የኢትዮጵያ መንግሥት የአሸባሪውን ህወሓት ግብዓተ መሬት ለማፋጠን እየሰራ ነው። ቡድኑ ፊትም በህግ ማስከበሩ ዘመቻ ግብዓተ መሬቱ እስኪቃረብ አርምጃ የተወሰደበት መሆኑ ይታወቃል። መቀሌ ላይ ሆኖ ያላቅራራውን ያህል ለሦስት አሥርት ዓመታት ትቶት ወደነበረው ዋሻ ተጠራርጎ ገብቶም እንደነበር የሚታወስ ነው።
አገር የማፍረስ የውክልና ጦርነት የሚያካሂደው ይህ አሸባሪ ኃይል በህግ ማስከበሩ ወቅት የነበረውን ሁኔታ አሳምሮ ያውቀዋል። ከዚያ አስከፊ ጦርነት እንዴት እንደተረፉ ራሳቸው የቡድኑ መሪዎች እየዘገነናቸው መናገራቸውን መገናኛ ብዙኃን አሰምተውናል።
ይህ ሁሉ ሆኖም ቡድኑ ከሽንፈቱ የሚማር አልሆነም። ወደ ሌላ የጦርነት አዙሪት ገብቷል። ‹‹ያደቆነ ሳይጣን ሳያቀስ አይተውም›› አንዲሉ አገር የማፍረስ ዓላማን አንግቦ በጥፋት ተልዕኮው ቀጥሎበታል። የሰላም ጠረን ጨርሶ በውስጡ የሌለ በመሆኑ መንግሥት የወሰደውን የተናጠል የተኩስ አቁም ለትግራይ ህዝብ ሰላም ማውረጃ ማዋል ሲገባው ለሌላ ጦርነት ድግስ አውሎታል።
በበቀል ስሜት በአማራና አፋር ክልል ላይ ጥቃት ከመሰንዘር አልፎ አንዳንድ አካባቢዎችን በወረራ በመያዝ ብዙ ጉዳት ያደረሰውም በዚሁ በተናጠል የተኩስ አቁሙ ወቅት ነው። በዚህ ለሰላም ሲባል በተሰጠ የጽሞና ጊዜ ንጹኃን ኢትዮጵያውያን ያለምንም ጥፋታቸው ውድ ዋጋ ክፍለዋል። በአፋር ክልል 107 ህጻናትን ጨምሮ ከ240 በላይ ንጹኃንን በተፋናቃዮች መጠለያ ጣቢያ እያሉ በከባድ መሳሪያ ተጨፍጭፈዋል። በአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን አጋምሳ አካባቢም ተመሳሳይ ጥቃት ተፈጽሟል። በሁለቱም ክልሎች በዚህ የክረምት ወቅት ወደ 500 ሺ የሚደርሱ ሰዎች ከሞቀ ቤታቸው እንዲፈናቀሉ አርጓል።
ከአማራ ከልል ጋር የማወራርደው ሂሳብ አለኝ ባለው መሰረት የዘረፋ እቅድ አውጥቶ አስፈጽሟል። የሚችለውን ዘርፏል፤ የማይችለውን አውድሟል። የቀረው የለም። ቡሃ አቃ ተሸክሞ ሄዷል፤ ሹሮና በርበሬ ገልብጦ ወስዷል። ሴቶችን ደፍሯል፤ ወጣቶችን ገድሏል። አረመኔያዊ ባህሪውን እንስሳትን ጭምር በመጨፍጨፍ አሳይቷል።
በቅርቡ ደግሞ ከሌላው አሸባሪ ቡድን ጋር ግንባር በመፍጠር በቀጣይ ሊፈጽም ያሰበው ጥፋት ፣ አሁንም ድረስ በመላ ኢትዮጵያ ሰርጎ ገቦችን እያላከ ሊፈጽም እያደባ ያለው የጥፋት ድግስ ቡድኑ እየደረሰበት ካለው ሽንፈት የማይማርና በቀጣይም ሌላ የጥፋት ድግስ ከመደገስ የማይቆጠብ መሆኑን ያመለክታል።
ይህ ሁሉ ሲታሰብ የኢትዮጵያ መንግሥት ቡድኑን ለመደምሰስ እያከናወነ ያለው ተግባር ትክክልና ሊፋጠን የሚገባው እንደሆነም ያመለክታል። መንግሥት በተናጠል የተኩስ አቁሙ መከላከያን ከትግራይ ሲያስወጣ ቡድኑ ከዚህ በኋላ ሊያመጣ የሚችለው ትርጉም ያለው ተጽእኖ አይኖርም የሚል ድምዳሜ ላይ ደርሶ ነበር። ቡድኑ ግን ዶሮ ሞቷ ላይቀር ስትንደፋደፍ ቤት ታጠፋለች እንደሚባለው በአልሞት ባይ ተጋዳይ ከንቱ ጥረቱ አሁንም ዜጎችና ሀገር የማይገባ ዋጋ እየከፈሉ ናቸውና መንግሥት አሁን በጀመረው የህልውና ዘመቻ በማያመላልስ መልኩ ቡድኑን መደምሰስ ይኖርበታል።
በሰሜን ዕዝ ላይ የፈጸመው የክህደት ተግባር ፣ ይህን ተከትሎ የሐገር ሉአላዊነት በሱዳን መደፈሩ፣ ለዓለም አቀፍ ተቋማትና ምዕራባውያን መንግስታት በሚመሰርታቸው የሐሰት ክሶች ኢትዮጵያ ላይ ጫናዎች እየተደረጉ መሆናቸው፣ ከሁሉም በላይ እያካሄደ ያለው የውክልና ጦርነት የተከፈለው ዋጋ ተከፍሎ ቡድኑ መደምሰስ ያለበት መሆኑን የሚያስገነዝቡ ናቸው።
ሀገር በእዚህ አሸባሪ ቡድን የተነሳ የምትገብረው ህይወትና ሀብት መቆም ይኖርበታል። ይህ ሊሆን የሚችለው ደግሞ ቡድኑ ጨርሶ ሲደመሰስ ብቻ ነው። ቅንጣቱም መቅረት የለበትም። ቀና እንዳይል እንዳያቆጠቁጥ አድርጎ መደምሰስ ያስፈልጋል።
አዎን የመንግሥትም ትእግስት ተሟጧል። የመጨረሻ ያለውን አማራጭም ይዟል። የመጨረሻው አማራጭ ጦርነትና ጦርነት ነው። ጁንታው የሚገባው ጦርነት እና ጦርነት ብቻ ስለመሆኑ የመከኑ ሰላማዊ አማራጮች ሁሉ ያስገነዝባሉ። መንግሥትም እየተካሄደ ባለው የህልውና ዘመቻ ለጁንታው በሚገባው በዚሁ ቋንቋ እየነገረው ያለበት ሁኔታ ተጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል።
መንግሥት የሀገር ሉአላዊነትን ለማስጠበቅ መላ ኢትዮጵያውያንን ይዞ በውጊያ ላይ ይገኛል። ሰሞኑንም ከአማራ ክልል፣ ከአፋር ክልል ልዩ ሃይልና ሚሊሺያዎች ጋር በመሆን የመከላከያ ሠራዊቱ አንጸባራቂ ድሎችን እየተቀዳጀ ነው። ቡድኑ ከገባባቸው ከእነዚህ ክልሎች አይቀጡ ቅጣት እየተቀጣ በመደምሰስ ላይ ይገኛል።
ቡድኑ ከፈጸማቸው ታሪክ ይቅር የማይላቸው የጥፋት ድርጊቶቹ የሚማር አይደለም፤ ይበልጥ የተወሳሰበ ደርጊት ይፈጽማል እንጂ። በአርሶ አደር ላይ ነው የመጣው። አርሶ አደሩ እኮ እንስሳቶቹ ብዙ ነገሩ ናቸው። እንኳን ሊገደሉበት ከብቶቹና ልጆቹ ሲቆጠሩበት እንኳ አይወድም። ከብቶቹ ማለት ልጆቹ ናቸው፤ እይኖቹ ናቸው። አሸባሪዎቹ የአርሶ አደሩን ከብቶች አርደው መብላታቸው፣ መንዳታቸው አንሶ መንዳት ሳይችሉ ሲቀሩ በጥይት ደብድበው መግደላቸው ምን ያህል ክፉ አንደሆኑ ያመለክታል። እንዲህ ያለው ርኩስ ድርጊት ታይቶም ተሰምቶም አያውቅም።
ከ85 በመቶ በላይ አርሶ አደር በሚገኝባት ሀገር ይህ አይነቱ ድርጊት መፈጸሙ የቡድኑ ክፋት እያደር እየከፋ መምጣቱን ያመለክታል። ቡድኑ በአርሶ አደሩ ልጆችና አይን ነው የተጫወተው። የመንግሥት የትእግስቱ መጨረሻም አንዱ ይሄው መሆን አለበት። በአይንና በልጅ የመጣ አይማርምና።
የቡድኑ ክፉኛ መመታትና እየተዳከመ መምጣት ያሳሰባቸው የውጭ ሀይሎች ድምጻቸው እየተሰማ ነው። የድርድርና የመሳሰሉትን ሀሳቦች በማምጣት የተያዘው የህልውና ዘመቻ እንዳይቀጥል ለማድረግ ይሞክሩ ይሆናል። የኢትዮጵያ መንግሥት ሁሉንም አማራጮች ተጠቅሞ ነው እዚህ የደረሰው ጁንታውን ከመደምሰስ ውጪ ሌላ አማራጭ አይኖረውም። የቅርቡን እንኳን ብንጠቅስ በተናጠል የተኩስ አቁሙ መጠቀም ይቻል ነበር። ውጊያው ያሳስበናል ሲሉ የቆዩ የውጪ ኃይሎች የተኩስ አቁሙን ከማድነቅ ባለፈ ሰላማዊ ሁኔታ አንዲመጣ መስራት ሲገባቸው ያንን አላደረጉም። እነዚህ ኃይሎች ብዙ መስራት ይቻል የነበረበትን መልካም አጋጣሚ አምክነውታል።
አሁን ያለው የኃይል አማራጭ መሆኑ ብቻ ለሁሉም ግልጽ መሆን አለበት። አሸባሪው ህወሓት የሚገባው ቋንቋም ይሄው ነው። ይህን አማራጭ በሚገባና በፍጥነት በመጠቀም የአሸባሪውን ህወሓት ግብዓተ መሬት መፈጸም ይገባል።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 20 ቀን 2013 ዓ.ም