ከእለታት አንድ ቀን ቀበሮ የሚበላ ነገር አጥታ በጣም ተራበች። ምግብ ፍለጋ ወደ አንድ አቅጣጫ ጉዞዋን ጀመረች። ብዙ ተጓዘች ግን ምግብ ማግኘት አልቻለችም። እናም ተስፋ ቆርጣ ሳለ ነበር ያልጠበቀችው ነገር የተመለከተችው። ለማረፍ በአንድ ዛፍ ስር ተቀምጣ ነበርና ወደ ላይ አንጋጠጠች። በዚህ ጊዜም አንዲት ቁራ ትልቅ ሙዳ ሥጋ በአፏ ይዛ እየበረረች እርሷ የተቀመጠችበት ዛፍ ላይ አረፈች። ሥጋውንም ስታይ ረሀቧ ጨመረ። በጣም ተቁነጠነጠች።
ይሁንና ስጭኝ ማለት ግን አልቻለችም። እንዳትነጥቃት ደግሞ ቁራዋ ዛፍ ላይ ነው ያለችው። እርሷ ደግሞ ዛፍ ላይ መውጣት አትችልም። ወደ ዛፉ መውጣት ብትሞክር ቁራዋ ትበራለች። ስለሆነም ቀበሮ ግራ ገባት። ስለሆነም ዘዴ ለመቀየስ ማሰላሰል ጀመረች። «ዛሬማ ይሄ ስጋ አያመልጠኝም፤ እንደምንም ማግኘት አለብኝ» ብላ የምታገኝበትን ስልት መፈለጓን ተያያዘችው። ከዚያ ቀበሮ የመጣላት ዘዴ ቁራን ማሞካሸት ወይም ማወደስ ነበር።
«ድምጿን ከፍ አድርጋ እጅግ የተዋበች ቁራ እዚህ ተቀምጣለች። ውበቷ ድንቅ ነው፣ የሚያምር ድምጽም አላት። እንደ ውበቷ ቢሆን የወፎች ሁሉ ንግሥት ትሆን ነበር» በማለት አወደሰቻት። ቁራዋም በቀበሮ የቀረበላትን መወድስ ስትሰማ ማመን ተስኗት እጅግ በጣም ተደሰተች፡፡ ከመደሰቷ የተነሳም በምስጋና ለቀበሮ ድምጿን ለማሰማት ስትሞክር በአፏ የነበረውን ሙዳ ሥጋ ለቀቀችው፡፡ ቀበሮዋም በፍጥነት የወደቀውን ሥጋ ጎርሳ ረሀቧን አስታገሰች። ከቆይታ በኋላ ግን ቁራም እንደተታለለች ገባት። ግን ሁለተኛ ላለመታለል ራስዋን ከማሳመን ውጪ ሥጋዋን ማግኘት ሳትችል ቀረች።
አንዳንድ ጊዜ መናገር በምን ወቅትና እንዴት ባለሁኔታ መሆን እንዳለበት አንመለከተውም። የሚታየን ያለንን ከአጣን በኋላ ነው። ሰዎች ይህ የአንተ ነበር፤ ይህ ደግሞ ታሪክህ አይደለም፤ እንትና እኮ እንትን አድርጎሃል ሲለን በአንድ ጊዜ ልባችን ውስጥ ይቀራል። እንቀበለውናም ያለምንም ማገናዘብ ወደ ተግባር እንገባለን። የንግግር ጦሩ ግን እኛንም ሆነ ሌሎችን ሲጠቅም አናየበትም። ወግቶ ሲገለን እንጂ! በተለይም ከብሔር፤ ከወሰን ጋር ተያይዞ የሚረጨው የጥላቻ ንግግር ያለንን እየነጠቀን ይገኛል።
ሲያሞግሱና ሀሳብ ሲሰጡ ብሎም ቃላቶች አምረው አምረው ሲቀርቡ ውስጡ ምን እንዳለ መመልከት ይበጃል። ለምን ሙገሳው በዛ የሚል ጥርጣሬ ማንሳትም ብልህነት ነው። ሁልጊዜ አዎንታዊ እይታ በእያንዳንዱ ዘንድ ላይኖር ይችላል። በሚገባ አሰላስሎ አዎንታዊነትን መከተል ግን ዋጋው ላቅ ያለ ነው። አሉታዊ አስተሳሰብን ለማስወገድ ይረዳል። ከዚህ ውጪ ግን በውሸት ቃላት መሸነጋገል ፋይዳ ቢስ ይሆናል። ለሰዎች ማዘን ሳይሆን ሰዎችን ወዳልተፈለገ መንገድ በመምራት ያላቸውን እንዲያጡ፤ ስለሰው እንዳያስቡና የራሳቸውን ደህንነት መጠበቅ ላይ ብቻ እንዲሰማሩ ያደርጋል። ልክ እንደቀበሮዋ ማለት ነው።
ለሆድ ብቻ ማሰብና መኖር ጥላቻንና ለቀጣይ ሆድ ሙላት ሌላ የጥላቻ ዘዴን መቀየስን ያለማምዳል። ምክንያቱም ሙዳ ሥጋው የተገኘው በሽንገላና ለራስ ብቻ በማሰብ ነው። ለራስ ብቻ መኖር ደግሞ ሰብዓዊነታችንን ያበላሻል። ስለሌሎች ችግርም እንዳናውቅ ያደርገናል። የጠፋብንን ነገር እንዳንረዳውም በር ይዘጋብናል። ተግባሩን እንጂ እውነታውን እንዳንገነዘብ ያደርጋል። በዚህም ከሰው መነጠልንና ጸብን ብቻ የምንሻ እንድንሆን ያደርጋል። ስለሆነም አንዳችን ለሌላችን መፍትሄ ከማፈላለግ ይልቅ በችግሩ መፍትሄ ላይ መቆም ሳይሆን እልባት መስጠት ይገባናል።
አንዳችን ለሌላው መሰል ወንድማችን ብቻ ሳይሆን ለራሳችን እንቅፋት መሆንም የለብንም። ቅንነት በማጣት በሽታ ታውሮ ከመጓዝም መቆጠብ አለብን። በመንገዳገድ ዘመናችንን መጨረስ ተገቢ አይደለም። ሰለጠንን ካልን ከጦርነት ይልቅ ንግግርና ውይይትን መምረጥ አለብን። ብዙዎች ማንነታቸውን፤ አብሮነታቸውን፤ መቻቻላቸውን ያጡት የጥላቻ ንግግርን በውስጣቸው ስላዘሉ ነውና ከዚህ መራቅ ባህሪያችን ልናደርገው ይገባል። መሸነጋገልን ማስቀረት፤ አስቦ መራመድ፤ ንግግሩ ምን እንደሆነና ምን እንደሚያስከትል ቀድሞ መረዳት ያስፈልጋል። ነገሮችን ሌሎች ሊያዩት በማይችሉበት አቅጣጫዎች ማየትም የሁልጊዜ ተግባር መሆን አለበት።
ሁሌም መመረጥ ያለበት የብዙዎች ዕብደትን ተከትሎ መጓዝን ሳይሆን፤ ጥፋት እንዳይከተል ምን ማድረግ አለብን የሚለው ነው። ከአንድ አካባቢ ወደ ሌላው አካባቢ የሄደ እንግዳ ከማንም በላይ የሚከበርበትና ከቤተሰቡ አባል በላይ እንክብካቤ የሚያገኝበት ጠንካራ ባህል እንዳለን ሁሉ ያንን ማቆየቱ ላይ ጠንክረን መስራት ይኖርብናል።
የሃይማኖት አባቶች፣ አገር ሽማግሌዎች፣ አባገዳዎች፣ ምሁራን፣ ወላጆች እንዲሁም በተለያየ ማህበራዊና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ውስጥ የሚገኙ ተደማጭ አካላትም ንግግራቸው አስተማሪ እንጂ ጸብ ጫሪ ሊሆን አይገባም። የቀደመውን የአገራችንን ጠንካራ የአንድነትና የመቻቻል እንዲሁም የመከባበር ባህል በመመለስና በማጠናከር አገራችንን ወደ ሰላምና ወደ ብልጽግና ለማምጣት ትልቅ ስራ መስራትም ይኖርባቸዋል።
ዛሬ ላይ እያጣን የመጣነው ሳያስቡ ግጭት ውስጥ መግባትን፤ ሳያገናዝቡ መናገርን፤ ለራስ ብቻ ለመኖር ሲባል ጥላቻ ንግግራችን አገር ማመስን ነው። ሰዎችን ለማድመጥና በትክክል ገስጸን ከጥፋት መንገዳቸው ለመመለስ ዝግጁ አይደለንም፤ በሽንገላችን ሞልተን እንጥላቸዋለን እንጂ። ይህ ግን ለእኛ ኢትዮጵያውያን ማንነታችንም ባህላችን ሊሆን አይገባም። ዛሬ የጣልነው ነገ ቀና ብሎ እንደሚያየን ማሰብ ያስፈልጋል። አንዱ ሲናገር ሌላው አዳማጭና አሳቢ መሆን አለበት። ሌላው ስለኛ የሚናገረውንም ነገር በጥሞና መመረመር ይገባናል። እንደቁራዋ በሽንገላ ማመን፤ እንደ ቀበሮዋ ለራሴ ብቻ ልኑር ማለት አገር አይገነባምና ልንተወውም ይገባል። ትላንትን መዘከርና ዛሬን መጠበቅም ለነገ ዋስትናችን መሆኑን አውቀን ከጥላቻ ንግግራችን መቆጠብ ልምዳችን ይሁን።
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2011