ሳምንታዊ የዋጋ ዝርዝር መውጣቱ ከህብረተሰቡ ጥሩ ምላሽ እያስገኘ ነው

– በመዲናዋ 193 የቅዳሜና የእሁድ ገበያዎች አገልግሎት እየሰጡ ነው

አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በየሳምንቱ እያሰራጨ ያለው የእህልና የፋብሪካ ምርቶች የዋጋ ዝርዝር ከህብረተሰቡ ጥሩ ምላሽ እያስገኘ መሆኑን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ገለጸ፡፡

በቢሮው የገበያ መረጃ ጥናትና ፕሮሞሽን ዳይሬክተር አቶ ሙሰማ ጀማል ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጹት፤ በንግድ ቢሮው በመንግሥት በተገነቡት ሶስቱ የገበያ ማዕከላት እንዲሁም በእሁድ ገበያዎች ላይ የሚለጠፈው የሰብልና የፋብሪካ ምርቶች የዋጋ ዝርዝር ከህብረተሰቡ ዋጋውን በዚህ ደረጃ እንድናውቅ መደረጉ መልካም ነው የሚል ምላሽ እያስገኘ ነው፡፡

በዋጋ ዝርዝሩ መሰረት ምርቶቹ መሸጣቸውን በተመለከተም ክትትልና ቁጥጥሩ እንደሚደረግ የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ ከክፍለ ከተማ እስከ ወረዳ ድረስ የተመደቡ የክትትል ቡድኖች ቅዳሜና እሁድ የሰአት ፈረቃ ወጥቶላቸው ክትትልና ድጋፍ ያደርጋሉ፡፡ በክትትልና ቁጥጥር ዙሪያም ከ600 በላይ ባለሙያዎች እንደተመደቡም ገልጸዋል፡፡

የዋጋ ዝርዝር ማውጣቱ የእሁድ ገበያዎች ከተጀመሩበት ጊዜ አንስቶ እንደነበረ ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ ህብረተሰቡ ወደ ገበያ ከመምጣቱ በፊት እንዲዘጋጅበት በማሰብ በተጠቀሱት አማራጮች የምርቶችን ዋጋ ይፋ ማድረግ ከተጀመረ ግን ሁለተኛ ሳምንት ማስቆጠሩን ገልጸዋል፡፡

ህብረተሰቡ ዋጋውን ቀድሞ አውቆ ከመምጣቱ አኳያ ጭማሪ የሚደረግበት ከሆነ፣ ቅሬታ ወይም አስተያየት ካለው የሚስተናገድበት ስልክ መቀመጡንም ጠቁመዋል፡፡

በከተማ ደረጃ የአንድ ዳይሬክተርና የአንድ ቡድን መሪ፣ በክፍለ ከተማ ደረጃ ደግሞ የአስራ አንዱንም ክፍለ ከተሞች ቡድን መሪዎች ስልክ በንግድ ቢሮው በማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ እንደተቀመጠም ገልጸዋል፡፡

በቀጣይም የዋጋ ዝርዝሩን በማህበራዊ ሚዲያ ብቻ ሳይሆን በትልልቅ መገናኛ ብዙኃንም እንዲሰራጭ መታቀዱን የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ በተለይም የገበያ ማዕከላቱ ዋጋ ለሳምንት የሚቆይ ስለሆነ ህብረተሰቡ እንዲያውቀው ማድረጉ አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በጤፍ ዋጋ ደረጃ እንኳ ብናየው በእነዚህ ገበያዎች ላይ እና ከእነዚህ ገበያዎች ውጪ ብናየው በኩንታል ከሁለት ሺህ 500 እስከ ሁለት ሺህ 800 ድረስ ልዩነት እንዳለው አንስተዋል፡፡

የሰብልና የፋብሪካ ምርት ዋጋ ዝርዝር መረጃን ለህብረተሰቡ ማድረስ የኑሮ ውድነቱን ጫና በተወሰነ ደረጃም ቢሆን ከመቅረፉ አኳያ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አመላክተዋል፡፡

የቅዳሜና እሁድ ገበያ ሲጀመር በአንድ ወረዳ አንድ ገበያ እንዲኖር ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን ያስታወሱት ዳይሬክተሩ፤ አሁን ላይ በ121 ወረዳዎች የገበያዎቹ ቁጥር 193 መድረሱን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ሂደት ውስጥ የአትክልት ዋጋ ላይ ያለው የዕለት ተዕለት ተለዋዋጭ ዋጋ አንድ ተግዳሮት መሆኑን ገልፀው፤ ዋጋ ዝርዝሩ ወቅታዊ ሁኔታን ታሳቢ ባደረገ መልኩ የሚስተካከልበትን መንገድ እየፈለጉ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም የቅዳሜና የእሁድ ገበያዎች የከተማዋን የእድገት ደረጃ የሚመጥኑና ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ለማድረግ ጥናት እየተጠና መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

ነፃነት አለሙ

አዲስ ዘመን ህዳር 11/2017 ዓ.ም

 

 

Recommended For You