እንግዶቿን ለመቀበል ያሸበረቀችው አርባ ምንጭ

ዜና ሀተታ

አርባ ምንጭ ሌት ተቀን በስራ ተጠምዳለች።በከተማዋ የመንገድ ጥገናና ግንባታዎች እየተካሄዱ ናቸው፡፡የሕዝብ መናፈሻዎች፣ ስታዲየምና የመብራት መስመሮች እየታደሱ ይገኛሉ፡፡አርባ ምንጭ ከተማ 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ለማዘጋጀት ሽር ጉድ እያለች ነው፡፡

ካለፉት ዓመታት በላቀ መንገድ ለማክበርና ከተለያዩ የሀገሪቷ ክፍል የሚመጡ እንግዶችን ለመቀበል ዝግጅት ከጀመረች ሰንበትበት ብላለች፣ አሁን ላይ ዝግጅቷን ወደ ማገባደድ ምእራፍ አድርሳለች። በሁሉም የዝግጅት ምእራፍ አርባ ምንጭ በሚገባ አሸብርቃለች።

የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን ቅድመ ዝግጅት ለመመልከት ከፌዴራል፣ ከክልልና ከከተማ አስተዳደር የተውጣጡ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች በደቡብ ኢትዮጵያ በ12 ዞኖች አምስት ቀን የቆየ ቅኝት አድርገዋል። በቅኝቱ ወቅት እንደታዘብነው በክልሉ የሚገኙ 32 ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በየደረጃው ዝግጅት እያደረጉ ነው።

ከዝግጅቱ መካከልም መገለጫቸው የሆኑ አልባሳትን፣ ቁሳቁሶችንና ማንነታቸውን ለእንግዶች ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸው ታዝበናል።በዓሉ የሚከበርባት አርባ ምንጭ ከተማ ዝግጅቷን ከጀመረች የቆየች ቢሆንም ያላለቁ ስራዎችን ለማጠናቀቅ ሌት ተቀን በስራ ተጠምዳለች። ሆቴሎችን ዝግጁ ከማድረግ ጀምሮ በከተማዋ እድሳት ተጠምዳለች፡፡

የመንገድ ጥገናው ከተማዋን ለእይታ ማራኪ አድርጓታል፣ በዓሉ የሚከበርበት የአርባ ምንጭ ዩኒቪርሲቲ ስታዲየም እድሳትም በጥቂት ቀናት ውስጥ ዝግጁ ይሆናል። የመብራት ጥገናዎችን ጨምሮ እንግዶች የሚጎበኟቸው ቦታዎች እድሳት ከተማዋን ልዩ ውበት አላብሷታል። የኮሪደር ልማቱ በትክክልም ለእንግዶቿ ምቹ እንደምትሆን የሚያመላክት ነው ብሎ መናገር ማጋነን አይሆንም።

ህዳር 29 ቀን የሚከበረውን የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን ዝግጅትን በተመለከተ የአርባ ምንጭ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ እንደገለጹት፤ በዓሉን አስመልክቶ የተለያዩ የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ይገኛል። በዋናነት በዓሉን በድምቀት ለማክበርና ለእንግዶች ምቹ ከማድረግ አኳያ ኃላፊነት ከተቀበልንበት ቀን ጀምሮ ከተማዋን የማስዋብ ስራ እየተሰራ ነው። በዚህም ለእንግዶች በሚገባ ምቹ ሆናለች ነው ያሉት።

በከተማዋ ያሉ ዋና ዋና መንገዶችን በኮሪደር የማልማት ስራ እየተሰራ መሆኑን የጠቀሱት ከንቲባው፤ ይህም አርባ ምንጭ አሸብርቃ ሙሽራዎቿን ለመቀበል የመጨረሻ ምእራፍ ላይ ትገኛለች። በጥቂት ቀናት ውስጥ ከተማዋን ለእንግዶች ምቹ የማድረጉ ሁኔታ ይጠናቀቃል፤ በዓሉ የሚከበርበት፣ ባዛርና ኤግዚቢሽን የሚካሄድባቸው ቦታዎችን የማስዋብ ስራዎች እየተጠናቀቁ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እንደ ከንቲባው ማብራሪያ፤ የጋሞ አደባባይ ግንባታ የጋሞን ማንነት፣ ትውፊትና ባህል በሚገልጽ መልኩ እየተሰራ ነው፡፡ አደባባዩ በዓሉ በሚከበርበት ቀን ይመረቃል። ይህም ለእንግዶች ልዩ የገጸበረከት ስጦታ ነው። በጋሞ 42 ደረጃዎች ያሉ ሲሆን፤ አደባባዩ ላይ የሚገነባው ግንባታ ይህን በሚገልጽ መልኩ ነው። ጋሞ በርካታ ብሔሮችን አቅፎ የያዘ መሆኑን የሚገልጽ ጭምር መሆኑን ጠቅሰዋል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አባይነህ አበራ በበኩላቸው፤ 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀንን ምክንያት በማድረግ እንግዶችን ለመቀበል የተለያዩ ዝግጅቶች እየተደረጉ ነው። ከዝግጅቱ ውስጥ እንግዶችን ባማረና የጋሞን ባህል በጠበቀ መልኩ ለመቀበል ዝግጅቶች እየተሰሩ ነው። ለበዓሉ መከበር አስፈላጊ የሆኑ ስራዎች ተጠናቀው እንግዶችን እየጠበቅን ነው ሲሉ አብራርተዋል።

ከምንም በላይ የሁሉም ብሔር ተወካዮች የሚያርፉበትን ቦታ ዝግጁ አድርገናል ያሉት ዋና አስተዳዳሪው፤ ህብረተሰቡ እንግዶችን ለመቀበልና በአርባ ምንጭ ከተማ በሚኖራቸው ቆይታ አስፈላጊውን ትብብር ለማድረግ በጉጉት እየተጠባበቀ ነው። እንዲሁም ሆቴሎችንና ሎጆችን በሚገባ አዘጋጅተን የቀኑን መድረስና የእንግዶችን መምጣት እየተጠባበቅን ነው ሲሉ ገልጸዋል።

አርባ ምንጭ ከተማ በዓሉን ካለፉት ዓመታት በደመቀ መልኩ ለማዘጋጀት እራሷን ሞሽራ ለእንግዶቿ ምቹ የመሆን ስራ ሰርታለች፣ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ቀድሞ በመለየት ከወዲሁ ዝግጅቷን እያጠናቀቀች ነው ብለዋል።

እንደ አቶ ዓባይነህ ገለጻ፣ አርባ ምንጭ ከተማና አካባቢው የቱሪስት መስህብ ቦታ በመሆኑ እንግዶች በቆይታቸው መጎብኘት የሚፈልጓቸው ቦታዎች ይኖራሉ። በዚህ ሂደት ውስጥ አስፈላጊውን አገልግሎት ለመስጠት ዝግጅት ተደርጓል። በዓሉን በማክበር ሂደት ውስጥ ምንም አይነት ችግሮች እንዳይገጥሙ ህብረተሰቡን የሰላም ባለቤት የማድረግ ስራ ተሰርቷል። ከከተማዋ ማሸብረቅ ጎን ለጎን እንግዶችን ከመቀበል ጀምሮ ተንከባክቦ ለመሸኘት ህብረተሰቡ ዝግጁ መሆኑን ገልጸዋል።

በሞገስ ጸጋዬ

አዲስ ዘመን ህዳር 11/2017 ዓ.ም

Recommended For You