ሃገራት በአትሌቲክስ ስፖርት ተተኪ ትውልዶችን የሚመለከቱትና የወደፊት ውጤታቸውንም የሚመዝኑት ዕድሜን ገደብ ባደረጉ የታዳጊና ወጣት ቻምፒዮናዎች ላይ ነው፡፡ የስልጠና ሂደታቸውን ለመገምገም እንዲሁም ጥንካሬና ጉድለታቸውን ለመለየት ጠቃሚ ውድድር እንደመሆናቸውም የአዳዲስ ቻምፒዮናዎች መፈጠሪያ የሆኑ ቻምፒዮናዎች ትኩረት ይሰጣቸዋል፡፡
ከሰሞኑም ለአምስት ቀናት ያህል በኬንያ አስተናጋጅነት ካሳራኒ ስታዲየም ሲካሄድ የቆየው የዓለም ከ20 ዓመት በታች የአትሌቲክስ ቻምፒዮና ተጠናቆ ሉኡካኑ ወደየሃገራቸው በመመለስ ላይ ይገኛሉ፡፡ በቀጣይ ተረኛ አስተናጋጅ የሆነችው ኮሎምቢያም የአዘጋጅነት ሃላፊነቱን በይፋ ተረክባለች፡፡
በኮቪድ 19 ምክንያት ለአንድ ዓመት የተራዘመው ቻምፒዮናው፤ ወረርሽኙ ከዓለም ላይ ባይጠፋም በከፍተኛ ጥንቃቄ ሊካሄድ ችሏል፡፡ ይህንን አስመልክቶም የዓለም አትሌቲክስ ፕሬዚዳንት ሰባስቲያን ኮ ለውድድሩ አዘጋጆች በአጠቃላይ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡ ስኬታማ ቻምፒዮና መካሄዱን የጠቀሱት ፕሬዚዳንቱ፤ ወጣት ተወዳዳሪዎቹ ባሳዩት ብቃትና ችሎታ መደነቃቸውንም ገልጸዋል፡፡
ከሶስት ዓመታት በፊት የቻምፒዮናው አዘጋጅ በነበረችው ቴምፔሬ ተስፋቸውን ያሳዩ አትሌቶች በቅርቡ በተጠናቀቀው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ላይ ተሳትፈው ውጤታማነታቸውን ማስመስከራቸውም ይህ ውድድር ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ያሳየ ነው፡፡ በናይሮቢ የታዩት ወጣቶች ደግሞ እአአ በ2024 በሚካሄደው የፓሪስ ኦሊምፒክ ቻምፒዮን የመሆን ተስፋቸው የሰፋ እንደሚሆንም ፕሬዚዳንቱ አብራርተዋል፡፡
በቻምፒዮናው አዘጋጇ ኬንያ በሜዳሊያ ብዛት በሰንጠረዡ ቀዳሚው ስፍራ ላይ ተቀምጣለች፡፡ ምስራቅ አፍሪካዊቷ የአትሌቶች ሃገር የበላይነቱን የያዘችው 8 የወርቅ፣ 1 የብር እና 7 የነሃስ በጥቅሉ 16 ሜዳሊያዎችን በማስመዝገብም ነው፡፡ ሁለተኛውን ስፍራ የያዘችው ፊንላንድ ደግሞ፤ 4 የወርቅና 1 የብር በድምሩ 5 ሜዳሊያዎችን አግኝታለች፡፡ ሌላኛዋ አፍሪካዊት ሃገር ናይጄሪያ በበኩሏ 4 ወርቅ እና 3 ነሃስ በአጠቃላይ 7 ሜዳሊያዎችን ወስዳለች፡፡
በሰበሰበቻቸው ሜዳሊያዎች ብዛት ኬንያን የምትከተለው ነገር ግን ባላት የወርቅ ሜዳሊያ ቁጥር በሰንጠረዡ አራተኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠችው ደግሞ ኢትዮጵያ ናት፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን 3 የወርቅ፣ 7 የብር እና 2 የነሃስ በጠቅላላው 12 ሜዳሊያዎችን አስመዝግቧል፡፡
ቻምፒዮናውን በጥሩ ውጤት ያጠናቀቀው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንም ወደ ሃገሩ ትናንት የተመለሰ ሲሆን፤ ቡድኑ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባላት በአበባ ጉንጉን አቀባበል እንዳደረጉላቸው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን በድረገጹ አስነብቧል፡፡
ስኬታማ እንደሆነ በተነገረለት በዚህ ቻምፒዮና፤ ከ20 ዓመት በታች 4 የዓለም ክብረወሰኖች የተመዘገቡ ሲሆን፤ 15 የቻምፒዮናው ክብረወሰኖች እንዲሁም 11 አካባቢያዊ ክብረወሰኖች መሻሻላቸውንም የዓለም አትሌቲክስ በድረገጹ አረጋግጧል፡፡ 259 የሚሆኑት አትሌቶች ደግሞ በየርቀታቸው የግል ፈጣን ሰዓታቸውን ለማስመዝገብ ችለዋል፡፡ 100 ሃገራት አትሌቶቻቸውን ባሳተፉበት በዚህ ቻምፒዮና 35 ቡድኖች ሜዳሊያ ሰንጠረዡ ውስጥ ሲካተቱ፤ 18 የሚሆኑት ደግሞ የወርቅ ሜዳሊያ አሸናፊዎች ለመሆን ችለዋል፡፡ ናሚቢያ እና እስራኤል በዚህ ቻምፒዮና የመጀመሪያ የወርቅ ሜዳሊያ በማግኘትም አዲስ ታሪክ ጽፈዋል፡፡
ሁለተኛውን በርካታ ሜዳሊያዎች ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን በበኩሉ፤ የቻምፒዮናውን አንድ ክብረወሰን በማሻሻል ተጠቅሷል፡፡ ይኸውም የወርቅ ሜዳሊያ ከተመዘገበባቸው ርቀቶች መካከል አንዱ በሆነው 3ሺ ሜትር የድሉ ባለቤት አትሌት ታደሰ ወርቁ የገባበት 1:43.76 የሆነ ሰዓት ነው፡፡ አትሌቱ ርቀቱን በማክረር ተወዳዳሪዎቹን በሰፊ ልዩነት በመምራት ማሸነፉ በቀጣይ የርቀቱ ምርጥ አትሌት እንደሚሆን ማሳያም ነው፡፡
ሁለተኛውን የወርቅ ሜዳሊያ ደግሞ በ800 ሜትር ሴቶች አትሌት አያል ዳኛቸው በ2:02.96 በመግባት አስመዝግባለች፡፡ ሌላኛው የወርቅ ሜዳሊያ በሴቶች 5ሺ ሜትር የተመዘገበ ሲሆን፤ አትሌት ሚዛን አለም በ16:05.61 በሆነ ሰዓት በማስመዝገብ ቀዳሚ ሆናለች፡፡
በዚሁ ርቀት የቡድን አጋሯን ተከትላ በመግባት የብር ሜዳሊያ ባለቤት የሆነችው ደግሞ አትሌት መልክናት ውዱ ናት፡፡ በ3ሺ ሜትር የግሏን ምርጥ ሰዓት በማስመዝገብ የነሃስ ሜዳሊያ ያጠለቀችው አትሌቷ፤ በተካፈለችበት ሌላኛው ርቀት የ5ሺ ሜትር ማጣሪያ ሁለተኛ ደረጃን በመያዝ ብታጠናቅቅም በቴክኒካዊ ችግር ከውድድር ውጪ እንድትሆን ተደርጋ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ቡድኑ ያሰማው ቅሬታ ተቀባይነት አግኝቶ አትሌቷ እንድትሳተፍ በመደረጓ ሜዳሊያውን የግሏ ለማድረግ ችላለች፡፡ የተቀሩት ሜዳሊያዎችም በወንዶችና ሴቶች 1ሺ500 ሜትር ሁለት የብር እና አንድ የነሃስ፣ 3ሺ ሜትር ሁለት ብርና ነሃስ፣ በ5ሺ ሜትር ሁለት ብር እንዲሁም አንድ ብር በ3ሺ ሜትር መሰናክል ወንዶች የተገኘ ነው፡፡
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18/2013