ባለንበት ዘመን አንድ ሀገር ከሌላው ሀገር ጋር የሚኖራት ግንኙነት ስኬት የሚመዘነው ከሁሉም በላይ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርቶ የሁለቱንም ሀገራት ህዝቦች እኩል ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል አቅም መፍጠር ሲችል ነው። ሀገራቱ ጎረቤታሞች ሲሆኑ ደግሞ እውነቱ ከዚህም ከፍ ብሎ የጋራ እጣ ፋንታን አብሮ እስከ ማሰብና መተግበር የሚደርስ ይሆናል።
ኢትዮጵያ ዛሬም ሆነ በቀደሙት ዘመናት ለጉርብትና ከፍ ያለ ከበሪታ፣ ዋጋ እና ትኩረት የምትሰጥ ሀገር ናት። ኢትዮጵያውያንም ቢሆኑ በእለት ተእለት ህይወታቸው ለጉርብትና የሚሰጡት ስፍራ ከፍ ያለ ነው። ለክፉም ሆነ ለደግ ከቅርብ ዘመድ ይልቅ ጎረቤት የተሻለ ነው ብለው የሚያምኑ፤ ይሄንንም “ከሩቅ ዘመድ የቅርብ ጎረቤት” በሚል ብሂላቸውን አጽንተው እውነቱን ለትውልድ የሚያሳልፉ ህዝቦች ናቸው።
ከዚህም የተነሳ ጉርብትና በማህበረሰባችን ውስጥ ጥንትም ይሁን ዛሬ ከፍ ያለ ቦታ የሚሰጠው ማህበራዊ እሴታችን ነው። ሀገራዊ ፖለቲካዊ አስተሳሰባችንም ከዚሁ ማህበራዊ እሴታችን የተቀዳ ነው። ከጎረቤት ሐገራት ጋር ያለን ግንኙነትም በአብዛኛው ለዚህ አስተሳሰብ የተገዛ ነው።
በቀደሙት ዘመናት ይሁን ባለንበት ዘመን ሐገራችን ከራሷ ድንበር አልፋ ከጎረቤት ሀገራት ጋር ወደ ግጭት የገባችበት ታሪካዊ አጋጣሚ የለም። ከዚህ ይልቅ ከአካባቢው ሀገራት ጋር የተሻለ ጉርብትና በመፍጠር አካባቢያዊ ሰላምና ልማት ለማስፈን ስትንቀሳቀስ ቆይታለች።
የአፍሪካውያንን የነጻነትና እራስን የመሆን ትግሎች በከፍተኛ ሁኔታ ከማገዝ ጀምሮ የፓን አፍሪካኒዝምን የነጻነትና አብሮ የማደግ ፍልስፍናን በማቀንቀን አፍሪካውያን የራሳቸውን እጣ ፈንታ በራሳቸው መቅረጽ እንደሚችሉ ሀዋሪያ በመሆን ብዙ ሰርታለች፤ ስኬትም አስመዝግባለች።
በተለይም የለውጡ ሀይል ወደ ስልጣን ከመጣበት እለት ጀምሮ ይህንን እውነታ በአዲስ መልክና ስትራቴጂ ማስቀጠል የሚያስችል ሰፊ ስራዎችን እየሰራ ይገኛል። በግጭት እና ትርምስ የሚታወቀውን የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ለመለወጥ ከፍ ባለ መነቃቃት እየተንቀሳቀሰ ነው። አካባቢውን የመተባበርና የልማት ቀጠና እንዲሆን እየሰራ ነው።
በአንድ በኩል በአካባቢው ዘላቂ ሰላም ለማምጣት በቀደሙት ዓመታት በአካባቢው ሀገሮች እና በሀገራት ውስጥም የተፈጠሩ የሰላም ችግሮችን በውይይትና በድርድር ለመፍታት ረጅም መንገድ ተጉዟል። በዚህም ሱዳን አበቃላት በተባለችበት ወቅት ከነበረችበት የመበታተን አደጋ መታደግ ችሏል።
በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ዓመታት ያስቆጠረውን ለብዙዎች ሞትና መፈናቀል ምክንያት የሆነውን ችግር ዓለምን ባስደመመ መልኩ በሰላም ስምምነት በመቋጨት በሀገራቱ መካከል አዲስ የትብብርና የወዳጅነት የታሪክ ምእራፍ መክፈት ችሏል። ለዚህም ዓለም አቀፉ ህብረተሰብ እውቅና በመስጠት ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የሰላም ኖቤል ሽልማት ሰጥቷል።
ከዚህም ባለፈ በአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በኢትዮጵያ፣ በኤርትራና በሶማሊያ መካከል አዲስ አካባቢዊ የትብብርና የወዳጅነት ግንኙነት በመፍጠር ለሀገራት ህዝቦች አዲስ ተስፋን ፈንጥቋል። ለግጭት አካባቢዎች ተጨባጭ ምሳሌ የሚሆን አዲስ የትብብር የታሪክ ምእራፍ መፍጠር ተችሏል።
የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ በእርግጥም ከግጭትና ከሁከት ወጥቶ የልማትና የትብብር ቀጠና እንዲሆን የሚያስችል የመሰረት ድንጋይ መጣልም ተችሏል። ይህ ታሪካዊ ክስተትም ለአንዳንድ ሀይሎች የስጋት ምንጭ ሆኗል። ይህንንም ተከትሎ እውነታውን ለመቀልበስ የተወጠኑ ሴራዎች በአካባቢው እየተስተዋሉ ነው።
ይህ ቀጠናዊ ሕብረት በአካባቢው ሀገሮች ህዝቦች ከፍ ያለ ተስፋን ይዞ የመምጣቱን ያህል ተግዳሮትም ይዞ መምጣቱ የአደባባይ ሚስጥር ከሆነ ውሎ አድሯል። ይህንን ተግዳሮት አሸንፎ ለመውጣት በተለይ የትብብሩ ተስፋ ባለቤት የሆኑ ሐገራት ህዝቦችና መንግስታት ተቀራርበው መስራት ይጠበቅባቸዋል።
በዚህ ፈታኝ ወቅት የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ሀገራቸው ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ያለውን አጋርነት በሚገልጽ መልኩ በኢትዮጵያ ይፋዊ ጉብኝት ለማድረግ አዲስ አበባ የገቡበት ክስተት ከፍ ያለ ታሪካዊ አንደምታ ያለው ነው። በኢትዮጵያና በኢትዮጵያ ህዝብም ከፍ ያለ ከበሪታ የሚሰጠው ነው።
በተለይም የፕሬዚዳንት ሳልቫ ኪር ጉብኝት በሁለቱ ሀገራት መካል ያለውን የትብብር እና አብሮ የመልማት ተስፋን እውን የማድረግ ተልእኮን የተሸከመ መሆኑ የሀገሪቱ መሪና ህዝብ በኢትዮጵያ እየሆነ ያለው ዕውነታ ከተግዳሮቶቹ በላይ በወዳጆቻችን ዘንድ ተስፋ የተጣለበት መሆኑን አመላካች ነው።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 ቀን 2013 ዓ.ም