ለውጪ ንግድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካላቸው የምርት አይነቶች መካከል የግብርና ምርት የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል። በአገሪቱ የሚመረቱ የግብርና ምርቶችን በዓለም አቀፍ ገበያ ለማስተዋወቅ በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ። ለዚህም ትልቅ ድርሻ ያለው የኢትዮጵያ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና የቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር ነው።
ማኅበሩ ከተቋቋመ ጊዜ ጀምሮ ከተለያዩ አገራት የሚያገኘውን ተሞክሮ ተግባራዊ በማድረግ የአገሪቷ የግብርና ምርት የሆኑትን የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና የቅመማ ቅመም ምርቶችን በዓለም ገበያ እያስተዋወቀ ይገኛል። ማኅበሩ በባለቤትነት ስሜት እነዚህን ምርቶች እያስተዋወቀ እንደሚገኝና ምርቶቹ ዓለም አቀፍ ዕውቅና እንዲያገኙ ሲያደርግ መቆየቱን የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና የቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ኤዳኦ አብዲ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንቱ ትናንት የተጀመረውን የጥራጥሬ ቅባት እህሎች እና ቅመማ ቅመሞች 13ኛ ጉባዔ አስመልክቶ በተሰጠው መግለጫ ላይ ጉባዔው ዓለም ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ኢትዮጵያን እየጎበኘ አገሪቷ በግብርናው ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም ማየት የሚችልበት መሆኑን አስታውቀዋል። እሳቸው እንደተናገሩት፤ ጉባኤው በተለይም የኢትዮጵያን የጥራጥሬና የቅባት እህሎች እንዲሁም የቅመማ ቅመም ምርቶችን ለማስተዋወቅና የገበያ ትስስር መፍጠር የሚያስችል ነው። ጉባኤው ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን፤ በአድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ከዛሬ ሕዳር 10 ቀን 2017 ዓ.ም ጀምሮ ለሁለት ቀናት የሚካሄድ ይሆናል።
ጉባኤው ‹‹ምርቶቻችን የወደፊት የኢኮኖሚያችን ምሰሶ፤ የብልጽግናችን ምንጮች ናቸው›› በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄድ ሲሆን፣ በጉባኤውም 430 የሚደርሱ ላኪዎች፣ አምራቾች፣ የሕብረት ሥራ ማኅበራትና በአግሪ ቢዝነስ ላይ የተሰማሩ የፋይናንስ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትና የሚመለከታቸው አካላት ይሳተፋሉ። ከዚህም ባሻገር ከተለያዩ አገራት ጥሪ የተደረገላቸውና በኢንዱስትሪው ሰፊ ልምድ ያላቸው እንግዶችና ትላልቅ ገዢዎች ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካ፣ ከቱርክ፣ ከእስራኤል፣ ከቻይናና ከሕንድ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣሉ። ይህ ሁነትም ለአገሪቱ ኢኮኖሚና ለቱሪዝም ዘርፉ የተለየ ዕድል የሚሰጥ ወሳኝ እንደሆነ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል።
መንግሥት በቅርቡ ወደ ሙሉ ትግበራ ያስገባው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለዘርፉ ከፍተኛ አበርክቶ እንዳለው ጠቅሰው፣ የዘንድሮውን ጉባኤ ለየት የሚያደርገውም ይህ ማሻሻያ በተተገበረበት ወቅት መካሄዱ መሆኑን አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና የቅመማ ቅመም ምርቶች ኤክስፖርት ከማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው አስቀድሞ በኪሳራ ይሰራ እንደነበረም ጠቅሰው፣ በዚህ የተነሳም ተወዳዳሪና አዋጭ እንዳልነበር ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ የተደረገው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በተለይም ለኤክስፖርት ዘርፉ የተለየ ድጋፍና ጉልበት ሰጥቶታል ሲሉ ገልጸዋል፤ ኤክስፖርቱ በራሱ ትርፋማ ሆኖ ለአርሶ አደሩ፣ ለአምራቹና ለሀገር የሚያስገኘው የውጭ ምንዛሪ ድርሻ ከፍ እንዲል ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው አብራርተዋል።
ፕሬዚዳንቱ አቶ ኤዳኦ እንዳስታወቁት፤ በምስራቅ አፍሪካ ካሉ አገራት ሰፊና ለም መሬት ያላት ኢትዮጵያ ይህን ትልቅ ዕድል መጠቀም አለባት። የግሉ ዘርፉ ተወዳዳሪ መሆን እንዲችል በቴክኖሎጂ አጠቃቀም፣ በእሴት ጭመራ፣ በሰው ኃይል ልማትና በሌሎችም አገሪቷ አሁን እየሄደችበት ካለችው የዲጂታል ኢኮኖሚ ጋር ባለሃብቱ አብሮ መጓዝ ይጠበቅበታል። ለዚህም በየዓመቱ የሚዘጋጀው ይህ ጉባኤ ትልቅ ድርሻ ይኖረዋል። ላኪዎች በጉባኤው ለመሳተፍ ከተለያዩ አገራት በተለይ ካደጉ አገራት ከሚመጡ የዘርፉ ባለድርሻዎች ሰፊ የልምድ ልውውጥ በማድረግና የገበያ ትስስር በመፍጠር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ የሚያገኙበት ነው።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሀብረቢ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ ከጥራጥሬና ቅባት እህሎች ካላት የምርት አቅም አንጻር ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሬ እያገኘች እንዳልሆነ ጠቅሰው፣ በ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያው አራት ወራት የተገኘው የገቢ አፈጻጸም ካለፉት ጊዜያት መሻሻል ማሳየቱ ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳሉት፤ በ2016 በጀት ዓመት ስድስት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል የጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች ወደ ውጭ ተልከው 675 ሚሊዮን ዶላር ማግኘት ተችሏል። በተያዘው በጀት ዓመትም ካለፈው ዓመት የተሻለ አፈጻጸም እንደሚኖር ይታመናል። ለዚህም በሩብ ዓመት የተመዘገበው አፈጻጸም እንዲሁም የአራት ወራት አፈጻጸም አመላካች ነው። በአራት ወራት ወደ ውጭ ለመላክ ከታቀደው የምርት መጠንና የውጭ ምንዛሬ ገቢ አንጻር በአማካኝ የእቅዱን ከ95 በመቶ በላይ ማሳካት ተችሏል።
በወጪ ንግዱ እየተመዘገበ ያለው ውጤት አበረታች እንደሆነ ጠቅሰው፣ ይህ ውጤትም በተለያዩ ጥረቶች የተገኘ ነው ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታዋ አስታውቀዋል:: በተለይም ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፣ ጥራት ላይ በመስራት ጥራቱ የተጠበቀ ምርት ለዓለም አቀፍ ገበያ በማቅረብ፣ የግብይት ስርዓቱን በማዘመን፣ ለላኪዎች የሚደረገውን ድጋፍ በማጠናከርና ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት መስራቱንም አመላክተዋል።
ሚኒስትር ዴኤታዋ እንዳሉት፤ የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከተሰጡት ተልዕኮዎች መካከል የውጪ ንግድን ማሳደግ አንዱ ነው። ከዚህ ጋር በተያያዘም ውጪ ምርቶችን በአገር አቀፍ ደረጃና በዓለም አቀፍ ደረጃ የማስተዋወቅ ሥራ መስራት ወሳኝ ነው። በመሆኑም የተለያዩ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎችን በመቅረጽ በተለይም ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ገበያ በቂና ጥራቱን የጠበቀ የግብርና ምርት ማቅረብ የሚያስችላት ትልቅ አቅም እንዳላት በመገንዘብ ይህንኑ የማስተዋወቅና ገበያ የማፈላለግ ሥራ በሰፊው እየተሰራ ይገኛል።
ለዚህም የንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ከጥራጥሬ፣ የቅባት እህልና ቅመማ ቅመም አዘጋጅቶ ላኪዎች ማኅበር ጋር በመሆን በየዓመቱ የሚያዘጋጀው ዓለም አቀፍ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህልና ቅመማቅመም ጉባኤ እንደሚጠቀስ ገልጸዋል። ዓለም አቀፍ ጉባኤው ላለፉት 12 ዓመታት ተካሂዷል፤ ዘንድሮም ለ13ኛ ጊዜ ይካሄዳል።
ይህ ዓለም አቀፍ ጉባኤ በወጪ ንግድ በኩል ከሚከናወኑ ተግባራት መካከል ዋነኛው ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ የተለያዩ አገራት ተሳትፎን እንደሚጠይቅ ገልጸዋል፤ በዚህ ጉባኤ ላይ ብቻ ከ22 እስከ 25 የሚደርሱ አገራት እንደሚሳተፉ ተናግረዋል።
ከሀገር ውስጥም እንዲሁ የተለያዩ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ላኪዎች፣ የኢትዮጵያን የጥራጥሬ፣ የቅባትና የቅመማ ቅመም ምርቶችን የሚገዙ ነጋዴዎችና በዘርፉ የተሰማሩ ምሁራን ይሳተፋሉ። በተለይም በአገሪቱ የሚገኙ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ዘርፍ የተሰማሩና በዘርፉ ጉልህ ሚና ያላቸው አካላት ጭምር የሚሳተፉ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ በተጨማሪም ባንኮች፣ ኢንሹራንሶችና የተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት የሚሳተፉበት ትልቅ ጉባኤ እንደሆነ አመላክተዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና የቅመማ ቅመም ምርቶች ገበያ ፍላጎት በከፍተኛ ደረጃ እያደገ ነው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ በኢትዮጵያ በኩልም ይህንን ተፈላጊ ምርት በበቂ መጠንና ጥራት ማምረት የሚያስችል ምቹ ሁኔታ ስለመኖሩም ገልጸዋል። በአገሪቱ ያለው ነባራዊ ሁኔታም ለዚህ ምቹ መሆኑን ይገልጻሉ። በተለይም እነዚህን ምርቶችና ሌሎች የተለያዩ ምርቶችንም እንዲሁ ለማምረት የሚያስችል ትልቅ አቅም እንዳለ አስታውቀው፣ ለዓለም አቀፉ የገበያ ፍላጎት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ ምርቶቹን በጥራት ማቅረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ጉባኤው በአገሪቱ ያለውን አቅም በጉባኤው የተሳተፉ ገዢ አገራት ይበልጥ እንዲረዱ ዕድል ይፈጥርላቸዋል ሲሉ ገልጸው፣ ገዢ አገራትና ላኪዎች ተገናኝተው የገበያ ትስስር እንደሚፈጥሩ ጠቁመዋል። በአሁኑ ወቅትም ከ25 የተለያዩ አገራት የሚመጡ 110 የሚደርሱ ገዢዎች አስፈላጊውን መስፈርት አሟልተው መመዝገባቸውን ጠቅሰው፣ በአገር ውስጥም እንዲሁ 430 የሚደርሱ ላኪዎች በጉባኤው ለመሳተፍ መመዝገባቸውን አስታውቀዋል። ገዢዎችና ላኪዎች በቀጥታ ተገናኝተው የግብይት ውል የሚፈጽሙበት መሆኑንም አመላክተዋል።
እሳቸው እንዳብራሩት፤ ጉባኤው የኢትዮጵያ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና የቅመማ ቅመም ምርቶች አጠቃላይ ግብይት የሚፈጸምበት ሲሆን፣ 30 በመቶ ያህሉ የውጪ ንግድ የውል ስምምነቶች የሚከናወኑበት ዓመታዊ ጉባኤ ነው። በጉባኤው የሚሳተፉ ላኪዎችና ገዢዎች የተለያዩ ስምምነቶች ላይ የሚደርሱበት፣ ስምምነቶች በተግባር እየተቀየሩ በቀጣይ በተለይም በጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና ቅመማ ቅመም ምርቶች የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ግኝት ከፍ ማድረግ የሚያስችል ትልቅ ጉባኤ ነው።
ከዚሁ ጎን ለጎን የኢትዮጵያ የጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና የቅመማ ቅመም ምርቶች አውደ ርዕይ የሚቀርብ ሲሆን፤ በአውደ ርዕዩም ኢትዮጵያ ምን አይነት ጥራጥሬ፣ የቅባት እህሎችና የተለያዩ የቅመማ ቅመም ምርቶችን እያቀረበች እንደሆነና ማቅረብ እንደምትችልም ጭምር ማሳየት ይቻላል። በጥራትም እንዲሁ በተለይም የሁመራ ሰሊጥ በምን ያህል ጥራት እንደሚቀርብ በማሳየት ነባር ከሆነው ገበያ በተጨማሪ አዳዲስ የገበያ መዳረሻዎችን ጭምር ማግኘት ያስችላል ብለዋል።
ከጉባኤው በተጨማሪ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቅርቡ ያስመረቀው ቋሚ የውጪ ንግድ ኤግዚቢሽን የሚጎበኝ ይሆናል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፣ በጉብኝቱም እንግዶች አገሪቱ በተለያየ ዘርፍ ያላትን እምቅ አቅም መመልከት ያስችላቸዋል ብለዋል። ይህም አዳዲስ የገበያ አማራጮችን በመሳብ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንደሚኖረው ጠቅሰው፣ ከዚህ በተጨማሪም የተለያዩ የቱሪስት መዳረሻና ጠቃሚ የሆኑ ቦታዎችን በመጎብኘት ኢትዮጵያ ያላትን ትልቅ አቅም እንዲረዱ ያግዛል ሲሉ ተናግረዋል።
በጉባኤው የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች የሚቀርቡ ሲሆን፤ በጥናታዊ ጽሁፉ በተለይም የአፍሪካ አገራት በዘርፉ ያሉበት ሁኔታ ይታያል። አለፍ ሲልም አፍሪካን ጨምሮ የተለያዩ አገራትን ፍላጎት በማየትና በመረዳት መረጃ በመለዋወጥ ላኪዎች ዕውቀት የሚያገኙበትና አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ የሚችሉበት ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪም በዘርፉ ጉልህ ድርሻ ያላቸውና በውጭ ምንዛሪ ግኝት የተሻለ አፈጻጸም ያስመዘገቡ ላኪዎች ዕውቅና የሚያገኙበትና ተሸላሚ የሚሆኑበት ሁኔታም አለ። የሽልማትና የዕውቅና ፕሮግራሙ ላኪዎቹ ሕጋዊ በሆነ መንገድ በመጓዝ አገሪቷ የውጭ ምንዛሪ ማግኘት እንድትችል እያደረጉ ያለውን ጥረት ለማበረታታት የሚያግዝ ይሆናል ሲሉ አብራርተዋል ።
የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው የወጪ ንግድ ገቢ እንዲያድግ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ሚኒስትር ዴኤታዋ ገልጸዋል። ኢትዮጵያ በጥራጥሬ እና ቅባት እህሎች ያላትን እምቅ አቅም በማስተዋወቅ አሁን ከሚገኘው ገቢ በላይ ለማግኘት በትብብር መስራት አስፈላጊና የግድ እንደሆነ ጠቅሰው፣ ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ፍሬሕይወት አወቀ
አዲስ ዘመን ህዳር 11/2017 ዓ.ም