አዲስ አበባ፣ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ቀዳማዊ ምኒልክ ሳይንስ ሼርድ ካንፓስ አላማ በተግባር የተደገፈ ትምህርት በመስጠት የላቁ ተመራማሪዎችን ማፍራት ቢሆንም በተግባር ግን ከመደበኛው ትምህርት የተለየ ትምህርት እየሰጠ አይደለም፡፡
ስሜ አይጠቀስ ያሉት የሼርድ ካንፓሱ ተማሪ ወላጅ እንደተናገሩት፣ከዛሬ አራት ዓመት በፊት በአንድ የውጪ ዜጋ በሆነ መምህር፣ በከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ እና በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪዎችን ለማፍራት አላማ አድርገው ስራው ቢጀመርም ተማሪዎቹ ግን ከመደበኛው ትምህርት የተለየ ነገር ማግኘት አልቻሉም።
የተማሪ ወላጅ እንደገለጹት፣ የትምህርት ቤቱ አላማው ተመራማሪን ማፍራት፤ በተግባር የተደገፈ ትምህርት በመስጠት የላቁ ተመራማሪዎችን ይበልጥ ማላቅና ለአገራቸው ብቁና ከዓለም እኩል ተወዳዳሪ የሚሆኑ ዜጎችን መፍጠር ቢሆንም አሁን ያለው ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ የራቀ ነው፡፡ ትምህርቱ ከመደበኛ በተለየ መልኩ እየተሰጣቸው አይደለም።
‹‹አሁን ተማሪዎቹ ያሉበት ሁኔታ አሳሳቢ ነው። ከመደበኛው የተለየ ትምህርት አይሰጣቸውም። የወላጅ ጉጉት ከመደበኛው ተለይቶ በተግባር የተደገፈ ትምህርት ያገኛል የሚለው ነው። ይሁንና እየተተገበረ ያለው በተቃራኒው ነው። ሳይንቲስትና ተመራማሪ ይሆኑልናል ብለን የላክናቸው ልጆች እየተቀለደባቸው ነው››ሲሉም የነበራቸው ተስፋና በተግባር እየሆነ ያለው አለመጣጣሙ አመልክተዋል።
የችግር ዋናው መንስኤ ባለቤት ኖሮት በሚገባ ያለመሰራቱ እንደሆነ የገለጹት የተማሪ ወላጅ፤ የተረከበው አካል ሼርድ ካንፓሱን ከዩኒቨርሲቲው እኩል አይመለከተውም። በዚያም ልክ ተማሪዎች በመንግስት እንዲደገፉ እያደረገ አይደለም። ይህ ደግሞ ወላጅ ልጆቹን ላለመጉዳት ሲል እንዲለቁ እያስገደደ ነው ይላሉ።
የ12ኛ ክፍል ተማሪው ኢዮብ ጸጋዬ እንደገለጸው፤ ከነበረበት ትምህርት ቤት የተለየ ትምህርት እያገኘ አይደለም፤ ለምን ተመርጬ ገባሁ የሚለው የዘወትር ጥያቄ ነው። ቤተሰብ ከዚህ ሊያስወጣው እንዳልወደደና አሁን ሦስት ወሩን ለማጠናቀቅ ብቻ እየተማረ ነው።
ሲመረጡ የሳይንስ ፍቅር ያላቸው ተብለው መሆኑን አስታውሶ፣ ሳይንስ ደግሞ በተግባር የተደገፈ ትምህርት በመሆኑ የተሻለ ውጤታማ ለመሆን አስቦ ቢመጣም በተግባር ያገኘው በተቃራኒው መሆኑ እንዳስከፋውም ገልጿል።
ከማትሪክ ውጤት በኋላ የመጀመሪያ ምርጫቸው እንዲከበርላቸው ለትምህርት ሚኒስቴርና ለሃገር አቀፍ ፈተናዎች ምዘና ኤጀንሲ መረጃቸው ሊሰጥ እንደሚገባም ተማሪ እዮብ አሳስቧል ።
የ11ኛ ክፍል ተማሪው ኤልያብ ምህረት በበኩሉ፣«አስረኛ ክፍል ላይ አገር አቀፍ ፈተና ስንፈተን ሁላችንም ሁሉንም ኤ አምጥተናል። አላማችን ውጤት ብቻ ሳይሆን ፍላጎትን ማግኘት ነው ። በመሆኑም መንግስት ይህንን ሊያሟላልን ይገባል» ይላል፡፡
ተማሪ ኤልያብ፤ መምህራን ሲያስተምሩ በዩኒቨርሲቲ ደረጃ እንደለመዱት ረጅም ሰዓት ነው። ተማሪው የለመደው ግን 45 ደቂቃ በመሆኑ ሁለቱን ለማመጣጠን እንደተቸገሩም ጠቅሷል፡፡
የ12ኛ ክፍል ተማሪዋ ያብስራ ጸጋዬ በበኩሏ፣ በኮተቤ በተግባር የተደገፈ ትምህርት፣ ለተመራማሪነት የሚያበቃና ልዩ ፍላጎታቸውን ያማከለ ትምህርት በሚገባ ይሰጥበት እንደነበር ታነሳለች። ምቹነቱም ቢሆን ከወንበር አቀማመጥ ጀምሮ የተሻለ ነበርና ያ ነገር ለተተኪዎቹ ሊስተካከልላቸው እንደሚገባ ታስገነዝባለች።
ካንፓሱ ከማንኛውም ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የሚወዳደር አይደለም። የሚወዳደረው ከራሱ ጋር ነው። ምክንያቱም ተማሪዎቹ በራሳቸው ልዩና የተመረጡ፤ መምህራኑም እንዲሁ ምርጦች ናቸው። ነገር ግን ችግሩ የሆነው በምርጫው ልክና በተባለው መጠን አለመሰራቱ ነው ትላለች፡፡
የካንፓሱ ዲን አቶ ጥበበ በላይነህ እንደሚናገሩት፤ በመንግስት አሰራር ብዙ የግዢ ሂደቶች ተጓተዋል። በዚህም ካንፓሱ የተፈለገውን ያህልም ምቹና ማራኪ መሆን አልቻለም። በዚያ ላይ መጀመሪያ ሲማሩበት የነበረው ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ በቀጥታ ወደዚህ ስለመጣ በአንድ ጊዜ ቦታውን ምቹ ማድረግ አዳጋች ሆኗል። ስለዚህም ከምቹነት አንጻር በዚህ ምክንያት የታሰበውን ያህል አልተሰራም።
ተማሪዎቹ በኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ ግቢ እያሉ ቤተ ሙከራው በሚማሩበት ክፍል ውስጥ ነበር፡፡ አሁን ግን ወደ ዚህ በመዛወሩ የተነሳ ብዙም ያልተጠቀሙበት ሁኔታ ተፈጥሯል ይላሉ።
የንድፈ ሀሳብ ትምህርት የበዛውና የተግባር ስራ እንዲሰሩ ለማድረግ ያልተቻለው ወጥተው የሚወዳደሩት በመደበኛ ትምህርታቸውን ሲከታተሉ ከቆዩ ተማሪዎች ጋር በመሆኑ ውጤታቸው ዝቅ እንዳይልና አዕምሯቸው እንዳይጎዳ በመፈለጉ እንደሆነ ይናገራሉ። ይሁን እንጂ በመጽሃፍቱ ላይ ያሉ ሙከራዎችን ሳይሰሩ የቀሩበት ሁኔታ የለም ነው ያሉት።
እንደ አቶ ጥበቡ ገለጻ፤ የካንፓሱ ዋና አላማ ልጆቹን በልዩ ፍላጎታቸው ለይቶ ማስተማርና ፍላጎታቸውን ማዳበር ነው። በፍላጎታቸው ላይ ተመስርተው ሲሰሩ ደግሞ የሚፈልጉትን አውቀው እንዲወጡ ይሆናሉ። በዚህም በሳይንሳዊ መንገድ ልዩ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው። በቀጣይ ግን ከ12ኛ ክፍል በኋላ ካንፓሱ ምንም መስራት ስለማይችል የሚፈልጉት ቦታ ላይ እንዲመደቡ ለማድረግ የትምህርት ሚኒስቴርና የሃገር አቀፍ ፈተናዎች ምዘና ኤጀንሲ ሊያስቡበት ይገባል።
አዲስ ዘመን የካቲት 17/2011
በጽጌረዳ ጫንያለው