ሰብዓዊ ዕርዳታ (Humanitarian Assistance) ትርጉሙ በድርቅ፣ በጦርነት፣ በጎርፍና በተለያዩ ምክንያቶች ለሰብዓዊ ቀውስ የተጋለጡ ወገኖችን መርዳት ሲሆን፤ ያ ሰው ማነው፣ አገሩ የት ነው፣ ሳይባል ምን ደረሰበት ተብሎ ብቻ የሚሰጥ ድጋፍ ነው።ዋናው ዓላማውም ክቡር የሆነውን የሰው ልጅ ከአደጋ መታደግ ብቻ ነው።
የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የተከሰተውን የህግ ጥሰት ለማስከበር ዕርምጃ መውሰድ ከጀመረበት ወቅት አንስቶ ሰብዓዊ ዕርዳታን ለተጎዱ ወገኖች ለማዳረስ የብሄራዊ አስቸኳይ ሰብዓዊ ዕርዳታ አስተባበሪ ኮሚቴ በማዋቀር በሦስት ዙሮች ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበርም ይታወቃል። መንግሥት የትግራይ አርሶ አደር እንዳይጎዳ በማሰብ የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ አድርጎ ከክልሉ ሲወጣ በክምችት ደረጃ 4 መቶ ሺህ ኩንታል ስንዴ፣ 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት እንዲሁም 14 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅ ለህብረተሰቡ ፍጆታ እንዲቀመጥ አድርጎ እንደነበርም ይታወሳል።
በተኩስ አቁም ስምምነቱ ምክንያት የመከላከያ ሠራዊት ከመቀሌ እና ሌሎች ከተሞች ለቆ ከወጣም በኋላ የዕርዳታው ፍሰት በአሸባሪው ህወሓት እንዳይስተጓጎል ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪ ድርጅቶች ጋር በመሥራት የበኩሉን አዎንታዊ ሚና ሲጫወት ቆይቷል።
መንግሥት በትግራይ ክልል የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ሲያደርግ አርሶ አደሮች ወቅታዊ የግብርና ሥራዎችን ተረጋግተው እንዲያካሂዱ እና ሰብዓዊ ድጋፉ ያለምንም ችግር እንዲቀጥል ለማድረግ የታሰበ ቢሆንም አሸባሪው ቡድን ግን ለትግራይ ህዝብ የተቀመጠውን ሰብዓዊ ዕርዳታ ለጦርነት ላሰለፋቸው ሠራዊቱ ቀለብ እንዲሆን አድርጎታል። በአሁኑ ወቅት አሸባሪው ህወሓት ለሕፃናት የቀረቡትን አልሚ ምግቦች ለሽብር ቡድኑ የጥፋት ተልዕኮ ለጦርነት በማዋል ላይ እንደሚገኝ ማስረጃዎች እየወጡ ነው።
ይህ ደግሞ ከዓለም አቀፍ መርህ ያፈነገጠና የአሸባሪ ቡድኑን ለህዝብ ደንታ ቢስነት በግልጽ ያሳየ ነው። መንግሥት ብሄራዊ ደህንነት አደጋ ላይ ሳይወድቅ መሰረታዊ የሆኑ የሰብዓዊ ዕርዳታዎች ለትግራይ ህዝብ እንዲደርስ ቁርጠኛ አቋም ይዞ በመሥራት ላይ ይገኛል። ከዚህም በላይ ከልማት አጋሮቹ ጋር በመሆን ለተረጂዎች ምግብ እና መድሃኒት እንዲደርስ ያለመታከት መሥራቱን የሚቀጥልበት ይሆናል።
ይሁንና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሓት ለተረጂዎች ዕርዳታ እንዳይደርስና ለሕፃናት የተላከውን ህይወት አድን ምግብ ለሽብር ተግባር ለማዋል እያደረገ ያለውን ኃላፊነት የጎደለው ድርጊት በመመልከት የዜጎች ደህንነት በከፍተኛ ሁኔታ አደጋ ውስጥ የወደቀ መሆኑን ሊገነዘበውና ሊያወግዘው ይገባል።
የሰብዓዊ ዕርዳታ አጋሮችና የልማት ድርጅቶች በዚህ ወቅት ትኩረት ሊሰጡት የሚገባው በተለይ የምግብ ዕርዳታው ተጋላጭ ለሆኑ ሕፃናት፣ ነፍሰጡር እና ጡት ለሚያጠቡ እናቶች ቀጣይነት ባለው መልኩ መድረሱን ማረጋገጥ መቻል ይሆናል። ይህ ካልሆነ የዕርዳታ ፍሰቱ ለተጎጂዎች ሳይሆን ዞሮ ህዝብን ለሚዋጋው፣ በህዝብ ላይ ለሚነግደውና ሀገር ለማፍረስ ለሚሯሯጠው አሸባሪ ቡድን ይሆንና የከፋ አደጋ ያስከትላል።
በቀጣይ በትግራይ ክልል ድጋፍ ለሚያሻቸው ሰዎች አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ቁርጠኛ ነን የሚሉ አካላት ከመንገሥት ጋር በመተባበርና የአገሪቱን ሉዓላዊነት ባከበረ መልኩ የዕርዳታ አቅርቦትን በትክክል ለትግራይ ህዝብ ስለመድረሱ እያረጋገጡ መስጠት ይገባቸዋል።
የአሸባሪውን ህወሓት ጥንተ ተፈጥሮ በመገንዘብና ርሃብን ለሌብነትና ለቁመራ የማዋል የቆሸሸ ታሪኩን በመረዳት ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለአሸባሪ ድርጅት ከለላ ከመሆንና የህዝቦችን ስቃይ ከማራዘም ራሱን ማቀብ ይኖርበታል። እንዲህ ዓይነት የስግብግብነት ተጨባጭ መረጃዎችን በመመልከትና ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን በመቆምም የምሥራቅ አፍሪካን ቀጣና የሽብር አውድማ ለማድረግ የሚሯሯጠውን ይህንን ኃይል አደብ ለማሰገዛት መተባበርም ይኖርበታል።
በአጠቃላይ አሸባሪው ህወሓት አሁንም ረሃብን እንደ ስትራቴጂ እየተጠቀመበት በመሆኑ በመረጃዎች ተረጋግጧል፤ ይህ ሁኔታ ልዩ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባና መቆም ያለበት ድርጊት በመሆኑ አሸባሪው ቡድን በየቦታው የሚፈጽማቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲያቆም ሁሉም የድርሻውን መወጣት ይኖርበታል!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 18/2013