ሩሲያ ለተመድ የቀረበውን የሱዳንን የተኩስ አቁም ሃሳብ ውድቅ ማድረጓ ውዝግብ አስነሳ

የሱዳን ተፋላሚ አካላት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ዩናይትድ ኪንግደም ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት ያቀረበችውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ሩስያ ድምጽን በድምጽ በመሻር መብቷ ውድቅ አድርጋዋለች። እርምጃውን ዩናይትድ ኪንግደም እና አሜሪካ በጽኑ አውግዘውታል።

የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴቪድ ላሚ ውሳኔውን “አሳፋሪ” ብለውታል። ሩሲያ ግን ሱዳንን ሳታሳትፍ በሱዳን ጉዳይ ጣልቃ ትገባለች ስትል ዩናይትድ ኪንግደምን ከሳለች።ለ19 ወራት የዘለቀው የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት ምክንያት ሆኗል ተብሏል። ከ11 ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎችም ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

የእርዳታ ሠራተኞች እንዳሉት ከሆነ፤ ግጭቱ በዓለም ላይ እጅግ የከፋውን ሰብአዊ ቀውስ የፈጠረ ሲሆን፤ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም ለረሃብ ተጋልጠዋል።የሱዳን ሰብዓዊ ተሟጋቾች የተባበሩት መንግሥታት ለግጭቱ ምላሽ ለመስጠት ቀርፋፋ ሆኗል በሚል ከፍተኛ ትችት ሰንዝረዋል።

ባለፈው ዓመት በሚያዝያ ወር የጀመረው ጦርነት በሀገሪቱ ሠራዊት እና በልዩ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) መካከል ለስልጣን በሚደረግ ሽኩቻ ነው።በዩናይትድ ኪንግደም እና በሴራሊዮን የቀረበው የሕዳር 9 ቀን 2017 ዓ.ም ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ሁለቱ ወገኖች ጦርነቱን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እና ብሔራዊ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ያለመ ውይይት እንዲጀምሩ ያሳሰበ ነው።

በተጨማሪም ሠራዊቱ እና አርኤስኤፍ ሲቪሎችን ለመጠበቅ ከዚህ ቀደም የተደረጉ ስምምነቶችን እንዲያከብሩ ጠይቋል። በተለይም አርኤስኤፍን በመጥቀስ በምዕራባዊው የዳርፉር ክልል እና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች ሲቪሎችን ለመጠበቅ የተደረሱ ስምምነቶችን እንዲያከበር ጠይቋል።

በተባበሩት መንግሥታት የሱዳን ተወካይ በበኩላቸው፤ በረቂቁ ውስጥ የሚፈልጓቸው አንቀጾች አልተካተቱም ብለዋል።ከሩሲያ ውጪ ሌሎቹ 14ቱ የፀጥታው ምክር ቤት አባል ሀገራት ረቂቁን ደግፈው ድምጽ ቢሰጡም ሩሲያ ድምጽን በድምጽ በመሻር ውሳኔዋ ምክንያት ረቂቁ ሳያልፍ ቀርቷል።

“ይህ የሩሲያ ውሳኔ ውርደት ነው። የሩሲያን እውነተኛ መልክም ለዓለም በድጋሚ ያሳያል” ሲሉ ላሚ በኒውዮርክ በተደረገው ስብሰባ ተናግረዋል።

“የሩሲያ ተወካይ ስልካቸውን ተጠቅመው በሙሉ ህሊናቸው እንዲመልሱልኝ እጠይቃለሁ። ምን ያህል ሱዳናውያን መገደል አለባቸው? ስንት ተጨማሪ ሴቶች መደፈር አለባቸው? ሩሲያ እርምጃ ከመውሰዷ በፊት ስንት ተጨማሪ ሕፃናት ያለ ምግብ መሞት አለባቸው?” ብለዋል።

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሊንዳ ቶማስ-ግሪንፊልድ በበኩላቸው፤ ሩሲያ የሱዳንን አስከፊ ሁኔታ ለመቅረፍ የሚደረገውን እንቅስቃሴ እያደናቀፈች መሆኑን በመግለጽ፤ የሱዳንን ህይወት በመጉዳት የራሷን የፖለቲካ ዓላማ ለማራመድ ሞክራለች” ሲሉ ወቅሰዋል።

የፀጥታው ምክር ቤት ውይይት ካለቀ በኋላ በተባበሩት መንግሥታት የሱዳን አምባሳደር አል ሃሪት ኢድሪስ አል ሀሪዝ መሐመድ አንዳንድ “ቅድመ-ሁኔታዎች” በረቂቁ ውስጥ የሉም ሲሉ ተናግረዋል።የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ለአርኤስኤፍ የምትሰጠውን ድጋፍ የሚያወግዝ አንቀጽ ሱዳን እንደምትፈልግ ገልጸዋል። የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ ግን ይህንን በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጋለች።

አርኤስኤፍ “ሰላማዊ ሰዎችን የማጥፋት ጦርነት ስለሚያካሂድ አሸባሪ” ተብሎ እንዲፈረጅ እንደሚፈልጉም አክለዋል።ጦር ኃይሉም ሆነ አርኤስኤፍ እስከጦር ወንጀል የሚደርስ የሰብአዊ መብት ረገጣ ፈጽመዋል በሚል ተከሰዋል ሲል የዘገበው ቢቢሲ ነው።

 አዲስ ዘመን ህዳር 11/2017 ዓ.ም

Recommended For You