ወይዘሮ ሣራ ዘመኑ ሠናይ በጋዜጣችን ለወላጆች ምክር የሚያካፈሉ እናት ናቸው። የህክምና ባለሙያ ሲሆኑ ልጆቻቸውን አሳደገው ለቁም ነገር አብቅተዋል። ነዋሪነታቸው በአሜሪካን ሀገር ሲሆን ለወገኖቼ የተወሰነ ነገር ከልምዴ ባካፈል ብለው በማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን መልእክቶችን ያስተላልፋሉ። ለዛሬም በመምህራንና ወላጆች መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት ካከፈሉን ምክሮች ውስጥ እነሆ።
እኛ ወላጆች ከልጆቻችን አስተማሪዎች ጋር ያለን ግንኙነት ምን ያህል ነው? የልጆቻችን አስተማሪዎችስ እኛን ያውቁናል? ይሄን ጥያቄ በያላችሁበት መልሱና ይህችን መልእክት አንብቧት።
ልጆቻችን ከ0 – 8ኛ ክፍል ባሉበት ዕድሜ አስተማሪዎች እኛን በቅርብ ቢያውቁን ለልጆቻችን ከፍተኛ ጥቅም አለው። ዋነኛው ጥቅም አንድ ተማሪ ከጀርባው ስለ ትምህርቱና ስለ ስነምግባሩ ግድ የሚለውና የሚከታተለው ወላጅ እንዳለ መገንዘባቸው ነው። ይህም በአስተማሪውና በተማሪው መካከል ላለው ግንኙነት ጥሩ ተጽኖ ይፈጥራል። ከዚህ በታች እንዴት ከልጆቻችን እስተማሪዎች ጋር ቅርበት መፍጠር እንደምንችል ሶስት መንገዶች እንመልከት።
አንደኛው መንገድ ትምህርት ቤት ከመከፈቱ በፊት አስተማሪን መተዋወቅ ዕድል ከተገኘ ዕድሉን መጠቀም ነው። ለምሳሌ ብዙ ትምህርት ቤቶች የአስተማሪና የተማሪ መተዋወቂያ ቀን (Open House) ያዘጋጃሉ። በዚህም ቀን ወላጆችም እንዲገኙ ይጋብዛሉ። ይህ ቀን የልጆቻችን አስተማሪዎችለመተዋወቅ ጥሩ ዕድል ይሰጠናል። በዚህ ቀን መገኘታችንን አስተማሪዎቹም ያጤናሉ።
ሁለተኛው መንገድ ትምህርት ቤት ከተከፈተና ትምህርት ከተጀመረ በኋላ እንደ አስፈላጊነቱ ከአስተማሪ ጋር ግንኙነት ማድረግ ነው። በተለይ ልጃችን በአንድ ትምህርት ደከም ብሎ ካየን ከአስተማሪ ጋር ቀጠሮ ይዞ ሄዶ ማነጋገር በጣም አስፈላጊ ነው። የንግግራችንም ዓላማ ከአስተማሪው ጋር ተባብረን እንዴት ልጃችንን መርዳት እንደምንችል ለመመካከር መሆን ነው ያለበት። በዚህ ዓላማ አስተማሪን ስንቀርብ አስተማሪው ልጃችንን ለመርዳት ያለው ፍላጎት ይጨምራል። በዚህ አጋጣሚም ከአስተማሪው ልጃችን ስላለበት ድክመትም ሆነ ችግር የበለጠ መረዳት እንችላለን። ከዚህም ተነስተን እኛም ልጃችንን ለመርዳት የበለጠ አቅም እናገኛለን።
ሦስተኛው መንገድ ደግሞ በልጆቻችን ትምህርት ቤት አንዳንድ የወላጅን ተሳትፎ በሚፈልጉ ነገሮች ላይ ተሳትፎ ማድረግ ነው። ለምሳሌ በትምህርት ቤት ውስጥ የወላጆች ኮሚቴ ካለ እዛ ውስጥ አባል በመሆን መሳተፍ ይቻላል። ከሌለም ደግሞ ማቋቋምም ይቻላል። አስተማሪን አነጋግሮ በሚያስፈልገው መርዳትም ይቻላል። በትንሹ ደግሞ ተማሪዎች ሪፖርት ካርድ በሚቀበሉ ቀን በቀኑ ተገኝቶ በዛ ካለው አስተማሪ ጋር በመገናኘትም ከአስተማሪ ጋር ጥሩ ቅርበት መፍጠር ይቻላል። ልጆቻችንንም የኛን ተሳትፎ ሲያዩ ለትምህርታቸው የምንሰጠውን ቦታ ተገንዝበው እነርሱም በበኩላቸው ትምህርታቸውን በተገቢው መንገድ የመከታተል ፍላጎታቸው የበለጠ ሊዳብር ይችላል።
ከዚህ በላይ የተጠቀሱትን ሦስት መንገዶችንበመጠቀም ከልጆቻችን አስተማሪዎች ጋር ጥሩ ግንኙነት መፍጠር እንችላለን ይህም ለልጆቻችን የትምህርት አቀባበል ላይ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል።
አዲሱ የትምህርት ዘመን እንደመቅረቡ ለልጆቻችን ትምህርት ውጤታማነት ከመምህራኖች ጋር ተባብረን እንስራ ብለናል። ቸር ይግጠመን።
አስመረት ብስራት
አዲስ ዘመን ነሃሴ 16/2013