ከአፍ እስከገደፉ በወጣት ሴቶች የተሞላው አዳራሽ ፀጥ ረጭ ብሏል። ከወይዘሮዋ አንደበት የሚወጣው ቃል አንዱም እንዲያመልጣቸው የፈለጉ የሚመስሉ ጆሮዎቸ በጉጉት ተቀስረዋል። የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ወጣቶችና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ̋የህይወት ልምዴን አካፍላለሁ” በሚል ሀሳብ በአዲስ አበባ ከተማ ከሁሉም ክፍለ ከተሞች ለተውጣጡ ሴቶች የህይወት ልምዳቸውን የሚያካፍሉትን ሴት ታሪክ በማድመጥ ላይ ናቸው።
በኤልያና ሆቴል በተዘጋጀ መርሀግብር የህይወት ልምዳቸውን ያካፈሉበት የአዲስ አበባ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተስፋ መቁረጥ የሰኬት እንቅፋት ̋አንቺ አትችይም” የሚሉ ድምጾችን ባለመስማት ሰርቶ ለማሳየት መጣር የስኬት ቁልፍ መሆኑን፤ ከሁለት አስርት አመታት በላይ በሀላፊነት ሲያገለግሉ የተለያዩ ተግዳሮቶችን ማለፋቸውን፤ እንዲሁም ከልጅነት እስከ እውቀት ያለፏቸውን የህይወት ወጣውረዶች ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚህ መልኩ አቅርበውታል።
በቅድሜያ እድሜዬ 48 ነው፤ ለሚቀጥለው ታህሳስ ልደት አብረን እናከብራለን ማለት ነው። ተወልጄ ያደኩት በአርሲ ዞን ነው። ብዙ ታላላቆቼ የትምህርት እድል ባያገኙም እኔ ግን በትንሽ እድሜዬ በአቅራቢያችን በነበረ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት በጊዜ ነበር ትምህርቴን የጀመርኩት። ትምህርት ቤቱ ትንሽ ከአካባቢያችን ራቅ ቢልም አንዳንዴ አባቴ በፈረስ እያደረስኝ አንዳንደ ጊዜ ደግሞ በእግሬ እየተመላለሰኩ እማር ነበር። ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴንም ከአካባቢያችን ወጣ ባለ ቦታ ከወንድሞቼ ጋር ሆኜ ከቤተሰብ ተለይቼ ጨረስኩኝ። በትምህርቴም ጎበዝ ነበርኩ አንዳለመታደል ሆኖ ግን የአስራ ሁለተኛ ክፍል ወጤቴ ዩኒቨርሲቲ እንድገባ እድል ባይሰጠኝም በመምህራን ማሰልጠኛ ተቋም ተምሬ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርት ሆንኩ። የመምህርነት ሰልጠና ላይ እያለሁም ግን ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ የሚሆን ወጤት ለማምጣት ነበር የምለፋው፤ እናም ተሳክቶልኝ ዲግሪ ለመከታተል የሚያበቃ ውጤት አመጣሁ።
ለእኔ ትዳርም ሆነ ለመውለድ መድረስ ካለኝ መንገድ ወደኋላ የሚያስቀረኝ አለመሆኑን ተረድቻለሁ። በመሆኑም ወደ ትዳር ህይወት ከገባሁ በኋላ የሁለት ልጆች እናት ሆኛለሁ። እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ቤተሰብ በእኔ እርዳታ ቤት የሚኖሩ የሚማሩ ቤተሰቦች አሉኝ። በትዳርም ለሀያ አምስት አመታት በስኬት ከባለቤቴ ጋር ነው የኖርነው። ባለቤቴ ለእኔ መምህሬ፤ መካሪዬ፤ አራሚዬም በአጠቃላይ ደጋፊዬ ነው።
በወቅቱ በሀገራችን ለመጀመሪያ ገዜ ለሚካሄድ የወረዳ ምርጫ ግንባር ቀደም ሆኜ በእጃችን ያለውን አድል በመጠቀም መሪ ለመሆን የሚያሰችል ሁኔታ በምኖርባት ወረዳ ሴት እጩ ተወዳዳሪ አለመኖሯን ሰምቼ ተወዳደርኩ። በወጣትነት ወደ ህዝብ አገልግሎት ብገባም የትምህርቴን ነገር ቸል አላልኩምና በሕግ የመጀመሪያ ዲግሪዬን ልይዝ ችያለሁ።
ከዛም በኦሮሚያ ፍትህ ቢሮ በአቃቤ ሕግነት እያገለገልኩ ለሁለተኛ ድግሪ በምማርበት ወቅት ትምህርት፣ ስራና ሀላፊነት አብሮ እንዳማይሄድ ሲነገረኝ ህዝብን የማገልገል ሁኔታን መርጬ ዊዚድሮ (ጊዜአዊ ትምህርት የማቋረጫ ፎርም) ሞልቼ ስራዬን መስራት ጀመርኩ፣ እንዲሁም በ1997 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆኜ በመመረጥ በተለያዩ ኃላፊነቶች አገልግያለሁ። ለስድስት ዓመታትም ያህል የኦሮሚያ ልማት ማኅበርን መርቻለሁ። ነገር ግን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገጠመኝን ተግዳሮት ፊት ለፊት በመጋፈጤ ከስራ ታገድኩ።
ይሁንና ከስራዬ ታገደኩ፣ እንዲህ ሆንኩ በሚል መከፋት ወደኋላ አልቀረሁም። መማር ስለነበረብኝ ሁለተኛ ዲግሪዬን ያዝኩ። ከእያንዳንዱ ክፉ ከመሰሉን ገጠመኞች መካከል ጥሩ አጋጣሚዎችን በመፈለግ እድሎችን መጠቀም ተገቢ ነው። እናንተ ወጣት ሴቶች ስለሆናችሁ እንቅፋትን እንደ ተራራ መመልከት ሳይሆን የመታችሁን ድንጋይ ለጥቅም ማዋል ነው ተገቢው ነገር።
እያንዳንዱን ውጣ ውረድ ለማለፍ ምን አቅም ሆነሽ ብትሉኝ ሌሎች የሚሉኝን ሳይሆን እኔ ማነኝ፣ ምን አችላለሁ ብዬ በመጠየቅ መስራት ከምችለው ነገር መምታት ከምችለው ግቤ ሊያስቀረኝ የማይችል መሆኑን ለራሴ ነግሬዋለሁ። አናንተም በራሳቸሁ መንገድ ራሳችሁን መሳመን አለባችሁ።
በህይወቴ የተለያዩ ነገሮች ነው የማደርገው፤ ያው በዚህ ደረጃ በኃላፊነት ላይ ሲኮን ሁልጊዜ ሥራን እያሻሻሉ መሄድም ያስፈልጋል። መረጃዎች ያስፈልጋሉ። አነባለሁ። ሁለተኛ ነገር ደግሞ እግዚአብሔርን ማምለክ በጣም እወዳለሁ። ያለኝን ትንሽ ሰአት ለሁለቱ አካፍላለሁ። ከቤተሰቤ ጋር ቡና መጠጣት፣ ማውራት፣ ውሏችን፣ ሕይወታችን አንዳንድ ነገሮች እናወራለን። ለጎረቤቶቼ ጎረቤት፣ ለቤቴ ምርጥ እማወራ፤ ለልጆቼ ተገቢውን ነገር በሙሉ የምታደርግ እናት፤ ለባለቤቴም ጥሩ ሚሰት ለመሆን ማድረግ የምችለውን ነገር ሁሉ አደርጋለሁ።
በተለይ “የማልረሳው” ብዬ የማስታውሰው ነገር አንዴ እኔ የምመራው ስብሰባ ኖሮ ልጄን የሚይዝልኝ ሰው አጣሁ፤ ያኔ ሰብሰባውን መሰረዝ የማይሆን ሲሆን ልጄን አዝዬ ስብሰባውን መርቼ ወጣሁ። ልጄን የሚይዝልኝ የለም ብዬ ከስብሰባው መቅረት እኔ ለምመራቸው ሰዎች ምን አይነት አርአያ ይሆናል ብዬ እራሴን ጠየኩ፤ ወሰንኩም። ሰው ጉድ እያለ ልጄን ይዤ ስብሰባ መርቻለሁ። በህይወት ውስጥ ያው ውጣ ውረድ አለ። በራስ ጉዳይ ብቻ አይታዘንም፤ በራስሽ ጉዳይ ብቻ መደሰት አይቻልም። እንደማንኛውም ሰው የማዝንበትም የምደሰትበትም ያጋጥመኛል፤ እያጋጠመኝ ነው የኖርኩት፤ ሁሌም ግን ከፊቴ ያሰቀመጥኩት አላማ ጋር ለመድረስ እተጋለሁ።
ወጣት ሴቶች ለቁሳዊ ነገሮች መጨነቅ ሕይወታቸውን እንዲቆጣጠረው በመፍቀድ ከሚገባው በላይ መሄድ የለባቸውም። ከዚህ ይልቅ በአስተሳሰብ ጤናሞች፣ ንጹሖች፣ በጎዎች . . . ከሁሉም በላይ ደግሞ ባህላቸውን ጠንቅቀው የሚያወቁ፤ ትችቶችን በማዳመጥ የማይደክሙ፤ የማይረቱ፤ ሁል ግዜ ንቁና አካባቢያቸውን የሚያስተውሉ፤ ከሚያስተውለት ነገር ወስጥ ወደፊት የሚያራምዳቸውን ነገር መፍጠር የሚችሉ ትጉህ መሆን አለባቸው።
በሀላፊነት ቦታ ላይ ሴቶች ካሉ ሁሌም ስኬት አለ። ሴቶች ውስጥ ትልቅ አቅመ አለ። ትችላላቸሁ። አላማብቻ ይኑራችሁ። በማንኛውም የህይወት መስመር ወስጥ መድረስ የምትፈልጉበት ግብ ይኑራችሁ። ያኔ ከጎን፣ ከፊት፣ ከኋላ የሉ ድምፆችን መስማት ትታችሁ ግባችሁ ጋ ለመድረስ ወደፊት ትገሰግሳላችሁ።
እጄ ላይ ያለን እድል እንዴት ወደ ስኬት መቀየር እችላለሁ? በሚል እሳቤ ራሳችሁን መምራት ትክክለኛመንገድ ነው። ሌሎች እድሎችን እስኪያመቻቹላችሁ መጠበቅ ተገቢ አይደለም። የስኬት ጉዞ ከራሰ ነው የሚጀምረው፤ እናንተ አንድ፣ ሁለት እያላችሁ ወደ ከፍታ መውጣት ስትጀምሩ ስኬት ራሱ ይከተላችኋል፤ ላለው ይጨመርለታል አይደል የሚባለው።
በህይወቴ ህዝብ እንደማገልገል የሚያስደስተኝ የለም፤ አቃቤ ህግ እያለሁ እንደ ፍትህ የሚያስደስተኝ ነገር የለም። የተዛባ ነገር፣ አረዳድ ሊሆን ይችላል። በፍርድም እጦት ሊሆን ይችላል። ያ ነገር ሲፈታ የተለየ ነገር ይፈጥርብኛል፤ የተለየ ስሜት የሚሰጠኝ እሱ ነው። አሁን ደግሞ በየአንዳንዱ ሰው ህይወት ውስጥ ያሉ ችግሮችን ማቅለል፤ ለሌሎች ድጋፍ መሆን፤ አስተዳደራዊ ክፍተቶችን በመሙላት ትክክለኛ የመሪነትን ስራ መስራት፤ ከህዝብ ማህፀን ወጥቶ ህዝብን እንደማገልገል የሚያስደስተኝ ነገር የለም።
ለኢትዮጵያ ካለኝ ኃላፊነት የራሷን ወጪ በራሷ መሸፈን የምትችል ሃገር እንድትሆንና እንደገናም እዛ ላይ መድረስ እንድንችል እመኛለሁ። እንደ አጠቃላይ እንደ ሃገር ጥንታዊ ታሪክ ያላት ብትሆንም ነገር ግን እድገቷም ዛሬ ያለችበትን በምናይበት ሰአት ወደ ኋላ ከቀሩ ሃገራት ተብላ የምትጠቀስ ሃገር ነች። ስለዚህ ለሃገሬ እድገትና ብልፅግና የዜጎቿን መበልፀግና መለወጥ ማየት እፈልጋለሁ።
ሴቶች ደግሞ የማደግና የመበልፀግን ሄደት ከሚያፋጥኑት መካከል ናቸው። በተለይ እንደእናንተ ገና ወጣት የሆኑ ሴቶች፤ ለሀገር ትልቅ አቅም ናችሁ። አቅም ሲባል ህዝብ ሀብት እንደመሆኑ በትንሽ ትጋት ብዙ መለወጥ የሚችሉ ሴቶች በእድገት ጎዳናው ላይ ከተቀላቀሉበት የሀገራችን አድገት እውን የሚሆንበት ቀን ቅርብ ይሆናል ማለት ነው።
ለሁሉም ነገር በማንኛውም ውጣ ወረድ ውስጥ እችላለሁ፣ አደርጋለሁ ብሎ በመስራት፤ ሀላፊነትን በአግባቡ በመወጣት ሁሉም በእምነቱ ፀሎት በማድረግ የራሱን ዋጋ ከፍ በማድረግ አላማን ማሳካት ይቻላል። እኔ በቤተሰቤ፤ በአላማዬና በመንፈሳዊ ህይወቴ ላይ በተመሰረተ መሰረት ላይ ቆሜያለሁ። ከእያንዳንዱ ጥንካሬ ጀርባ የእነዚህ የሶስቱ ድምር ውጤት አለ። በማለት አጠቃላይ የህይወት ልምዳቸውን፣ እስከደረሱበት ደረጃ ድረስ ያለውን ተሞክሯቸውን፤ የመጡበትን የህይወት መንገድ ከነውጣ ውረዱ በቅደም ተከተል ለታዳሚ ወጣት ሴቶቹ አካፍለዋል።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2013