ከአንዳንድ ጉዳዮች እንጀምር፤ በተለይም ከቀዳሚዎቹ ተነስተን ወደ አሁኖቹ እንምጣ። በዚህም የሥነጽሑፋችንን፤ በተለይም የሥነግጥማችንን ላይ/ታች ጉዞ እንመልከት።
በርእሳችን “አሁናዊ ይዞታ” ስንል “ኮንቴምፖራሪ” ማለታችን መሆኑን፤ “ከመቼ ጀምሮ” የሚለውን ለጊዜው በ”ታሳቢ” አልፈነው፤ ካስፈለገም ድህረ 1983 ዓ.ም ብለነው ማለፍ የሚቻል መሆኑን ገልፀን ወደ ጉዳያችን እንሂድ።
እጓለ ዮሀንስ ግጥምን፣ ገጣሚንና ቅኔን በተመለከተ በ”የከፍተኛ ትምህርት ዘይቤ”ያቸው ላይ “የፍልስፍና ሕዝባዊ አቀራረብ ግጥም ይባላል”፤ “ቅኔ […] ምስጢር የተሞላ የረቀቀ ፍልስፍና የተከማቸበት”፤ “ባለቅኔውም ሰሚውም በህሊና ርቀት የተራመዱ” መሆናቸውን አስነብበውናል።
ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን “ሥነግጥም የሥነጽሑፍ ሁሉ፤ የፈጠራ ሁሉ የደም ጠብታ ነው።” በማለት የግጥምን ከፍታና የገጣሚነትን ከባድ ሀላፊነት ሲገልፅ ሰይፈ መታፈሪያ ፍሬው በበኩሉ የግጥም ጉዳይ በአገኝ አጣሁ የሚሆን አለመሆኑንና መጣርና መጋርን የሚፈልግ መሆኑን “መዝ ላጥ ዋጥ አይደለም” ሲል ይገልፀዋል።
ገና በ1961 ዓ.ም “የልብ ወለድ ሥነጽሑፍ ጉዞ” በሚል ርእስ ለንባብ ባበቃው ጥናቱ “ሥነ ጽሑፍ የሰው ሐሳብና ስሜት በኪነት ኃይል ግዘፍ ነሥቶ አካል ገዝቶ የሚታይበት ጥበብ ነው። የአማናዊ ሥነጽሑፍም ምንጭ የሰው ልጅ እውነታ ሬያሊቲ ነው። እውነታውም በልደትና በሞት መካከል የተዘረጋው ህላዌ ነው።” ሲል ሥነጽሑፍን ከበየነውና “ከ1933 እስከ 1960 ድረስ ስላለው የአማርኛ ሥነጽሑፍ ጉዞ አንዳንድ ነገር ለማውሳት እወዳለሁ።” በማለት ሂሳዊ ምዘናውን ለታሪክ ያኖረው ዮሀንስ አድማሱ፤
“በጠቅላላው በነዚህ በሀያ ሰባት ዓመታት ውስጥ አማርኛ ያፈራው ሥነጽሑፍ ብዛት እንጂ ጥራት የለውም። ከጥልቀት ይልቅ ግልብነት፥ ከውበት ይልቅ አስቀያሚነት፣ አስቀያሚነት ውበት ነው ወይም ውበት አለው ካልተባለ በቀር፥ ከሥነ ጽሑፋዊ ዕውነት ይልቅ የአንቀፀ ብጹዓን ምኞት ይገኝበታል። ሥነጽሑፍ የሕይወት ኂስ በመሆን ፈንታ የወሸነኔ ስሜት መግለጫ ሆኗል። እስካሁን ድረስ አካሄዱ አጉል ነው፤ የጎድን ነው። አቅጣጫ ያለው አይመስልም። የወደፊት አካሄዱን መተንበይ ባይቻልም እስካሁን ድረስ ተመልክተን በተገነዘብነው አካሄድ ለወደፊት አካሄድ አብነት የሚሆን አይደለም። በአጭሩ በሀያሰባት ዓመታት ዕድሜ ውስጥ ያፈራነው የአማርኛ ሥነጽሑፍ ከአዝመራው ጋር ሲነፃፀር ደረጃው፥ ጥራቱና አስደሳችነቱ አለመጠን ዝቅ ያለ ነው። እያደር ይጫጫል፤ እየሰነበተ ይደገድጋል፤ እየባጀም፥ እየከረመም ይመነምናል። ለዚህ አሳዛኝ፥ ከቶም ድቀታዊ ሁነት ምክንያት ከሆኑት ከብዙዎቹ ነገሮች ሦስቱን ጠቅሼ ከመዘርዘሬ አስቀድሜ ጥራት፥ ወጥነት፥ ጥልቀትና ውበት ያላቸው ሁለት መጻሕፍት መጥቀስ እወዳለሁ።” ካለ በኋላ እነዚህን ሁለት መፃህፍትም ‘እንደወጣች ቀረች’ና ‘ፍቅር እስከ መቃብር’” መሆናቸውን ይገልፃል። “አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ወልደ አባ ተክሌ፥ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ፥ ዮፍታሔ ንጉሤ፥ ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ፥ አለቃ ታዬ፥ ወዘተ…” ደራሲያንንም በኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ውስጥ “አብነት” መሆናቸውን ያረጋግጣል።
ዮሀንስ በዚህ ጽሁፉ በርካታ ከጊዜው ቀደሙ አስተያየቶችን የሰጠ ሲሆን በተለይ ከሀላፊነት አኳያ “ቴክኒክ ማወቅ የማንኛውም ደራሲ፥ በተለይም የገጣሚ ተግባርና ግዴታ ነው።” በማለት ያስቀመጠው ዛሬም፣ ወደፊትም ሳይጠቀስ የሚታለፍ አይደለም።
ዮሀንስ አድማሱ ይህን ያለው ለውጥ ለማምጣት ነበር ግን ያ ሊሆን አልቻለም። በ12/11/2001 ዓ/ም በኢትዮጵያ ቴቪ መዝናኛ ፕሮግራም (እሁድ ከ9:30 ጀምሮ)፣ ሙዚቀኞች፣ ገጣሚያን፣ አቀናባሪዎችና ጉዳዩ ቀጥታ የሚመለከታቸው በተሳተፉበት “የዘመናችን መዚቃና ግጥም”ን አጠቃላይ ይዞታ የተመለከተ ውይይትን፤ እንዲሁም ደራሲና ጋዜጠኛ ደምሴ ጽጌ በ”ቁም ነገር” (ቅ.7፣ ቁ.18) ላይ የሰጠውን ሂስ አጠቃለን ስንመለከት “የዘመኑ ስራዎች ድግግሞሽ ይበዛባቸዋል፤ ድምፃዊያንም ሆኑ ገጣሚያን የድሮውን መገልበጥ ይቀላቸዋል፣ ስራዎቹ ብዛት እንጂ ጥራት የላቸውም፤ “አይዶል” የሚባለውም ቢሆን አስተምህሮቱ መገልበጥ ነው፤ ግጥሞቹም ሆኑ ዜማዎቹ የኢትዮጵያዊነት ስሜት የላቸውም፤ የአገራችን ታሪክ ተረስቷል፤ ጆሮ ገብ አይደሉም፤ ስራዎቹ የሚጠበቅባቸው ረቂቅነት፣ የውበት ነገር ጭራሽ የላቸውም፣ ጊዜያዊ እንጂ ርቀት መጓዝ የሚችሉ አይደሉም፤ የመንፈስ ድህነት ይታይባቸዋል፤ ከድሮዎቹ ጋ እንኳን ሊወዳደሩ አጠገባቸው እንኳን የሚደርስ የለም፤ የግጥምና ይዘት ችግር አንቆ ይዟቸዋል፤ ግማሹ ከህንድ፣ ግማሹ ከአውሮፓ፣ ግማሹ … እየመጣ እዚህ የሚገጣጠም ዜማና ግጥም ነው ያለው፤ ማንነት የላቸውም ክልሶች ናቸው …
… ሁሉም አንድ አይነት ዘፈን/ዜማ መዝፈን ደረጃ ላይ ደርሰዋል፤ በአንድ ጉዳይ ላይ ይረባረባሉ፤ በአንድ ሰው ፈጠራ ላይ የተንጠለጠሉ ናቸው፤ ኢትዮጵያዊው የሙዚቃ ቅኝት ዘሩ ጠፍቷል፤ ርእይ የላቸውም የተደበላለቀ ነገር ነው የሚሰማው፣ የሚታየውም፤ አሁን ያሉት፣ እየተመረቱ የሚቸበቸቡት፣ በየቀኑ “ነጠላ”፣ ድርብ እየተባ(ባ)ሉ የሚያጮሁት … ለመጪዎቹ የሙዚቃ፤ በአጠቃላይም የጥበብ ጠንቆች ናቸው፤ አብዛኞቹ ጭብጨባ የሚነዳቸውና ገበያ ተኮር ናቸው።
(ይህ ጽሑፍ “በሙዚቃ ስራ ውስጥ ዋናው ጉዳይ መልእክቱ ሳይሆን ቅንብሩ ነው” ከሚሉት የአገራችን ዋና ዋና የሙዚቃ ሀያሲያን ጋር እንደማይስማማ ይታወቃል። ለዚህ ደግሞ የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ “በሙዚቃ ስራ ውስጥ ዋናው ጉዳይ ቅንብሩ ሳይሆን መልእክቱ ነው” የሚል ፍፁም ተቃራኒ ሀሳብ ስለሚይዝ ነው። በመሆኑም፣ ከዚሁ አቋሙ በመነሳት በሙዚቃ ስራዎቻችን ውስጥ ግጥሙ (ሞቻቸው) ላይ በማተኮር አስተያየታችንን እንቀጥላለን።)
ከግጥም ስራዎች ጋር በተያያዘ እጅግ እየዘገየም ቢሆን ሞቅ ያሉ ውይይቶች መካሄዳቸው አልቀረም። ከእነዚህም መካከል አንዱ በደራሲያን ማህበር አማካኝነት የሚካሄደው ሲሆን፤ በጌታቸው በለጠ አስተዳደር ዘመን የተካሄደውና “ከሁሉም” የኪነጥበብ ዘርፎች በሚባል ደረጃ የተሳተፉበት፤ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡበት፣ የሶስት ትውልዶችን ስራዎች የመረመረና ሥነግጥማችን እየወረደ መምጣቱ የተመለከተበት መድረክ አንዱና ተጠቃሽ ነው። በጥናቶቹ እንደተመለከትነው ከሆነ የአሁኑ ዘመን ግጥሞች ጠዋት ተመርቶ ማታ መርካቶ እንዲሉ “ፋስት ፉድ ናቸው”፤ ዘላቂነት የላቸውም።
ደምሴ “ሥነጽሑፋችንን ከየት የወረደ ዳፍንት ነው አፍኖ የያዘው?” በሚል ርእስ በሰጠው ሂስ የዘመኑን ግጥምና ገጣሚያን እንደሚከተለው ይሸነቁጣቸዋል፤
ሥነጽሑፋችን በተለይም ስነግጥማችን ቀጭጯል፣ ደቋል፣ ተጨባጭ የጥበብ ወለላ የለውም፣ ህትመታቸው አንሶ አንሶ 200 ጠርዝ ላይ ደርሷል፤ ለመሸጥ አልቻሉም፣ በቁጥር እንጂ በጥበብ ወድቀዋል፤ ማንነት የላቸውም፤ አብዛኞቹ የቃላት ክምር (ድድር) እንጂ ግጥም ሊያሰኝ የሚችል ብቃት የላቸውም። የሚነግሩን አዲስ ነገር፣ የሚያሳዩን ውበት የላቸውም፤ የሚነበብ አይደሉም፣ ቢነበቡም የመታወስ ብቃት የላቸውም። ድንቅነታቸው በደራሲዎቻቸውና ለውሸታም አድናቂዎቻቸው ብቻ ነው …. (እያለ ይቀጥላል)።
ገጣሚያኑን በተመለከተም፤ “አያነቡም [ዮሀንስም በ1961 “ደራስያኑ የሚያነቡ አይመስልም።” ማለቱን ልብ ይሏል]፣ አይመራመሩም፣ ቀደምት ስራዎችን አይፈትሹም፣ የእለት ተእለት ገጠመኞቻቸውን ገልባጮች ናቸው። እርስ በርስ ይገለባበጣሉ፤ [ይዘራረፋሉም]። የውጪ ስራዎችን አያነቡም፤ ያለማንበብ ደዌ ተጠናውቷቸዋል። የንባብ ጉድለት የጥበብ ጉድለት እንደሚያስከትል አያውቁም ….”። መፍትሄውም እነዚህን ማሻሻል መሆኑን በአፅንኦት ያሳስባል።
ሌላው “ሁለት የታወቁ የአማርኛ የግጥም ደራስያን (ተስፋዬ ገሠሠና በዕውቀቱ ሥዩም) ለአንድ የዑመር ኻያም ግጥም በየፊናቸው የሰጡትን ትርጉም ወይም ዕይታቸውን ላካፍላችሁ፡፡” በማለት አስተያየታቸውን የሚሰጡትና የሁለት ዘመን (ትውልድ) አባላት ገጣሚያንን የሚያነፃፅሩት ፕሮፌሰር ሽብሩ ተድላ ሲሆኑ ናቸው።
ፕሮፌሰሩ “ወጣት የአማርኛ ደራስያን (ገጣሚዎች) በርክተዋል፣ ብዙ ናቸው፤ የባህላችንም አለኝታዎች ናቸው፣ እኛ በርቱ እንበላቸው፣ ማበረታታቱ በተለይ የዕድሜ ባለፀጋዎች ኃላፊነት ነው ብዬ እገምታለሁ፡፡ ከዚህ አንፃር ታይታ፣ ይች የእኔ ጽሑፍ ለወጣት ደራስያን እንደ ማበረታቻ ትወሰድልኝ፣ ስለግጥም መወያየት ባህል ተንኳሽ ትሁንልኝ፡፡” በማለት በአክብሮትና ትህትና በምላጭ የመግፈፍ ያህል የሰላ ሂሳቸውን ይሰነዝራሉ።
“ግጥም አጠር፣ መጠን ባለ መጠን የተለያዩ ትርጉሞችን ለመስጠት ያመቻል፤ በጣም ዝርዝር ከሆነ፣ ሌላ ፍች አያስፈልገውም ይሆናል፡፡ ምንም እንኳን ‘ግጥም’ ‘የሥዕልን’ ያህል የተለያዩ ትርጉሞችን ለመስጠት ዕድልን ባያበርክትም፣ የምርጥ አጭር ግጥም፣ ፍችው (ትርጉሙ) የሚያበርክተው የጥበቷ ተቃራኒ ነው፣ ትርጉሙ መጠነ ብዙ ሊሆን ይችላል፡፡ በውስን ቃላት የተዋቀረ፣ ነጥሮ የወጣ፣ ብዙ ትርጉም ያለው ሲሆን፣ በአንፃሩ ያለ የሌለውን ማዕድ አድርጎ ያቀረበ ግጥም ግልብ ይሆናል፡፡ የዑመር ግጥሞች በአራት መስመሮች ነው የሚቋጩ፤ ስለሆነም ውብም፣ ፍልስፍና አዘልም ናቸው፡፡ እያንዳንዱ ትርጉመ ብዙ ሊሆንም ይችላል፡፡” ካሉን በኋላ ተስፋዬ ገሠሠ “መልክአ ዑመር”፤ በዕውቀቱ ሥዩም በበኩሉ “የማለዳ ድባብ” በሚሉ ርእሶች የተረጎሟትን (ከፐርሽያን (ፋርስ) ቋንቋ በኤድዋርድ ፊትዝጀራልድ ወደ እንግሊዝኛ የተቀለበሰው) ግጥም አርኬ (ሩባያት) እንካችሁ ይሉናል።
Here with a loaf of bread beneath the Bough,
A Flak of wine, a Book of Verse-and Thou
Beside me singing in the Wilderness
And Wilderness is Paradise enow.
የሚለውን ግጥም ምን ያህል በተራራቀ መልኩ እንደተረጎሙት፤ ይህም ምናልባት በሁለቱ ገጣሚያን መካከል ያለው የእድሜ ልዩነት (40 አመት) ያመጣው ጣጣ ሊሆን እንደሚችል በማብራራት ያላየናቸውን እንድናይ አድርገውናል።
ሌላው እጥር ምጥን ያለና ደፋር አስተያየት የምናገኘው ከፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም የ”ፍትህ” ጋዜጣ አምድ ሲሆን፤ እሱም በአሁኑ ዘመን የብዕር ብልግና በዝቷል። ላደባባይ መብቃት የሌለባቸው ሁሉ እየበቁ ነው። የዚህ ሁሉ ምክንያቱ ደግሞ የጎበዝ ሃያሲ አለመኖር ነው የሚለው ነው። ባጭሩ ባለጌ ብእሮች በዝተዋል፤ አራሚ፣ አቃኝ፣ መካሪና አቅጣጫ አሳይ ናቸው ተብለው የሚገመቱት ሃያሲያን ሽታቸውም የለም ነው ፕሮፌሰሩ እያሉን ያሉት።
“አየህ ሼክስፒር ለእንግሊዝ ትልቅ ቅርስ ነው። እንደ ትልቅነቱም ቅርሱ እንዳይበላሽ በመንግሥት ደረጃ ይጠበቃል። የሼክስፒር ሥራዎች ሌላ ሀገር በመድረክ ላይ ሲቀርቡ በትክክል ካልተሰሩ፣ ባህሉን አቃውሰው ካሳዩ፣ ዝግጅታቸው ጥሩ ካልሆነ፣ ጉዳዩ በአምባሳደሩ ደረጃ ተመክሮበት ነገሩ እንዲስተካከል ተብሎ ‘እርዳታ እናድርግላችሁ’ ብለው እንግሊዞች ይጠይቃሉ። ይኽም የሚሆንበት ምክንያት የሼክስፒር ሥራዎች የእንግሊዝን ታሪክና ባህል ስለሚወክሉ እንደ ቅርስ ተቆጥረው ነው። የሚለውን ከፈረሱ አፍ ሰምተው ከከተቡት አንብበናል። ልክ እንደ እንግሊዝ ኢትዮጵያስ እንዲህ አይነት ገጣሚ አያስፈልጋት ይሆን?? ሥነጽሑፋችንስ ደምሴ ከሚለው ዳፍንት ውስጥ ወጥቶ ከእንደነዚህ አይነቶቹ ተርታ ተሰልፎ የምናየው መቼ ነው? ይህንን ስንመኝ ለደራሲ/ገጣሚዎቻችን ብለን ሳይሆን ለራሳችን ብለን መሆኑ ሊታወቅልን ይገባል።
እርግጥ ነው፣ በዚህ ባለንበት ዘመን ሥነጽሑፍ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ “ፈጠራ ሞቷል” የሚሉ አስተያየቶች በአለም ዙሪያ በብዛት የሚሰሙበት ዘመን ነው። በአሁኑ ዘመን ሼክስፒርን የመሰለ ገጣሚና ባለቅኔ የሚጠብቅ ካለ እሱ እውነትም ምስኪን ሰው ነው፤ ፒካሶን፣ ዋልተን፣ ማርክ ትዌን ወዘተ የሚጠብቁ ካሉ እነሱ እውነትም የተባረኩ ናቸው። እዚህም ከበደን፣ ፀጋዬን፣ ጥላሁንን፣ መሀሙድን፣ ዮሀንስን፣ ገብረ ክርስቶስን ወዘተ የሚጠብቁ ካሉ እውነት እውነት እላችኋለሁ እነሱ ብፁአን ናቸው።
የዘመኑ ግጥም በ”ባጃጅ” (የቀንድ አውጣ ኑሮ) ትራንስፖርት ወደ የውድቀት ቁልቁለት የሚኬድበት (ስለሺ ደምሴ በአንድ ወቅት እንዳለው የጥበብ ዘርፉ የስነምግባር ግድፈት ሁሉ የሚፈፀምበት ሆኗል)፣ በ”አዳምና ሚስቱ” (ኗሪ አልባ ጎጆዎች)፣ በ”ንድፍ” (ዙረት)፣ “አልይሽ አትይኝ” (እውቀትን ፍለጋ) የጀንደር ጦርነት የሚታወጅበት፣ በ”ወ” (በቴቪ የተነበበ) ስር ተወሽቆ/ተደብቆ እዬዬ የሚባልበት፣ የዜማና ድምፆች፤ ቴክኒክና ስታየል ወዘተ ጉዳይ ምንዛሪው “ብሄር”፤ ዘር፣ “ቀለም፣ ኃይማኖት፣ ፆታ …” ሳንለይ የሚለው የቂል በሆነበት በዚህ ዘመን ከላይ የጠቀስናቸውንና የእነሱን ዘመኖች የሚጠብቅ ካለ እውነትም ለምን ብፁእ አይሆን?
በምድር ላይ እያየነው ያለነው በፈጠራ ስራ(ዎች) ውስጥም ሆነ በስራ(ዎች) ወቅት ለቋንቋና አጠቃቀሙ መጨነቅና መጠበብ የቀረበት፣ ዘመን ተሻጋሪ ስራን ማግኘት ከማእድን ፍለጋ የጎደጎደበት፣ ቋንቋን መደበላለቅና ያለ አውዱ ማደበላለቅ ፋሽን የሆነበት፤ የዜማና ግጥም ህብራቸው የጠፋበት፤ የአንድ ሰው የኮምፒውተር ቅንብር አጀብ የሚባልበት፣ ጥበብ በ”ከተፋ” ሙያ በሰለጠኑ ባለሙያዎች የምትከፈትበት፤ ጥበብ በአይዶሎች አይድል የሆነችበት ወዘተረፈ ዘርዝረን በማንጨርሰው አዘቅት ውስጥ መሆኗን ነው። ይህ ደግሞ ውድቀት ነው። የጀርመኑ ጎት እንደሚለው ከሆነ የሥነጽሑፍ መውደቅ የማህበረሰቡ (እሱ “ኔሽን” ነው ያለው) መውደቅ በመሆኑ ከዚህ ዳፍን ውስጥ በፍጥነት መውጣትን ግድ ይላል።
በፈጠራ፣ በተለይም በሥነጽሑፉ ዘውግ፣ በተለይ በተለይ የሙዚቃው አካባቢ ምን ያህል በድርቅ እንደተመታ ለማሳየት ያህል ከላይ ያለውን እንበል እንጂ፤ ድርቁን “ፐፐፐ …” በማለት ለማለምለም የሚሞክሩ፤ ከኤፍኤም አካባቢያዊ ጣቢያዎች እስከ አነስተኛና ጥቃቅን መድረኮች፣ ከማህበራዊ ድረ-ገፆች እስከ በብእር ሥም የራስን ስራ እስከማንቆለጳጰስ የዘለቀ የጋዜጣና መጽሔቶች ገፆች ድረስ ጩኸቱ ሌላ ነው። ጩኸቱ ከፍ ይበል፣ ያደንቁርም እንጂ መሬት ላይ ያለው እውነታ ግን ዝም ተብሎ በ”ሪያሊዝም” የሚታለፍ፣ በ”ናቹራሊዝም” የሚፈታ ጉዳይ አይደለም። በጩኸት ላንግስህ ቢሉትም አይሆንም።
ዘመኑ፣ አንዳንድ የቀድሞ ትውልድ አባላት ባይኖሩና ምሰሶ ሆነው ባያቆሙት፣ በእውነት ቆሞ ስለመሄዱ እርግጠኛ መሆን ይቸግራል።
በመጨረሻም፣ እንደሚታወቀው ጥበብ ማእከሏ ሰው ነው። በመሆኑም ነው “ከሰው ለሰው ….” የሚባለው። በመሆኑም በሰው ልጅ ላይ የሚፈፀም ማንኛውም ኢፍትሀዊ ተግባርም ሆነ በአገርና ወገን ላይ የሚደርስ መከራ ለኪነጥበብ ህብስተ መና ከሰማይ እንደወረደላት ነው የሚቆጠረው። ከዚህ አንፃር አሁን ያለንበት እውነታ፣ የኢትዮጵያን “አፈርሳለሁ” እና “አታፈርስም” ግብግብ፤ የህልውና ስጋት ወዘተ ለፈጠራ ሰዎች ግዙፍ ግብአት (ልክ እንደ ጥላሁን “ዋይ ዋይ ሲሉ”፣ እንደ ፀጋዬና ጂጂ “አድዋ” …) ነውና ወደፊት፣ እየተካሄደብን ያለውን የውክልና ጦርነት ጭምር ከማጋለጥና ለታሪክ ከማስቀረት (በዚህ በኩል አዝማሪዎች አሁኑኑ የተሳካላቸው ይመስላል፤ ምክንያቱም እያሰሙን ያሉት ዜማና ግጥሞች ወቅቱን ከመግለፅና ባንዳዎችን ከማጋለጥም በላይና ኢትዮጵያዊነትን ከማፅናት አኳያ እያደረጉት ያለው ተግባር እዚህ ሊጠቀስ የሚችል ነውጥ)፣ የተዋጣላቸው ስራዎችን እናነባለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን።
ግርማ መንግሥቴ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18/2013