አዲስ
አበባ፡- በህገ
ወጥ ተግባር እየተፈጠረ
ያለውን የኑሮ ውድነት
ለመግታት ከፌዴራል እስከ
ወረዳ ባለው መዋቅር
ግብረ ኃይል መቋቋሙን
ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር
አስታወቀ፡፡
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የንግድ ዕቃዎች ዋጋ ጥናት፣ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር አቶ ካሳሁን ሙላት ትናንት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደገለጹት፤ ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ህገ ወጥ ተግባር በሚፈጽሙ አካላት ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ ግብረ ኃይል ተቋቋሞ ወደ ተግባር ገብቷል፡፡
ግብረ ኃይሉ በየደረጃው ባሉ ከፍተኛ አመራሮች የሚመራ መሆኑን ያመለከቱት አቶ ካሳሁን ፣ የኢኮኖሚ አለመረጋጋቱ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ አሠራሮች ጠንከር ባለ መንገድ ይተገበራሉ ብለዋል፡፡
በህገ ወጥ ተግባር ላይ በተሰማሩ ግለሰቦች ላይ የማያዳግም አስተዳደራዊ ዕርምጃ ይወስዳል ያሉት አቶ ካሳሁን፤ በአካል በመገኘትም ክትትል እንደሚደረግ አስታውቀዋል፡፡
ያለአግባብ የተከማቹ የዘይት፣ የሩዝ፣ የጨርቃ ጨርቅና የብረት ምርቶች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የጠቆሙት አቶ ካሳሁን ፣ግብረ ኃይሉ በየሁለት ሳምንቱ ከክልልና ከከተማ አስተዳደሮች ጋር በበይነመረብ ቋሚ ስብሰባዎችን በማካሄድ በችግሮች ላይ አቅጣጫ ያስቀምጣል ብለዋል፡፡
እንደርሳቸው ማብራሪያ፤ ስንዴ፣ ስኳር፣ ዘይትና የመሳሰሉ መሰረታዊ የምግብ ሸቀጦችን እጥረት ለመቅረፍ በሀገር ውስጥ ከሚመረተው በተጨማሪ ከውጭ ለማስገባት መንግሥት ገንዘብ መድቦ ወደ ሀገር ውስጥ እያስገባ ነው፡፡
በአሁኑ ወቅት 53 ነጥብ ዘጠኝ ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ለስርጭት ዝግጁ ተደርጓል፡፡ ሁለት ሚሊዮን ኩንታል ስኳር ግዥ ተፈጽሞ ወደ ሀገር ውስጥ በመጓዝ ላይ ይገኛል፡፡ አራት ሚሊዮን ኩንታል የዳቦ ስንዴ ግዥ የተፈጸመ ሲሆን፤ ከመስከረም ወር ጀምሮ ወደ ሀገር ውስጥ ይገባልም ብለዋል፡፡
በምግብ ዘይትና በሌሎች የምግብ ሸቀጦች ላይም የአቅርቦትና ፍላጎት መካከል ልዩነቶች እንዳሉ የተናገሩት አቶ ካሳሁን፤ ችግሮችን ለመቅረፍ የአገር ውስጥ ፋብሪካዎችን የማበረታታትና ድጋፍ የማድረግ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለመጪዎቹ በዓላት ለህብረተሰቡ የሚሰራጭ 24 ነጥብ ሦስት ሊትር ዘይት ጅቡቲ መድረሱን የጠቆሙት አቶ ካሳሁን ፤ ከሚቀጥለው ሳምንት መጨረሻ ጀምሮ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
ከአገር ውስጥ ፋብሪካዎች ቡሬ የሚገኘው ፊቤላ የምግብ ዘይት ፋብሪካ 16 ነጥብ አምስት ሚሊዮን ሊትር ዘይት ያመርታል፡፡ 11 ሚሊዮኑ ከበዓል በፊት ተመርቶ ይደርሳል ብለዋል፡፡ አማሬሳ የምግብ ዘይት ፋብሪካም በቅርቡ ወደ ተግባር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የኮምኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር ወይዘሮ አበባ ታመነ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የተቋቋመው ግብረ ኃይል ከፌዴራል እስከ ወረዳ ድረስ ባለው መዋቅር ችግሮችን ይከታተላል። በየደረጃው ያሉ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ አካላት እንዲጠየቁ ያደርጋል፡፡
የህብረት ሥራ ማህበራት የሚያስገቧቸውን ምርቶች በፍትሐዊ መንገድ ለህብረተሰቡ እንዲያደርሱ ክትትል ይደረጋል፣ ከህብረተሰቡና ከኬላ አካባቢዎች በሚደርሱ ጥቆማዎች በቂ ክትትልና ቁጥጥር ያደርጋል ብለዋል፡፡
ህብረተሰቡ ግብረኃይሉ ውጡታማ እንዲሆን ህገ ወጥ ድርጊቶችን በመጠቆም የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዋለልኝ አየለ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 21 ቀን 2013 ዓ.ም