በዓለም አቀፍ ደረጃ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ በቀን ከ3 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ምንዛሪ ማስገኛ ስለመሆኑ ይገለጻል፡፡ በየዓመቱ ዕድገት የሚታይበት ይህ ዘርፍ፣ አሁንም ከፍተኛ ገንዘብ የሚንቀሳቀስበት ነው፡፡ ከዕድገቱ ጋር ተያይዞ የቱሪዝም ዘርፉ ከተለያዩ ክንውኖች ጋር ተቀናጅቶ እንዲዘጋጅ በአዲስ ጽንሰ ሐሳብ እየተሠራበት ይገኛል፡፡ ይህም ‹‹ማይስ›› ወይም በእንግሊዝኛ ምኅፃረ ቃል (MICE) በሚል ይታወቃል። ዓለም አቀፋዊ ከሆኑ ስብሰባዎች ጋር ተጣምሮ የሚካሄደውን አዲሱን የቱሪዝም ጽንሰ ሐሳብ በተለይ የበለጸጉት ሀገራት ተቀብለው መተግበር ከጀመሩ ዓመታት አስቆጥረዋል። ሀገራቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢያቸውን እያሳደጉበት ስለመሆኑም መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡
ለዚህም እንደማስረጃ በ2023 የዓለም ባንክ ያወጣውን ጥናት እናንሳ። በ2023 ከ‹‹ማይስ ቱሪዝም›› በአውሮፓ የቱሪዝም ገበያ በግምት ከ401 ነጥብ 95 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ተገኝቷል። በ2024 እስከ 459 ነጥብ 43 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ይገኛል ተብሎ ይገመታል። በእስያ 183 ነጥብ 47 ቢሊዮን ዶላር ከ‹‹ማይስ›› እንግዶች ገቢ የተገኘ ሲሆን፤ በሰሜን አሜሪካ ደግሞ ያለው የ‹‹ማይስ ቱሪዝም›› ገበያ 130 ነጥብ 926 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ማስገኘቱን የዓለም ባንክ ጥናት ያሳያል ፡፡
ምዕራባውያኑ ያላቸውን መልካም አጋጣሚ ይበልጥ ሳቢና ምቹ በማድረግ ገንዘብ ሲያገኙ በ‹‹ማይስ ቱሪዝም›› ኢኮኖሚዋን ማቅናት የሚያስችሏት ብዙ መልካም አጋጣሚዎች የነበሯት ኢትዮጵያ በሚጠበቀው ደረጃ ከዘርፉ ልትጠቀም እንደሚገባ ይነሳል። ኢትዮጵያ ለአውሮፓ፣ ለመካከለኛው ምሥራቅና ለሌሎችም የአፍሪካ ሀገሮች አማካይ ጂኦግራፊያዊ አካባቢ ላይ መገኘቷ፣ የተመቸ የአየር ፀባይዋ፣ ፀጥታና ሰላሟ፣ የሕዝቧ እንግዳ ተቀባይነት ስብሳባዎችን ለማዘጋጀት ምቹ እንድትሆን ያደርጋታል ተብሎ ይታመናል፡፡ በተጨማሪም አዲስ አበባ ከኒው ዮርክ እና ጄኔቫ በመቀጠል ሶስተኛዋ የዲፕሎማቲክ ከተማ እንደመሆኗ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን፣ የአፍሪካ ሕብረት፣ ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ መድረኮችን የምታስተናግድ መሆኗም ተመራጭ ያደርጋታል፡፡
ዓለም አቀፍና አኅጉር አቀፍ ኮንፈረንሶች ሲካሄዱ፣ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች በርካታ ጥቅሞችን ይዘው ይመጣሉ፡፡ ለአብነትም፤ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች ለአውሮፕላንና ለሆቴል የሚያወጡትን ወጪ ጨምሮ ለምግብ፣ ለመዝናኛ፣ በሀገር ውስጥ ብቻ የሚገኙ ጌጣጌጦችና አልባሳትን ለመሸመት የሚከፍሉት ገንዘብ ገበያ ላይ አዎንታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል። ኢትዮጵያ ከባህል፣ ከተፈጥሮና ከታሪክ ቱሪዝም ባሻገር ለኮንፈረንስ አመቺ እና ተመራጭ የሚያደርጋት ቢሆንም፤ ለ‹‹ማይስ ቱሪዝም›› ተገቢውን ትኩረት ሰጥታ አልሰራችም። ይህም በቱሪዝም ተወዳዳሪ ሊያደርግ የሚችል ሥራ ባለመሠራቱ ሀገሪቱ ከማይስ ቱሪዝም ማግኘት የሚገባትን ጥቅም አሳጥቷታል። ከዚህ በተጨማሪም እድሏን ለሌሎች ሀገራት ጭምር አሳልፋ ሰጥታለች ።
በአፍሪካ በየዓመቱ ከ450 በላይ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች እንደሚካሄዱ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በአህጉሪቱ ከሚደረጉ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች የኢትዮጵያ የአስተናጋጅነት ድርሻ አነስተኛ ነው። በአፍሪካ የሚደረጉ አብዛኛዎቹ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች በደቡብ አፍሪካና በሩዋንዳ ከተሞች ይደረጋሉ። ሀገሪቱን በቱሪዝም ተወዳዳሪ ሊያደርግ የሚችል ስራ ባለመሰራቱ እድሏን ለደቡብ አፍሪካ፣ ለሩዋንዳ እና ለኬኒያ አሳልፋ ሰጥታለች ማለት ይቻላል። ለአብነት ኬኒያ በኮንፈረንስ ቱሪዝም በምታገኘው ገቢ ተጠቃሚ ለመሆን የቻለች ሲሆን፣ በዘርፉ በምታደርገው እንቅስቃሴ ሳቢያም በርካታ ኮንፈረንሶች በሀገሪቱ እንዲካሄዱ የተመቻቸች በመሆኗ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ለምታገኘው ከፍተኛ ገቢ አስተዋጽኦ ማድረጉ ይነገራል፡፡
ኬኒያ ከቱሪዝም ዘርፍ በየዓመቱ ከሰባት ነጥብ ሰባት ቢሊዮን ዶላር በላይ በማግኘት ትጠቀሳለች፡፡ ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች፣ የመሰብሰቢያ አዳራሾች፣ የገበያ ማዕከላት፣ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎች ጥንካሬ፣ የጉዞ ወኪሎች ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ከሚያስፈልጉት መካከል ናቸው። ኬኒያ በዚህ ረገድ የተሟላች ነች። እንደ ኬኒያ ሁሉ ደቡብ አፍሪካ፣ ሩዋንዳ በዘርፉ ብቁ የሚያደርጓቸውን ሥራዎች በመሥራታቸው ውጤታማ ለመሆን ችለዋል።
በአንፃሩ ኢትዮጵያ በተለያዩ መንገዶች ለኮንፈረንስ አመቺ ብትሆንም ያላት እምቅ አቅም እና ዕድሏን ለሌሎች አሳልፋ ሰጥታለች። ለዚህም በርካታ ምክንያቶች የሚቀርቡ ሲሆን በመጀመሪያ ደረጃ መንግሥት ለዘርፉ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ አለመሥራቱ ይጠቀሳል። በተለይም በቱሪስት መሰረተ ልማት መሟላትና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ መሠራት ያለባቸው ሥራዎች አልተሠሩም፡፡ አንድ የስብሰባ አዳራሽ የተለያዩ የመሰብሰቢያ ክፍሎች ያስፈልጉታል፤ ዓለም አቀፍ ኮንፈረንሶች በሚዘጋጁበት ጊዜም በርካታ ቋንቋ ተናጋሪዎች ይኖራሉ፡፡
በመሆኑም በቋንቋ መግባባት የማይችሉ ተሳታፊዎች አስተርጓሚ ያሻቸዋል፡፡ ይህን የሚያሟሉ ደረጃቸውን የጠበቁ የኮንፈረንስ ማዕከላት ቁጥር ማነስ፣ የግል ባለሃብቱ በዘርፉ ያለው ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆን እንዲሁም በዘርፉ የሰለጠነ የሰው ኃይል እጥረት ለኮንፍረንስ ቱሪዝም መዳከም እንደ ችግር ይጠቀሳሉ። ስለዚህ ኢትዮጵያም ካሏት የቱሪዝም መስህቦች በተጨማሪ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ዕድል ቢኖራትም የዘርፉን ማነቆዎች በተሳለጠ አሠራር መፍታት ባለመቻሏ ኋላ መቅረቷ ፀሀፊውን ጨምሮ የብዙዎች ቁጭት ነው፡፡
በሀገሪቱ ለዘርፉ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት ቢቻል ለውጥ ማምጣት እንደሚቻልም ይታመናል። ስለ ‹‹ማይስ ቱሪዝም›› ያለውን ግንዛቤ ማሳደግ ከተቻለ እንዲሁም ዘርፉ ተገቢውን ትኩረት ካገኘ አበረታች ውጤት ማምጣት እንደሚቻል የብዙዎች እምነት ነው። ከዚህ አንጻር ባለፉት ስድስት ዓመታት መንግሥት ትኩረት ከሰጣቸው አምስቱ የኢኮኖሚ መሻሻያ ዘርፎች መካከል ቱሪዝም አንዱ እንደሆነ ይታወቃል። መንግሥት የሚያከናውናቸው ልማቶች ‹‹ማይስ ቱሪዝም››ን ታሳቢ ያደረጉ እንደሆኑ መገመት ይቻላል። ይህም ዘርፉ ትኩረት ከሰጠው ኮንፈረንስ ቱሪዝምን ከገቢ ማስገኛነት በተጨማሪ፤ የሀገርን ገጽታ በመቀየር፣ በማስተዋወቅ ረገድ መጠቀም የሚያስችል መሆኑን ምልክቶች መታየት ጀምረዋል። በተለይም በአዲስ አበባ እየተከናወኑ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች ከተማዋ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ምቹ እንድትሆን ትልቅ ዕድል እየፈጠሩ ይገኛሉ።
በመዲናዋ ከ2011 ዓ.ም ወዲህ የአዲስ አበባ ከተማን የቱሪዝም ልማት ሥራዎች ለማስፋት በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል። ከእነዚህም መካከል አንድነት ፓርክ፣ እንጦጦ ፓርክ፣ ወዳጅነት አደባባይ፣ የዓድዋ ድል መታሰቢያና ሌሎች ከተማዋን የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ የተሠሩ ሥራዎች ይጠሳሉ። እነዚህ የልማት ሥራዎች ከተማዋ ዓለም አቀፍና አህጉር አቀፍ ስብሰባዎችን ለማከናወን ቀዳሚ ተመራጭ እንድትሆን አድርገዋታል፡፡ በቅርብ ጊዜያት የተከናወኑ የአፍሪካ የመከላከያ ሚኒስትሮች ስብሰባ፣ ዓለም አቀፍ የፈጠራ ውድድሮች፣ የካፍ ጉባዔን ጨምሮ የከተሞች ፎርም ለአብነት ይጠቀሳሉ። በዚህም የተከናወኑና በመከናወን ላይ የሚገኙ የልማት ተግባራት መዲናዋ ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ምቹ ከተማ እንድትሆን አስችለዋታል ።
በተለይም በዓድዋ ድል መታሰቢያ ውስጥ የተገነቡ ትልልቅ የመሰብሰቢያ አዳራሾችም ከተማዋ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ኮንፈረንስ እንድትሆን ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳበረከተ ይታመናል። በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄደ ያለው የኮሪደር ልማትም ከተማዋን በማደስ የተለየ ገጽታ እንድትላበስ ያስቻለ ሌላው ግዙፍ ፕሮጀክት ነው ። መንግሥት የቱሪዝም ዘርፉን መሰረት ባደረገ መልኩ በአጭር ጊዜ በተሠሩ ሥራዎች በዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃት በመፍጠር ተስፋ ሰጪ ውጤቶች ታይተዋል ።
አሁንም ሀገሪቱ ከዘርፉ የተሻለ ጠቀሜታ ለማግኘት በርካታ ሥራዎች ማከናወን ይኖርባታል ። በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉት ደረጃቸውን የጠበቁ የኮንፈረንስ ማዕከላትን ቁጥር ማሳደግ፣ የግል ባለሃብቱ በዘርፉ ያለውን ተሳትፎ ማሳደግን እንዲሁም በዘርፉ ያለውን የሰለጠነ የሠው ኃይል እጥረት መቅረፍን ይጠይቃል፡፡ ሌላው በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳድሮ ለማሸነፍም ዘርፉን የሚመራና የሚያስተባብር ተቋም እንደሚያስፈልግ ይታመናል። በ2013 ዓ.ም የ‹‹ማይስ ቱሪዝም››ን የሚመራ የኢትዮጵያ ኮንቬንሽን ቢሮ መመስረቱ ሌላው በጎ ጅማሮ ተደርጎ ይቆጠራል። የቢሮው መቋቋም በሀገሪቱ የስብሰባ ማዕከላት እንዲገነቡ፣ ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋና በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ ሁነት አዘጋጆች እንዲበራከቱ ጉልህ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በዚህ ረገድ ቢሮው የተቋቋመበትን ዓላማ መሰረት በማድረግ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባዋል።
በተጨማሪም በሀገራችን የተለያዩ አካባቢዎች ያለውን የጸጥታ ሁኔታ አስተማማኝ ማድረግ፤ ከተለያየ የዓለም ክፍል ወደ ሀገሪቱ ለመምጣት ያቀዱ ወይም አቅደው የመጡ ጎብኚዎች አስፈላጊ መረጃዎችን ማግኘት የሚችሉበትን ዘመናዊ ስርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ በዚህም የመንግሥት ተጠሪ ተቋማት ለኮንፈረንስ ቱሪዝም የሚሆኑ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ማለትም ሆቴሎች፣ መዝናኛ ሥፍራዎች፣ የትራንስፖርት አቅራቢዎች፣ አስጎብኚዎች ደረጃውን የጠበቀና ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ የመከታተል፣ የመቆጣጠር እና የመደገፍ ተግባራት መከናወን ይኖርባቸዋል።
በጥቅሉ ኢትዮጵያ ዓለም አቀፋዊ ከሆኑ ስብሰባዎች ጋር ተጣምሮ ከሚካሄደው የቱሪዝም ዘርፍ ተጠቃሚ ለመሆን የጀመረችው ጥረት በጎ ውጤት ማሳየት ጀምሯል። በመንግሥት በኩል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎች ለታየው ፍንጭ ከፍተኛ ሚና አላቸው። ሆኖም የ‹‹ማይስ ቱሪዝም›› እንደሌላው የቱሪዝም ዓይነት አይደለም፤ እንደ ገቢ ማስገኛ ዘርፍ ብቻ የሚታይ አይደለም። የሀገርን ገጽታ በመቀየር፣ ሀገርን በማስተዋወቅ፣ ለሚዲያም ቅርብ ከመሆን አንፃር ትልቅ ጥቅም አለው፡፡ ስለሆነም ለዘርፍ ይበልጥ መጎልበት መንግሥት ከሚያከናውናቸው የልማት ሥራዎች ባሻገር የግሉ ዘርፍ ትብብር ሊጠናከር ይገባል። ስለዚህ በዘርፉ የሚገኘውን ጥቅም ለማግኘት ሁሉም ጠንክሮ በመሥራት የበኩሉን መወጣት ይኖርበታል፡፡
ዳንኤል ዘነበ
አዲስ ዘመን ህዳር 11/2017 ዓ.ም