በ2022 ኳታር በምታስተናግደው የዓለም ዋንጫ ለመሳተፍ የማጣሪያ ጨዋታውን የፊታችን ነሐሴ 28 እና ጳጉሜን 02/2013 ዓ.ም ከጋና እንዲሁም ከዚምባቡዌ ብሔራዊ ቡድን ጋር የሚያደርገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ዝግጅቱን በአዳማ ማድረግ ከጀመረ ሰንብቷል። በአሠልጣኝ ውበቱ አባተ የሚመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም ዋንጫ ለማለፍ ከደቡብ አፍሪካ፣ ጋና እና ዚምባቡዌ ጋር እንደተደለደለ ይታወቃል።
ብሔራዊ ቡድኑ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ለመሳተፍም ከፊቱ ላሉበት ወሳኝ ጨዋታዎች ከነሐሴ 4/2013 ዓ.ም ጀምሮ አዳማ ላይ መቀመጫውን በማድረግ ሲዘጋጅ የቆየ ሲሆን፤ ነገ ከሴራሊዮን አቻው ጋር በባህርዳር ዓለም አቀፍ ስቴድየም የወዳጅነት ጨዋታ ያደርጋል። የፊታችን ዕሁድ ደግሞ በተመሳሳይ ዩጋንዳን ይገጥማል። የብሔራዊ ቡድኑን ዝግጅት በተመለከተም አሰልጣኝ ውበቱ ከትናንት በስቲያ ወሎ ሰፈር በሚገኘው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፅህፈት ቤት መግለጫ ሰጥተዋል።
አሠልጣኝ ውበቱ አብዛኞቹ ተጫዋቾች ቤትኪንግ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ከተጠናቀቀበት ከግንቦት 20 ቀን 2013 በኋላ ውድድርም ሆነ ቋሚ ልምምድ ላይ እንዳልነበሩ ጠቅሰው፣ በዝግጅታቸው ተጫዋቾቹን ለጨዋታ ቶሎ የማብቃት ሥራ ላይ ትኩረት ሰጥተው ሲሠሩ መቆየታቸውን ገልጸዋል። አሰልጣኙ ዝግጅታቸውን እያደረጉ የቆዩት ለሃያ ስምንት ተጫዋቾች ብቻ ጥሪ በማድረግ ነው፡፡ ካላቸው አነስተኛ የተጫዋቾች ስብስብ አንፃር አሁን ላይ የተጫዋቾች ቅነሳ እንደማይደረግ ጠቁመው፣ ከዚህ በኋላም ለአዲስ ተጫዋቾች ጥሪ እንደማይደረግ አስረድተዋል። በግብፅ ሊግ እየተጫወተ የሚገኘው አማካኙ ሽመልስ በቀለ ብቻ የክለብ ጨዋታዎቹን ሲጨርስ ቡድኑን እንደሚቀላቀል ጠቁመዋል።
አሠልጣኙ ባለፉት ሳምንታት ለተጫዋቾቻቸው ሲሰጥ የነበረው ልምምድ በአካል ብቃት እና ሥነ-ልቦና ላይ ያተኮረ መሆኑን በመጥቀስ በታክቲካዊ ጉዳዮች ላይም ትኩረት እንደተደረገ አመላክተዋል። በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግና ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳታፊ የሆኑት የፋሲል ከተማና ኢትዮጵያ ቡና ተጫዋቾችን በቡድናቸው ለማካተት ሊገጥማቸው የሚችለውን ችግር አስመልክቶ በሰጡት አስተያየትም፣ ከክለቦቹ ጋር ውይይት እንደተደረገ ጠቁመዋል፡፡
ይህ የብሔራዊ ቡድን ግዳጅ እንደሆነ እና ሁለቱ የማጣሪያ ጨዋታዎች እንደተጠናቀቁም ተጫዋቾቹ ወደየክለቦቻቸው እንደሚሄዱ አስረድተዋል። ከጨዋታ መደራረብ ጋር ተያይዞ ብሔራዊ ቡድኑ በጥቂት ቀናት ልዩነት የወዳጅነት ጨዋታዎቹን ጨምሮ አራት ግጥሚያዎችን ማድረጉ ጫና ይኖረዋል የሚል ስጋት እንዳለም ተጠቁሟል፡፡ ‹‹አራት ጨዋታዎችን በጥቂት ቀናት ልዩነት ማድረግ ጫና አለው። ግን በወዳጅነት ጨዋታዎቹ ላይ ተጫዋቾቹ ላይ ያለውን ጫና ለመቀነስ እና ሁሉም ተጫዋቾች ያለውን ጫና እንዲጋሩት እናደርጋለን። ግን በዋናነት የቡድኑ 70 እና 75 በመቶ የሚሰለፉ ተጫዋቾች ስለሚታወቁ ያን ያህል ጫና አይፈጠርም።›› በማለት አሰልጣኙ ምላሽ ሰጥተዋል።
የአቋም መፈተሻ ጨዋታዎቹ በሁለቱ አገራት መልካም ፍቃደኝነት የተገኙ መሆናቸውን የገለጹት አሰልጣኝ ውበቱ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑም ከፍተኛ ጥረት እንዳደረገ ተናግረዋል። በተለይ የዩጋንዳው ጨዋታ ሙሉ በሙሉ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጥረት መገኘቱ የተገለጸ ሲሆን፤ የሴራሊዮን ጨዋታ ደግሞ ፌዴሬሽኑ ከስመጥር ስፖርት እና ኢንተርቴመንት ጋር በጋራ በመሆን ያመቻቸው መሆኑ ተነግሯል።
በአሠልጣኝ ጆን ኬይስተር የሚመራው የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ አስተናጋጅነት ለሦስት ቀናት በሚከናወን ውድድር ላይ ተሳታፊ እንደሚሆን ይታወቃል። ብሔራዊ ቡድኑ ከፊቱ ላለበት ንዑስ ውድድር አቋሙን ለመፈተሽ ይረዳው ዘንድ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጋር የነገውን የወዳጅነት ጨዋታ እንደሚያደርግ ታውቋል።
የሴራሊዮን ብሔራዊ ቡድን ከቤኒን ጋር በነበረው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ ህግ ጥሷል በሚል የ5 ሺ ዶላር ቅጣት በካፍ እንደተጣለበት የሚታወስ ሲሆን፣ በኢትዮጵያ የአቋም መለኪያ ጨዋታ እና በዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውድድር የሚጠቀምበትን ስብስብ ይፋ አድርጓል። በዚህም አሠልጣኝ ጆን ኬይስተር ለሦስት ግብ ጠባቂዎች፣ ሰባት ተከላካዮች እና አማካዮች እንዲሁም ለስድስት አጥቂዎችን በአጠቃላይ ለ23 ተጫዋቾች ጥሪ በማድረግ ትናንት አዲስ አበባ መድረሳቸው ታውቋል።
ከስምንት ዓመት በኋላ ወደ አፍሪካ ዋንጫ መመለሳቸውን ያረጋገጡት ዋልያዎቹ፣ ባሳለፍነው ሳምንት የአፍሪካ ዋንጫ የምድብ ድልድል ሲወጣ ከአዘጋጇ ካሜሩን፣ቡርኪናፋሶና ኬፕቨርዴ ጋር መደልደላቸውን በተመለከተም አሠልጣኝ ውበቱ አባተ ገለጻ አድርገዋል።
‹‹የአፍሪካ ዋንጫ ድልድልን በተመለከተ እኛ ቋት 4 ላይ ነበርን። ከበላያችን ያሉት ሦስት ቋቶች ውስጥ ደግሞ ጠንካራ ቡድኖች ናቸው ያሉት። በህጉ መሰረት ደግሞ እኛ በሌሎቹ ቋት ውስጥ ካሉ ጠንካራ ቡድኖች ጋር ነው የምንደለደለው። የሆነውም ይህ ነው። ከዚህኛው ጠንካራ ቡድን ይሄኛው ጠንካራ ቡድን ይሻላል የሚለው ሌላ ነገር ነው። ብቻ እኛ ቋት ውስጥ ከነበሩት ቡድኖች ጋር አይደርሰንም ነበር። ስለዚህ በደረጃ ከሚበልጡን ጋር ተመድበናል›› ሲሉ አብራርተዋል።
‹‹በእርግጠኝነት የምነግራችሁ ነገር እንደ ትናንቱ በፍራቻ አይደለም የምንጫወተው። ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታዎች ላይ በርከት ያሉ ግቦችን እያገባን በጥሩ አጨዋወት ስንጫወት ነበር። ስለዚህ በቀጣይም ይህ ይቀጥላል። እስከ ጥር የተወሰነ ጊዜ ስላለን የጀመርነውን ነገር እያስቀጠልን እንሄዳለን። በአጠቃላይ በምድባችን የተለየ ነገር ለማሳየት እንሞክራለን›› በማለት አሰልጣኝ ውበቱ ተናግረዋል።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2013