ማርም ሲበዛ …

ጥንዶቹ የራሳቸውን ጊዜና ቦታ መርጠው ከአንድ ሆቴል ግቢ ተቀምጠዋል። ያዘዙትን ጥሬ ሥጋ ለመብላት እየተዘጋጁ ነው። አስተናጋጁ ከወዲያ ወዲህ ሲል ቆይቶ ትዕዛዛቸውን አደረሰ። ሥጋው ከትሪ ሆኖ በእንጀራ እንደተሸፈነ ከጠረጴዛቸው መሀል አረፈ። ለቁርጥ የተዘጋጀ፣ በአዋዜና ሰናፍጭ የተሞሸረ ጥሬ ሥጋ። መቼም ሥጋን አብዝቶ ለሚወድ ተመልካች አቀራረቡ ለዓይን ያጓጓል።

ወዳጆቼ! የጥሬ ሥጋ አምሮት አይጣል ነው። ትዕዛዙ ደርሶ የልብ እስኪሞላ ዓይን ቢቀላውጥ ቢቃብዝ አይፈረድም። አንዳንዱማ ቀድሞ ከከረሜላው አስጎርዶ፣ በአዋዜው ለውሶ ፣ በአፉ ካላደረሰ ይሞት ይመስለዋል። እንዲህ ዓይነቱ ሥጋ አፍቃሪ ደግሞ ሰው፣ ዓይን እስኪገባ ቢቁነጠነጥ አይታዘቡትም።

አንዳንዴ እኮ ለጥሬ ሥጋ የበዛ ፍቅር ያላቸው አንዳንዶች ለአምሮታቸው ብቻ በሥጋ ቤት ደጃፍ ይዟዟራሉ ይባላል። እንግዲህ ማድረጋቸው ኪሳቸው ባልሞላ፣ እጃቸው ባጠረ ጊዜ ነው። እዚህ የሚያደርሰው የጥሬ ሥጋ አምሮት ወደው ፈቅደው ሲያገኙት ደግሞ ብዙዎች ከነሙሉ ክብሩ በወጉ ያስተናግዱታል። አስቀድሜ ወደጠቆምኳችሁ ጨዋታ ልመለስ። ወደ ሁለቱ ጥንዶች ጉዳይ ።

ጥንዶቹ ያዘዙት ጥሬ ሥጋ ቀርቦላቸዋል። አስቀድሞ የመጣው ጉሮሮ ማርጠቢያ /ድራፍትና ለስላሳ / በየፊታቸው ተቀምጧል። እንግዲህ ከአፍታ በኋላ በእጆች የገቡ ስል ቢላዎች ኃይላቸውን ሊያሳዩ ነው። ሁለቱም ከየወንበራቸው ጠጋ ብለው ማዕዱን ሊጀምሩ ተዘጋጁ። ሽፍንፍኑ እንጀራ ተገለጠ። ሥጋው በአዋዜና ሚጥሚጣ ጣፍጦ ሊጎረስ አይቀሬ ሆነ።

ይህ ከመሆኑ በፊት በድንገት ጠረጴዛቸውን የተጋራ አንድ ሰው ሁኔታውን በፍጥነት ይቀይረው ያዘ። ከሰማይ ይውረድ ከምድር ይፈንቀል ያልታወቀው ወጣት ደርሶ ይንቀዠቃዣል። ሁኔታው ይለያል። ጸጉሩን በግማሹ ተላጭቶ በግማሹ ሹርባ ተሰርቷል። ይህ ብቻ አይደለም። ከጎናቸው ተቀምጦ አብሪያችሁ ካልታደምኩ፣ ካልበላሁ፣ ካልጠጣሁ እያለ ነው።

በድርጊቱ የተደናገረው ሰው ከእነሱ ምን እንደሚፈልግ አጥብቆ ጠየቀው። ወጣቱ አንዳች ያፈረ አይመስልም። የሰውዬውን የድራፍት ብርጭቆ በእጁ አፈፍ አድርጎ ይጎነጭለት ያዘ። በዚህ ብቻ አልበቃውም። ‹‹እንብላ፣ እንጠጣ ማለት የኖረ ባሕል መሆኑን እያስረዳ እጁን ወደትሪው ሰደደ። ደጋግሞ መጉረስም ጀመረ።

ይህ ሰው ከዚህ ቀድሞ ከሰዎቹ አግባብና ትውውቅ የለውም። ከእነሱ ተቀምጦም ገበታቸውን እንዲጋራ አልፈቀዱለትም። ለእሱ ግን ይህ ሁሉ ምኑም አልሆነም። ይባስ ብሎ የድርጊቱን ትክክለኛነት ለማሳየት ሙግት ይዟል። ሁኔታውን ላስተዋለ የሚሠራው ሁሉ እጅግ አስገራሚና አስደንጋጭ ነው።

አሁን ከሁለቱ ሰዎች ወንድዬው ትዕግስቱ እያለቀ ነው። ያለ እሱ ይሁንታ በገበታው እጁን ሰዶ እየጎረሰ በነገር የሚያደርቀውን ጎረምሳ ውስጡ አልተቀበለውም። የእሱ ንዴትና የወጣቱ ቅጥ ያጣ ድፍረት በግንባር ተፋጠዋል። ይህ ሁኔታው ያሳሰባት ሴት ነገሩን ለማብረድ ትሞክራለች። ደጋግማ ‹‹ተወው ይብላ በቃ፣›› ማለቷ ሰውየውን አብሽቆታል። እሷም እንደእሱ ነውረኛነቱን በግልጽ እንድትቃወም እየፈለገ ነው።

ሰውዬው አብራው ካለችው ሴት ‹‹ተወው ይሉት ቃል መደጋገሙን ባልተገባ ትርጉም ይዞታል። ወጣቱ ለእነሱ አለመግባባት ጭምር ሰበብ መሆን ጀምሯል። ገበታው በድፍረት የሚራቆትበት ሰው አሁንም ንዴቱ አልበረደም። ወጣቱ እንዳሻው ከእጁ መጠጥ እየተጎነጨ፣ ከማዕዱ እየቆረሰ ነው።

ሰውየው በቀላሉ ሊያስቆመው አልቻለም። ንግግሩ በንዴት ተይዟል። የእሱን ጥሬ ሥጋ ትቶ ሽሮውንና በየዓይቱን ገዝቶ እንዲበላ በጩኸት እየነገረው ነው። ብሽቀቱ በሁለመናው እየተነበበ ጉሮሮውን በያዘው ቢላዋ እንደሚወጋው ያስጠነቅቀዋል። የደፋሩ ወጣት ድርጊት ግን መስመር መሳቱን ቀጥሏል። የእጁን ጠቅልሎ አብራው ላለችው ሴት ሊያጎርስ እየተንጠራራ ነው።

ወዳጆቼ ! ማንም ህሊና ያለው ወንድ አይደለም አብራው ላለችው ፤ በድንገት ላወቃት ሴት ክብር ይጨነቃል። ይህ ደፋር ወጣት ግን እንዲህ ዓይነቱን ቀይ መስመር መሻገሩን እያሳየ ነው። አሁንም በሁለቱ መሀል የ‹‹እረፍ አላርፍም›› ውዝግቡ ቀጥሏል። የበዛ አብሽቅነት፣ ከትዕግስት አልባነት ጋር በአደባባይ እየተዋጉ ነው።

ሁኔታው በዚህ ቢያበቃ ጥሩ ነበር። የወጣቱ ድርጊት ዓይን ያወጣ ይባል ሆኖ ሰውየውን ያውክ፣ ያናደድ ይዟል። አሁን ደግሞ የቀረበውን ገበታ በድንገት አንስቶ ወደ ሌላ ጠረጴዛ ይዞት ሄዷል። ቀጣይ ርምጃው አፍታ አልቆየም። ልክ እራሱ እንዳዘዘው ሁሉ ከትሪው ላይ እየጠቀለለ መጉረስ ጀመረ።

በገዛ ገበታቸው የበይ ተመልካች የሆኑት ጥንዶች በግርምታ እያስተዋሉት ነው። ያለአንዳች ይሉኝታ ከገበታቸው እያነሳ የሚጎርሰው ምግብ የእነሱ ቢሆንም ሊያዙበት አልቻሉም። ከዚህ በኋላ ሰውዬው ከነትዕግስቱ አልቆየም። ንዴት በላዩ እየተንተከተከ አብራው ላለችው ሴት ከስፍራው እንድትርቅ ማሳሰቢያ ሰጠ። በድንገት ከመቀመጫው እመር ብሎ ሲነሳ እጁ ባዶ አልነበረም። ቢላዋውን ወጣቱ ወዳለበት አቅጣጫ አስተካክሎ ወረወረው። ደግነቱ ስለቱ አቅጣጫውን ስቶ ከመሬት ላይ አረፈ።

እንዲህ ከሆነ በኋላ ሲንቀዠቀዥ የነበረው ወጣት በድንጋጤ ‹‹እግሬ አውጭኝ›› ሲል ተፈተለከ። ቢላዋው እንደሳተው አላመነም። ደጋግሞ የፈጣሪን ስም ተጣራ። ሰውዬው ከኋላው እንደተከተለው ባወቀ ጊዜ ደግሞ እጁን እየጠቆመ እንዲህ አለው ‹‹ካሜራ፣ካሜራ፣ ካሜራ››።

እንግዲህ ወዳጆቼ! ይህ ሁሉ ነውርነት የተፈጸመው ለማህበራዊ ሚዲያ ፍጆታው ሲባል ነው። ወጣቱ ከማያውቃቸው ጥንዶች መሀል ተገኝቶ ያለቅጥ ሲያውክ ሲያበሳጫቸው የቆየው ‹‹ፕራንክ›› ይሉትን ዘመን አመጣሽ ቅጥ አልባነት ዕውን ለማድረግ ነበር።

በነገራችን ላይ ከፈረንጆቹ ልማዶች ጠቃሚ የምንላቸውን መጠቀማችን አዲስ አይደለም። ይህን ስናደርግ አስፈላጊነቱ ታምኖበትና ጉዳታቸው ጭምር ተለይቶ ነው። አሁን ላይ በየማህበራዊ ገጾች የሚስተዋለው ጉዳይ ግን ከመስመር ያለፈ ሆኗል። እንደ ማሳያ የጥሬ ሥጋውን ጉዳይ ብንመለከት ሕይወት ሊያሳጣ፣ አካል ሊጎዳ የሚችልበት አጋጣሚ ያሰፋዋል።

በዘመናችን የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች ላይ በርካታ ጉዳዮችን ማየት ጀምረናል። ደርሰው መንገደኞችን የሚያውኩ፣ በድንገቴ አጋጣሚ ሰዎችን የሚያስደነግጡና በራሳቸውም ላይ ከጥፊ ያለፈ ጉዳትን የሚያስተናግዱ ተበራክተዋል። ያለ ባለቤቱ ፈቃድ ቪዲዮ የሚሰሩና ለነውርነታቸው ዕውቅና እየሰጡ እንዲጨበጨብላቸው የሚሹትንም ቤት ይቁጠራቸው።

እንደውም ከሰሞኑ ሙታን ካረፉበት የመቃብር ሥፍራ ገብተው በሙዚቃና ዳንስ አካባቢውን የሚያውኩ ወጣቶች በየማህበራዊ ገጾች ሲዘዋወሩ አይተን ታዝበናል። ይህ ሁሉ ሲደረግ በሕግ አካላት፣ በሃይማኖት አባቶችና በማህበረሰቡ ድርጊታቸው የሚኮነን ካልሆነ የነገውን አስነዋሪ ድርጊት የምንቆጣጠርበት መንገድ የሚዘጋብን ይሆናል።

‹‹ማርም ሲበዛ ይመራል›› እንዲሉ በየጊዜው የሚስተዋሉትን ቅጥ አልባነት ከወዲሁ መቅጨት ያስፈልጋል። እንዲህ ካልሆነ ግን ባሕል ፣ ሃይማኖትና መልካም እሴት ያሏቸውን ማንነቶች ይዞ መቀጠሉ አስጊ ሊሆንብን ነው። ማሩ ጥፍጥናው አልቆ እንደሬት ሳይመረን በፊት እያንዳንዳችን ከእያንዳንዳችን ወገናዊ ኃላፊነትን ልንጋራ ግድ ይለናል።

መልካምሥራ አፈወርቅ

 አዲስ ዘመን ህዳር 11/2017 ዓ.ም

 

Recommended For You