ከስድስት አሥርት ዓመታት በላይ የኦሊምፒክ ተሳትፎ ታሪክ ያላት ኢትዮጵያ በተጠናቀቀው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ የመክፈቻ ስነስርዓት እንዳላት ደማቅ ታሪክ ደምቃ መታየት አለመቻሏ ኢትዮጵያውያንን ማስቆጣቱ ይታወቃል። ከመቶ ሚሊየን ሕዝብ በላይ ያላት በባህልና በታሪክ ገናና ስም የገነባች አገር በዚያ የኦሊምፒክ መክፈቻ ስነስርዓት በሁለት ሰዎች ብቻ ያውም በማይወክላት አልባሳት በታላቁ መድረክ ደብዝዛ መታየቷ አስደንጋጭ ክስተት ሆኖ አልፏል። ለዚህ አሳፋሪ ስህተት በመክፈቻ ስነስርዓቱ ኢትዮጵያን ወክሎ በባህል አልባሳት ያጌጠው የልኡካን ቡድን ስቴድየም ዘግይቶ መድረሱ በምክንያትነት ተጠቅሷል።
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴም ባለፈው ሳምንት በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫ በመክፈቻው ስነስርዓት ኢትዮጵያን የሚወክለው ልኡክ ስቴዲየም ለመድረስ ከማርፈዱ በተጨማሪ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ በቶኪዮ የነበረው ጥብቅ ቁጥጥርና ገደብ ምክንያት መሆኑ ተጠቅሷል። በተለይም ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ በኦሊምፒኩ የሚወዳደሩ አትሌቶች ብቻ በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ ባንዲራ ይዘው እንዲገቡ መፈቀዱ መደረጉ፣ ኢትዮጵያ አትሌቶቿን በተለያዩ ዙሮች ከፋፍላ ይዛ መጓዟ በመድረኩ ይዛ ልትቀርብ የምትችለው ስድስት አትሌቶችን ብቻ መሆኑ በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ደብዝዛ እንድትታይ ምክንያት ተደርጎ ተጠቅሷል።
ባንዲራ አንግቦ በባህል ልብስ አጊጦ ኢትዮጵያን በሚወክልና በሚመጥን መልኩ በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ ሊቀርብ የነበረው ልኡክ ወደ ስቴድየም ለመምጣት ባያረፍድ እንኳን ቁጥሩ የተገደበ መሆኑ በራሱ ደምቆ እንዳይታይ እንደሚያደርግ በመግለጫው ተጠቅሷል።
ከኦሊምፒኩ መጠናቀቅ በኋላ በሚካሄደው የፓራሊ ምፒክ ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ ወደ ቶኪዮ ያቀናው የልኡካን ቡድን ግን ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መክፈቻ ያጣችውን ግርማ ሞገስ በፓራሊምፒክ መክፈቻው ስነ ስርዓት ላይ ደምቃ እንድትታይ አድርጓል ።
የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ አንግበው በመክፈቻ ስነስርዓቱ ላይ የሚቀርበው የልኡካን ቡድን ቁጥር ስድስት ብቻ እንዲሆን መወሰኑ ኢትዮጵያ ደምቃ እንዳትታይ ማድረጉ በኦሊምፒክ በኩል ምክንያት ተደርጎ የተጠቀሰውን ሃሳብ ውድቅ የሚያደርግም ተግባር የፓራሊምፒክ ልኡኩ በተግባር አሳይቷል። በሰባት ሰው ብቻ በመክፈቻ ስነስርዓቱ ደምቆ መታየት እንደሚቻል የፓራሊምፒክ ልኡኩ ማረጋገጡን በስፍራው የተነሳው ፎቶግራፍ ብቻ በቂ ማሳያ ሊሆን ይችላል።
የኦሊምፒክ ቡድኑ ተከፋፍሎ በተለያዩ ዙሮች መጓዙ እንዳለ ሆኖ ሁለት መቶ ሃምሳ ሚሊየን ብር በጀት ተመድቦለት ከመቶ በላይ ልኡክ የያዘው ኦሊምፒክ በታላቁ መድረክ ማሳየት ያልቻለውን የአገር ክብር ጥቂት ልኡክ እጅግ ባነሰ በጀት የተጓዘው የፓራሊምፒክ ቡድን በማሳየቱ አድናቆትን አትርፏል።
የቶኪዮ 2020 የፓራሊምፒክ ጨዋታ ከትናንት በስቲያ በድምቀት ሲከፈት በመክፈቻ መርሐግብሩ በኮቪድ – 19 ምክንያት ሁሉም የልኡካን ቡድን አባላት በሰልፉ መታደም ባይችሉም ሰባት የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ልዑክ አባላት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው በማውለብለብና የኢትዮጵያን ባህል የሚገልፅ አለባበስ በመልበስ በሰልፉ ስነ ስርዓት ላይ ታድመዋል ።
በሰልፍ ስነ ስርዓቱ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በአትሌት ትዕግስት ገዛኸኝ አማካኝነት ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ተደርጓል ። የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቶ አለም ገብረመስቀልና አቶ ፍቃዱ ዋቅጅራን ጨምሮ ሌሎች የልዑካን አባላት በስታዲየሙ በተዘጋጀላቸው የክብር ቦታ በመገኘት ፕሮግራሙን መከታተል ችለዋል ።
ከኦሊምፒክ ስፖርቶች እኩል በመገናኛ ብዙኃንም ይሁን በመንግሽት ጭምር ትኩረት እየተሰጠው የማይገኘው የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ እንቅስቃሴ አትሌቶች በአገር ውስጥ በክለብ ደረጃ ታቅፈው መንቀሳቀስና የውድድር እድሎችን ማግኘት የዘወትር ፈተናቸው መሆኑ ይታወቃል፤ እነዚህን ፈተናዎች አልፈው በውድድሮች የሚያስመዘግቡት ውጤት ወደፊት ባሉት ቀናት የሚታይ ቢሆንም፣ በታላቁ መድረክ ኢትዮጵያን በአግባቡ መወከል ችለዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20/2013