ከብዙ ውጣ ውረዶች በኋላ የተካሄደው የቶኪዮ 2020 ኦሊምፒክ እንደተሰጋው በኮቪድ-19 ምክንያት ብዙ ጉዳት ሳያስከትል ተጠናቋል። የኦሊምፒኩን መጠናቀቅ ተከትሎ የስፖርት ቤተሰቡ ትኩረት ወደ ፓራሊምፒክ ውድድሮች ዞሯል። ከነገ ነሐሴ 18 – 30/2013 ዓ.ም በሚካሄደው የቶኪዮ 2020 ፖራሊምፒክ ጨዋታ የሚሳተፉ አገራትም ቀደም ብለው ወደ ስፍራው አቅንተዋል። በዚህ ውድድር ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ፖራሊምፒክ ቡድንም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት ባለፈው ረቡእ ምሽት በሸራተን አዲስ አሸኛኘት ተደርጎለታል።
በአሸኛነት ስነ ስርዓቱ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሰው የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ለልዑካን ቡድኑ በማስረከብ የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል። የኢፌድሪ ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ኤሊያስ ሽኩር እና የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንት አቶ አለም ገብረመስቀልም ብሔራዊ ቡድኑ መልካም ውጤት እንዲገጥመውና በድል እንዲመለስ ምኞታቸውን ገልፀዋል ። በቶኪዮ 2020 ፖራሊምፒክ ጨዋታ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ ስፖርት በሶስት አትሌቶች የምትወከል ሲሆን ቡድኑ ባለፈው ቅዳሜ ወደ ጃፓን አቅንቷል። የኢፌድሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴም ለቶኪዮ ፓራሊምፒክ ተሳትፎ አስፈላጊውን መመዘኛ ላሟሉ የኢትዮጵያ ቡድን አባላት አሸኛኘት ማድረጋቸው ይታወቃል። የአካል ጉዳተኛ መሆን ማነስ ያለመሆኑን ያነሱት ፕሬዚዳንቷ አትሌቶቹ የአገራቸው ሰንደቅ አላማ ከፍ ብሎ እንዲውለበለብ ያደርጉ ዘንድ መልካሙን ተመኝተውላቸዋል።
ኢትዮጵያ በፓራሊምፒክ ውድድር መሳተፍ የሚችሉ በርካታ ዜጎች እንዳሏት የጠቀሱት አትሌቶቹ የእነርሱ ተሳትፎ ህብረተሰቡና የሚመለከታቸው አካላት አካል ጉዳተኝነት የተሻለ ግንዛቤና ትኩረት እንዲያገኝ በከፍተኛ ደረጃ ይረዳል ማለታቸውን ከስፖርት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ::
አምስት አባላት ያካተተው የኢትዮጵያ ፓራሊምፒክ ብሔራዊ ቡድን በቱኒዚያ አስተናጋጅነት እ.ኤ.አ መጋቢት 14-21/2021 በተካሄደው የ2021 የቶክዮ ፓራሊምፒክ ጨዋታ የሚኒማ ማሟያ ( ማጣሪያ ) ውድድር ላይ ተሳትፈዋል።ከብሔራዊ ቡድኑ ውስጥ አንዱ የሆነው አትሌት ታምሩ ከፍያለው በ1500 ሜትር 03:56 በሆነ ሰዓት ውድድሩን ጨርሶ ለቶኪዮ ፓራሊምፒክ ጨዋታ ኢትዮጵያን የሚወክል ይሆናል። በተጨማሪም አትሌት ያየሽ ጌቴ በሙሉ ለሙሉ አይነስውራን 200 ሜትር ውድድር 28፡99 በሆነ ሰዓት በመግባት ውድድሩን አሸንፋ ኢትዮጵያን ለመወከል እንደበቃች ይታወሳል።
በዓይነ ስውራን ጭላንጭል በ1500 ሜትር በተደረገው የማጣሪያ ውድድርም አትሌት ትግስት ገዛኸኝ ውድድሩን 4:31:53 በሆነ ሰአት አንደኛ በመሆን አጠናቃ ኢትዮጵያን የምትወክል ሆናለች። አትሌቶቹ በማጣሪያ ውድድሩ ወቅት ከፍተኛ ዝናብና ቅዝቃዜ የአየር ንብረት የነበረ በመሆኑ ትልቅ ፈተና ቢገጥማቸውም ችግሮቹን ሁሉ ተቋቁመው ውድድራቸውን በድል በማጠናቀቅ ኢትዮጵያን በታላቁ መድረክ ለመወከል በቅተዋል።
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በፓራሊምፒክ የተሳተፈችው እ.አ.አ 2004 አቴንስ በተዘጋጀው ውድድር ሲሆን፤ ከዚያ በኃላ በተሳተፈችባቸው የፓራሊምፒክ ጨዋታዎች የተለያዩ ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል። ኢትዮጵያ ባለፈው የሪዮ ፓራሊምፒክ ውድድር ላይ በተለያየ የሩጫ ርቀቶችና በተለያዩ የጉዳት ምድቦች ከሁለት መቶ ሜትር እስከ አንድ ሺ አምስት መቶ ሜትር አምስት አትሌቶችን ማሳተፏ ይታወሳል።
አትሌት አፅብሃ ገብሬ በ1,500 ሜትር፣ መገርሳ ታሲሳ 400 ሜትር፣ ታምሩ ደምሴ በ400 ሜትርና 1,500 ሜትር እንዲሁም ኃይሉ ኃይሌ 1,500 ሜትር በወንዶች የተሳተፉ ሲሆኑ፣ በሴት የንጉሥ ደሴ በ400ና በ200 ሜትር ርቀት ተሳትፋለች።ኢትዮጵያ በዚያ ውድድር ሦስት አትሌቶችን ብቻ ለማሳተፍ ተፈቅዶላት የነበረ ቢሆንም የሩሲያ የፓራሊምፒክ አትሌቶች አበረታች መድሃኒት መጠቀማቸው በመረጋገጡና ከሪዮ መታገዳቸውን ተከትሎ ሁለት ተጨማሪ አትሌቶችን በተለያዩ ርቀቶች እንዲሳተፉ ዕድል ፈጥሮላት እንደነበር ይታወሳል፡፡
በዚህ ፓራሊምፒክ ውድድር በሃያ ሁለት የስፖርት አይነቶች አምስት መቶ አርባ ፉክክሮች የሚካሄዱ ሲሆን አራት ሺ አራት መቶ ያህል የተለያዩ አገራት አትሌቶች ይሳተፋሉ። ውድድር ሰደፈ ከሚካሄድባቸው ስፖርቶች መካከል ከአትሌቲክስ በተጨማሪ ብስክሌት በመምና በጎዳና ላይ ተከፍሎ የሚካሄድ ሲሆን ቮሊቦል፣ የዊልቼር ቅርጫት ኳስ በሁለቱም ፆታ ይካሄዳል። የዊልቼር ራግቢ ስፖርት በድብልቅ ፆታ ውድድር የሚያስተናግድ ሲሆን በርካታ አዳዲስ የውድድር አይነቶችም ለመጀመሪያ ጊዜ ፉክክሮችን ያስተናግዳሉ።
ከኦሊምፒክ መጠናቀቅ በኋላ የፓራሊምፒክ ውድድሮች መካሄድ ከጀመሩ ሃምሳ ሰባት አመታት ተቆጥረዋል።እኤአ የ1964ቱን ጨምሮ ጃፓን ይህን ታላቅ ውድድር ለሁለተኛ ጊዜ የምታስተናግድ የመጀመሪያዋ አገር ሆናለች። ቶኪዮ የመጀመሪያውን የፓራሊምፒክ ውድድር ባስተናገደችበት ወቅት ሶስት መቶ ሰባ ስምንት አትሌቶች ከሃያ አንድ አገራት ተውጣጥተው በዘጠኝ የስፖርት አይነቶች ተፎካካሪ ነበሩ።
ቶኪዮ ሰማንያ ሺ ተመልካች በሚይዘው ስቴድየም ኦሊምፒኩን በስኬት ያስተናገደች ሲሆን ግዙፉ ስቴድየም በኮቪድ-19 ስጋት ተመልካች አልባ እንደነበር ይታወቃል። ይህ ስቴድየም የፓራሊምፒኩን መክፈቻና የመዝጊያ ስነስርአት እንዲሁም የአትሌቲክስ ውድድሮችን የሚያስተናግድ ቢሆንም ተመልካች በአካል ተገኝቶ ውድድሮችን ለመታደም ጊዜውና የጤና ስጋት አልፈቀደለትም። የፓራሊምፒኩን ውድድሮች በስቴድየም ተገኝቶ ለመመልከት ግን በታሪክ ትልቅ የሆነ ሁለት ነጥብ ሶስት ሚሊየን የስቴድየም መግቢያ ትኬት ተሸጦ ያለቀው በጊዜ ነበር።
ቦጋለ አበበ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 17/2013