የህወሓት የትግል አጀማማር በተደጋጋሚ ጊዜ እንደተገለፀውና ዶክተር አረጋዊ በርሄም “የህወሓት የፖለቲካ ታሪክ” በሚል መፅሀፋቸው እንዳሰፈሩት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ ኖራ የብሔሮች እኩልነት እንዲረጋገጥ ህዝቡ አጥቶት የነበረው ፍትህ እንዲሰፍን በጠቅላላው በአገሪቱ ውስጥ ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩ ማስቻል የሚል እላማ የያዘ እንደነበር አስቀምጠዋል። እንግዲህ ድርጅቱም የተመሰረተው ይህንን ታሳቢ ባደረገ መልኩም ነው።
ይህንን ዓላማቸውን ደግሞ ገና ከአዲስ አበባ ሳይወጡ ጀምሮ በጽሁፍ አስቀምጠው ነው ትግልን የተቀላቀሉት። ትግሉ እንደተጀመረም ፍጹም የቆመለትን አላማ ከግብ ለማድረስ የጣረ በታጋዮች መካከልም መተማመንና መደማመጥ ሀሳብን በነጻነት መግለጽን ያሳየ በጠቅላላው የትግሉን አካሄድ በሚገባ ያወቀ እንደነበር ይኸው የዶክተር አረጋዊ መጽሀፍ የያትታል። ነገር ግን ሁኔታዎች ዋል አደር እያሉ ሲመጡ መልካቸውን እየቀየሩ እንዲያውም በውስጡ አክራሪና ጽንፈኛ ሰዎች እያቆጠቆጡ በመምጣታቸው የመገንጠል አላማን ሁሉ አነገቡ፤ በዚህም ውስጥ ውስጡን የበላይነት ለመያዝ የቻሉም እንደነበሩ ይገለጻል። ከዚህም አልፈው ይህንን አስተሳሰባቸውን በማኒፌስቶ ደረጃም እስከማውጣት ደርሰው ነበር።
ነገር ግን ትግሉ አላማውን በፍጹም ሊስት አይገባውም በማለትና በመታገል ወደተነሳበት አላማ ለመመለስም ከውስጥ መስራች የነበሩት ታጋዮች ከፍተኛ የሆነ ጥረት አድርገዋል፤ ነገር ግን ለይስሙላ ሃሳባቸውን የተቀበሉ ቢመስሉም በአስተሳሰብ ደረጃ የተለወጡ ስላልነበሩ ውስጥ ውስጡን እየሰሩ ድርጅቱ ላይ ብዙ ችግር እንዲፈጠር አልፎም መስራቾቹን ካነሱት ትግል እንዲገለሉም ሆነ። መስራቾቹን ከትግሉ ካባረሩ በኋላም ብዙ ሽኩቻዎች ያስተናገዱ ቢሆንም ድል ቀንቷቸው የደርግን ስርዓት መገርሰስ ቻሉና ስልጣን ያዙ።
ያንን መጥፎ አስተሳሰባቸውን ግን በህገ መንግስት ደረጃ ሳይቀር አስፍረው በመላው አገሪቱ ዛሬ እስከደረስንበት ደረጃ ድረስ ያሉ በርካታ ችግሮችን ለመፍጠር ችለዋል። ይህ ሁኔታ ደግሞ ዴሞክራሲያዊ አካሄድን የተከተለም አልነበረም። በመሆኑም ደርግ ስልጣን ሲይዝ “ኢትዮጵያ ትቅደም” ቢልም ያለውን ያህል ኢትዮጵያን አስቀድሟል፣ ህዝቧንም ጠቅሟል ማለት ዘበት ነው። ህወሓቶችም ድል ቀንቷቸው ስልጣን ቢይዙም እንደ አነሳሳቸው በበጎ ህሊና ባለመቀጠላቸው እንደውም ለህዝቡ በከተማ የነበረውን ደርግ ከጫካ በመጣው ደርግ የመቀየር ያህል ሆኖበት እዚህ ደርሷል።
በመሆኑም ህወሓት ልክ ወደ ስልጣን ሲመጣ የህዝቡን ዴሞክራሲያዊ መብት መጠበቅ ጉዳዩም አልነበረም፤ ይህ መጥፎ ሀሳቡ ደግሞ ላለፉት 27 ዓመታት አብሮት ኖሮ ዛሬም በስሙ በሚነግደው የትግራይ ህዝብ እንዲሁም መላ አገሪቱን በእኩይ ተግባሩ እያመሰ እያተራመሰ አገርንም ለማፍረስ ከጀሌዎቹ ጋር ከፍተኛ የሆነ ስራን እየሰራሰ ነው።
ማሕበር ገስገስቲ ብሄረ ትግራይ (ማገብት) ምስረታ ጀምሮ በኋላም ህወሓትን ከመሰረቱት ጥቂት ሰዎች መካከል ዶክተር አረጋዊ በርሄ አንዱ መሆናቸው ተደጋግሞ ተነስቷል። በወቅቱ የትግሉ መስራችና ከፍተኛ አመራር ይሁኑ እንጂ ከድርጅቱ በልዩነት ተሰናብተዋል። ዶክተር አረጋዊ በርሄ ከረጅም ዓመት የስደት ህይወት በኋላ ለውጡን ተከትሎ ወደአገር በመግባት የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲን መስርተው በሊቀመንበርነት እየሰሩ ነው። አሁን ላይም የህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር በመሆን መንግስት የሰጣቸውን ሃላፊነት በመወጣት ላይ ይገኛሉ። እኛም በተለይም አሁን ላይ ህወሓት አገርን ለማፍረስ እየሄደበት ያለውን ርቀት ከቀደመ ባህርይው ጋር እያነጻጸሩ ይነግሩን ዘንድ ቃለ ምልልስ አድርገናል።
አዲስ ዘመን ፦ ህወሓት ሲመሰረት በመልካም ሀሳብ በታጋዮቹ መካከልም ፍጹም ዴሞክራሲያዊ በሆነና በመተማመን መመስረቱ ተደጋግሞ ይነሳል፤ ነገር ግን ውስጥ ውስጡን እየሄዱ ደግሞ ሴራ የሚሸርቡ አካላት እንደነበሩም ይነሳልና ይህ ሳታውቁት ወይም እያወቃችሁት በመካከላችሁ የተፈጠረ ችግር ነው ?
ዶክተር አረጋዊ፦ በጠቅላላው ሲታይ በትግሉ ውስጥ ለግል ጥቅሙ ስልጣንን አብዝቶ የሚፈለግ እና ለህዝብ ጥቅም የወገነ ነበር። ይህ ደግሞ ችግሩን ፈጥሯል። የዛን ጊዜ የስልጣን ጥማቸው ሰላሳ አመት እንኳን በስልጣን ላይ ቆይተው በቃን እንዳይሉ እያደረጋቸው መሆኑን እየታዘብን መጥተናል። እነዚህ አሁን ላይ ራሳቸውን ወደ ጁንታነት የቀየሩት አባላትም ያን ጊዜም ቢሆን ህልማቸው ሁሉ ስልጣን ብቻ ነበር፤ የህዝብን ህይወት ማስተካከልና መለወጥ ለእነሱ እንደ ትርፍ ነገር የሚታይ ነበር። ይህ ደግሞ ባለፉት 30 ዓመታት በተግባር ያሳዩት ሀቅ ነው። በጽሁፍም ቢሆን መጀመሪያ ቻርተር ብለው ያዋቀሩት ቀጥሎም ወደህገ መንግስት የቀየሩትን ማየት በቂ ይመስለኛል። በመሆኑም ይህ የስልጣን ጥማታቸው በመካከላችን የተወሰኑ ልዩነቶች እንዲፈጠሩ አድርጎ ነበር፤ በዚህም ደግሞ እኔን ጨምሮ የተወሰኑ ሰዎችን ለመምታት ተልዕኮ ተሰጥቷቸው ሴራን የሚሸርቡ አካላትም ነበሩ።
አዲስ ዘመን፦ ህወሓት ሲመሰረት መስራች በኋላም አመራር ነበሩ፤ በመካከል ግን በተፈጠሩ ልዩነቶች ምክንያት ከድርጅቱ ተሰናብተዋል፤ በወቅቱ ይህ ሁኔታ ምን ፈጠረብዎት?
ዶክተር አረጋዊ፦ ብዙ አቅደሽ ብዙ ዋጋ ከፍለሽ ነገ ደግሞ ለህዝቤ አዲስ ቀን አወጣለሁ ብለሽ ከጀመርሽው ትግል መውጣት በጣም ደስ የማይል ስሜትን ይፈጥራል፤ ነገር ግን ሰዎቹ እያወቁ ወደ ጥፋት መንገድ እየሄዱ ዝም ማለት እንደ አንድ ዜጋ የህዝብ አደራ እንዳለበት ግለሰብ በጠቅላላው ህሊና እንዳለው ሰው እጅግ በጣም ከባድ ስህተት ነው።
እኔ በበኩሌ ትግሉንም የተቀላቀልኩት የህዝቡን የዘመናት ችግር ወይም ጥያቄ በተቻለኝ አቅም ራሴን ሰውቼ ለመፍታት ስለነበር እነሱ ከዚህ መስመር ሲያፈነግጡ አቅጣጫውን አሳይቼ ለመቀጠል ጥረት አድርጌያለሁ፤ ግን ደግሞ የማይሆን ሲሆን ትግሉን አቋርጬ መውጣት ነበረብኝ። እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ በጣም ከባድ ነበር።
አዲስ ዘመን፦ ይህ የጁንታው የቀደመ ባህርይው ደግሞ ለዛሬው ማንነቱ መሰረት ነው ማለትስ ይቻላል?
ዶክተር አረጋዊ ፦ የብሔር ትግል ሁለት ስለት ያለው ነው፤ አንዱ የመገንጠል አዝማሚያ ሌላው ደግሞ በዴሞክራሲያዉ አካሄድ መብትን የማስከበር አዝማሚያ ነው። በዚህ የተነሳ ደግሞ የመገንጠል አዝማሚያው ላይ የሚያደሉ ቡድኖች ውስጥ ውስጡን እየተጠናከሩ መጥተው ለዴሞክራሲያዊ አንድነት የሚተጉትን ከመድረክ ከፍተው ስልጣን ይይዛሉ፤ በእኛ አገርም የሆነው ይኸው ነው።
የህወሓት ጀንታ ቡድኖችም ገና ስልጣን ላይ ሲወጡ ጀምሮ የመገንጠሉን ሀሳብ ይዘት በህገ መንግስቱ ውስጥ አስገብተው ከፋፍለህ ግዛ ለሚለው ዘይቤያቸው እንዲመቻቸው አገራችንን ከፋፍለውታል። አሁን በጦርነት የተደገፈ እንቅስቃሴ የሚያደርጉትም ሲነሱ ጀምሮ ለነበራቸው አላማ ማስፈጸሚያ ነው። በመሆኑም አንድነት ዲሞክራሲ ፈላጊ ህዝብ ተባብሮ እነዚህ ጠላቶቹ ላይ መዝመት እንጂ አሁን ግማሹ ስለ ርስቱ ሌላው ስለ መሬቱ ሌላው ደግሞ ስለሌላ ጥቅሙ ብቻ የሚያንጎራጉር ከሆነ ለእነዚህ አጥፊዎች ሲነሱም ጀምሮ በጥፋት ለተነሱ ቡድኖች አላማ ማስፈጸሚያ መሆን እንደሆነም ማወቅ ያስፈልጋል።
የቀድሞ በተለይም በትግል ሜዳ ዋል አደር ያለ ያመጣው የስግብግብነት ለእኔ ብቻ የማለትና ሰዎችን ያለማመን ሁኔታው ለዛሬ ማንነቱ ትልቅ መሰረትን ጥሏል። ያ ባይሆን ኖሮ ትግሉ ጽንሰ ሃሳቡ እጅግ ያማረ ብሎም ለአገርና ህዝብ የሚጠቅም ነበር። ነገር ግን ስግብግቦች የትግሉን መንገድ አሳቱት፤ ከዛም በኋላ ስልጣን ላይ ሲቆይም ሁሉን ለራሱ ጠቅልሎ መያዝን ብቻ አስቀደመ። አሁን ደግሞ የባሰው ነገር አገርን ወደሚያተራምስ ህዝብን ወደሚያስጨርስ ጦርነት ውስጥ ገቡ ማለት ነው። ይህ እንግዲህ በእዛ ትግል ሜዳ ላይ ይዞት የመጣው ያዳበረው ባህርይው ነው።
አዲስ ዘመን ፦ አሸባሪው ህወሓትን መለስ ብለው ሲያስቡት ግን እንደዚህ ባለው ሁኔታ አገርን የሚክድ ይመስልዎት ነበር? ይህ ቀን እንደሚመጣስ አስበው ያውቃሉ?
ዶክተር አረጋዊ ፦ አዎ ህወሓት ለኢትዮጵያ በጎ እንደማያስብ አውቅ ስለነበርም ነው እኔ መጀመሪያውኑ ድርጅቱን ለቅቄ የሄድኩት። ከዛ በኋላም ስለ አገሬና ህዝቦቿ ግድ ይሰጠኝ ስለነበር ምንም እንኳን በሩቅ ቢሆንም ስታገለው ነው የኖርኩት፤ በመሆኑም ህወሓት ሲፈጥረውም ጀምሮ መልካም የማይታየው ከራሱ ውጪ ስለ ሌላው ደንታ የሌለው በመሆኑ አገሪቱን አሁን እንዳደረጋት እንደሚያደርጋትና ቁልቁል እንደሚያወርዳት ከጅምሩም ያስታውቅ ነበር።
እንዲያው ልብ ብለሽ ከሆነ ህወሓት በስልጣን ላይ በነበረባቸው አመታትም ቢሆን በህዝቦች መካከል ሲሰብክ የኖረው ልዩነትን እንጂ አንድነትን አልነበረም። ኢትዮጵያውያን አንድ ከሚያደርጓቸው ነገሮች ይልቅ ልዩነቶቻቸው ላይ እንዲያተኩሩም ነው ሲሰራ የቆየው፤ ይህ ደግሞ ህዝቦች ከወንድማማችነት ይልቅ እንደ ጠላት እንዲተያዩ አድርጓቸዋል ።የኢትዮዸያ ህዝብ አንድነት እኩልነት ፈለጊ ቢሆንም እነሱ ግን ውስጥ ውስጡን እየሄዱ ሲለያዩት ሲያባሉት ቆይተው አሁን ደግሞ እርስ በእርሳችን እንድንጨራረስ ጦርነት ለኩሰው ቁም ስቅል እያሳዩ ነው። እዚህ ላይ ግን ይህ አሸባሪ ቡድን እንዲህ የልብ ልብ እንዲሰማው ወይም ይህንን መሰሉን እኩይ ተግባሩን እንዲፈጽም ያስቻለው የህዝቦች አንድ አለመሆን ይመስለኛል። ከመጀመሪያውም ጀምሮ እኩይ ተግባሩን እየተከታተለ የሚያከስም የሚያጨናግፍ ተባብሮ በአንድነት የሚቆም ህዝብ ቢኖር ኖሮ እዚህ ባልደረስን ነበር። አሁንም ግን ጊዜው አልቋል ማለት ስላይደለ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ትግራዋይንም ይጨምራል ተባብረን በቃችሁ ልንላቸው ፣ከላያችን ልናወርዳቸው የሚገባበት ወቅት ላይ ነን።
አዲስ ዘመን፦ አሁን ላይ የጁንታው ቡድን በተለይም በአማራና አፋር ህዝቦች ላይ ከፍተኛ የሆነ የዘር ማጥፋት ጥቃቱን በሰፊው እያደረገ ነው፤ ይህ እንደው ኢትዮጵያን አፍርሶ የሚመኘውን ነገር ለማግኘት እየሄደበት ያለው አካሄድ ይሆን ይሆን?
ዶክተር አረጋዊ ፦ እነዚህ ሰዎች እኮ በጣም ክፉ ከመሆናቸው የተነሳ ክፋታቸው ተዘርዝሮ አያልቅም። የኢትዮጵያን አንድነት ማፈራረስን እንደ አላማ ይዘው ሲንቀሳቀሱ ነበር። አሁን ደግሞ በግላጭ ጦርነት አውጀውና ከሌሎች የውጭ ጠላቶች ጋር እጅና ጓንት ሆነው በመስራት ላይ ናቸው።
ለምሳሌ አሁን ላይ በአፋርና አማራ ክልል ላይ እየገቡ ህዝብን ለማባላት እያደረጉት ያለው ጥረት እጅግ አስነዋሪ ከመሆኑም በላይ እየፈጸሙ ያለው ፍጅትም ለመገንጠል አላማቸው ይጠቅመናል ብለው የያዙት አካሄድ ይመስለኛል ። ምክንያቱም ከአማራው ከአፋሩ ከተለያዩ ለብቻቸው አገር ለመመስረት ለሚያስቡት ሴራ ማስኬጃ የሚሆናቸውን አቋራጭ መንገድ የመፈለግ አንዱ መንገዳቸው ነው።
በሌላ በኩልም የአፋርም ሆነ የአማራ ህዝብ ከትግራይ እህት ወንድሞቹ ጋር የአንድ አገር ልጅ መሆኑን በመገንዘብ የእነዚህን ባንዳዎች ስራ ወደጎን በመተው አብሮ ለመቆም መተባበር ሴራቸውን ማክሸፍ ነው እንጂ እነሱ በሚቀዱለት ቦይ እየተጓዘ እርስ በእርስ መጫረስና እነሱን ወደግባቸው ማድረስ የለበትም።
አሁን ላይ እኮ እነዚህ የወንበዴ ቡድኖች ራሳቸው አሸባሪ ብለው ከፈረጁትና ሲያሳድዱት ከኖሩት ሸኔ ጋር ጥምረት ፈጥረናል በማለት በአደባባይ እያወሩ ነው። ይህ እንግዲህ የሚያሳየው ሀሳባቸው እንዲሁም ስራቸው በሙሉ አገርን ማፍረስ፣ እነሱም የእኔ ነው የሚሉትን ይዘው መገንጠል እንደሆነ ህልማቸው በግልጽ ያሳየ ነው። አሁንም በአፋርና በአማራ ክልሎች ላይ የሚያደርጉትም ግፍ የዚህ ተቀጽላ ነው። ነገር ግን ህዝቡ ነቅቶና አልፎ ማሰብ መቻል ደግሞ አለበት።
አዲስ ዘመን፦ ጁንታው ቡድን አሁን ላይ የጦርነት አድማሱን በማስፋት ላይ ይገኛል፣ የዚህ ሁኔታ አካሄድ ለእርስዎ ምን ዓይነት መልዕክት ያሳያል?
ዶክተር አረጋዊ፦ አዎ ጁንታው ቡድን ህልሙን ለማሳካት አሁን ላይ ጦርነቱን ከትግራይ አልፎ ሌሎች አጎራባች ክልሎች ላይ ሁሉ እንዲደርስ ከፍተኛ ስራ እየሰራ ነው፤ አንዳንድ ቦታዎችም ላይ አለ ነው የሚባለው። እዚህ ላይ ግን እንደሚመስለኝ ጁንታው ቡድን በዚህን ያህል ደረጃ አድማሱን ሊያሰፋ የቻለው በእኛ አንድነትን በምንፈልግ አካላት በኩል ድክመት ስላለ ይመስለኛል። ይህንን ያልኩበት ዋናው ምክንያት ደግሞ የእነሱን እኩይ ሀሳብ ቀደም ብለን ተገንዝበን ነበር ፤ ለምሳሌ እራሳቸው ያረቀቁትን ህገ መንግስት አንቀበልም ሲሉ። ትግራይ የኢትዮጵያ አካል አይደለችም ብለው በይፋ ሲያውጁ። ብቻቸውን ተገንጥለው ክልል ለመምራት ምርጫ ውስጥ ሲገቡ ߹ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ውሳኔ አንቀበልም ሲሉ እንዲሁም በየአካባቢው ምሽግ ሲቆፍሩና ህጻናትና ወጣቶችን እየመለመሉ ለጦርነት ሲያሰለጥኑ እያየንና ምልክቶች እየተሰጡን ነበር፤ እነዚህ ምልክቶ ደግሞ ተገቢው ምላሽ አልተሰጣቸውም። ይህ ሂደታቸው ደግሞ እዚህ ለመድረሳቸው ትልቅ ምክንያት ሆኗል።
በመሆኑም በእኛ በኩልም ማለትም በፌደራል መንግስት በኩልም እነዚህን የወንበዴ ቡድኖች በአፋጣኝ ዋጋቸውን መስጠት ላይ ከፍተኛ የሆነ ክፍተት አለብን።
አዲስ ዘመን፦ ይህ አሸባሪ ቡድን እያሳየው ካለው እኩይ ባህርይው አንጻር ከትግራይ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ነቅሎ ለመጣል ምን መደረግ ነው ያለበት?
ዶክተር አረጋዊ፦ አዎ እነዚህ እኩይ ተግባር ያነገቡ ስብስቦች ህዝቡን በመሩበት ጊዜም ሆነ አሁን ሰላም እየሰጡ ዴሞክራሲን እያሰፉ እንዲሁም ደሃው በልቶ ጠግቦ እንዲያድር አላደረጉም፤ አሁን ደግሞ ለራሳቸው የስልጣን ጥማት ብለው በለኮሱት እሳት ብዙሀኑ እየተለበለቡ ነው፤ በመሆኑም ይህንን ቡድን ከራሳችን ከላይ መንግለን ለመጣል ከእኛ የሚፈለገው መተባበርና አንድ መሆን ብቻ ነው።
በነገራችን ላይ አሁን ከጁንታው ቡድን ጋር የገጠምነው ጦርነት የህልውና እንጂ ርስት የማስመለስ አይደለም፤ ይህ ደግም በሚገባ ሊታወቅ ይገባል። ይህ መሬት የአማራ ነበር። ሌላው የትግራይ ነው እያልንም ጦርነቱን ለሁለቱ ክልሎች ብቻ መስጠትም የለብንም፤ ጉዳዩ የህልውና የመኖርና ያለመኖር ብሎም የመጥፋት የመፈራረስና በአንድነት የመቆም መሆኑን አውቀን ከዳር እስከ ዳር ያለው ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድ ልብ መካሪ በመሆን መተባበር ብቻ ነው ልኩን ሊያሳየው ብሎም ከትግራይም ሆነ ከኢትዮጵያ ትከሻ ላይ እንዲወርድ ሊያደርገው የሚችለው።
መሬት ወደ አማራ ሄደ፤ ትግራይ ገባ፤ አፋር የኔ ነው ወዘተ ምንም የሚያጣላን አይሆንም፤ ምክንያቱም መሬቱ የኢትዮጵያ እኛም ኢትዮጵያውያን ነን። በመሆኑም አንድነት እኩልነት ፈለጊዎች እስከሆንን ድረስ ለዚህ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥር ስርዓት ለማምጣት እንጂ መጣር ያለብን በማይረባ አጀንዳ በተለይም ደግሞ እነሱ ባቀበሉን አጀንዳ መወሰድም እዛ ላይ ጊዜያችንን ማባከንም አይኖርብንም።
እነሱ አንድነታችን በጣም ስለሚያስጨንቃቸውና እኛ አንድ ስንሆን ሊያወድሙን ስለሚፈልጉ እነሱ ከሚያወድሙን ይልቅ እኛ ቀድመን ብናወድማቸው ለአገራችን አንድነት እኩልነት ቆምን ማለት ስለሆነ በዚህም መንገድ መራመድ እጅግ በጣም አስፈላጊ ነው።
አዲስ ዘመን፦ አሸባሪው ህወሓት በአሁኑ ወቅት ህጻናትን ለጦርነት እየመለመለ ማሰለፉ ብቻ አገር አፍራሽ ትውልድ እንዳይቀጥል የሚፈልግ መሆኑን ማሳያ ሊሆን አይችልም? በዚህ ላይ የእርስዎ አቋም ምንድን ነው?
ዶክተር አረጋዊ ፦ ህጻናት የ10 እና የ11 ዓመት ልጆችን ለጦርነት ማሰለፍ አለም አቀፍ ወንጀል ከመሆኑም በላይ በጥብቅ የተከለከለ ነው። ምናልባትም እንደ ዘር ማጥፋት የሚታይ ወንጀል ነው። እነዚህ ልጆች እኮ ትምህርት ቤት መሄድ የነበረባቸው ናቸው፤ አሁን አሸባሪው ህወሓት ለራሱ የስልጣን ጥማት ብሎ ከእናታቸው ጉያ እየነጠቀ ወደ ጦርነት ያስገባቸው። ይህ የሚያሳየው ቡድኑ ከራሱ ውጪ ማንንም የማይፈልግ በተለይም ነብስ ላላወቁ ልጆች ምንም ዓይነት ርህራሄ የሌለው መሆኑን ነው።
በመሆኑም ማንም ሞቶ እነሱ ብቻ ያጧትን ስልጣን እንዲያገኙ ብቻ እየተመኙ እንዳሉም ይህ ትልቅ ማሳያ ነው። በመሆኑም ይህ ሽብርተኛ ቡድን ስር ሰዶ ተጨማሪ እልቂትና መከፋፈልን በአገራችን ላይ እንዳይፈጥር ተቀናጅቶና ተባብሮ መመከት ያስፈልጋል።
አዲስ ዘመን ፦ ከዚህ ቀደም ቡድኑ በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ሲያሳድደው ሽብርተኛ ብሎ ሲፈርጀው ከነበረው ሸኔ ጋር ተጣምሬያለሁ እያለ ነውና እንደው ይህ ምንን ያመለክታል?
ዶክተር አረጋዊ፦ አሸባሪው ህወሓት ሆነ ኦነግ ሸኔ አላማ የሌላቸው ለሚሰሩት ስራ ምንም የሚከተሉት መርህ የሌላቸው ከመሆናቸው አንጻር አሁን ላይ አዳኝ ታዳኝ እንዳልነበሩ ተጣምረው አገር ለማፍረስ መነሳታቸው ለጥቅማቸው ሲሉ የሚገለባበጡ ተገለባባጮች መሆናቸውን ያሳያል።
በመሆኑም እነዚህ ቡድኖች በተለይም ህወሓት በስልጣን ላይ በነበረ ጊዜ ሽብርተኛ ብሎ ፈርጆት ሲያሳድደው እንዲሁም ኦነግም “ህወሃሓት የሰራኝን ስራ ለማወራረድ ገና ብዙ ይቀረኛል” እያለ በየፊናቸው ሲፎክሩ ኖረው አሁን ደግሞ አገር የማፍረስ ራዕያቸውን በጋራ ሆነው ሊያሳኩ መነሳታቸው መርህ አልባ መሆናቸውን በግልጽ ያሳዩበት ነው።
ሁለቱም ቡድኖች ቆምንለት ለሚሉት ህዝብ ደንታ የሌላቸው፤ እነሱ የሚያስቡት አልያም የሚፈልጉት ስልጣንና ስልጣን እንዲሁም ጥቅም ብቻ ነው፤ ለዚህ ማሳያው ደግሞ የነገ አገር ተረካቢ ህጻናትን ለዛሬ ስግብግብ ፍለጎታቸው እሳት ውስጥ እየማገዱ ነው።
ለራሳቸው ጥቅምና የስልጣን ጥማት ውጪ ለአገርና ለህዝብ የማይቆሙ ቡድኖች በሆነ ወቅት ላይ አንዲት የምታስማማቸውን ነገር ከውስጥ ለይተው በማውጣት ለጊዜው ይጠቅመናል ያሉትን ነገር ከማድረግ ወደኋላ አይሉም ። ይህ ሁኔታም የስግብግቦች የተለመደ አካሄዳቸው ነው።
እንደነዚህ አይነት ቡድኖች ጥቅመኛና የራሳቸውን ምቾት ብቻ የሚያስቀድሙ ከመሆናቸው አንጻር አንዳንድ ጊዜ እስከ ዛሬ ሲሄዱበት የነበረውን አካሄድ ሁሉ በመርሳትና እንዳልነበር በመቁጠር ለጥቅማቸው ሲሉ ይጣመራሉ ።አሁንም እያየን ያለነው ነገር ይህንን ነው፤ ምናልባት እነዚህ ቡድኖች ግባችን የሚሉት አገር የማፍረስ ስራቸው ጋር ሲደርሱ ዳግም በመወነጃጀልና አንዱ የአንዱ ጠላት በመሆን ሲሰለፉ ደግሞ የምናይበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን አውቃለሁ።
ሁለቱም አላማቸው መገንጠልና አገርን ማፍረስ ነው፤ ይህ ሁኔታ ደግሞ በተለይም ደጋፊዎቻቸው እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ በአግባቡ ሊረዳው ይገባል። ሸኔ ኦሮሞ ተበድሏል ተጠቃሚ አልሆነም ብሎ ነፍጥ አንግቦ ጫካ ከገባ ምናልባት አርባ አመት ይበልጠዋል፤ ግን ደግሞ የኦሮሞን ህዝብ ከመግደል እንዲንገላታ ከማድረግ ባለፈ ምን የሰራው ስራ የለም። በተመሳሳይ ህወሓትም ቢሆን ህዝቤ በሚለው የትግራይ በህዝብ ይነግድ እንጂ ህዝቡ ከተረጂነት እንዲወጣ አላደረገም፤ የትግራይ ህዝብ በዚህ ዘመን እንኳን የሚጠጣው ንጹህ ውሃ የለውም ። ይህ የሚያሳየው ሁለቱም ቡድኖች ለራሳቸውና ለጥቅም አጋሮቻቸው የቆሙ የእኩይ ምግባር ባለቤቶች መሆናቸውን ነው።
አሁን ተጣመሩ አልተጣመሩ የሚያመጡት ለውጥ የለም ፤ ምክንያቱም ህዝቡ በተለይም ከለውጡ በኋላ ኢትዮጵያዊነቱን እያስቀደመ አንድ ወደመሆን እየመጣ ነው። ስለዚህ እነዚህ ሀይላት የጀመሩት አካሄድ የማይሆን ከመሆኑም በላይ በግሌ እንደማይሳካላቸው እርግጠኛ ነኝ ።
አዲስ ዘመን፦ እዚህ ላይ ግን እንደው ሁለቱ ቡድኖች ተጣምረናል ማለታቸው በተለይም ቆመንላቸዋል ከሚሉት ህዝብ አንጻር ምን ማለት ነው፤ የሚኖረው ጥቅምስ ምንድን ነው?
ዶክተር አረጋዊ፦ እነሱ ለህዝብ ይቆማሉ ብሎ ማሰብ እጅግ በጣም የዋህነት ነው። እነሱ ለህዝብ ቅንጣት ታክል ርህራሄ የላቸውም። ሃሳባቸው ወደ ስልጣን መምጣት ብቻ ነው። ይህ ግን እንኳን በውን በህልምም የሚሆን አይመስለኝም። ምክንያቱም ህዝቡ ወደአንድነቱ እያዘነበለ እየተጠናከረ ነው። በመሆኑም አሁንም የማይሆን ነገር ጀምረዋል፤ አይሳካም፤ እነሱም ተከብሮ ማለፍ ስላላደላቸው ከዚህ ቀደም እንዳየናቸው ጓደኞቻቸው የውርደትን ጽዋ ይጎነጫሉ።
አዲስ ዘመን ፦ አንዳንድ ምዕራባውያን አገራት አሸባሪው እስከ አሁን በአገርና በህዝብ ላይ ይህንን ሁሉ በደል እያደረሰም ጫናዎችን ለመፍጠር እየሞከሩ ያሉት የኢትዮጵያ መንግስት ላይ ነውና እንደው ይህ ለምን ይመስልዎታል? የዚህ አካሄድ መጨረሻውስ ምን ሊሆን ይችላል ይላሉ?
ዶክተር አረጋዊ ፦ የውጭ ሀይሎችም መርህ አልባ ናቸው ማለት ይቻላል ።በተለይም ደግሞ ግብጾችና የአውሮፓ መንግስታት መርህ አልባ መሆናቸውን የሚያሳየው ጁንታው ቡድን ስልጣን ላይ እያለ የተጭበረበረ ምርጫ በማድረግ ላይ ሆኖ እንኳን ጥሩ የተሳካ ተዓማኒ የሆነ ምርጫን አደረገ ሲሉን ነው የኖሩት። አሁንም መርህ አልባ ስለሆኑ የህወሓት ተላላኪ ሆነው ከስነ ምግባር ውጪ በሆነ ሁኔታ የተለያዩ ዘገባዎችን ያወጣሉ ። ይህ ደግም መኮነን ያለበት ጉዳይ ነው።
በመሆኑም ጁንታውን ቡድንም ሆነ እነዚህን ወገንተኛ የሆኑ የውጭ ሚዲያዎች ተባብረን ነው መታገል ያለብን፤ የውስጥም ይሁኑ የውጭ ሀይሎች ባለው ቀዳዳ እየገቡና ቀዳዳው ሰፍቶ ህዝብ እንዲተራመስ በዚህ አጋጣሚ ደግሞ የእነሱ ተላላኪዎች ስልጣን ላይ እንዲወጡ የማድረግ ስትራቴጂ እየተከተሉ በመሆኑ ሁሉም ህዝብ ከሊቅ እስከ ደቂቅ ይህንን ተገንዝቦ መተባበርና ልዩነትን ወደጎን ትቶ በአንድ መቆም አገርን ያሻግራል።
ተደጋግሞ እንደሚነገረው ጣሊያንን አድዋ ላይ ተባብረን ነው ያሸነፍነው ፤ ህዳሴ ግድባችንን 81 በመቶ ያደረስነውና ሁለተኛውን የውሃ ሙሌት በተሳካ ሁኔታ ያካሄድነው በመተባበራችን ነው። በመሆኑም ከተባበርን እነዚህን ተገንጣዮች ማሸነፍ ብቻ ሳይሆን አገራችንንም ማሳደግ ማዘመን ስለምንችል ልዩነቶቻችንን በሁለተኛ ደረጃ አስቀምጠን በትልቁ ጉዳያችን ላይ እጅ ለእጅ መያያዝና መተሳሰብ ይጠበቅብናል።
አዲስ ዘመን፦ ለነበረን ቆይታ በጣም አመሰግናለሁ።
ዶክተር አረጋዊ ፦ እኔም አመሰግናለሁ።
አዲስ ዘመን ነሐሴ 17/2013