ከታህሳስ 2012 ዓ.ም ጀምሮ በቻይና ውሃን ከተማ የጀመረዉ የኮሮና ተዋህሲ ዓለምን አዳርሷል። በዓለም አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስርጭትን የሚመዘግበው ድረ ገፅ (WorldOMeter) እንደሚያሳየው በዓለም ከ220 በላይ ሀገሮችን አጥቅቷል። እስከ ትላንት ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ 211 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። ከ4 ሚሊዮን አምስት መቶ በላይ ሰዎች ሞተዋል፣ ከ1.3 ሚሊዬን በላይ ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።
በአውሮፓ 54 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 1,1 ሚሊዮን ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። በአሁኑ ወቅትም ከ3,900 በላይ አዲስ የተያዙ ሰዎች እንዳሉ መረጃዎች እያሳዩ ነው። በሰሜን አሜሪካም ከ46 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ 971,894 የሚሆኑ ሰዎች ህይወት ጠፍቷል። አዲስ የተያዙ ሰዎች ቁጥርም ወደ 23,497 መድረሱም ተሰምቷል። በኢስያ አህጉርም ከ67 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተይዘዋል፣ ከነዚህም ውስጥ 989,185 ሰዎች የሞቱ ሲሆን 36,735 በላይ ሰዎች አዲስ በቫይረሱ እንደተያዙ ድረ ገፁ ያሳያል።
ወደ አፍሪካ ስንመጣ በአህጉሩ 7,5 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፣ ከ188,382 በላይ ሰዎች በወረርሽኙ ሳቢያ ህይወታቸው አልፏል። በአፍሪካ ከሚገኙ ሀገራት መካከል ደቡብ አፍሪካ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዚያ እና ኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ስርጭት በቅደም ተከተል በመጀመሪያው ረድፍ ይገኛሉ። በደቡብ አፍሪካ 2,6 ሚሊዮን ሰዎች ተይዘው 78,983 ሰዎች ሞተዋል።
በሞሮኮ 799 ሺህ ሰዎች ተይዘው 11,587 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል። በቱኒዚያም ከ635 ሺህ በላይ ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል፣ ከእነዚህም ውስጥ 22,394 የሚሆኑት ሞተዋል። ወደ ኢትዮጵያም ስንመጣ የኮሮና ተኅዋሲ ስርጭት እና የሟቾች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መሆኑ ስጋት ቀስቅሷል። እስከ ትላንት ድረስ 293,737 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን ከ4,500 በላይ ሰዎች ሞተዋል።
ይህ አሃዝ የሚያሳየው አሁን የቫይረሱ ስርጭት በአፍሪካ ሃገራት እየተስፋፋ መሆኑን ነዉ። የጤና ሚኒስቴር ያወጣዉ ዘገባ የሚያሳየው በተለይ በመዲናዋ አዲስ አበባ ቫይረሱ በከፍተኛ ፍጥነት እየተዛመተ እንደሆነ ነው። በኢትዮጵያ ኮሮና ተዋህሲ ከጤና ችግርነቱ ባሻገር የኢኮኖሚ፤ የሥነ ልቦና ጫናን ጨምሮ በርካታ ማኅበራዊ ችግሮችን ደቅኗል። ያም ሆኖ በኢትዮጵያ የኮሮና ቫረስ ተገኘ በተባለብት ወቅት ይታይ የነበረዉ ጥንቃቄ እየላላ መሆኑ ብዙዎችን አሳስቧል። የጥንቃቄዉ መላላት በበሽታው የሚያዙ፤ በፅኑ የሚታመሙና ህይወታቸውን የሚያጡ ወገኖቻችን ቁጥር ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ በከፍተኛ መጠን እየጨምረ ይገኛል። ሰሞኑን እንደሚስተዋለው በርካታ ሰዎች በየቀኑ በተከታታይ ህይወታቸውን እያጡ ነው። ይህም ሁሉም የማሕበረሰብ ክፍል ማስክ በማድረግ፣ የእጅን ንጽህና በተደጋጋሚ በመጠበቅ፣ በማንኛውም ቦታ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ እና የኮቪድ-19 ክትባት በመከተብ የወረርሽኙን ስርጭት እና መዛመት መቆጣጠር ይኖርበታል።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንደገለፀው ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ግለሰቦች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እያሻቀበ በአንድ ቀን ብቻ 25 ግለሰቦች ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የገቡ ሲሆን በአጠቃላይ 308 ግለሰቦች በአሁኑ ሰዓት በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ። ከ53 ቀናት በኋላ ከፍተኛው ቁጥርም ሆኖ ተመዝግቧል።
አሁንም የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ችላ ልንለው የሚገባ ጉዳይ አይደለም። የብዙዎችን ህይወት እየነጠቀ ብዙዎችን ደግሞ አካላዊ እና ማህበረሰባዊ ቀውስ ውስጥ እየከተተ ይገኛል። ስለሆነም እያንዳንዱ ግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሐይማኖት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራት፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የጤና ባለሙያዎች፣ መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል ማስክ ማድረግ፣ የእጅን ንፅህና በአግባቡ መጠበቅ እና ርቀትን መጠበቅ እና የኮቪድ-19 ክትባት መከተብ ግድ ነው። እነዚህን የኮቪድ-19 የመከላከያ መንገዶች የሚተገብሩ ከሆነ እራስዎን እና ቤተሰብዎን ከኮቪድ-19 ቫይረስ ተጋላጭነት ይቀንሳሉ ለወረርሽኙ መዛመትም ምክንያት አይሆኑም።
የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እነደገለፀው የሥርጭቱ ፍጥነት ከፍ እያለ የመጣው በማህበረሰቡ ውስጥ መዘናጋት ስላለ ነው። አሁን ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስችል የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥራ እየተከናወነ ነው። ይህም ሥራ በአንዳንድ ተቋማትና አካባቢ ተግባራዊ ሲሆን፣ በተወሰኑ አካባቢዎችና ማኅበረሰቦች ዘንድ ደግሞ መዘናጋትና ደንታ ቢስነት ስሜት ማሳደሩ ይስተዋላል።
ተዘዋውረን ባየናቸው ጎዳናዎች እንደታዘብነው በተለያዩ ቦታዎች ቫይረሱ ተረስቶ ሰዎች እንደቀድሞው የእጅ ሰላምታ ሲጨባበጡ፣ ሲሳሳሙ፣ ሲተቃቀፉ አስተውለናል። በምግብ ቤቶች፣ መጠጥ ቤቶች እና በትራንስፖርት መጓጓዣ ላይ ሰዎች በተለይ ወጣቶች ሳይጨናነቁ አፍ ለአፍ ገጥመው ማውራትና መጫወት እየተለመደ መጥቷል። ይህም ወጣቶችን የማይነካ ይመስል የሚታየው መቀራረብና ንክኪ ቫይረሱ እንደሌለ ወይም ለጉዳት እንደማይዳርግ አስመስሎታል። በገሃድ እየሆነ ያለው እውነት ግን ቫይረሱ ዕድሜና ፆታ ሳይለይ ሁሉንም እየቀሰፈ መሆኑ ነው።
በመሆኑም በማኅበረሰቡ ውስጥ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ማካሄድ ተገቢ ሲሆን የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመግታት አሁንም ማኅበራዊ መራራቅ፣ እጅን በሳሙናና በውኃ በደንብ መታጠብ፣ እንዲሁም አለመጨባበጥ አማራጭ መፍትሄዎች ናቸው።
ስለሆነም እያንዳንዱ ግለሰብ፣ ቤተሰብ፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የሐይማኖት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራት፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ የጤና ባለሙያዎች፣ መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የበኩላቸውን ሚና መጫወት ይኖርባቸዋል። ሁላችንም በማንኛውም ማህበራዊ ግንኙነታችን ወቅት ርቀትን በመጠበቅ፣ ማስክ በማድረግ፣ የእጅን ንፅህና በአግባቡ በመጠበቅ እና የኮቪድ-19 ክትባት በመከተብ የቫይረስ ተጋላጭነት መቀነስ ይገባናል። በዚህም ለወረርሽኙ መዛመትም የበኩላችንን አስተዋፅኦ እንዳደረግን ልንቆጥረው ይገባል።
ዘላለም ግርማ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 17/2013