አሸባሪው ህወሓት ህዝብን ከህዝብ ጋር የማባላትና ሀገርን የማፈራረስ እቅድ ይዞ በሀገሪቱ በተለያዩ አቅጣጫዎች ይንቀሳቀሳል። የሀገርን ሰላም የማደፍረስ፣ ነዋሪውን ከቀዬው የማፈናቀል፣ ንብረት የማውደምና የሀገርን ኢኮኖሚ የማዳከም እቅዱን ለማሳካት ቀን ከሌሊት ሳያሰልስ እየሠራ ይገኛል። ሀገርን የማፍረስ ዓላማውን ለማሳካት ለምዕራባውያን ተላላኪ በመሆን ጭምር የባንዳነት ሥራውን አጠናክሮ ቀጥሏል።
አሸባሪው ህወሓት ቀደም ሲልም ይሠራ የነበረው ለሀገር ልማትና ሰላም ሳይሆን ሀገርን የመዝረፍ፣ ንብረት የማሸሸ እንዲሁም ህዝብ ከህዝብ ጋር ተስማምቶ በጠንከራ አንድነት ላይ የተመሰረተ ሀገር እንዳይኖር ነበር። ለዚህም የውሸት ትርክቶችን ሲፈጥርና እውነታውን ሲያዳፍን ኖሯል።
አሁንም ሳይታክት የሚሠራው በተላላኪነት የሚያገለግላቸውን ምዕራባውያን ሃሳብ ለማሳካትና በአንድ ጀንበር ያጣውን ስልጣኑን መልሶ ለመቆናጠጥ ነው። ለዚህም ያልቆፈረው ጉድጓድ፤ ያልፈነቀለው ድንጋይ የለም። ሆኖም ግን ህዝብ ከውስጡ አውጥቶ ጥሎታልና ወደስልጣን ማማው ለመወጣጫ የሚያገለግለው መሰላል አላገኘም። የእሱን ጽዋ ህዝብ አላነሳ ሲለውም የተለያዩ ትንኮሳዎችን በየአቅጣጫው በመፍጠር የጥፋት ሱሱን አጠናክሮ ቀጥሏል።
የጥፋት ዓላማውን ለማሳካትም በራሱ አምሳል ከቀረጸው አሸባሪው የሸኔ ቡድን ጋር ጋብቻ መፈጸማቸውን በአደባባይ አሳውቋል። በየአቅጣጫውም ህዝብን መዝረፍ፣ ማፈናቀል፣ ሀገር ማውደምን የእስትራቴጂው ግብ አድርጓል። ይሄንኑ እኩይ ዓላማውን ለማሳካትም የሚጠቀመው ንጹሐኑ ወደ ጦርነት እንዲገቡና እንዲማገዱ ማድረግ ነው።
የአሸባሪው ቡድን ህወሓት ገና ከመነሻውም የሚታወቀው የህዝብ ልጅ፣ የህዝብ አገልጋይና ለህዝብ የቆመ ሆኖ ሳይሆን የህዝብን ረሀብ ለማስታገስ የመጣን የዕርዳታ ምግብ ለጦር መሳሪያ መግዣነት ሲያውል ነው። ቀደም ሲል ከደርግ ጋር በነበረው የትጥቅ ትግል ወቅት የትግራይ ህዝብ ረሀብና ጉስቁልና የነገደ፤ በዚህም ለዜጎች ረሀብ ለመድረስ ከዓለም አቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች የተሰጠውን የዕርዳታ እህል ወገኑን ከእልቂት ሳያተርፍ ምግቡን ሸጦ ለጦር መሳሪያ መግዣ ያዋለ ቡድን ነው።
ለአሸባሪው የህወሓት ቡድን ትልቁ እርካታ ወገንን መታደግና ህይወት ማትረፍ ሳይሆን፤ በሰብዓዊነት ድጋፍ ስም በመጡ ሀብቶች ለራሱ መበልጸግና ለህልውናው ማቆያ ይሆነኛል ያለውን የጦር መሳሪያ መግዛት ነው። አሁንም እያደረገ ያለው የጭካኔ መንገድ ይሄንኑ የታሪክ ስህተቱን፤ የጭካኔ ጥጉን የደገመም፣ ያስታወሰም ነው።
ምክንያቱም አሸባሪው ህወሓት አሁንም በተግባር እያደረገ ያለው ከትግራይ ህዝብ የወጣ ለትግራይ ህዝብ የቆመ አለመሆኑ ጉልህ ማሳያ ነው። በትግራይ ክልል ሕፃናት ፣ሴቶችና አረጋውያን ረሀብ መቋቋሚያ የመጣን ምግብ ለሕፃናት የቀረበውን ኃይልና ሙቀት ሰጪ ብስኩት ሳይቀር ዓላማውን ለማስፈፀም ለሽብርና ጭፍጨፋ ተግባር ላሰለፋቸው ታጣቂዎች እንዲውል እያደረገ ይገኛል።
ይህም ብቻ ሳይሆን ጁንታው ለትግራይ ህዝብ ደንታቢስ መሆኑን በተለያዩ ማስረጃዎች ማረጋገጥ ተችሏል። አንዱ ማሳያው ለጦርነት እየመለመለ የሚያሰልፈው ዕድሜያቸው ለውትድርና ያልበቁ ሕፃናትንና ታዳጊዎችን ነው። የራሳቸውን ልጆች ሰላምና መረጋጋት ባለበት የውጭ ሀገራት በኢትዮጵያውያን ሀብትና ገንዘብ በቅንጡ ትምህርት ቤት እያስተማሩ መከራዋን በልታና በችግር ተጠብሳ ያሳደገችውን የደሀዋን የትግራይ እናት ልጆች በአንድ በኩል በችግር እንዲጠበሱ እያደረገ በዕርዳታ የመጣን የዕርዳታ ምግብ እንኳን ልጁን ለውጊያ ለሰጠ ብቻ በሚል አረመኔያዊ ተግባር ምግብን እንደመያዣ እየተጠቀመበት ይገኛል። ይህም አልበቃ ብሎት ለሕፃናቱ የመጣን ኃይልና ጉልበት ሰጪ የዕርዳታ ምግብ ሳይቀር ላሰለፈው ሠራዊት በማከፋፈል ሕፃናትና ሴቶች በረሀብ እንዲያልቁ ፈርዶባቸዋል።
በእርግጥ አሸባሪው ህወሓት ሀገርን የመሸጥ የባንዳነት ተግባሩ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ነው። ‹‹መሸጥ የለመደ እናቱን ያስማማል›› እንደሚባለው የአበው አባባል ሁሉ ጁንታውም ዛሬ በሀገር ላይ ይሄን ሲያደርግ በግልጽ ቢታይም በስልጣን በቆየባቸው ዘመናት ሁሉ የሀገርን ሀብት ሲዘርፍ ፣ ሲሸጥ ኖሯል። ዛሬም እንደ መዠገር ተጣብቆ አልላቀቅ ያለው ‹‹እኔ ካልዘረፍኩ ፣ በገፍ የምዘርፈው ካልሆነ ይፍረስ ›› ብሎ መሆኑ ለማንም ግልጽ ነው።
አሁንም እንቅልፍ የነሳው ሩጫ በአንድ ጀንበር ያጣውን ስልጣኑን ከውጪ ኃይሎች ጋር ተባብሮ ለመመለስ ፤ ይሄ ካልሆነ ሀገር እንድትፈርስ ነው እንጂ አንድም ጊዜ ለትግራ ህዝብ ብሎ የሠራውም፤ የሚሠራውም መልካም ነገር የለም። ለወገኔ ለትግራይ ህዝብ ብሎ ከማሰብ ይልቅ ለትግራይ ህዝብ ደንታ የሌለው መሆኑን አሁንም በተግባር እያስመሰከረ ይገኛል።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 19/2013