የተተገበሩ ማሻሻያዎች ሀገሪቱን በዓለም ገበያ ተጽዕኖ ፈጣሪ እያደረጋት መሆኑን ሚኒስቴሩ አስታወቀ

አዲስ አበባ፦ መንግሥት ያከናወናቸው የፖሊሲና የአሰራር ማሻሻያዎች ሀገሪቱን በዓለም ገበያ ተጽዕኖ ፈጣሪ እያደረጋት መሆኑን የንግድና ቀጣናዊ ሚኒስቴር አስታወቀ። 13ኛው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬና የቅባት እህሎች ጉባኤ ትናንት በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

የንግድና ቀጣናዊ ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ መንግሥት የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ፣ ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተመን እና ሌሎች የፖሊሲና የአሰራር ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ማድረጉ ሀገሪቱን በዓለም ገበያ ተጽዕኖ ፈጣሪ እያደረጋት ነው።

በዚህም የጥራጥሬና የቅባት እህሎች የውጭ ንግድ በመጠን እና በውጭ ምንዛሪ ግኝት አድጓል ያሉት ካሳሁን (ዶ/ር)፤ እነዚህ ምርቶች ለሀገሪቱ ኢኮኖሚያዊ እድገት ለመጠቀም መንግሥት ለዘርፉ ተዋናዮች ማበረታቻ እያደረገ ነው ብለዋል።

በዚህ ረገድ የሀገር በቀል ኢኮኖሚና የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያዎች መንግሥት በዘርፉ የተሰማሩ ኢንቨስተሮችን ለማበረታታት ትልቅ አቅም መፍጠሩን አስረድተው፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣናን ለመተግበር እየሰራች እንደሆነ ተናግረዋል።

ሚኒስቴሩም የውጭ ንግድ ብዝሃነትና ተወዳዳሪነት እንዲጎለብት እየሰራ ነው። ከዚህ ውስጥ አንዱ የሀገሪቱን ሀብትና አቅም በዓለም አቀፉ መድረኮች ማስተዋወቅ ተጠቃሽ ነው ያሉት ካሳሁን (ዶ/ር)፤ ኢትዮጵያ በጥራጥሬ እና በቅባት እህል ወጪ ንግድ በየዓመቱ በአማካይ 800 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ታገኛለች ነው ያሉት።

መንግሥት ባለፉት ጊዜያት ያከናወናቸው የፖሊሲና የአሰራር ማሻሻያዎች የውጭ ባለሀብቶችን ተሳትፎ በማሳደግ የሀገሪቱን ዓለም አቀፋዊ የንግድ እንቅስቃሴ ያጎለብታል ያሉት ካሳሁን (ዶ/ር)፤ ይህም ለዘርፉ ተዋንያኖች አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የኢትዮጵያን ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ ኤዳኦ አብዲ በበኩላቸው፤ በጉባኤው የውጭ ሀገራት ተሳታፊዎች እና ላኪዎች የተገኙ መሆኑን ገልጸው፤ ከዓለም አቀፍ ገዢዎች ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠርና ምርቶችን በማስተዋወቅ በኩል የሚኖረው ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል።

ባለድርሻ አካላት የገበያ መዋዠቅና የሎጀስቲክስ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ዘመናዊ አሰራሮችን ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው ገልጸው፤ ኢትዮጵያ በዓለም ገበያ ላይ ያላትን ተሳትፎ ለማሳደግ ቴክኖሎጂዎችን ከግብርና ንግድ ጋር ማጣመር እንደሚገባም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በጥራጥሬና ቅባት እህሎች ዘርፍ ትልቅ አቅም አላት። ይህንን አቅም አሟጦ በመጠቀም ሀገራዊ የውጭ ንግድ ገቢን ማሳደግ እንደሚቻል ተናግረው፤ መንግሥት ለዘርፉ የሰጠው ትኩረት በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው እና በሌሎች የአሰራር ሥርዓቶች እንደሚታይ ተናግረዋል።

ጉባኤው፤ የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ ቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማህበር ከንግድና ቀጣናዊ ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እንዳዘጋጀም ገልጸዋል።

ሳሙኤል ወንደሰን

አዲስ ዘመን ህዳር 11/2017 ዓ.ም

 

 

 

Recommended For You