተደረገ እየቀጠለ የሚሄድ ነው።
በዚህ ህመም የተጠቁ ሠዎችም ጊዜያቸውን ሁሉ አላምርም ወይም ጎደሎ አለብኝ የሚሉት ላይ ብቻ ያተኩራሉ።
ችግሩን ለመሸፈን ሜካፕ እና የተለያዩ ነገሮች ያደርጋሉ፡፡ ብሎም ፕላስቲክ ሰርጀሪ እስከማድረግ ይወስናሉ። ሰው ሁሉ ስለጉድለታቸው የሚያወራና የሚተቻቸው ይመስላቸዋል። ራሳቸውን ከሌሎች ጋር ያነፃፅራሉ። ራሳቸውን ከሰው ያገላሉ። ለከፍተኛ ጭንቀት፣ ድብርትና ራስን ማጥፋት ሊዳረጉ ይችላሉ። መፍትሔው የስነአእምሮ ሀኪም ወይም ባለሙያ ጋር በመሄድ ህክምና ማግኘት ነው።
በተለይ የአዕምሮ ስነባህሪ ህክምና (Cognitive Behavior Therapy) የተባለው የህክምና አይነት በጣም የሚያግዝ ህክምና ነው። የአእምሮ ህመም አይነቱ ብዙ እንደመሆኑ መጠን ህክምናውም እንደዛው ብዙ አማራጭ ያለው ነው።
ልጆችን ከስር ጀምሮ መከታተል የወላጅ ሀላፊነት ሲሆን እያንዳንዳቸው የሚገጥሟቸውን ችግሮች በጊዜ መፍትሄ መስጠት ይገባል። እንደቀላል እያሰብን ከአፋችን የምናወጣቸው፤ አንቺ ሸፋፋ፤ ባሪያ፤ አስቀያሚ እና መሰል ተራ የሚመስሉ ቃላት ልጆቹ እንደዛ ነን ብለው እንዲያስቡ ስለሚያደርጋቸው ለአእምሯቸው መጠንቀቅ ተገቢም ነው።
ልጆቻችን ለገፅታቸው አዎንታዊ አስተያየት በመሥጠት መልካቸውን እንዲወዱት እና በራሳቸው የሚተማመኑ እንዲሆኑ ልናግዛቸው ይገባል ብለዋል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2013