በቅርቡ በተጠናቀቀው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ ኢትዮጵያ ያልተጠበቀና ዝቅተኛ ውጤት ማስመዝገቧን ተከትሎ የውድድሩ ዋና ባለ ድርሻ አካላት በሆኑት የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መካከል ለተመዘገበው ውጤት ተጠያቂ ላለመሆን ጣት መቀሳሰሩ ቀጥሏል።
ባለፈው ሳምንት ጉዳዩን አስመልክቶ መግለጫ የሰጠው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለተበላሸው ውጤት የኢትዮጵያን ሕዝብ ይቅርታ በመጠየቅ የተለያዩ ስህተቶች የተፈጠሩት በአትሌቲክስ ፌዴሬሽን አመራሮች፣ አሰልጣኞችና የተለያዩ ባለሙያዎች መሆኑን ገልፆ ነበር። በተለይም የተጠቀሱት አካላት ከአትሌቲክስ ዓለም አቀፍ ገበያ ጋር በጥቅም የተሳሰሩ በመሆናቸው ጉዳት ያለባቸው አትሌቶች መሆናቸው እየታወቀ እንዲወዳደሩ በማድረግ እንዲሁም በአትሌቶች ምርጫ ላይ ከጥቅም ጋር በተያያዘ አቅም ያላቸውን አትሌቶች በማስቀረትና በተገቢው የአየር ንብረት እንዳይዘጋጁ በማድረግ ውጤት እንዲበላሽ ማድረጋቸውን ጠቁሞ ነበር። ይህን የኦሊምፒክ መግለጫ ተከትሎም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የሚሰጠው ምላሽ ሲጠበቅ ነበር።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የአትሌቲክስ ውድድርና የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮና አፈፃፀም ላይ ትኩረቱን ያደረገ ጋዜጣዊ መግለጫ ትናንት ማምሻውን በስካይ ላይት ሆቴል የሰጠ ሲሆን፣ በኦሊምፒኩ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጣልቃ ገብነት በውጤት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ማሳደሩን ገልጿል።
ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንቱ አትሌት ገዛኸኝ አበራ፣ አቃቤ ነዋዩ ዶክተር በዛብህ ወልዴና የፅህፈት ቤት ሃላፊው አቶ ቢልልኝ መቆያ ናቸው፡፡ ፌዴሬሽኑ በተሰጠው ሃላፊነትና ተግባር መሰረት አትሌቶችናአሰልጣኞችን የመምረጥ እንዲሁም የማሳወቅ ሃላፊነትና ተግባሩ በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጣልቃ ገብነት ችግሮች በመፈጠራቸው በአግባቡ ተናቦ መስራት እንዳይቻል በማድረጉ ለተበላሸው ውጤት ምክንያት ስለመሆኑ መደበቅ እንደማይቻል ገልጿል።
በ3ሺ ሜትር ለኦሊምፒክ ሲዘጋጅ የቆየው አትሌት ለሜቻ ግርማ በፌዴሬሽኑ ፍላጎት ለስምንት ወራት ልምምዱን ሲሰራ መቆየቱን ያስታወሰው የፌዴሬሽኑ መግለጫ፣ አትሌቱ ከደረሰበት የእግር ጉዳት እንዲያገግም የህክምና ድጋፍ ሲደረግለት ቢቆይም እስከ መጨረሻ የአትሌቶችን ዝርዝር ማሳወቂያ ቀን ባለማገገሙ ስሙ ለኦሊምፒክ ኮሚቴ ሳይተላለፍ እንደቀረ ጠቁሟል። ኦሊምፒክ ኮሚቴ አትሌቱን በማንኛውም ጊዜ ማስመዝገብ እንደሚቻል እያወቀ ፌዴሬሽኑን ማማከር ሲገባው በራሱ ስልጣን እንዲወዳደር ማድረጉ አግባብነት እንደሌለው ጠቁሟል። ያም ሆኖ አትሌቱ ባስመዘገበው ውጤት ፌዴሬሽኑ ደስተኛ መሆኑን አስረድቷል።
ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለረጅም ጊዜ የአትሌቶችን ጤንነት፣ አመጋገብና ሌሎች የጤና አጠባበቅና ክትትል የሚያደርጉ የፌዴሬሽኑ የህክምና ባለሙያዎች እያሉ ከአትሌቶች ጋር በመቆየት ሙያቸውን ያልተወጡ ሌሎች ሃኪሞችን በማሳተፍ በአትሌቶች ስነ ልቦና ላይ ተፅእኖ መፍጠሩን የጠቀሰው የፌዴሬሽኑ መግለጫ፣ ለተበላሸው ውጤት በፌዴሬሽኑ ላይ የተሰነዘረው ወቀሳ ተቀባይነት እንደሌለው ገልጿል።
በየትኛውም የኦሊምፒክ ጨዋታ ላይ ባልታየና ባልተለመደ መልኩ የቡድን መሪና የቴክኒክ ቡድን መሪን ከድጋፍና ክትትል ውጪ በማድረግ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የሆኑ አመራሮችን በመመደብ ያላዘጋጁትን አትሌትና አሰልጣኝ እንዲመሩ ማድረግ፣ የፌዴሬሽኑን አመራሮች ከፋፍሎ ግማሹን አገር ውስጥ በማቆየት ግማሹን ደግሞ ቶኪዮ ሆቴል ውስጥ በመገደብ ‹‹ኢ ሰብዓዊ›› ድርጊት ተፈፅሟል፣ ይህም በአሰላለፍና በውጤት ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል ሲል ፌዴሬሽኑ አስታውቋል፡፡
በተለይም የፌዴሬሽኑን ፕሬዚዳንትና የአትሌቲክስ ቡድን መሪውን ከማንኛውም እንቅስቃሴ በመገደብ የተሰጣቸውን ሃላፊነት በአግባቡ እንዳይወጡ ሲደረግ በወቅቱና በስፍራው የነበሩት የኢፌዴሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር እንዲሁም የስፖርት ኮሚሽን አመራሮች መፍትሄ መስጠት አለመቻላቸውና በዝግጅትም ወቅት የተፈጠሩ ስህተቶችም እንዲታረሙ እርምጃ አለመውሰዳቸው ነገሮችን አንዳባባሰም በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡
ከዚህ ባሻገር ለውጤቱ መጥፋት ሁለት ቦታ የሚረግጡ አሰልጣኞች ሚና ከፍተኛ እንደነበር የፅሕፈት ቤት ሃላፊው አቶ ቢልልኝ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ ጠቁመዋል፡፡ የውጤቱን መበላሸት ተከትሎ ለኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት ቀርቦላቸው የነበረው በውጤቱ መበላሸት ስልጣን የመልቀቅ ጥያቄ ለፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉም ከጋዜጠኞች ቀርቦ፣ ‹‹የመረጠኝ አካል አታስፈልጊም ካለኝ በደስታ›› በማለት ምላሽ ሰጥታለች፡፡
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 21/2013