እውነትና ንጋት እያደር ይጠራል እንዲሉ፤ የጨለመው ሲገፈፍ፣ የዳመነው ሲዘንብ፣ የጨገገው ሲገለጥ ንጋት ይሆናል። ይሄኔ የተደበቀ እውነት መገለጡ፤ የተዳፈነው ፍትህ አደባባይ መውጣቱ አይቀሬ ነው። የኢትዮጵያ የዓመታት ጩኸት፣ የምዕራባውያኑ በተለይም የአሜሪካ እና ተከታዮቿ ጫና እና የእጅ አዙር ጦርነት፤ በአሸባሪው ህወሓት የባንዳነት ተልዕኮ ፈጻሚነት የሽብር ተግባር በጨለማና ንጋት ትንቅንቅ ውስጥ ገብተው ኢትዮጵያውያን የእውነት አሸናፊነትን፣ የፍትህ ኃያልነትን ሲናፍቁ፣ የተዳፈነውን ለመግለጥም ሲታገሉ ኖረዋል።
በተለይ ኢትዮጵያውያን ዓመታትን ሲከፋፍላቸው፣ ሲያጣላና ሲያጋድላቸው፣ አስሮ ሲያንገላታ እና ሰብዓዊ ክብራቸውን ነጥቆ ሲያሰቃይና ሲገድላቸው የኖረውን የዛሬውን አሸባሪ ቡድን ከጫንቃቸው ላይ ከጣሉ በኋላ የኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ከአንዳንድ አገራት ጋር የሚያደርጉት ትንቅንቅ ከፍ ብሎ ታይቷል።
ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያውያን በዚህ ቡድን የደረሰብን ግፍና በደል በዓለም ተገልጦ የቡድኑ ተጠያቂነት ነግሶ ማየትን ይሻሉ። በአንጻሩ አሜሪካና ተከታዮቿ የዚህ ቡድን ህልውና መቀጠል እነርሱ በምስራቅ አፍሪካ ያላቸውን ጥቅም ማስቀጠል መሆኑን ስለሚያምኑ የቡድኑን ችግር ደብቀው ለህልውናው ሲቆሙ ቆይተዋል። ይህ ድጋፍና አይዞህ ባይነት ያልተለየው የሽብር ቡድን ታዲያ ዓላማውም ግቡም ሊያስተዳድራትና እንደሻው ሊያደርጋት ያልቻላትን አገር ማፍረስን የመጨረሻው አማራጭ አድርጎ ሰራ።
በዚህም በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ ከፈጸመው ጥቃት ጀምሮ በማይካድራ፣ ሁመራ፣ ወዘተ ንጹሃንን በገፍ ጨፈጨፈ፤ አቃጠለ፣ አፈናቀለ፤ ሃብት ንብረታቸውን አወደመ። ይሄን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት አገርን የማዳን እርምጃ ሲወስድ የዘር ማጥፋት እየተፈጸመብኝ ነው አለ። ይሄኔ የአሸባሪው ቡድን በንጹሃን ላይ የፈጸማቸው ግፍና በደሎች ያልታያቸው አንዳንድ አገራትና ተቋሞቻቸው በመንግሥት ላይ ዘመቱ፤ ዘር ማጥፋት፣ ሰብዓዊ ጥሰት፣ የጦር ወንጀል፣… የሚሉ ድምጾች በረከቱ። መንግሥት ተኩስ አቁሞ ከክልሉ እንዲወጣም ወተወቱ።
ኋላ ደግሞ መንግሥት ተልዕኮውን ጨርሶ ለሰብዓዊነት ድጋፍ ቅድሚያ በመስጠት ሰራዊቱን ከክልሉ ሲያስወጣ፤ የሞተውን ቡድን አክመውና አብልተው ከመቃብር አስነሱት። እናም በአፋርና በአማራ ክልሎች ላይ ዘምቶ ንጹሃንን በጅምላ ጨፈጨፈ፤ ንብረት አወደመ፣ በመቶ ሺዎች እንዲፈናቀሉ አደረገ። ይሄን ተግባር መላው ኢትዮጵያውያን አውግዘው ቡድኑን ዳግም ለመደምሰስ በአንድ ተሰለፉ።
ታዲያ በአፋርና አማራ ክልሎች በአሸባሪው ህወሓት የዘር ማጥፋት ጭፍጨፋ ሲካሄድ ማየትም መስማትም ያልፈለጉት እነዚህ
አገራት፤ ይሄን ጊዜ የቀደመ ዜማቸውን ዳግም አደሱ፤ ስለትግራይ ሴቶች መደፈር፣ ስለ ሰብዓዊ ድጋፍና ሌላም በሚዲያዎቻቸው ፊታውራሪነት አቀነቀኑ። ይባስ ብለውም በመንግሥት ላይ ጫና ለማሳደር፤ በሉዓላዊት አገር ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት ቋመጡ።
ይሄን ህልማቸውን እውን ለማድረግ ደግሞ በእጃችን ነው ብለው ያሰቡትን የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤትን እንደ ዓላማቸው ማስፈጸሚያ ለመጠቀም ለሁለተኛ ጊዜ የኢትዮጵያን የውስጥ ጉዳይ ይዘው ቀረቡ። ይሁን እንጂ እውነት እና ፍትህ ተቀብራ አትቀረምና በምክር ቤቱ እንዳሰቡት ጉዳያቸውን በቀጥታ ወደውጤት መቀየር ሳይችሉ ቀሩ።
ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ በምክር ቤቱ ጣልቃ መግባትን የሚያቀነቅኑ አገራትን ሀሳብ ወደጎን ብለው የኢትዮጵያ ጉዳይ በራሷ በኢትዮጵያ ሊፈታ የሚችል ነው እና ጣልቃ መግባት አያስፈልግም የሚለውን ሀሳብ ያራመዱት ሩሲያ፣ ቻይና፣ ህንድ እና ኬንያን የመሳሰሉ አገራት የጣልቃ ገቦችን ሃሳብ መና ስላደረጉት ነው።
በዚህም የሃሰት የሴራ መረብ መበጣጠስና እውነትም ከሰለለችበት ወጥታ መፋፋት ስትጀምር፤ መድረኩ ወደ ፍትህ አደባባይነት ተለወጠ። የሴረኞችን ምኞት የሚገዳደረው ሲመጣ ሀሰትና እውነት በአደባባይ በይፋ መታየት ጀመሩ። ኬንያን የመሳሰሉ የአፍሪካ አገራት ኢትዮጵያ ኮሎኒያሊዝምን በመዋጋት ሂደት የተጫወተችውን ሚና፤ አፍሪካውያን ስለነጻነታቸውና አንድነታቸው እንዲሰሩ ስለፈጸመችው ተጋድሎ መስክረው ይሄን ያደረገች አገር ለውስጥ ችግሯ እንደማታንስና የምዕራባውያን ጣልቃ ገብነት እንደማያስፈልጋት አስገነዘቡ።
እንደ ሩስያ፣ ቻይና፣ ህንድና ቬትናም ያሉት አገራት ደግሞ ኢትዮጵያውያን የራሳቸውን ጉዳይ በራሳቸው የመፍታት አቅሙም ልምዱም ያላቸው እንጂ የሌሎች ጣልቃ ገብነት እንደማያስፈልጋቸው፤ አገራትም ጣልቃ ለመግባት ከመሞከር ይልቅ ፍትሃዊ በሆነ መልኩ የሰብዓዊ ድጋፍ በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች ማድረስ ስለሚቻልበት ሂደት ማሰብ ተገቢ ስለመሆኑ አሳሰቡ።
በዚህም የኢትዮጵያውያን እውነት ሲገለጥ፤ የምዕራባውያኑ የሴራ መረብና የሽብርተኛው ተላላኪዎች ክፉ ምግባር መታየት ጀመረ፤ የጭቆናና ጫና ቁልል ሲሟሽሽ ፍትህ በአደባባይ ከፍ ብላ መራመድ ጀመረች። እናም ቢዘገይ እንጂ እውነት መገለጡ፤ ፍትህም መረጋገጡ አለመቅረቱ እውን ሆነ። ምክንያቱ ደግሞ እውነትንና ፍትህን የያዘችው ኢትዮጵያ ሁሌም አሸናፊ በመሆኗ ነበር!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 22/2013