ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች፣ ሲምፖዚየሞች፣ ስልጠና እና የተለያዩ ኩነቶች በማዘጋጀትና በስፋት በማካሄድ፣ እንዲህ ላሉ የተለያዩ ኩነቶች ተመራጭ ሀገር ሆና ስትንቀሳቀስ ቆይታለች። ክልል ከተሞችን ጨምሮ በመዲናዋ አዲስ አበባ ከተማ ይካሄዱ የነበሩ ኩነቶችን ተከትሎም ደረጃቸውን የጠበቁ ሪዞርቶችን ጨምሮ የሆቴልና መስተንግዶ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማት በስፋት ተገንብተዋል። መንግሥትም የሆቴል ኢንቨስትመንቱ እንዲስፋፋ በማበረታቻዎች በመደገፍ ሚናውን ሲወጣ ቆይቷል። በእንዲህ ያለው እንቅስቃሴ ውስጥም ሰፊ ቁጥር ላለው ዜጋ የሥራ ዕድል ተፈጥሯል። በሀገር የኢኮኖሚ ዕድገት ላይም የማይናቅ ሚና ተፈጥሯል።
ስብሰባንና ኤግዚቢሽንን ማዕከል ያደረገው እንቅስቃሴም ‹‹ማይስ ቱሪዝም›› በመባል ይታወቃል። ማይስ ከቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፎች አንዱ ሲሆን፣ ብዙ ሀገሮች ዘርፉን በኢኮኖሚ ማስገኛነት በመጠቀም ለውጥ አስመዝግበውበታል። ኢትዮጵያም ወደዚሁ በመንደርደር በእንቅስቃሴ ላይ እያለች ነው ሁለተኛ አመቱን የያዘው ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታ ተከስቶ በእንቅስቃሴው ላይ ጥላውን የጣለበት። በሽታው እንቅስቃሴን በመገደብ ዓለም በሩን ዘግቶ በቤቱ ውስጥ እንዲቀመጥ በማድረጉ ከሁለት አመት በፊት እንደነበረው ስብሰባዎችም ሆኑ ሌሎች ኩነቶች በስፋት እየተከናወኑ አይደለም።
ቱሪዝም በስፋት ይጎርፍበት በነበረው በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ያጋጠመው የሰላም መደፍረስ ለቱሪስት እንቅስቃሴ መገደብ የራሱ አሉታዊ ተጽዕኖ ፈጥሯል። ችግሮቹ በዚህ መልኩ ቢገለጹም ማይስን ጨምሮ በአጠቃላይ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከተቀዛቀዘበት እንዲወጣ ሥራዎች መሰራት እንዳለባቸው በተለይም 2014 በጀት አመትን ለመቀበል የቀናት ጊዜ በቀረን በአዲስ አመት በአዲስ ተስፋ የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን ማነቃቃትና ውጤትም ማምጣት እንደሚገባ እምነት ተይዞ ተግባራዊ ሥራዎች ተጀምረዋል።
ከተግባራዊ እንቅስቃሴዎችም የማይስ ቱሪዝምን ለማንቀሳቀስ መንግሥትና የግል ባለድርሻ አካላት በጋራ ለመሥራት ሰሞኑን የተከናወነው የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ፊርማ ይጠቀሳል። የመግባቢያ ሰነድ የፊርማ ስምምነቱ የተፈረመው በቱሪዝም ኢትዮጵያ ድርጅትና ኦዚ በተባለ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ድርጅት መካከል ሲሆን፣ ስምምነቱን በተመለከተ፣ ማይስን ጨምሮ በቱሪዝም ኢንዱስትሪው የኮቪድ በሽታና የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ ተጽዕኖ ተቋቁሞ እስካሁን የተሰራውን፣ በ2014 በጀት አመት ደግሞ በዘርፉ ሊከናወን ስለታቀደው አጠቃላይ እንቅስቃሴ የቱሪዝም ኢትዮጵያ ድርጅትና የኦዚ ድርጅት ኃላፊዎች እንደሚከተለው አስረድተዋል።
የቱሪዝም ኢትዮጵያ ድርጅት ዳይሬክተር አቶ ስለሺ በቀለ እንደገለጹት ፤ ብዙዎች የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ከመዝናናት እንዲሁም በዓላትን መሠረት በማድረግ ቤተሰባዊ ግንኙነት ከመፍጠር ጋር ብቻ ያያይዙታል። ነገር ግን የቱሪዝም ዘርፎች ከተለያየ ነገር ጋር እየተቆራኘና ስያሜም እየተሰጠው በየቀኑ የቱሪዝም ዘርፍ ይወለዳል። ማይስ ቱሪዝም አንዱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ዘርፍ ነው ። ይሁን እንጂ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ባለመታወቁ እየተሰራበት አይደለም። ተፈጥሮአዊ፣ታሪካዊና ባህላዊ እሴቶችን በመጎብኘትና በማስጎብኘት ላይ መሠረት ያደረገ እንቅስቃሴ ነው የጎለበተው። በአሁኑ ጊዜ ግን መንግሥት ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው የሰጠውን ትኩረት በመጠቀም ቱሪዝም ኢትዮጵያ ድርጅት ማይስ ቱሪዝም ኢንዱስትሪን እንደ አንድ መዳረሻ ጥቅም ላይ እንዲውል እየሰራ ይገኛል።
ከዓለም ሀገራት ወደ ኢትዮጵያ ለተለያየ ስብሰባ ይመጣሉ። የኢትዮጵያ አየር መንገድን በመጠቀም ወደተለያዩ ሀገራት የሚሸጋገሩ መንገደኞችም ጥቂት የማይባሉ ናቸው። የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የተለያዩ ዓለምአቀፍ ድርጅቶች በመኖራቸው በሀገሪቱ ትልልቅ ውሳኔዎች ይወሰናሉ። በዚህም ትልልቅ የሚባሉ ስብሰባዎችን የማስተናገድ አቅም መፍጠር ችላለች። በተጨማሪም ኢትዮጵያ በአየር ንብረቷ ተመራጭ ናት። በመሆኑም ከስብሰባ፣ ከኤግዚቢሽንና ከንግድ እንቅስቃሴ ጋር ለተያያዘው ማይስ ቱሪዝም ምቹ በመሆኗ እንደሀገር ይህን መጠቀም ይቻላል። በኢትዮጵያ ዘርፉን ለመጠቀም የሚያስችሉ ዕድሎች ቢኖርም በማይስ ቱሪዝም የተቃኘ ባለመሆኑ የሚፈለገውን ያህል ርቀት መሄድ አልተቻለም።
ሳይሰራበት የቆየውን ማይስ ቱሪዝም ታሳቢ በማድረግ ከዘርፉ ለመጠቀም ለቱሪዝም ኢትዮጵያ ድርጅት ተጠሪ የሆነ የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ በቅርቡ ተቋቁሟል። ቢሮው ማይስ ቱሪዝም ላይ ብቻ ትኩረት አድርጎ ነው የሚሰራው። የማይስ ቱሪዝም መለያ (ብራንድ) ተቀርፆ በይፋም ተመርቋል። ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ሆቴሎች፣ የስብሰባ ማዕከሎች፣ የትራንስፖርት ተደራሽነትና አጠቃላይ አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን የያዘ ሰነድም ተዘጋጅቷል። ሰነዱ ኢትዮጵያን ከሌሎች ሀገሮች ለስብሰባ፣ ለንግድ እንቅስቃሴና ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ እንድትሆን የሚያስችልና ኢትዮጵያን የሚያስተዋውቅ ነው። በተጨማሪ ስብሰባዎችን ጨምሮ የተለያዩ ኩነቶችን ወደ ኢትዮጵያ ከሚያስመጡ ልምድ ካላቸው የዘርፉ የግል ድርጅቶች ጋርም በጋራ በመሥራት ዘርፉን በማሳደግ ተጠቃሚ ለመሆንም ጥረት እየተደረገ ነው። የግል ድርጅቶቹ ስብሰባዎችና የተለያዩ ኩነቶች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲካሄድ በማምጣት ብቻ ሳይሆን፣እነርሱም ትልልቅ አጀንዳዎችን በመቅረጽ ስብሰባዎችን በማካሄድ ዘርፉ ላይ ሚና ይወጣሉ።
እንዲህ ባለው እንቅስቃሴ የሚጠቀሰውና ቱሪዝም ኢትዮጵያ አብሮ ከሚሰራቸው ድርጅቶች መካከልም አንዱ የሆነው ኦዚ ፣ ማይስ ኢስትአፍሪካ የሚል በአመት አንድ ጊዜ የሚዘጋጅ ኩነት አለው። በአዲስ የተቋቋመውና ተጠሪነቱ ለቱሪዝም ኢትዮጵያ የሆነው ኮንቬንሽን ዋና ተግባሩም በአጋርነት ለሚሰሩ ተቋማት የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠትና ማገዝ ሲሆን፣ በጋራ የሚሰሩ ሥራዎች ደግሞ ወደ አንድ ማዕከል መጥተው እንዲከናወኑና ውጤታማም እንዲሆኑ ነው።
የኮቪድ ተጽዕኖና ወቅታዊው የሀገሪቱ ሁኔታ ዘርፉን ለማንቀሳቀስ እየተደረገ ላለው ጥረት ያለውን ምቹነት በተመለከተ አቶ ስለሺ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ፣ ኮቪድ 19 ቫይረስ ወረርሽኝ በሽታን ለመከላከል በዘርፉ ላይ የሚገኙ ባለድርሻ አካላት መከላከያ ክትባት እንዲወስዱ ከአዲስ አበባ ከተማ ጤና ቢሮና ከጤና ሚኒስቴር ጋር የቅድመ ዝግጅት ሥራ ተሰርቷል። በሌላውም ዓለም ክትባት እየተሰጠ በመሆኑ ተቀባዩም የሚመጣውም የመከላከል ሥራ ከሰሩ የኮቪድ ሥጋት ይወገዳል። ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ከሀገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ የነበረው ሥጋትም ተወግዷል።
በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ከጦርነት ጋር ተያይዞ ያለው የደህንነት ሥጋት፣ ጫና ማሳደሩ ቢታወቅም ኢትዮጵያ ውስጥ እንደሌላው ዓለም አንድ አካባቢ ችግር ሲኖር ችግሩ በመላው ኢትዮጵያ ውስጥ አይፈጠረም። በመሆኑም በአዲስ አበባ ከተማ፣ ደቡብ፣ ምዕራብና ምሥራቅ የኢትዮጵያ ክፍሎች ከደህንነት ሥጋት ቀጠና ነፃ በመሆናቸው ለቱሪስቱ ምቹ ማድረግ እንዲሁም ስብሰባዎች፣ ኤግዚቢሽኖችንና ሌሎችንም ኩነቶች ማዘጋጀት ይቻላል። ጎን ለጎንም የሀገርን ገጽታ መገንባት ይጠበቃል። በተለይም በሎጆችና ሆቴሎች ኢንቨስትመንት ላይ የተሰማሩና በልዩ ማበረታቻዎች እንዲንቀሳቀሱ በቱሪዝም ኢትዮጵያ በኩል ለተለዩት ማበረታቻ እንዲደረግ በፌዴራል ኢንቨስትመንት ቦርድ እንዲጸድቅ ተደርጓል።
ከእነዚህ መካከልም ገርአልታ፣አፋር ኤርታሌ ባሌ ሰሜን ተራሮች ብሄራዊ ፓርክ፣ ደቡብ አርባ ምንጭ፣ ነጭ ሳር ፓርኮች በሚገኙበት ልዩ ማበረታቻ የሚያስፈልጋቸው ተብለው የተለዩ ናቸው። ማበረታቻውም ለአምስት አመት ግብር የማይከፈልበት የሆቴልና የሎጅ ኢንቨስትመንት እንዲካሄድ ነው። በአጠቃላይ ደግሞ ልዩ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት የሚያስፈልጋቸው 50 ቦታዎች ተለይተዋል። እነዚህን ሁሉ ታሳቢ ያደረገ የማስተዋወቅ ሥራ መሰራት አለበት።
እንደ አቶ ስለሺ፤ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያጋጠመውና ለፀጥታም እንደስጋት የሚነሳው ጉዳይ መፍትሄ እንደሚያገኝ ታሳቢ ተደርጎ ነባር ኢንቨስትመንቶችን ማጠናከር፣ አዳዲስ ኢንቨስትመንቶችም እንዲመጡ ሥራ መሰራት አለበት።በኮቪድ፣ በምርጫና በፀጥታ ችግሮች የተዘጋ ሀገር ተደርጎ መወሰድ የለበትም።እንደሀገር ሰፊ የሆነ የበጎ አድራጎትና የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች ሲሰሩ መቆየታቸው ችግርም ቢኖር ሥራ መስተጓጎል እንደሌለበት አንዱ ማሳያ ነው። እንደቱሪዝም ተቋም ዘርፉን የሚያግዙ ኢንቨስትመንቶች እንዲስፋፉ፣የቱሪዝም ኢንተርፕራይዞች እንዲመሰረቱ፣ በዘርፉ የተፈጠሩ የሥራ ዕድሎች እንዳይመክኑ፣በዘርፉ ተስፋ መቁረጥ እንዳይፈጠር በማበረታታት ሀገራዊ ኃላፊነትን መወጣት ስለሚገባ ቱሪዝም ኢትዮጵያ ድርጅት ይህንኑ በማድረግ ላይ ይገኛል።
ማይስ ቱሪዝም ስለሚኖረው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታም አቶ ስለሺ እንዳስረዱት፤ ማይስ ቱሪዝም ቱሪስቱ ከሚነሳበት ሀገር ጀምሮ ኢትዮጵያ እስኪደርስ ባለው ሂደት ውስጥ የመሬትና የአየር መጓጓዣ ትራንስፖርት፣ የመኝታና የምግብ አገልግሎት፣ አስጎብኝውና ሌላውም በውስጡ ያለው ተዋናይ ሰፊ በመሆኑ የዘርፉ የእሴት ሰንሰለት ረጅም ነው። በቅርቡም ኮቪድን ለመከላከል በዘርፉ ውስጥ ተጨማሪ ባለድርሻ ገብቷል። ይሄ ሁሉ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታውን ያጎላዋል።
በ2014 ዓ.ም ከተያዘው ዕቅድም ከወዲሁ የተጀመሩትን ሥራዎችንም አቶ ስለሺ እንደተናገሩት ለቱሪስቱ ምቹና የንጽህና መጠበቂያ ማሟላት የሚጠቀስ ሲሆን፣እስካሁን በአፋርና በተለያዩ ዋና ዋና ፓርኮች ሥራዎች ተሰርተዋል። በምሥራቅ አፍሪካና በአፍሪካ ደረጃም ከኬኒያ፣ ጅቡቲ፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳና ሩዋንዳ ጋር የቀጠና ቱሪዝም ሥራ ተጀምሯል። ኢትዮጵያ ምድረ ቀደምት ሀገር በመሆኗ በተለያዩ ቋንቋዎች ለሌላው ዓለም ለማስተዋወቅ፣ በተለይም የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችን እንደ አንድ መስኮት በመጠቀም ሥራዎችን ማከናወን የዕቅዱ አካል ነው።
ሀገር በቀል የሆነውና በማይስ ቱሪዝምና ተያያዥ በሆኑ ሥራዎች ለ12 አመታት ሲሰራ የቆየው ኦዚ ድርጅትም ከመንግሥት ጋር በአጋርነት ላለፉት ስምንት አመታት መሥራቱን የድርጅቱ ኃላፊ አቶ ቁምነገር ተከተል አስታውሰዋል።
እርሳቸው እንዳሉት ትብብሩ እንደ ሁለት የተለያዩ አካላት የንግድ ሥምምነት ሳይሆን፣ ተጋግዞ የቱሪዝም ዘርፉን በማነቃቃት ሀገርን በጋራ ለማሳደግ እንደሆነ መወሰድ አለበት ብለዋል። አቶ ቁምነገር እንዳሉት ድርጅታቸው ጥረት የሚያደርገው የተለያዩ ኩነቶች እንዲካሄዱ ብቻ ሳይሆን፣ ስመጥር የሆኑ የሆቴል ባለቤቶች ኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ በመሳብም ሚናውን ይወጣል። በተለይም በኮቪድና በተለያየ ምክንያት ተጎድቶ የቆየውን የማይስ ቱሪዝም እንቅስቃሴ ለማነቃቃት፣ አዳዲስ የቱሪዝም ኢንቨስትመንት ዕድሎችን መንግሥት እንዲጠቀምባቸው ድርጅታቸው ያግዛል። መንግሥትና የግሉ ዘርፍ ጉልበቱን በአንድ ላይ አድርጎ ከተንቀሳቀሰ እስካሁን ባልተሰራበት የማይስ ቱሪዝም የበዛ ጥቅም ማግኘት ይቻላል።
ለምለም መንግሥቱ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2013