አሸባሪው ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ ሲያሻው በሰብዓዊ ጋሻነት ፤ ለመደራደሪያነት በማገት፤ ሌላ ጊዜ ነፍስ የማያውቁ ብላቴናዎቹን ከጉያው እየነጠለ በሕዝባዊ ማዕበል በጦርነት በመማገድ፤ በስሙ የሚላክለትን እርዳታ በመሸጥና ለፖለቲካዊ ጥቅም ሲል እንዳይደርሰው መንገድ በመዝጋትና ድልድይ በማፍረስ በርሀብ እንደ ቅጠል እንዲረግፍ በማድረግ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸመበት ይገኛል። የዚህ የሽብር ቡድን የኋላ ታሪኩ ሲፈተሽ በዘር ማጥፋት ወንጀል የተካነና በርካታ ማንነቶችን ኢላማ ያደረገ ሆኖ እናገኘዋለን ። ለዚህ ነው አሸባሪው ሕወሓት ለአገዛዝ የበቃውም ሆነ ለ27 አመታት በኢትዮጵያ፤ ከለውጡ ወዲህም ከሶስት አመታት በላይ በትግራይ በመንበሩ የቆየው ፤ ሰሞነኛው የአማራና የአፋር ክልሎች የወረረው ዘር በማጥፋትና ዘር በማጽዳት የከረመ ልምምዱ እየተመራ ነው። የሜሪያም ዌቢስተር የእንግሊዘኛ መዝገበ ቃላት ዘር ማጥፋትን/Genocide/እንዲህ በስሱ ይበይነዋል። “the deliberate and systematic destruction of a racial, political, or cultural group .”ወደ አማርኛ ሲመለስ፦ሆን ብሎ ዘይዶ ዘርን የፖለቲካ ወይም የባህል ቡድን ወይም ስብስብ ማጥፋት።”ይላል። በዚህ ብያኔ ብቻ እንኳ በትግራዋይ በወልቃይት በአማራና በራያ ላይ እንዲሁም በኦርቶዶክሳውያን እና በእነ ኢዲዩና ኢህአፓ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል ማለት ይቻላል። እንግዲህ ሕወሓት በ1968 ዓም ማንፌስቶው አማራንና የኦርቶዶክስ ተዋህዶን በግልጽ በጠላትነት ፈርጆ መንቀሳቀስ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በአማራ በኦርቶዶክሳውያንና በተከታዮቿ ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል። ቤተ ክርስቲያኗ በትግራይ የነበራትን ማህበራዊ ልዕልና እንድታጣ ሆን ብሎ በቁሟ አፍርሷታል። ቤተ መቅደሷን የጦር መሳሪያ ማከማቻና ምሽግ፤ አጸዷን የመሳሪያና የብር መቅበሪያ ያደረገው፤ አገልጋዮቿንና ልጆቿን ካድሬ አንጋችና የሸፍጡ ግንባር ቀደም ተዋናይና ተባባሪ ማድረግ የተሳካለት መጀመሪያ ስላፈረሳት ነው ።
በትጥቅ ትግሉ ወቅት የኢዲዩ ደጋፊና አባል ናቸው ያላቸውን ከ40ሺህ በላይ ትግራዋይን ለዛውም ነቃ ያሉ አርሶ አደሮችንና ልሒቃን ወይም የማህበረሰቡ አስኳልና የማዕዘን ራስ የነበሩትን በግፍ ገድሏል። ይህን ያደረገው ርዕዮተ አለሙና የፓርቲው ፕሮግራም ያለተቀናቃኝ ብቸኛ ገዥ ሀሳብ ሆኖ እንዲወጣ ነው። ዛሬም በተግባር እየሆነ ያለው ይሄው ነው። ሕወሓት ወደ ጣኦትነት የተቀየረው እንዲህ ባለ ቅየዳ ነው። በ17 አመቱ የትጥቅ ትግል ከ60ሺህ በላይ የትግራይ ወጣቶች በከንቱ ከመሰዋታቸው ባሻገር ቁጥራቸው ከዚህ የማይተናነስ አካል ጉዳተኛ በማድረግ ትግራዋይ እናቶችን የወላድ መካንና ጧሪ ደጋፊ አልባ አድርጓል። ደም ምሱ የሆነው ይህ አሸባሪ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ወቅት በተከተለው የተሳሳተ የውጊያ ስልት ከ70ሺህ በላይ ወጣቶችን አስጨርሷል። ይሄን ወጣት ያስጨረሱትን የሕወሓት ጄኔራሎች ነው እንግዲህ እነ ማርቲን ፕላውትና ቢቢሲ የጦር ስትራቴጂስት እያለ የሚያንቆለጳጵሳቸው። በጦርነቱ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሩጠው ያልጠገቡ ወጣቶችን አካል ጉዳተኛ አድርጎ፤ በብዙ ቢሊዮኖች የሚቆጠር የሀገር አንጡራ ሀብት አውድሞ ለሰላም ስምምነት አልጀርስ ሲገኝ ግን የቀደመው አልነበርም። ይህ አልበቃ ብሎት የድንበር ግልግሉ ፍርድ ቤት ባድመን ለኤርትራ ወስኖ እያለ ለኢትዮጵያ ተወሰነ በማለት በሰማዕታቱ አጽም ተሳልቋል። ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላም ያ ለሀገሩ የዘመተና መስዋዕት የከፈለ ወጣት ፍትሕን እኩልነት ነጻነትንና ዴሞክራሲን ሲጠይቅ አደገኛ ቦዘኔ ብሎ ከመፈረጅ አልፎ በ97 ምርጫ በመለስ ትዕዛዝ በአንድ ቀን በአግአዚ ልዩ ኃይል ከ200 በላይ የአዲስ አበባ ወጣቶችን በጭካኔ ጨፍጭፏል ።
ገና ከምስረታው እንደሱ የደርግን ወታደራዊ አገዛዝ ለመታገል ጫካ የገቡትን ኢህአፓ፣ ኢዲዩና የትግራይ የፖለቲካ ድርጅቶችን እንደራደር፣ ልዩነታችንን በውይይት እንፍታ እያለ እያግባባ እውነት መስሏቸው ለውይይት ሲመጡ አንድ በአንድ የጨረሰ አረመኔና የዘር አጥፊ ስብስብ ነው። እነ ስሁልን፣ ሙሴን፣ ዩሐንስ ገ/መድህን/ዋልታ/ ሀየሎምንና ሌሎቹ በሀሳብ የተለዩትን እልፍ አእላፍ ታጋዮችንና ልጆቹን እንደ ድመት የበላ፤ በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም በሰሜን እዝ፣ በመከላከያ ሰራዊታችን ላይ ዘግናኝ ጭፍጨፋ የፈጸመ፤ በሀገራችንና በሕዝባችን ላይ እንደፈጸመው ክህደት ከጀርባ ወግቶ ወይም በጥይት ደብድቦ በርካቶችን የገደለ ማህበረሰብንና ዘርን የጨረሰ አሪዮስ ነው። ለጊዜያዊ ፖለቲካዊ ጥቅም ሲል የሀውዜንን ሕዝብ በገበያ ቀን በአውሮፕላን አስፈጅቶ ሙሾ የሚያወርድና የአዞ እንባ የሚያነባ የሀፍረተቢሶች ስብስብ ነው። በ77 ድርቅ ለትግራይ ሕዝብ የተላከ እርዳታን ሸጦ የጦር መሳሪያ የገዛ ትግራዋይን በርሀብ የጨረሰ ለፖለቲካዊ ቁማር ምንም ከማድረግ የማይመለስ ቡድን ነው። ባለፉት 47 አመታት በክልሉ የሚገኙ እንደ ኩናማ ያሉ ህዳጣን ጎሳዎችን ዘር ያጠፋ፤ ከ1972 ዓም ጀምሮ የወልቃይት የጠገዴ አማራዎችን፤ እንዲሁም በኮረምና አላማጣ የራያዎችንና የአማራዎችን ዘር ያጸዳ፤ እስከ አንገቱ በዘር ማጥፋትና በጎሳ ማጽዳት ወንጀል የተዘፈቀ የአሸባሪዎች ስብስብ ነው።
ጥቅምት 30 ቀን 2013 ዓ.ም በማይካድራ ሳምሪ በተባለ የአሸባሪው ወጣት ገዳይ ክንፍ ዛሬ በስደተኝነት ስም በሱዳን የሚገኘው ከ1700 በላይ አማራዎችን በገጀራ በፋስ በብረት በማጭድና በጩቤ በመጨፍጨፍ የዘር ማጥፋት ወንጀል ፈጽሟል። መንግስት ለሰብዓዊነትና ለትግራይ ሕዝብ የጥሞና ጊዜ በሚል ያወጀውን የተናጥል የተኩስ አቁም እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የአማራና የአፋር ክልሎችን ዜጎችን በማንነታቸው እየገደለ እያረገፈ በጅምላ ባልታወቁ ስፍራዎች እያሰረ ሴቶችን እየደፈረ እያጋዘና እየዘረፈ ይገኛል። በግልጽ በአደባባይ ከአማራ ጋር የማወራርደው ሒሳብ አለኝ ባለው መሠረት ሒሳቡን በግፍ እያወራረደ ይገኛል። ይህ ጸረ ኢትዮጵያ የሆነ ተላላኪና አሸባሪ ቡድን በአፋር ክልል ተመሳሳይ ለማየት የሚዘገንኑ ለመስማት የሚሰቀጥጡ ጭካኔዎችን እየፈጸመ ሲሆን በተለይ በፈንቲ ረሱ ዞን ጋሊኮማ ጊዜያዊ መጠለያ በወረራው ከቀዬአቸው ተፈናቅለው ይገኙ የነበሩ 107 ህጻናትን ጨምሮ 240 ሴቶችንና አረጋውያንን በከባድ መሳሪያ በመጨፍጨፍ ጥርሱን የነቀለበትንና እንደ ልማድ የያዘውን የዘር ማጥፋት በአፋር ሕዝብ ላይ ፈጽሟል።
ከዚህ ሁሉ ወንጀሉና ግፉ በኋላ መንግስት በሕገ መንግስቱ የተጣለበትን የሀገሪቱን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ለማስከበር የሕግ የበላይነትን ለማረጋገጥና የዜጎችን በሰላም ወጥቶ የመግባት መብት ለማስከበር መንቀሳቀስ ሲጀምሩ በእብሪት ሀገር ሲወርና ሲፎክር እንዳልነበር ጅራፍ ራሱን ገርፎ ራሱ ይጮሀል እንዲሉ ተከበብሁ ተወረርሁ የትግራዋይን ዘር ሊያጠፉ ነው እያለ በቅጥረኛ አለማቀፍ ሚዲያዎች ፤ በእነ ማርቲን ፕላውት በአውሮፓና በአሜሪካ በኤርትራውያን ስደተኞች ስም በሀሰተኛ ማስረጃ የተሰገሰጉ የአሸባሪው ቤተሰብና ቅጥረኛ “ስደተኛ”፤ በተከፋይ ሎቢስቶችና ውሸት ሰላቂዎች፤ በሰብዓዊ መብት ተሟጋች ነን ባዮችና በሌሎች ባንዳዎች የድረሱልኝ እዬዬውን ያቀልጠዋል። ሰሞኑን የኢፌዲሪ መንግስት ኢትዮጵያውያን ሉዓላዊነታቸውን ለማስጠበቅና የሀገራቸውን ክብር ላለማስደፈር ቆርጠው እንዲነሱ ጥሪ ሲያቀርብ እንደተለመደው እየየው ከየአቅጣጫው እንደ ገደል ማሚቶ መስተጋባት ይጀምራል። አበክሮ ጉሮሮውን መጠራረግና መሳል ጀምሯል።
ገና ከአሁኑ የጆ ባይደን የጸጥታ አማካሪ ተኩሱ በፍጥነት ቆሞ ድርድር በአስቸኳይ ይጀመር የሚል ቀጭን ትዕዛዝ በቲዊተር አስተላልፈዋል። ሀገር በማፍረስና በመበተን ልምድ ያካበተው የፕሬዚዳንቱ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ለዚሁ ተግባር ካለፈው እሁድ ጀምሮ በዩናይትድ አረብ ኤሚሬትስ በጅቡቲና በኢትዮጵያ ለዘጠኝ ቀናት የስራ ጉብኝት ወደ አካባቢው እንደሚመጡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል። በጉብኝታቸው ጅቡቲ የተካተተችው አሸባሪው ሕወሓት የጅቡቲን መንገድ ለመዝጋት ያደረገው ሙከራ ስለከሸፈ ጅቡቲ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የወደብ አገልግሎት እንደ መያዣና መደራደሪያ ለመጠቀም አበክሮ ሴራ ተሸርቦ ስለመሆኑ ለመተንበይ ነቢይ መሆንን አይጠይቅም። በነገራችን ላይ ከ80 በመቶ በላይ የውጭ ንግዳችንን ሀሳብ በጅቡቲ ወደብ ላይ ጥለን ለሽ ማለታችን እንዲህ ላለ አደጋ እንደሚዳርገን እንደ ዶ/ር በለጠ በላቸው ያሉ ሀገር ወዳጆች አበክረው የወተወቱ ቢሆንም ሰሚ ያገኙ አይመስልም። ከጂቡቲ ጋር ያለንን ስትራቴጂካዊ ግንኙነት የወደብ አገልግሎት ከመግዛት በላይ የ120 ሚሊዮን ሕዝብ የህልውና ጉዳይ መሆኑን ዶ/ር በለጠ ሰሞኑን በሸገር ካፌ ከመዓዚ ጋር ሲጨዋወቱ አጽንኦት ሰጥተው ባሳሰቡበት ማግስት አሜሪካ ጂቡቲ ስስ ብልታችን የአኬሊስ ተረከዛችን መሆኗን ተገንዝባ በእሷ ልትመጣብን መሆኑ ግና ያልሰራነው የቤት ስራ እንዳለብን ያነቃናል። አሸባሪው ሕወሓት እንዲህ ባለ ትብታብ ውስጥ ነው የከተተን። 120 ሚሊዮን ሕዝብን ወደብ አልባ አድርጎ መልሶ ይሄን ድክመታችንን ለፖለቲካዊ ጥቅሙ ሊያውለው ተዘጋጅቷል። ሕወሓትን ልዩ ደመኛ ጠላት የሚያደርገው ይሄ ተግባሩ ነው። በዘር ከፋፍሎ አንድነታችንን አዳክሞ፤ በልዩነትና በመጠራጠር እንድንተያይ አድርጎ፤ በዚሁ ደካማ ጎናችን መልሶ እያጠቃን ነው።
ከፍ ብሎ ለማሳየት እንደሞከርሁት አሸባሪው ሕወሓት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የዘር ማጥፋት ወንጀል ያልፈጸመበት ኢትዮጵያዊ የለም። በኢትዮጵያዊ ብሔርተኛ በኦርቶዶክሳውያን በሙስሊሞች በተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወዘተረፈ ላይ ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል የዘር ማጥፋት ጎሳ የማጽዳት ወንጀል ፈጽሟል። በትግራይ ከአንድም ሁለት ሶስት ትውልድ አጥፍቷል። የ12ና የ13 አመት ህጻናትን በማዕበል በእሳት ከመማገድ በላይ ምን የዘር ማጥፋት አለ። ከድህነት አዙሪት እንዳይወጣ ሆን ብሎና አቅዶ ኢትዮጵያውያንን በማደህየት ለዘር ማጥፋት ሲያመቻቸው ኑሯል። ይህ የሽብር ስብስብ በዚህ እኩዩ ተግባሩ ሳይጸጸት በተደጋጋሚ ሀገርን ለማፍረስ እና እንደ ማይካድራ ጋሊኮማ ለሌላ ዙር ዘር ማጥፋት ሲዘጋጅ መንግስት ለሰብዓዊነት ሲል አውጆት የነበረውን ተኩስ አቁም ተገዶ ሲያነሳ ደግሞ አሸባሪው ሕወሓት የትግራይን ሕዝብ ሊያጠፉ ነው እያለ ጡሩንባውን እየነፋ ነው። ሌላው ይቅርና የለውጥ ኃይሉ ይህ ጦርነት እንዳይነሳ በአደባባይ ከ20 ጊዜ በላይ የሽምግልና የእርቅ ጥረት አድርጓል። ተገዶ ወደ ጦርነት ሲገባም ንጹሐን እንዳይጎዱ ሰራዊቱ ዋጋ ከፍሏል። የተናጠል የተኩስ አቁም ያደረገውም ለትግራዋይ በማሰብ ነበር። አሸባሪው ሕወሓት እንደ አጼ ልብነ ድንግል ጦር አውርድ እያለ መሬትን 40 ጅራፍ ገርፎ፤ በዳቢሎሰኛ ጾም ጸሎት ባመጣው ጦርነት የተፈጠረውን ምስቅልቅልና ያፈረሰውን መሠረተ ልማት ለመጠገንና መልሶ ለማቋቋም በስምንት ወራት ብቻ 100 ቢሊዮን ብር ወጭ አድርጓል። የትግራይ ክልልን የ11 አመታትን በጀት አመት ባልሞላ ወጭ ያደረገውን የዐቢይ መንግስት ትግራዋይን ሊያጠፋ ተነሳ ቢባል ከራሱ ከአሸባሪውና ከጭፍራው በስተቀር ሰሚ የለውም። አሸባሪው ግን ትግራዋይን ከልጅ እስከ አዋቂ በአሽሽ እያሰከረ በሕዝባዊ ማዕበልነት ለእሳት እየማገደ ትግራይን ሰው አልባ ምድረ በዳ ሊያደርጋት ቆርጦ ተነስቷል። እንግዲህ ዜጋ ሀገር ይፍረድ ! ዘር አጥፊው ማነው !? መልሱ ቀላል ነው። እሱም አሸባሪው ሕወሓት ነው ።
ፈጣሪ ሀገራችንንና ሕዝቧን አብዝቶ ይባርክ !
አሜን።
በቁምላቸው አበበ ይማም (ሞሼ ዳያን)
fenote1971@gmail.com
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18/2013