አዲስ አበባ፡- የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለስልጣን የተለያዩ የችሎት ሥራዎችን እንዲሰራ በአዋጅ ውክልና የተሰጠው ቢሆንም በአንድ ዳኛ መጓደል የተነሳ በስድስት ወር ውስጥ በአስተዳደር ዳኝነት ችሎት ምንም አይነት ውሳኔ አልሰጠም።
የባለስልጣኑ የአስተዳደር ዳኝነት ችሎት ሰብሳቢ አቶ ኪዳኔ ጸጋዬ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ ባለስልጣኑ የተለያዩ ንግድ ነክ ጉዳዮችን እስከ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ድረስ የመመልከት ስልጣን አለው። በዚህም ተቋሙ በራሱ ምርምር አድርጎ የከሰሰውን፤ ነጋዴ ከነጋዴ ጋር የተካሰሰውን፤ ሸማች ነጋዴን የከሰሰውን ክስ በማየት ውሳኔ መስጠት ቢጠበቅበትም በዚህ ስድስት ወር ውስጥ ግን ምንም አይነት ውሳኔ የመስጠት ሥራ አልሰራም።
እንደ ሰብሳቢው ገለጻ፤ ማንኛውም የአስተዳደር ችሎት ውሳኔ በህጉ መሰረት በሦስት ዳኞች የሚከናወን ነው። ይሁንና አንድ ዳኛ በትምህርት ወደ ውጪ አገር በመሄዱ የተነሳ ግን ስድስት ወር ሙሉ ምንም አይነት ውሳኔ አልሰጠም። ይህ በመሆኑ ደግሞ በተለይ የተገልጋይና የተገልጋይ ጠበቆችን እንግልት ጨምሯል። በህጉ መሰረት መዝገቦች በወር ውስጥ ውሳኔ መሰጠት አለበት፣ ዛሬ ግን ከስድስት ወር በላይም ውሳኔ ያልተሰጣቸው መዝገቦች አሉ።
«ዳኛው የመልቀቂያ ጥያቄ ያስገባው ግንቦት ላይ ቢሆንም እስካሁን በእርሱ ምትክ ሹመት ባለመከናወኑ አንገታችንን እየደፋን ነው» ያሉት አቶ ኪዳኔ፤ ዳኛ ጠፍቶ ነው የሚል ግምት እንደሌላቸውና እነርሱም ከተለያዩ ቦታዎች መጥተው እየሰሩ እንደሆነ ተናግረዋል። በተቋሙም ቢሆን እዚህ ገብተው የመስራት አቅም ያላቸው ዳኞች በርካታ እንደሆኑ ገልጸው፤ በሹመት ሳቢያ ስድስት ወር ሙሉ መጠበቃቸው ዋጋ እያስከፈላቸው መሆኑን አስረድተዋል።
ቀደም ሲል ማለትም ከሀምሌና ነሃሴ በፊት እጅ ላይ የነበሩት መዝገቦች 20 ብቻ እንደሆኑ ከእነርሱም ውስጥ 16ቱ መታየታቸውን የገለጹት አቶ ኪዳኔ፤ ከመስከረም በኋላ አንዱ ዳኛ የለቀቀ በመሆኑ አራቱ መዝገቦች ሊታዩና ውሳኔ ሊያገኙ አልቻሉም። በዚያው ልክ አሁን ላይ እየመጡ ያሉ መዝገቦች በጣም በርካታና ወቅታዊ ውሳኔን የሚሹ ቢሆንም ምንም አይነት ውሳኔ መስጠት ባለመቻላችን የምናደርገው ጠፍቶናል ብለዋል።
«ፍትሃዊ ውሳኔ የሚባለው የመጡ ክሶች በጊዜው ውሳኔ ማግኘታቸው ነው። «የዘገየ ፍትህ እንዳልተሰጠ ይቆጠራል» እንደሚባለው አሁን መዝገቦች በብዛት እየተጠራቀሙ መጥተዋል፤ በዚያ ላይ ጊዜያዊና ወቅታዊ፣ እንዲሁም ፈጣን ውሳኔ የሚሹ ናቸው። ሆኖም ይህንን ማድረግ ግን አልተቻለም» ያሉት ደግሞ በባለስልጣኑ የአስተዳደር ዳኝነት ችሎት ዳኛ መቅደስ መኩሪያ ናቸው።
እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ ሹመቱም ሆነ ምርጫው የሚከናወነው በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽህፈት ቤት ነው። የባለስልጣኑ ድርሻ ዳኛ መጉደሉን ለንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ማሳወቅ ነው። ንግድ ሚኒስቴርም በተሰጠው ኃላፊነት ለጠቅላይ ሚኒስቴር ቢሮ እንዲሾምለት ጥያቄ ያቀርባል። በዚህ ተዋረዳዊ የአሿሿም ስርዓት ጥፋቱ የማን እንደሆነ ባልታወቀ ምክንያት ስድስት ወር ሙሉ ምንም አይነት የአስተዳደር ውሳኔ እንዳይሰጥ አድርጓል።
በእርግጥ ጉትጎታው በአስፈላጊነቱ መጠን ተደርጓል ለማለት አያስደፍርም የሚሉት ዳኛዋ፤ ሿሚዎቹ ተናበውና ተግባብተው በአጭር ጊዜ መፍትሄ መስጠት ሲችሉ ስድስት ወር ሙሉ ያለስራ እንድንቀመጥ አድርጎናል ብለዋል። በዚህም አዳዲስ ክሶችን መመልከትና መዝገቦችን ማገላበጥ ላይ ብቻ መወሰናቸውንም ተናግረዋል።
እንደ ዳኛ መቅደስ ገለጻ፤ ውሳኔ ከሌለ ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ አይሰራም። ይህ ደግሞ ተያያዥነት ያላቸው ክፍሎችም ያለስራ እንዲቀመጡ ያደርጋል። በተጨማሪ ወቅታዊ ውጤት የሚያስፈልጋቸው ሥራዎች ኪሳራቸው እንዲሰፋ በማድረግ ከወጪ አንጻር ተገልጋይ፣ ተቋሙና አገር እንዲጎዳ ያደርጋል። በኢኮኖሚው ዕድገትም ላይ የራሱን አሉታዊ አስተዋጽኦ ያሳርፋል። ከዚህ በተጨማሪም መዝገቦች ተበራክተው ዳኞች ላይ ጫና ስለሚያሳርፉ ቀጣይም ሥራ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳርፋል። ጥራት ያለውና ፍትሃዊ ውሳኔ እንዳይወሰንም ያደርጋል።
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2011
በጽጌረዳ ጫንያለው