ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረጉ ውስጣዊና ውጫዊ ጫናዎች በከፍተኛ ሁኔታ የጨመሩበት ሁኔታ ይስተዋላል። በተለይ በሃገራችን የመጣውን ሁለንተናዊ ለውጥ ተከትሎ የኢትዮጵያዊነት ስሜት ዳግም ማንሰራራትና የኢትዮጵያውያን ዳግም ትንሳኤ እውን መሆን የተስፋ ጭላንጭል ያልተመቻቸው የውስጥና የውጭ ጠላቶች ይህንን ተስፋ ለማጨለም በተለያዩ መንገዶች በኢትዮጵያ ላይ የከፈቱትን የማዳከም ዘመቻ አጠናክረው ቀጥለዋል።የነዚህ ጫናዎች አንድምታ ደግሞ መንግስትን ጫና ውስጥ መክተትና ተላላኪ መንግስት በመፍጠር ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ማንበርከክ ነው። በዚህ ሂደት ደግሞ ንፁሃን ዜጎች የገፈቱ ቀማሽ እየሆኑ ይገኛሉ፡፡
ሰሞኑን አሸባሪው ህወሃት በተለይ በአማራና በአፋር ክፍሎች እየፈጸመ ያለውን ግፍና የጥፋት ተግባር ስንመለከት ለዚህ አንድ ማሳያ ነው።ቡድኑ በአማራ ክልል በንጹሃን ዜጎች ላይ ከባድ መሳሪያ በመተኮስ ጭምር ንፁሃንን እየገደለ ሲሆን ንብረታቸውን እየዘረፈና ከፊሉንም እያጠፋ ይገኛል።በዚህ ጥቃትም አምስት የአንድ ቤተሰብ አባላትን ጨምሮ ያለአባትና እናት ያስቀራቸው ህጻናት እና አረጋውያን በርካቶች ናቸው። ከዚህም ባሻገር እንስሳትን በመግደልና ሰብልን በማውደም የፈጸመው አሳፋሪ ተግባርም ቡድኑ ምን ያህል ኢትዮጵያን ለማጥፋት እየሰራ ያለ ሽብርተኛና አጥፊ ሃይል መሆኑን በገሃድ ያሳያል፡፡
በሌላ በኩል የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉት ጫናም ከመቼውም ጊዜ በላይ በተጠናከረ ሁኔታ ቀጥሏል። ሰሞኑን በተባበሩት መንግስታት ድርጅትና አንዳንድ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር በሚፈልጉ ሃይሎች ጥሪ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ ሰብሰባ የተቀመጠው የፀጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር ምን ያህል በከፍተኛ ሁኔታ እየተሰራ እንደሆነ ማሳያ ነው።ይህ ስብሰባ ምንም እንኳን ለእውነትና ለፍትህ በቆሙት እንደነ ቻይና፣ ሩስያና ህንድን በመሳሰሉ ሃገራት ጠንካራ አቋም ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ከታቀደልት ዓላማ አንጻር ባይሳካም ጫናው ግን ምን ያህል በኢትዮጵያ ላይ የበረታ እንደሆነ ማሳያ ነው፡፡
ይህ ምክር ቤት በአንድ በኩል በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በከፍተኛ ሁኔታ በቀውስ ውስጥ የገቡ በርካታ ሃገራት መኖራቸው እየታወቀ ከነዚህ ሁሉ ቅድሚያ ሰጥቶ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር መንቀሳቀሱ ቡድኑ በኢትዮጵያ ላይ ምን ያህል የተለየ ተልዕኮ ይዞ እየሰራ እንደሆነ ያሳያል።በሌላም በኩል በተለይ በርካታ የምዕራባውያን ሚዲያዎች፣ የእርዳታ ድርጅቶችና የሰብአዊ መብት ተቋማትም ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ሲሰሩ ሲታይ እነዚህ ሃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር በከፍተኛ ሁኔታ ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን ያመለክታል፡፡
ሰሞኑን ዋሽንግተን ፖስት የተባለው የአሜሪካ ሚዲያ ከአሸባሪው ደብረጽዮን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶንዮ ጉቶሬዝ የተላከ ደብዳቤ ይዞ ወጥቷል።ይህ ደግሞ ድርጅቱ ምን ያህል ከፍትህ እና ከቆመለት ዓላማ ያፈነገጠ ተግባር ውስጥ እንዳለ የሚያሳይ ነው።ምክንያቱም እኚህ ሰው ከአንድ የአልቃይዳ ወይም የአይ.ኤስ.አይ.ኤስ ወይም የሌላ አሸባሪ ቡድን በዚህ መልኩ ደብዳቤ ለመቀበልም ሆነ ተደራደሩ ለማለት ፈጽሞ አያስቡትም።ነገር ግን ሽብርተኝነት ለአሜሪካም ሆነ ለኢትዮጵያ አንድ ነው።ደብረጽዮን በኢትዮጵያ ሽብርተኛ እንደሆነው ሁሉ የአይ.ኤስ.አይ ኤስም ሆነ የቦኮሃራም መሪዎች ለአሜሪካ ሽብርተኛ ቡድኖች ናቸው።ልዩነቱ አንዱ ኢትዮጵያን ዋነኛ የሽብር ማዕከል አድርጎ መስራቱና የሌላው ዒላማ ደግሞ ሌላ መሆኑ ብቻ ነው።
ከዚህ አንጻር አሜሪካ አንድም ጊዜ ከአሸባሪ ድርጅት ጋር የመደራደር ፍላጎት ኖሯት አያውቅም።በአሜሪካ ታሪክ ትልቅ የሽብር ድርጊት የፈጸመው ቢንላደን በአሜሪካ ላይ ላደረሰው ጥፋት የቀረበለት ውሳኔ ድርድር ሳይሆን ጊዜ ጠብቆ ማጥቃት እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው። ከዚህም አልፎ ሽብርተኞችን ለጠቆመ በሚሊየን ዶላሮች የሚቆጠር ገንዘብ ስጦታ ለመክፈል እንደምትችል በተደጋጋሚ ጥሪ አቅርባለች።ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያን የሚያሸብሩ አካላትስ ከነዚህ የሚለዩት በምን ይሆን? ይህ አሜሪካ ለኢትዮጵያ ያላትን የተዛባ ግምት ከማሳየት ውጭ የተለየ ትርጉም ሊሰጠው አይችልም፡፡
አሜሪካም ሆነች የሰብአዊ መብት ተቋማት ድምጻቸው የሚሰማው ኢትዮጵያ በአሸባሪው ቡድን ላይ እርምጃ መውሰድ ስትጀምር ነው። ከዚህ በተቃራኒ ግን የሽብር ቡድኑ ንጹሃንን ሲጨፈጭፍ ዝምታን ሲመርጡ ይታያል።ለምሳሌ በማይካድራ፣ በጋሊ ኮማና አጋምሳ ስለተጨፈጨፉ ንፁሃን ዜጎች ድምጻቸውን ሲያሰሙ አይታይም።ሰሞኑን በአማራ ክልል በርካታ ንፁሃን ዜጎች በከባድ መሳሪያ ጭምር ሲጨፈጨፉ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለው አልፈውታል።ከዚህ በተጻራሪው ግን በሀሰት መረጃ ሳይቀር የመንግስት ሃይሎች ሰብአዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል የሚል ክስ ሲፈጥሩ ይስተዋላል።ሆኖም ጥፋቶችን ሁሉ በእኩል ማውገዝ የገለልተኝነት መለኪያ ሊሆን ይችላል።ከወንጀሎች መካከል መርጦ አንዱን መኮነንና ሌላውን በዝምታ ማለፍ ግን ፍርደ ገምድልነት ነው፡፡
ያም ሆነ ይህ ግን ኢትዮጵያ ዛሬም ለሰላም ያላት ቁርጠኝት ከማንም በላይ ነው።በተለይ ሰላሟን ለማደፍረስ የሚጥሩ ሃይሎችን ፈጽሞ አትታገስም። ከዚህም ባሻገር በውጭም ሆነ በውስጥ ጠላቶች ጩኸትና ድንፋታ ተሸብራ ማንም እንደፈለገ እንዲጠመዝዛት እጇን አትሰጥም።ኢትዮጵያ ለእውነት መቆምን ዓለም ፍትህን በተጠማበት የጭለማ ዘመን ጀምሮ ኖራ አሳይታበታለች። በቀጥተኛው የቅኝ አገዛዝ ዘመንም አልተቀበለችውም፤ አሁንም በተዘዋዋሪ በሚደረገው የቅኝ ልግዛህ አካሄድ ከመስመሯ ፈቀቅ ሳትል እውነትን ይዛ እስከመጨረሻው ትጓዛለች።
መላው ኢትዮጵያውንም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ስለሃገራቸው ነባራዊ ሁኔታና ስለተያያዘቸው የእውነት መስመር ለዓለም ማህበረሰብ ሃቁን ለማሳወቅ ከመንግስት ጎን በመቆም መንቀሳቀስ ጊዜው የሚጠይቀው ወቅታዊ ጥያቄ ነው።እውነትን ይዘን እና ጫናውን ተቋቁመን ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማሻገራችን የማይቀር እውነት ነው!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 23 ቀን 2013 ዓ.ም