አስቴር ኤልያስ
በተደጋጋሚ በሰራዊቱ ቤት በተግባር የሚያየው ነገር ያበሳጨዋል፤ ተራው ወታደር፣ ለየመኮንኑ ወይዛዝርት ከመላላክ እስከ ዘንቢል ይዞ ገበያ መሄድ ያሉት ነገር በጣም ይሰቀጥጠዋል። አንድ ቀን ግን ይህን እያየ መበሳጨትን ስላልፈለገ አንድ ወዳጁን ለብርቱ ጉዳይ እንደሚፈልገው ይነግረውና የገዛ ደሙን በስሪንጅ እንዲቀዳለት ይለምነዋል። የውስጡን ብሶት በተቀዳው ደሙ ቀለምነት በመጠቀም ማመልከቻውን ይጽፍ ጀመር – የዛሬው የህይወት ገጽታ እንግዳችን ሻለቃ ተስፋዬ እምሩ።
ለአዲስ አበባ በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ቢሾፍቱ ገጠር አካባቢ ተወልደው ያደጉት ሻለቃ ተስፋዬ እምሩ፣ በአጼ ኃይለስላሴ፣ በደርግና በኢህአዴግ ዘመን አገራቸውን ያለምንም ማወላወል በእውነተኛ ወታደራዊ ስሜት አገልግለዋል። ከፍ ያለ ቦታ ለመድረስ በራሳቸው ስራና ብርታት መሆን እንዳለበት ያምናሉ እንጂ አለቆቹን ባዩ ቁጥር መሽቆጥቆጥን ነፍሳቸው አጥብቃ ትጸየፈዋለች።
ባለታሪካችን፣ በ1954 ዓ.ም የስምንተኛ ክፍል ተማሪ ሳሉ አባታቸው ያርፋሉ፤ በዚህ ምክንያት ትምህርታቸውን መከታተል አልቻሉም። በወቅቱ የኢትዮጵያ አጠቃላይ ሁኔታ የሚያሳየው ትምህርትም ሆነ ስራ መግባት የሚችለው ወገን ዘመድ ያለው ብቻ መሆኑን ነው። እዛው ቢሾፍቱ ሁለት ወንደላጤ መምህራንን እያገለገሉ መማሩን ቀጠሉ፤ ነገር ግን ሁለቱ መምህራን መካከል የተፈጠረ የርስ በርስ ቅራኔ ወደእሳቸውም ተጋብቶ ከዚህም እንዲባረሩ ምክንያት ሆነ። ስለዚህም ትምህርታቸውን ጥለው እዛው ቢሾፍቱ ወደአየር ወለድ ካምፕ እየሄዱ የተገኘውን ፍርፋሪ እየቀማመሱ ትምህርታቸውን ለመቀጠል ሞከሩ፤ ነገር ግን ይህም አልሆነም።
ያለ ጉቦ፣ ያለ አማላጅና ያለ ሁነኛ ዘመድ መግባት የሚቻለው ሰራዊቱ ቤት ብቻ ነበር። ትምህርታቸውን ለመቀጠል ባለመቻላቸውና አንረዳህም ያሉትን ዘመዶቻቸውን እንዲሁም እንዳይማሩ ያስባረረውን መምህር ለመበቀል ሲሉ ሰራዊት ቤት ለመቀጠር ወሰኑ። በቀጥታ ከቢሾፍቱ ከሌሊቱ 11 ሰዓት ላይ ይነሱና በእግራቸው በመጓዝ ከጠዋቱ 3 ሰዓት አዲስ አበባ አራተኛ ክፍለ ጦር ይደርሳሉ። ይሁንና ልጅ ነህ በሚል ሊቀጥሯቸው አልወደዱም። እርሳቸውም ሌላ መሄጃ አልነበራቸውምና ቁመታቸው አጭር በመሆኑ ቢያሳጣቸውም በክብደታቸው ደግሞ እንዳይጥሏቸው ድንጋይ በኪሳቸው በመያዝ በድጋሚ ቢሞክሩም ሊሳካላቸው አልቻለም።
በሶስተኛው ቀን ግን አዛዡ ሻምበል ታደሰ ገብረዮሐንስ መጥተው ነበርና በመውደቃቸው መናደዳቸውን አስተውለው ‹‹አምጧት ለኳስ ትሆነናለች›› በማለታቸው ገቡ። ወደውስጥ ሲዘልቁም ያዩት ነገር በጃንሆይ ፈቃድ የባለውለታ ልጆች ተብለው ከጎንደር፣ ከትግራይ፣ ከጎጃምና ከተለያዩ ቦታዎች የልጅ ወታደር በሚል ማስልጠኛ ጣቢያ ውስጥ ተሰብስበው ነበርና ከእነርሱ ጋር ቀላቀሏቸው።
የልጅ ወታደር ከሚባሉት ጋር ቆዩ፤ የስድስት ወር ኮርሱንም አጠናቀው ተመለሱ። በ1956 የቀረውን የትምህርት ጊዜ በኮከበ ጽባህ በማታው ክፍለ ጊዜ መማር ጀመሩ፤ በ1959 ዓ.ም አስረኛ ክፍል ሲደርሱ በአሜሪካን አገር በማቴሪያልስ ማኔጅመንት ሰፕላይ ኢንስትራክተርነት አጭር ኮርስ የመማር እድል በመከላከያ አጋጠማቸው። በዚህም አካውንቲንግ ስፔሻሊስት እና ስፔሻል ፐርፐስ ኢኪዩፕሜንት ስፔር ፓርት ስፔሻሊስት በሚል ሁለት ዲፕሎማ ያዙ። እዛ ሊያስቀሯቸው ሞከሩ። እርሳቸው ግን መቅረት አልፈለጉም። ያልቀሩበት ዋናው ምክንያት ከኢትዮጵያ አገራቸው ጋር ያላቸው ቁርኝት በቀላሉ የሚበጠስ ባለመሆኑ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በአገረ አሜሪካ በኮርስ ስልጠና ላይ እያሉ ‹‹Black go back›› የሚል ጽሁፍ በማየታቸውም ጭምር ነው።
ሰው መሆናቸውን እስኪጠራጠሩ ያደረሳቸው ንግግር
በአንድ ወቅት አገር ቤት የአንደኛ ደረጃ ተማሪ በነበሩበት ወቅት ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለስላሴ እሳቸው ወደሚገኙበት ስፍራ ለጉብኝት ይመጣሉ። እያንዳንዳቸው ምን እንደሚፈልጉ እየዞሩ ይጠይቋቸዋል። ተጠያቂ ተማሪዎች መሻታቸውን ለንጉሱ ይገልጹላቸዋል፤ ጥያቄው እርሳቸው ዘንድ ደረሰና ምን እንደሚፈለጉ ሲጠየቁ ‹‹እኔ አባቴ ስለሞተብኝ የሚረዳኝና የሚያስተምረኝ የለኝም፤ ስለዚህ አዳሪ ትምህርት ቤት ገብቼ እንድማር ይፍቀዱልኝ›› ይሏቸዋል። እርሳቸውም ቀበል ያደርጉና ‹‹አይ! አንተማ ከብት ነው ማገድ ያለብህ›› ይሏቸዋል።በዚህ ጊዜ ‹‹እኔ ሰው አይደለሁም›› በሚል የበታችነት ስሜት ተሰማቸው። ሰው ስለመሆናቸው መጠራጠር ጀመሩ። በዚህም የአውሬነትና የበቀለኝነት መንፈስ ተጠናወታቸው። በውስጣቸውም ይኸው መንፈስ ሲገላበጥ ተሰማቸው። ይህን ስሜት ተከትለውም የረዳት ማጣቱም ተጨምሮበት ሰራዊት ቤት በመግባት የናቃቸውን ሁሉ ለመበቀል ቢወስኑም፤ ሰራዊት ቤት የገጠማቸው ስብዕና እና የሚሰጣቸው ትምህርት ግን እንኳን ወገንን ለመግደል ቀርቶ ተኩሶ ቢያቆስልም እንኳ መግደል እንደማይቻል ነው። ይህ መልካም የሆነ ትምህርት በውስጣቸው የፋፋውን በቀል ኩምሽሽ አደረገባቸው።
በደማቸው ማመልከቻ እስከመጻፍ ያደረሳቸው ጉዳይ
በሰራዊቱ ቤት የስልጣን እርከኑ ከመከባበር ባለፈ ተራውን ወታደር እንደቤት አገልጋይም ጭምር የሚያስቆጥር ነው። ተራው ወታደር ከመኮንኖቹ ሚስቶች ጋር ዘምቢል ይዘው ጉልትና ገበያ በመንከራተት ያገለግላሉ። ይህን አካሄድ አዕምሯቸው በፍጹም ሊቀበለው አልቻለም። መኮንኖችንም ሆነ ተራውን ወታደር የቀጠረው መንግስት ነው። ስለዚህ ተራው ወታደር ለመኮንኑ እንዴት አሽከርና ገረድ ይሆናል! በማለት ከእያንዳንዱ ጋር መጣላት ይጀምራሉ።
በዚህ ጊዜ እርሳቸው እንደ ልዩ ፖለቲከኛ ተደርገው ይታዩ ጀመር። አንዳንድ ጥቅማጥቅሞች በሚኖሩበት ጊዜ ቅድሚያውን የሚያገኙት እነዛ ዘምቢል ይዘው ወዲህ ወዲያ ለሚሉት ነው። በችሎታው የሚንቀሳቀሰው ግን ይልቁኑ እጣ ፈንታው በበላዮቹ መኮንኖች መጠመድ ሆነ። ስለዚህ ይህን ሁኔታ እልባት ለመስጠት ሲሉ በደማቸው ቀለምነት ማመልከቻቸውን እንዲህ ሲሉም ይጀምራሉ፤ ‹‹ሁላችንንም የቀጠረን መንግስት፤ ደመወዝም የሚከፈለን መንግስት ሆኖ ሳለ ከዚህ ውስጥ የተወሰኑቱ ግን የቤት አሸከር ሆነዋል፤ በዚህም ስራቸው ለሙያ ማሻሻያ የሚመጣው ገንዘብ ለእነርሱ ሆኗል።…›› እያለ የሚቀጥል ማመልከቻ ጽፈው አስገቡ።
ይሁንና ያጋጠማቸው የተመኙት ነጻነት ሳይሆን እስር ቤት ነው። የመታሰራቸው ምስጢር ማመልከቻው በደም ለምን ተጻፈ በሚልም ጭምር ሲሆን፣ ይህም ከፍተኛ ወንጀል ነው ተባለ። እርሳቸው ማመልከቻቸውን በብዕር አሊያም በእስክሪቢቶ መጻፍ አቅቷቸው ሳይሆን ከፍተኛ ትኩረት እንዲያገኝ በማሳባቸው ነው የገዛ ደማቸውን እንደቀለም የተጠቀሙበት።
ለ42 ያህል ቀናት ታስረው ወደመጨረሻው ፍርድ በተቃረቡበት አካባቢ አንደኛው ትሁት አዛዥ ‹‹ይህ ወታደር በጣም ልጅ ነው፤ እዛው በአርጩሜ ቢጤ ገረፍ ገረፍ አድርጋችሁ ተውት›› ባሉት መሰረት ወደመደበኛ ስራቸው ተመለሱ። ይሁንና ይህ የሆነው እርሳቸው ከአሜሪካ ሰልጥነው በመጡበት ሙያ ተፈላጊ በመሆናቸው ቀን ቀን ከአሜሪካኖች ጋር ሲሰሩ ይውሉና ማታ ማታ ግን ወደተለመደው እስር ቤት ይሄዱና እንደውሻ ግልገል ይታሰራሉ።
አንድ ቀን ምርር አላቸው። አራት ኪሎ አካባቢ አብረዋቸው የሚያሳልፉት ጓደኞቻቸው ናፈቋቸው፤ ይህንን እያሰላሰሉ ባለበት አንድ ቅዳሜ የተለመደ ስራቸውን እያከናውኑ ባለቡት ድንገት ጥግ በተቀመጠ አንድ በርሜል ውስጥ በመግባት ራሳቸውን ይደብቃሉ። ሁሌ ወደእስር ቤት የሚያደርሷቸው ፖሊሶች እጃቸውን ይዘው ሊወስዷቸው ቢፈልጓቸው ከወዴት ያግኟቸው። ግርግር ሆነ፤ በር ላይ ያሉ ጥበቃዎቹን ሊያስሩ ሆነ፤ ይሄኔ በእርሳቸው ምክንያት ሌላ ሰው መጎዳት የለበትም በሚል ከተደበቁበት ወጡና ሊያስሯቸው የመጡትን በድንጋይ አስፈራርተው ወደውጭ አመለጡ፤ ይሁንና ቅዳሜና እሁድን ውጭ አሳልፈው መድረሻ ስለሌላቸው ተመልሰው ቀን ቀን ወደሚሰሩበትና ማታ ማታ ወደሚታሰሩበት መስሪያ ቤታቸው መጡ። ማዕረጋቸውን ግን ገፈፉባቸው። ነገር ግን የእስር ጊዜያቸውን በማጠናቀቃቸው በዚሁ መስሪያ ቤት ስር እንደሆኑአሜሪካኖቹ ይዘዋቸው ወደአስመራ በመሄድ ሲሰሩ ቆዩ።
በአንድ ወቅት የስራቸው ባህሪ ከአሜሪካኖቹ ጋር ወደሐረር ያመጣቸዋል። ሀረር ወዳለው ክፍለጦር ሲደርሱ በወቅቱ ጓድ መንግስቱ ኃይለማርያም የመሳሪያ ግምጃ ቤት አዛዥ ነበሩ፤ ባለታሪካችን የመጡበትን ትምህርት አስተምረው ከጨረሱ በኋላ በመኮንኖች ክበብ ግብዣ ተዘጋጀ። ከቡድናቸው ውስጥ ሃምሳ አለቃ አሜሪካዊውን ሲጋብዙ የበታች ሹም ከሚባሉት ውስጥ እርሳቸውም ናቸውና ተነጥለው እንዲቀሩ አደረጓቸው።
በዚህ ጊዜ ጓድ መንግስቱ ‹‹ይህም ያም የበታች ሹሞች ናቸው፤ ስራውን ደግሞ የበለጠ የሚሰራው ተስፋዬ ነው፤ ስለምን ተነጥሎ ይቀራል›› የሚል ነገር ሲያነሱ፤ በወቅቱ መንግስቱ መቶ አለቃ ነበሩና የበላይ አለቆች ለምን ህግ ጥሰህ ተናገርክ፤ ሌላ ይገባህ ነበር፤ ነገር ግን በሚል በዛው ምሽት ጓድ መንግስቱ ተጭነው ወደበረሃ እንዲወርዱ አደረጓቸው።
ግምጃ ቤት የቆለፉባቸው ዘጠኝ ጄነራሎች
ባለታሪካችን የበታች ሹም እንደሆኑ የተለያዩ ግርግሮች ኢትዮጵያን ይጎበኟታል። በዚህ ሁሉ እርሳቸው ቀልጠፍ ያሉ በመሆናቸው ግንባር ቀደም ናቸው። በ1960ዎቹ አካባቢ እንደገና አንድ ጥያቄ ለወቅቱ መንግስት አቀረቡ። ረብሻው ደግሞ በየትምህርት ቤቱ በተማሪዎች እየበረታ መጣ።የአጼ ኃይለስላሴን አገዛዝ የሚቃወም በዛ። በክፍላቸው ካሉት አንድ ቁጥር ተቃዋሚ ደግሞ እርሳቸው ናቸው።
አንድ ቀን ጄነራሎቹ ነገሌ የሚገኘውን የጦሩን ጥያቄ ተቀብለው ወደአዲስ አበባ ሲመለሱ እርሳቸው ወደ 80 ያህል ተማሪዎች ከየክፍሎቹ በድንኳን ሰብስበው ሰፕላይ ኮርስ ያስተምሩ ነበር። በዚህ ጊዜ የመሳሪያ ቤቱን ግምጃ ቤት ሰብረው ተማሪዎቹን መትረየስ አስይዘው ፓርላማ ዙሪያውን ከበው ይጠባበቁ ጀመር። ዘጠኝ ጄነራሎች ወደፓርላማው ሲመጡ ግምጃ ቤቱን ከፍተው አስገቧቸውና በላያቸው ላይ ቆለፉ።
ባለታሪካችንን የሚወዱ አንድ አስተባባሪ ‹‹ተስፋዬ!›› ሲሉ ጠርተዋቸው ‹‹እነዚህ የቆለፍክባቸው መኮንኖች አባቶችህ ይሆናሉ፤ ማዕረጋቸውም ቢታይ በአንተ ደረጃ
የሚታሰሩ አይደሉም፤ ይነስም ይብዛ አገር ያገለገሉ ናቸው›› ሲሏቸው፤ ባለታሪካችንም ተማሪዎቹን አግባብተዋቸው ከፍተው ያስወጧቸዋል። ነገር ግን ሌሎቹ ስርዓቱን አደጋ ላይ የጣሉትን ከሌሎች አጋሮቻቸው ጋር አስረው ስለነበር፤ ይህንኑ ለጃንሆይ ይነግሯቸዋል። ፍርድ እንዲሰጡም ያሳስቧቸዋል። ለጊዜው የተቀበሉ መሰሉና እነርሱ ራሳቸው መልሰው ተጠርው ሌሊት እንዲገደሉ ያዛሉ። ይሁንና በጊዜው የተለያዩ ጉዳዮች አገዛዙን ሰቅዘው ያዙ። በዚህ መሃል የእነርሱ ጉዳይ በግርግር ተረሳ።
ይሁንና ያልተገባ ነገር ሲያዩ ማለፍ ስለማያስችላቸው እውነቱን ከመናገር አይቆጠቡም። ወዲህ ወዲያ ማለታቸው ያልተመቻቸው መኮንኖች ደግሞ ጥምድ ያደርጓቸዋል። በመሆኑም እርሳቸውን መበቀል የሚፈልጉ በመኖራቸው አንድ የሚወዷቸው ሻለቃ ያለምንም ልብስ እና ስንቅ አንድ መኪና አዘው በውድቅት ሌሊት ከአንድ ሰው ጋር ወደአሰብ ይልኳቸውና ከዛ ቅስቅስ እንዳይሉም ያስጠነቅቋቸዋል። አሰብም የመከላከያ ትራንዚት ኃላፊ ሆነው ቆዩ። እዛው እያሉ በአገሪቱ በርካታ ነገሮች ተከናወኑ።
የወያኔ ማስፈራሪያ እና የእድገት በህብረት ዘመቻ
ደርግም የአጼ ኃይለስላሴን አስተዳደር ተረከበ። እርሳቸው አሰብ እያሉ ደርግ የመጀመሪያውን ኮሚቴ ሲያዋቅር እርሳቸው አሰብ ነበሩ። ተስፋዬ ወዴት ነው ቢባል እርሳቸው የሉም። የለውጥ ሃዋሪያ በሚባለው ምርጫ ውስጥም እርሳቸውን ለማካተት ሲፈለጉ አልተገኙም። በመጨረሻ ግን እድገት በህብረት በሚባለው ዘመቻ ላይ በአዝማችነት ተሳተፉ።
በወቅቱ ያቀኑትም ወደትግራይ ነው። በእድገት በህብረት የተሳተፉ ኢትዮጵያውያን ያለጠብመንጃ ጠላትን የተዋጉ እንደሆነ ነው ባለታሪካችን የሚያስታውሱት። ያለፍርድ ቤት ህዝባዊ ፍትህን ያሰፈኑ፤ ህዝብን አንድ ያደረጉ ናቸው ይላሉ ያን ትውልድ። በወቅቱ ስራቸው፤ መሰረት ትምህርት ማስተማር፣ ጎጂ ባህሎች ምን ምን እንደሆኑ ማስገንዘብ፤ ስለሴቶችና ስለጾታ እኩልነት መግለጽ፤ ያለአግባብ የተያዘውን መሬት ነጥቀው ለገበሬው ማስረከብ በመሆኑ ከማህበረሰቡጋር ያላቸው መግባባት በጣም አስደሳች ነበር።
ዓመት ያህል በአካባቢው የቆዩ ሲሆን፣ የወያኔ ሰላዮች በመፈጠራቸው አሻጥሮች በዙ። በወቅቱ እነዚህ የወያኔ ሰዎች የትግራይ ተወላጆችን ከመሃል ከመጡ ሰዎች ጋር ግንኙነት ብታደርጉ ወየውላችሁ በማለት ያስጠነቅቋቸዋል። ሌላው ቀርቶ እድገት በህብረት ውስጥ ያሉ የእነርሱ ቅጥረኞች ጭምር በመላላክ ሊያስፈሯሯቸው ይሞክራሉ። እንዲያውም መሬት የተነጠቁትን ባላባቶችንና ፖሊስን በማስተባባር ውድቀት ሌሊትን ተገን አድርገው በጥይት ሽብር ፈጠሩባቸው። መሳሪያዎቻቸው ኋላቀር በመሆኑ ግን እምብዛም እንዳልፈሯቸው ነው ባለታሪካችን የሚናገሩት። እርሳቸው አንድ ሽጉጥ ስላላቸው እርሷን ሌሊት ላይ ያስጮሁና መለስ ብለው ተማሪው መሃል ግብት ብለው ይተኛሉ። ተማሪዎችንም አይዟችሁ ይሏቸዋል። በዚህ አይነት ፈተና እና ስቃይ በትግራይ ቆይተው የሚወስዳቸውም በማጣታቸው በመጨረሻም በእጃቸው ላይ የሚገኙትን እቃ በመሸጥ ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው ይገባሉ። ይሁን እንጂ አዲስ አበባ ሲደርሱ ቤታቸው ተወርሶ፣ ‹‹እድገት በህብረት›› ተብሎ ደረት ሲደቁላቸው የነበሩ ሰዎች ‹‹እብደት በህብረት›› ብሏቸው እረፍ አሉ። ባለታሪካችን የኢትዮጵያን ህዝብ ታሪኩ ብዙ ነው ከማለት በዘለለ ‹‹ጊዜ አይቶ የሚያነሳ፤ ጊዜ አይቶ የሚክድ ነው›› ይሉታልም።
ትዳር ለመመስረት የቸገራቸው ጉዳይ
ቀደም ሲል ብዙዎች ባለታሪካችን የራሴ ከሚሉት ሰዎች አንደበትም ሆነ ከጃንሆይ በተለያየ ጊዜ የተሰነዘረባቸው ቃላት በራስ መተማመን እንዳይኖራቸው አድርጓቸዋል። ከዚህም የተነሳ ‹‹እኔ ሰው አይደለሁም›› የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሰዋል። ስለዚህ ምንም እንኳ እጮኛ መያዝም ሆነ ትዳር መመስረት ቢፈልጉም ሴቶችን ቀርበው የመጠየቅ ድፍረቱ የላቸውም።
ይሁንና አንድ ቀን የልብ ወዳጃቸው የሆነ አንድ ሰው ወደቡና ቤት ይወስዷቸውና ከቡና ቤት ሴቶች ውስጥ አንዷን ያነጋግሩላቸውና በግድ ይዘህ ሂድ ብሏቸው ያገናኟቸዋል። ከዚያ አብረው ሄዱ። በኋላም እንደ እድል ሆኖ ማርገዟን ሰሙ፤ በቃ በስምንት ብር ቤት ተከራይተው አስቀመጧት። ሴት ልጅም ወለደችላቸው።
ኢህአፓ በመባላቸው የደረሰባቸው ስቃይ
እርሳቸው ከእድገት በህብረት መልስ ባሉበት ቀበሌ የወጣት ማህበር አባል ሆኑ። በወቅቱ ደግሞ የኢህአፓ ወሬ በጣም የተናፈሰበት ጊዜ ነው። እርሳቸው ባሉበት ቀበሌ ደግሞ የቀበሌ ሊቀመንበር አስመራጭ ተብለው ይመረጣሉ። አስመራጭ ሆነው ሳለ ነዋሪው መልሶ እርሳቸውን ሊቀመንበር አድርጎ ይመርጣቸዋል። ባለታሪካችን የተመረጡበት ቀበሌ የፕሬዚዳንት መንግስቱ መኖሪያቸው አካባቢ በመሆኑ ጓድ መንግስቱ ተሳትፎ ያደርጋሉ።
ባለታሪካችን፣ በሊቀመንበርነታቸው የቀበሌውን ነዋሪ በብዙ ስራ ደስ አሰኝተዋቸዋል። በስራቸውም ምስጉን ናቸው። ነዋሪዎቹ በሚያደርጓቸው ስራዎች ሁሉ ተጠቃሚ መሆን ስለጀመሩ በእጅጉ ይወዷቸዋል። የህዝቡንም ጥያቄ ተሯሩጠው ይመልሳሉ። በዚህ የተነቃቃ ስራቸው ደስተኛ ያልሆኑና ሰውን በሐሰት ቀብረው ራሳቸውን ከፍ ለማድረግ የሚሹ አልጠፉምና ከእነዚህ ውስጥ የቅርብ ጓደኛቸው የሆኑ ግለሰብ ‹‹ኢህአፓ ነው›› ብለው አስፈረጇቸው።
በዚህ መሃል እርሳቸው ሊቀመንበር በሆኑ ጊዜ መሳሪያ አስረክቡ የሚል ነገር ነበርና አንድ ጠንቋይም እንደማንኛውም ሰው የያዘውን መሳሪያ እንዲያስረክብ ይጠየቃል። ጠያቂው የገዛ ወንድሙ ነውና አልሰጥም ሲል ወንድሙን ተኩሶ ይገድለዋል። በዚህ ጊዜ ባለታሪካችን የሚያምኑት በህግ ነውና ጠንቋዩን ወስደው ያስሯቸዋል።
የአብዮት ጥበቃና ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ ኮሎኔል ይደውሉና ‹‹ያሰርከውን ሰውዬ ሂድና ፍታ›› ይሏቸዋል። እርሳቸውም ቀበል ያደርጉና ‹‹ጌታዬ እኔ ለህግ ሰጥቻለሁ፤ ያሰረው ህግ ስለሆነ የሚፈታውም የሚፈርድበትም ህግ ነው›› ቢሏቸውም እንዲፈቱት ግን አጥብቀው ያስጠነቅቋቸዋል። በዚህ መሃል ኢህአፓ ብሎ ያስፈረጃቸው ሰውዬ ይህን ክፍተት በማግኘታቸው ምቹ ሁኔታን ይፈጥርላቸዋል። ስለዚህም ጠንቋዩን ያስፈቱታል።
ይሁንና ባለታሪካችን ብርቱ ብርቱ ጓደኞች ነበሯቸውና ህግ ተላልፎ የወጣውን ጠንቋይ እንደገና መሳሪያውን እንዲሰጥ ቤቱ ድረስ ሄደው ይጠይቁታል። ጠንቋዩም ዘብነን ብሎ ‹‹ህጋዊ ነኝ›› ይላቸዋል። ህጋዊ ስለመሆኑ ማስረጃ እንዲያሳያቸው ሲጠይቁት ‹‹የአብዮትና የዘመቻ መምሪያ ኃላፊ›› የሚል ማህተም የተመታበት ወረቀት ያሳያቸዋል። በዚህም አዝነው ይመለሳሉ።
በዚህ መብከንከን ውስጥ ያሉ ይኸው ኢህአፓ እያለ የሚከታተላቸው ሰው፣ በስብሰባ ላይ ‹‹የሌላው ቀበሌ ከጸረ አብዮተኛ እየጸዳ የእኛ ቀበሌ የማይጸዳው ለምንድን ነው›› የሚል ሐሳብ ሰነዘረ። በዚህ ጊዜ ባለታሪካችን ቀበል ያደርጉና ጸረ አብዮተኛ ማንን ምን እንደሆነ እንደማያውቁና በየቤቱም ሄደው ህዝቡን ልጅህ ጸረ አብዮተኛ ነውና አምጡ ማለቱ እንደሚቸገር ገልጸው ከፈለገ ደግሞ መንግስት ራሱ ጸረ አብዮተኛውን ይለይ ሲሉ ሁሉም ነዋሪ አጨበጨበላቸው። ይሁንና ይኸው ግለሰብ ‹‹ጸረ አብዮተኛ እንዳይመነጠር አሳደመ›› በሚል ይከሳቸዋል።
በማግስቱ እርሳቸው አገር አማን ነው ብለው ስራቸውን እየሰሩ ባሉበት አንድ ጂፕ መኪና መጥታ አጠገባቸው ቆመች፤ ያለምንም ንግግር አንዱ ከመኪናው ወርዶ ማጅራታቸውን ይዞ ወደመኪናው ጨመራቸውና መጓዝ ጀመሩ። ቢያለቅሱ፤ አምላካቸውን ቢያማርሩ ምንም ጠብ የሚል ነገር ጠፋ፤ የተለያዩ ኮሚቴዎች የተዋቀሩበት ቤተ መንግስት ወስደው ያስቀምጧቸዋል።
በስፍራው ወደ 16 የሚጠጉ ቀንደኛ የኢህአፓ ሰዎች ናቸው የተባሉትም አሉ፤ እርሳቸው የተቀመጡበት መቀመጫ ጎረበጣቸው፤ በተቀመጡበት እንደእንጨት ቀጥ ብለው መቀመጥ እንጂ አንገትን መለስ ቀለስ ማድረግ ደግሞ በጥብቅ የተከለከለ ነው። ከ16ቱ ውስጥ አንድ አንድ እያለ ከመካከላቸው እየተወሰዱ አለቁና ማምሻው አካባቢ ደረሱ። ለመንጠራራትም የሚጎረብጣቸው ነገር ሰላም ስለነሳቸው ለማወቅም ቀስ ብለው ሲሞክሩ ጠባቂዎቹ በብርሃን ቅጽበት ዘለው አጠገባቸው መጡ፤ እርሳቸው በወቅቱ ከወደመቀመጫቸው አካባቢ ሲነካካቸው የዋለው ነገር እባብ ነበር የመሰላቸው። አስነስተው ሲያዩት ጉዳዩ ጩቤ ነበር።
ጠባቂዎቹ፣ ‹‹አሃ! ዱለት ልትሰሪን ነበር ማለት ነው!!›› እያሉ ጩቤውን አገላብጠው ሲያዩ የሻገተ ነው። ስለዚህ ‹‹ይሄ ልጅ ይህን ጩቤ አላመጣውም፤ የቆየ ነው›› ተባባሉ፤ ‹‹ይሄ ልጅ ኢህአፓ ነው ወይስ አይደለም›› ሲሉም አከሉ። የቀሩት እርሳቸው ብቻ ሆኑ። እርሳቸው በእርግጥም ስለ ኢህአፓ የሚያውቁት ነገር የለም፤ ስራና ስራ ላይ ብቻ ነበር ትኩረታቸው። በወቅቱ ‹‹ኢህአፓ ነው አይደለም››የሚባባሉ ጥበቃዎች የጋራ መግባባት የላቸውም ነበር።
በዚህ ወቅት ኢህአፓ ነው አይደለም በሚለው ጉዳይ መተማመን ላይ መድረስ ባለመቻላቸው ከእነርሱ ከፍ ያለ ኃላፊ በመጥራት እንዲመረምረው ሲያደርጉ፤ ሌላ የኃላፊው ተላላኪ ድንገት አይቷቸው ‹‹ይሄ እኮ በሰራዊቱ ቤት የታወቀ መምህር የነበረ ነው›› አላቸው። አንዳንዱ ደግሞ ‹‹ይህ ልጅ እኮ ነው በአደባባይ ኃይለስላሴን ስልጣን ለምን አያስረክቡም ብሎ የጠየቀው›› አሏቸው። ይህ ደግሞ እንደ ኢህአፓ ጥያቄ ተደርጎ ተወስዷል። ይህ ከጠንቋዩ መታሰር ጋር ተጨምሮ ‹‹ውሰዱትና ይመርመር›› አስባላቸው። ስለዚህም የወቅቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ሶስት ጳጳሳትም ወደነበሩበት እስር ቤት ያስገቧቸዋል። በእነርሱ አይን እርሳቸው ከሁሉ የበታች የሚባሉ አይነት ናቸው። በዚህ ሁሉ ግን እርሳቸው ምንም የሰሩት ወንጀል ባለመኖሩም ሆነ ኢህአፓ ባለመሆናቸውም ምንም አይነት ፍርሃት በውስጣቸው የለም።
ተስፋዬን ውለዱት
በዚህ መሃል በየቦታው ያለው ህዝብ የሚሊሻ ስንቅ ለማዘጋጀት ጥሪ ይደርሰዋል። እርሳቸው በሊቀመንበርነት ሲመሯቸው የነበሩ የቀበሌ ነዋሪው፣ ‹‹ተስፋዬ ልጃችን ነው፤ ከዚህም ባለፈ ተላላኪያችን ነው ማለት ይቻላል፤
የሚደነግጥልንም እርሱ ነውና የት አለ›› ሲል ይጠይቃል። ነዋሪው በዚህም አላበቃም፤ ‹‹በስልጣን ሽኩቻ ካልገደላችሁት በስተቀር አምጡት›› በሚል ቀበሌውን ወጥሮ ይይዛል። ያሳሰራቸው ግለሰብ፣ ‹‹እኛም አናውቅም፤ ታስሯል ሲሉ ነው የምንሰማው›› ሲል ይመልሳል። ነዋሪውም ‹‹እናንተ የማታውቁ ከሆነ እንግዲያውስ የደርግ ተወካይ ጥሩልን›› ቢሉም መጥራት አለመጥራታቸው ባለመታወቁ ምላሽ ይጠፋል።
በዚህ ጊዜ የነብርን ጭራ አይይዙም፤ ከያዙ አይለቁም ሆነና ነዋሪዎቹ ሁሉም በዕለተ ሐሙስ ለመገናኘት ቀጠሮ ይዘው ይለያያሉ። በዚያ ቀን አሁንም ይመጣል የተባለው የደርግ አመራር አልመጣም። ህዝቡ በመመካከርና ባንዲራ በመያዝ ወደ ስድስት ሰዓት ገደማ ሰላማዊ ሰልፍ ይወጣል። ፕሬዚዳንት መንግስቱ መኖሪያቸው እዛው ባዕታ አካባቢ ነበርና የሰልፉን ሁኔታ ይጠይቃሉ፤ ፈጥነውም ተስፋዬ የሚባል ሰው ማን እንዳሰረ ይጠይቃሉ። የጠየቋቸው ሰዎች ደግሞ ሻለቃ ተስፋዬን የወነጀሉና ወደእስር ቤት ወስደው ያጎሯቸው ቢሆንም፤ ስላደሙባቸው‹‹ተስፋዬን ማን እንዳሰረው አናውቅም›› አሉ።
ሰላማዊ ሰልፍ ከወጣው ህዝብ መሃል ኮሚቴ ተመርጦ ሌሎቹ ወደቤታቸው እንዲመለሱ ተደረገ። ባለታሪካችን ሁሉም እስር ቤት ቢፈለጉ ይጠፋሉ። እርሳቸው ከታሰሩበት እስር ቤት ወደ ምሽት 11 ሰዓት ገደማ ድንገት ስልክ ይደወላል፤ የስልኩን መልዕክት የተቀበለው ግለሰብ ‹‹አንዴ! አንዴ! ከታሰራችሁት መካከል ተስፋዬ እምሩ የሚባል እስረኛ አለ?›› ሲል ‹‹እጃቸውንም ድምጻቸውንም ከፍ በማድረግ ‹‹አዎ! አለሁ›› ሲሉ ይጮሃሉ። ሁሉም እስረኛ ሊረሸኑ እንደሆነ በማሰብ ‹‹አይዞህ›› ሲሉ ያጽናኗቸው ጀመር።
እርሳቸው ግን ቶሎ ሞተው መገላገልን ነው የመረጡት። የወሰዷቸውም መጀመሪያ የሄዱበት ቤተ መንግስት ነበር። እዛ ያሉት ሁሉ ‹‹የቱ ነው ተስፋዬ የተባለው እንዲህ አገር ያሸበረው!›› እያሉ ያዩአቸው ጀመር። መጀመሪያ የተቀመጡበት ቦታ ተቀመጡ፤ ‹‹ለአንድ ገራፊ ስጡትና ይመርመር›› ተባሉ። ተራቸውም ደርሶ ወደክፍሉ ለመገረፍ ሲገቡ ከእርሳቸው በፊት ሲደበደብ የቆየው ግለሰብ ስጋው እስከመቆራረጥ ደርሶ ስለነበር እጅግ መረበሽ ጀመሩ። እርሳቸው ፈልገው የነበረው ወዲያው የሚግድላቸውን ነገር ነው።
በዚህ መሃል ቀድሞ ያስተማሩት አንድ 50 አለቃ ሪፖርት ሊሰጥ ሲመጣ እና እርሳቸው ተሰቅለው ሊገረፉ ሲል እኩል ይሆናል። ‹‹እንዴ! እንዴት አይነቱን ልጅ ነው ልትገርፉ ያሰባችሁት›› ይልና ለአለቃው በመግለጹ አንዲት ብጣሽ ወረቀት ከአለቃው በመላኳ ለገራፊው ትሰጣለች። ገራፊውም ‹‹አሃ! እዚህ ዘመድ አለህ ማለት ነው›› ሲላቸው ‹‹እንኳን እዚህ የትም ቦታ ያለ መድሃኒያለም ምንም ዘመድ የለኝም›› ይሏቸዋል። ነገር ግን አለቃ ወደተባለው ሲደርሱም ‹‹እህ! ለመሆኑ ምን ያህል መሳሪያ ነው ለዘመቻ ያዘጋጃችሁት?›› ሲሏቸው፣ ‹‹ጌታዬ እኔ ምን አውቃለሁ፤ እስረኛ ነኝ›› ይሏቸዋል። ‹‹ድሮስ ኢህአፓ ያምንልኛል ብዬ ነው!?›› ይሉና ‹‹ለዛሬ የሆነ ቦታ እሰሩት፤ ስለመሸ ነገ እንመክርበታለን›› ብለው ይወጣሉ። እንዲህ ያሉት በጨለማ እንዲገደሉ ስለፈለጉ ነበር።
ባለታሪካችንን ፖሊሶች ይረከቧቸዋል፤ ጉዳዩ ፕሬዚዳንቱ ዘንድ የደረሰ በመሆኑም ሁሉም ይጠነቀቁ ጀመር። ፖሊሶቹ ምሽቱን ለሚጠብቁ ተረኛ ፖሊስ ሲያስረክቡ ተፈራርመው ነው። ምሽት ላይ ማስክ የለበሱ ወስደው ሊደፏቸው መጡ። ነገር ግን ጠባቂዎቹ፣ ከደርግ ምርመራ ክፍል ላይ ፈርመው የወስዷቸው በመሆኑ ፊርማቸው ካልተቀደደ እንደማይሰጧቸው ገለጹላቸው። ገዳዮቹ ለኃላፊያቸው በመናገራቸው ኃላፊው፣ ‹ስጡ እንጂ›› ሲል ደወለ፤ ነገር ግን ‹‹ጌታዬ እርስዎ ራስዎ ቢመጡ እንኳ አንሰጥም›› አሉ፤ ነጋ። በብዙ ሞክረው አልሳካ ሲላቸው አለም በቃኝ እስር ቤት ያስገቧቸዋል።
ለሁለት ወር ያህል የታሰሩበት ዓለም በቃኝ እስር ቤት ባሉበት ሁሌ ዓርብ ዓርብ ሰው እየተጠራ ይረሸናል። አንድ ቀን የእርሳቸውም እጣ ደረሰና ባላሰቡበት ሰዓት ተጠርተውከአንድ ጓደኛቸው ጋር ጫኗቸው። ነገር ግን ያጅቧቸው ሁለት ወታደሮች ቦታ ስለሞላባቸው እርሳቸውና ጓደኛቸው ውረዱ ተባሉ። ያው በቀጣይ ሳምንት እንደሚወስዷቸው አውቀው ተመለሱ። ግን አልተደሰቱም፤ ከዚህ ሁሉ ጭንቅ ቶሎ ሞተው መገላገልን ስለሚፈልጉ ተናደዱ፤ ተማረሩም።
አንድ ቀን ማለዳ ላይ ባለቤታቸው የሚበላ ነገር ይዘው መጥተው ‹‹አይዞህ ትፈታለህ ብሎሃል ጓደኛህ›› ሲሏቸው፤ ‹‹አይ ምን የእኔ ብጤ ደሃ ነው፤ ምን ችሎታ ኖሮት ያስፈተኛል ደግሞ›› ይላሉ፤ ጓደኛቸው ግን በአቅሙ ብዙ ነገሮች እንዲለወጡ መስዋዕት ከፍለው ነበርና በእርግጥም ጊዜው ደርሶ ‹‹ተዘጋጅ ልትወጣ ነው››ተባሉ። ይሁንና ፋይላቸው በመጥፋቱ በዕለቱ ሳይወጡ ይቀራሉ። በማግስቱም፣ በሶስተኛውም ቀን ሲፈለግ ይጠፋና ሳይወጡ ቀሩ። በአራተኛው ቀን ግን አብዮታዊ እርምጃ ከሚወሰዱባቸው የስም ዝርዝር ውስጥ እስኪ እዩ ሲባል እዛ ይገኙና ይፈታሉ።
እንደተፈቱም ጓድ ለገሰ አስፋው ቢሮ ይገቡና ‹‹ለዚህ ያበቃኝ ጥፋት ምንድን ነው? ጥፋቴን ሳላውቅና ሳላርም የትኛው ቦታ አልሰራም›› ይሏቸዋል። ጓድ ለገሰም የሚሉት ጠፋቸው ‹‹ስማ! በቃ አብዮት ልጇን ትበላለች የሚለውን መፈክር አታውቅም? ይሄ አጋጣሚ ነው›› አሏቸው። በቃ ከዛ በኋላ ወደየትም አልሄዱም የካቲት 66 ወደሚባል ፖለቲካ ትምህርት ቤት ገብተው ተማሩ፤ ወደቀድሞው ስራቸው እንዲመለሱ ቢለምኗቸው ‹‹አልመለስም፤ ወታደር ነው የምሆነው›› ብለው አሻፈረኝ አሉና ሰልጥነው በ1969 የሱማሊያን ወረራን ለመመከት ወሰኑ። ጦርነቱንም አሸንፈው የአንደኛ ፓራኮማንዶ ብርጌድ ፖለቲካ ኃላፊ በመሆን ወደሰሜን አቀኑ፤ ‹‹የምስራቁ ድል በሰሜንም ይደገማል!›› በሚል አቅንተው እዛ አካባቢ ሲዋጉ በነበረበት ጊዜ የወያኔው አባል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ያመለጣቸው ለትንሽ እንደሆነ ነው የሚናገሩት።
ወያኔ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ለማዕረግ ስልጠና ጦላይ እንዲገቡ አደረጋቸው። ቀጥለውም ከእነርሱ ጋር እንዲሰሩ ሲጠይቋቸው ‹‹ትናንት አብዮታዊት ኢትዮጵያ ወይ ሞት ስል የነበርኩ ሰው ነኝ፤ አገር ገንጣይና አስገንጣይ ስል ነበር፤ ስለዚህ ከእናንተ ጋር አልሰራም›› አሉ። በዚህም ልዩ እስር ቤት አስገቧቸው። ሁለተኛ ያገቧት ባለቤታቸውም ወታደር ነበረችና ከእስር ሲወጡ ወደእርሷ ወላጆች ቤት ሄደው አብረው መኖር ጀመሩ። ይሁንና ባለቤታቸውን ከአምስት ዓመት በፊት በሞት አጥተዋቸዋል።
የታምራት ላይኔ ለደርግ ወታደር ጥይት እንጂ መብት አይገባውም ማለት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ታምራት ላይኔ በአንድ ወቅት የደርግ ወታደሮች ጡረታ ይሰጠን ብለው ተሰልፈው እያለ ‹‹ለእናንተ ጥይት እንጂ መብት አይገባችሁም›› ይሏቸዋል። ቢሆንም እንደምንም 300 ብር ጡረታ ማግኘት ቻሉ። ስለማትበቃቸውም በጥበቃ ስራ ተቀጠሩ። በሙያቸው ሌላም ስራ መስራት ቢጀምሩም መቀጠል ባለመቻላቸው ለቀው ወጡ፤ በአሁኑ ወቅት ያሉት በጡረታዋ ገንዘብ ብቻ ነው። ባለቤታቸውም ከጎናቸው ባለመኖሯ ያዝናሉ። እስካሁንም በባለቤታቸው ወላጆች የጭቃ ቤት ውስጥ ናቸው። ህሊና ሸጦ ትርፍ ማጋባስን አጥብቀው ይጠላሉ። እንዲያ አይነት አስተሳሰብ ኖሯቸው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ከፍተኛ ኢንቬስተር ይሆኑ ነበር። ገና በልጅነታቸው አባታቸው፣ ‹‹ልጄ የሰው ንብረት ያለአግባብ ከአንተ ጋር ብትቀላቅል ጥቁር ውሻ ውለድ›› ያሏቸውን ሁሌ ያስታውሳሉ።
መልዕክት
እርሳቸው ሶስት መንግስትን አሳልፈዋል፤ ይህ ትውልድ ቆም ብሎ ማሰብ እንጂ እንደ ግሪሳ ባላስተዋለው ነገር መብረር የለበትም ይላሉ። በኃይለስላሴም በደርግም ሆነ በኢህአዴግ የተለያዩ ችግሮች ነበሩ። ኢትዮጵያ እጆቿን ወደእግዚአብሔር ትዘረጋለች የሚለው እውን ይሆን ዘንድ ዶክተር ዐብይን እግዚአብሄር አመጣቸው። ስለዚህ ዛሬ እርሳቸው እየሰሩ ያሉት ነገር የሚዳሰስና ተጨባጭ የሆነ ነገር ነው፤ ይህን አምነን የማንቀበል ከሆነ ችግር፤ ዶክተር ዐብይን ገሚሱ ወደብሄርና ጎሳ ሊወስደው ይፈልጋል። ሌላው ደግሞ ስሙን ሊያጠለሽ ይፈልጋልና ይህ አግባብ ባለመሆኑ እንተባበረው ይላሉ።
ዶክተር ዐብይ፣ አገርን ወደከፍታ ይዞ ለመውጣት ሲባክንና የተናገረውን ከመቅጽበት ሲተገብር እያየን ማመን ያቃተኝ ስለምንድን ነው ሲሉ በመጥቀስ፤ ትውልዱ ግን ቆም ብሎ እንዲያስተውል ይመክራሉ። የቱንም ያህል የተለያዩ ችግሮች ቢደቀኑብንም ይህ ሁሉ የመጣው በእኛ አስተሳሰብ መዋዠቅ ነው ሲሉም ይናገራሉ። ማየት ማመን ነውና ይህ ህዝብ ሙት ናፋቂ እንዳይሆን ይሻሉ፤ የሰው ልብ ጥማት ያለፉ ገዢዎችን መመኘት እንዳይሆን ይመክራሉ። ስለዚህም ከዐብይ ጋር በትኩረት መስራት አገርን ውጤታማ ያደርጋልና እንበርታ ሲሉ መልዕክታቸውን ያስተላልፋሉ።
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 23/2013