ዓለም ከቴክኖሎጂ የታረቀችበት ዘመን ላይ እንገኛለን፤ ሃገራትም እንደተቃኙበት የኢኮኖሚ ደረጃ የቻሉትን ማድረግ የሚችሉበትን ኃይልና አቅም አዳብረዋል:: ይህ የዓለም ነባራዊ ሁኔታ ደግሞ አነሰም በዛም በእያንዳንዱ ሃገር የየራሱ መልክ ሊኖረው የግድ ብሏል:: ለአብነት ያህል ከ50 ዓመት በፊት የነበረው የዓለም ሁኔታ ከአሁኑ በእጅጉ የተለየ ነው:: በመሆኑም ከግለሰብ አስከ ሃገር ትናንት በነበሩበት የሉም፤ ጊዜውን መምሰል አማራጭ የሌለው በመሆኑ የተሻለ ሆነው ለመገኘት ሁሉም በፊናቸው ይጥራሉ::
በዚህ እሳቤ ስፖርትን ብንገመግም በእርግጥም የከዚህ ቀደሙ ሁኔታ በጭራሽ ከአሁኑ ጋር አይመሳሰልም:: እድገቱ ከጊዜው ጋር ሊራመድ የግድ ነው፤ ካልሆነ ግን ተወዳዳሪም ስኬታማም ለመሆን አይቻልም:: የኢትዮጵያን ስፖርት ብንመለከት በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተገኘው በአንድ አትሌት በተደረገ ተጋድሎ በሮም ኦሊምፒክ ላይ ነው:: ማንም ሊክደው የማይችለው ይህ ሃቅ እንደ ጠዋት ጀምበር በሂደት እየጎላ ስለመምጣቱም ታሪክ ማስረጃ ነው:: ይሁን እንጂ እንደ ጊዜው ከተመለከትነው ባለፉት 70 እና ከዚያ በላይ ዓመታት የኢትዮጵያ ስፖርት ከሚገባው ስፍራ ተገኝቷል ለማለት አያስደፍርም::
በእርግጥ ለዚህ በርካታ ምክንያቶችና ሰበቦች ሊነሱ ይችሉ ይሆናል፤ ነገር ግን አሁን እንዳለው አይነት ሁኔታ ሲገጥም በቁጭት መብሰልሰሉ፤ ከጊዜያቸው ቀድመው የተፈጠሩ ጀግኖችም ምነው አሁን ኖረው በሆነ ለማለትም ያዳዳል::
የኢትዮጵያን ስፖርት ከምንም አንስተው በዓለም ደረጃ እንዲታወቅ ያደረጉ፣ ተጽእኖ ፈጣሪነታቸውም ከሃገር አልፎ በአህጉርና ዓለም አቀፍ ደረጃ የሆነ፣ ስፖርትን ከስፖርተኝነት አንስቶ የሚያውቁትና እስከ አመራርነት በመድረስ ብቃታቸውን ያስመሰከሩ የስፖርቱ ሰዎች በእርግጥም በዚህ ወቅት ይናፈቃሉ:: ለዚህ ደግሞ ከታላቁ ኢትዮጵያዊ የስፖርት አባት ይድነቃቸው ተሰማ ልቆ የሚነሳ ሊኖር አይችልም::
ብዙዎች የኢትዮጵያ እግር ኳስ አባት ይሏቸዋል፤ ነገር ግን እርሳቸው ለአፍሪካ ስፖርትም ብርሃን ናቸው:: ስፖርት በኢትዮጵያ እንደ አንድ ዘርፍ እንዲታይና እንዲዋቀር እንዲሁም ‹‹ኋላ ቀር›› የምትባለውን አህጉረ አፍሪካን ስፖርታዊ ቅርጽ በማስያዝ በኩል የእኚህ ሰው ድርሻ እጅግ ታላቅ ነው:: ለዚህም ነው በወቅቱ ጋዜጠኞች ‹‹የኢትዮጵያ ስፖርት መዝገበ ልሳን፤ መዘክር››እንዲሁም ‹‹የጅብራልታር ቋጥኝ›› እየተባሉ የሚንቆለጳጰሱት::
ይህ ያለንበት ጊዜ የእርሳቸውን ዓይነት የስፖርት አመራር መፈለጉ እንዲሁም አርዓያነታቸው እርሳቸውን መሰል አመራር እንዲፈጠር ለማድረግ መቻሉ ደግሞ ታሪካቸውን ለማውሳት የግድ ይላል:: ይህም ብቻ ሳይሆን ታላቁ ሰው ይህችን አለም በህይወት የተለዩት በዚህ ሳምንት ነሃሴ 13 ቀን 1979 ዓም እንደመሆኑ ስራቸውን ማውሳት አስፈላጊ ነው፤ በመሆኑም የዛሬው አዲስ ዘመን ስፖርት ማህደር ገጽ ባህርን በጭልፋ ቢሆንም ታላቁን የስፖርት አባት በጥቂቱ ሊዘክራቸው ወደደ:: ታሪካቸውን በጥቂቱ አውስተን ስማቸው ዛሬም ድረስ ከመቃብር በላይ እንዲነሳ ያደረገው ስራቸውና ለስፖርት የከፈሉት መሰዋዕትነት የሚከተለውን ይመስላል::
የታዋቂው ባለ ቅኔ ነጋድራስ ተሰማ እሸቴ ልጅ የሆኑት አቶ ይድነቃቸው የተወለዱት በ1914 ዓ.ም በጅማ ከተማ ነው:: ይሁንና እድገታቸውና የተማሪነት ጊዜያቸውን ያሳለፉት በአዲስ አበባ መሃል አራዳ ነው:: በተፈሪ መኮንን እና በዳግማዊ ምኒሊክ ትምህርት ቤቶች ሲማሩም በአእምሯዊና በአካል ብቃት ማሰልጠኛ ትምህርቶችን ፈጥኖ የመቀበል ከፍተኛ ችሎታ እንደነበራቸው ከቻምፒዮን መጽሄት ጋር ካደረጉት ቃለምልልስ መረዳት ይቻላል:: ታዲያ በጊዜው ስፖርት ከመውደዳቸው የተነሳ በአትሌቲክስ እና በብስክሌት ስፖርቶች ነበር የሚካፈሉት፤ ነገር ግን ከሁለቱም ሳይሆኑ እግር ኳስን መርጠው ከ8 ዓመታቸው ጀምሮ እስከ 37ኛ ዓመታቸው ድረስ ሲጫወቱት ቆይተዋል::
በታዳጊነት እድሜያቸው ነፍሳቸው በሚወዱት እግር ኳስ ተስባ ስማቸውን ከታላላቅ ተጫዋቾች እኩል ለማስጠራት ከሚያደርጉት ጥረት ጎን ለጎን ጽሁፎችን በማገላበጥና በማንበብ የዓለም የስፖርት መዋቅርና ተወዳጅነትን ለመረዳት ችለዋል::
በኢትዮጵያ አንጋፋ የሆነው የእግር ኳስ ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመጀመሪያዎቹ ተጫዋቾች መካከል አንዱ ይድነቃቸው ነበሩ:: በወቅቱ ክለቡን የመሰረቱት 11 ታዳጊዎች ከአርመን ኮሚዩኒቲ ቡድን ጋር ለመጋጠም በያዙት የቀጠሮ ዕለት አንድ ተጫዋች በመጉደሉ በሰፈር የሚያውቁትን ይድነቃቸውን ጋበዟቸው:: ግብዣው በቀረው ጓደኛቸው ምትክ እንዲገቡላቸው ቢሆንም ቅሉ ይድነቃቸው ጎበዝ ኳስ ተጫዋች መሆናቸውንም ያውቁ ነበር::
በጨዋታውም ቅዱስ ጊዮርጊስ የመጀመሪያ ጨዋታውን 2ለ0 በማሸነፍ ሲያጠናቅቅ አንዷ ግብ የተቆጠረችው በአዲሱ የቡድን አባላቸው እንደነበር፤ ፈለቀ ደምሴ በ2005ዓም ባሳተመው ‹‹የኢትዮጵያ እግር ኳስ ጉዞ›› የተሰኘ መጽሃፍ ይነበባል:: አሁንም ድረስ በክለቡ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጣቸው ሰው ሲሆኑ፤ ቅዱስ ጊዮርጊስ የስፖርት ክለብ በስማቸው የታዳጊዎች ውድድርና አካዳሚ ከመሰየሙም ባለፈ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ላይ ታላቁን ሰው ይዘከራል::
አጋጣሚው ይድነቃቸውን ቋሚ የክለቡ አባል ሲያደርጋቸው፤ ስፖርቱ፣ ክለቡና ተጫዋቾቹ በመልካም መነቃቃት ላይ ሳሉ ፋሺስት ጣሊያን በድጋሚ ኢትዮጵያን ወረረ:: በዚህ ምክንያት መልካም ጅማሬ ያሳየው ስፖርት መልኩን ቢቀይርም፤ ከተጫዋችነት ባለፈ በርካታ ህልም የነበራቸው አንባቢው ይድነቃቸው ግን አርፈው አልተቀመጡም:: ይልቁኑ ጠላት ከሃገር እንደተባረረ የወጠኑትን የሃገር አቀፍ የስፖርት ጽህፈት ቤት ዕውን ለማድረግ ደፋ ቀና ማለቱን ተያያዙት::
የሚረዷቸውን ሰዎች እያፈላለጉም የፌዴሬሽን እንዲሁም የውድድር ስርዓትና ደንብን ወደ አማርኛ በመተርጎም አዘጋጅተዋል:: ታዲያ በዚህ ወቅት ትምህርት ጨርሰው በተለያዩ መስሪያ ቤቶች ቢሰሩም ጥሪያቸው ከስፖርት በመሆኑ በ1936 የስፖርት ጽህፈት ቤት ሲቋቋም ስራቸውን እርግፍ አድርገው በመተው በስፖርቱ ተጠቃለሉ::
እጅግ አስደናቂው ነገር ደግሞ በጽህፈት ቤቱ የሚሰሩት በነጻ ነበር፤ በመሆኑም ሌላ ስራ መፈለጋቸው የግድ ሆነ:: ለስፖርቱ የሚከፍሉት መስዋዕትነት ቅንጣት ያህል የማያስከፋቸው የስፖርት ሰው በ1940 ዓ.ም በድጋሚ ፌዴሬሽኑ ሲቋቋም አሁንም ሌላኛውን ስራቸውን ትተው ወደሚወዱት ስፖርት ተመለሱ::
በእነዚህ ዓመታት ታዲያ ይድነቃቸውና ሌሎች በጎ ፈቃደኞች ባዘጋጁት የውድድር ደንብ አማካኝነት በክለቦች መካከል ውድድር ማድረጋቸውን አላቋረጡም:: ውድድሮች እንዳይቋረጡም በራሳቸው ወጪ ሜዳ በማስተካከል ጭምር ይሳተፉ ነበር:: ይሁንና በዚህ ወቅት ዓለም አቀፉ ደንብ ተጫዋቾች የፌዴሬሽን አመራር መሆን እንደማይችሉ የሚገልጽ በመሆኑ አቶ ይድነቃቸው ዋና ጸሃፊነታቸውን አስረከቡ::
ለስፖርት ባላቸው ጥልቅ ፍቅር የተነሳም ተሳትፏቸው ከተጫዋችነት ባለፈ ማንኛውንም ስፖርት ነክ ጽሁፍ በማንበብ በስፖርት አመራርነትም አቅማቸውን ማጎልበት መቻላቸው እንዲደነቁ ያደርጋቸዋል:: በ1952ዓም የኢትዮጵያ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን ሲመሰረትም ወደ ስፖርት አመራርነት በመመለስ ዋና ጸሃፊ መሆናቸውን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በ1995ዓም ባሳተመው መጽሄት ህይወታቸውን በዳሰሰበት ጽሁፉ አመልክቷል:: እስከ 1973 ዓ.ም ድረስም በረዳት ሚኒስትርነት እንዲሁም በኮሚሽነርነት አገልግለዋል::
እነዚህን ሁሉ ዓመታት ችግሮች ቢገጥሟቸውም በጽናት እያለፉና በእውነት ስለ ስፖርት ፍቅር እየተጉ በመሆኑ በተወዳጅነት እና በውጤታማነት ሊዘልቁ ችለዋል:: ከስራቸው ውጪ የስፖርት እና የታሪክ ትርጉም ጽሁፎችንም በማዘጋጀትና ለአመራርነት ይረዳቸው ዘንድም ራሳቸውን ኪስዋሂሊ እና አረብኛ ቋንቋዎችን በማስተማርም አርዓያነታቸውን አጉልተዋል::
አንደበተ ርቱዕና አርቆ አሳቢ መሆናቸውም ስራቸው ከሃገር አልፎ አፍሪካንም የሚዳስስ ስራን ለግማሽ ምዕተ ዓመት ተግብረዋል:: እ.አ.አ 1957 የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን መስራቾች አንዱ ሲሆኑ፤ አስተዋጽኦቸው የጎላ በመሆኑ ከ1964-1972 ድረስ የኮንፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነዋል:: ከ1972-1987 ደግሞ ፕሬዚዳንት፣ የአፍሪካ ስፖርት ምክር ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባል እንዲሁም የአፍሪካ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማህበር የክብር ፕሬዚዳንት ነበሩ:: ዓለም አቀፉ የኦሊምፒክ ኮሚቴ እ.አ.አ በ1972 በሉክዘምበርግ በነበረው ስብሰባም ለሃገራቸውና ለአፍሪካ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በማድነቅ የኮሚቴው አባል አድርጓቸዋል::
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በ1958 ዓ.ም ሲቋቋም ይድነቃቸው በፕሬዚዳንትነት ተመርጠው፤ እስከ 1972ዓም ድረስ ባሉት አራት የስልጣን ዓመታት በአመራርነት ከዚያም በኃላ በአባልነት ቆይተዋል:: ይህም ብቻ ሳይሆን በሮም፣ ቶኪዮ፣ ሜክሲኮ፣ ሙኒክ እና ሞንትሪያል ኦሊምፒኮች የቡድን መሪ በመሆን ሃገራቸውን በዓለም አቀፍ መድረክ አስተዋውቀዋል::
ይድነቃቸው ከሞራል እንዲሁም ከስፖርታዊ ጽንሰ ሃሳቦች አኳያ የሚያራምዱት እሳቤም አስተዋይነታቸውን በእጅጉ የሚያንጸባርቅ ነው:: ይኸውም የአልኮልና ሲጋራ ማስታወቂያዎች በአፍሪካ ስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎች እንዳይለጠፉ ማገዳቸውን ማስታወስ ይቻላል:: ከአፓርታይድ አገዛዝ ጋር በተያያዘም በወቅቱ በደቡብ አፍሪካ ይደርስ በነበረው የጥቁሮች ጭቆና ሃገሪቷ ከማንኛውም ዓለም አቀፍ ውድድሮች እንድትታገድ የተጫወቱት ሚና ይበልጥ ከበሬታን እንዲያገኙ አድርጓቸዋል::
የክለብና የብሄራዊ ቡድን ተጫዋች፣ አሰልጣኝ እና የስፖርት አስተዳደር አዋቂው ይድነቃቸው በስራቸው ካተረፉት ዝና እና ከበሬታ ባለፈ ከመንግስትና ከታላቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች በርካታ ሽልማቶችንም ተቀዳጅተዋል:: የኢትዮጵያን ባለዘንባባ፣ የክብር ኮከብ ባለኮርደን እና የቀይ ባህር ኒሻን ጨምሮ፤ ከጊኒ፣ ኮትዲቯር፣ ግብጽ፣ ዲሞክራቲክ ኮንጎ የክብር ሜዳሊያዎችን አግኝተዋል:: የአፍሪካ ስፖርት የበላይ ምክር ቤት የላቀ አገልግሎት የወርቅ ሜዳሊያ፣ ኢንተርናሽናል ጎልድ ሜርኩሪ፣ የአሜሪካ ስፖርት አካዳሚ አንጸባራቂ አገልግሎት ሽልማት፣ የግሪክ መንግስት የቅዱስ ባስሊዎስ የአርበኝነት ሜዳሊያ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ሽልማቶችንም በህይወት ሳሉ ወስደዋል::
ከዚህ ዓለም በሞት ከተለዩም በኋላ ፊፋ የመጨረሻውን ሽልማት የላቀ አገልግሎት የወርቅ ሜዳሊያ ለቤተሰቦቻቸው ሰጥቷል:: ካፍም ለላቀው አገልግሎታቸው ልዩ የወርቅ ሜዳሊያ ሸልሟቸዋል:: ሞሮኳዊው ንጉስም በካዛብላንካ የሚገኝን ስቴድየም በስማቸው እንዲጠራ አድርገዋል:: የተለያዩ ሃገራት መገናኛ ብዙሃንም ስራቸውን በማንሳት ዘክረዋቸዋል:: በኢትዮጵያም ክለቦች፣ ውድድሮች፣ የስፖርት ማዘውተሪያዎች በስማቸው እንዲሰየሙ ተደርገዋል::
ዘመናቸውን ቀድመው የኖሩት እኚህ ታላቅ የስፖርት ሰው ታሪካቸውና ስራቸው ቢተረክ በውስን አምድ ሊጠቃለል አይችልም:: በመሆኑም በስፖርቱ ስላበረከቱት አስተዋጽኦ በሰጡት አስተያየት ጽሁፉን እንቋጨው ::
‹‹… የኢትዮጵያን ስፖርትና መዋቅሩን ልቤ እስከተመኘበት አድርሼዋለሁ:: እኔ ራሴ ክብር፤ ሽልማት አግኝቼበታለሁ:: አልፎ አልፎ ችግር ቢቀላቀልም፤ በስፖርቱ አደባባይ በሃገርም ሆነ በውጪ ሃገር የሰላምና የደስታ ዘመናት አሳልፌያለሁ:: ዛሬም በአፍሪካና በዓለም ደረጃ ልጅ ሆኜ በጋዜጣ በማየት እመኘው የነበረውን የመሪነት ስፍራ ተቀዳጅቻለሁ:: ስፖርት የቤተሰቤን ሰላምና ፍቅር ስላላቃወሰው፤ ከ40 ዓመት በፊት ስንተዋወቅ ካገባኋት ባለቤቴና አስር ልጆቼ ጋር በሰላም እኖራለሁ:: በተሰማራሁበት መስክ ለሃገሬም፣ ለልጆቼም፣ ለራሴም የተመኘሁትን ውጤት ስላገኘሁ የሚቀረኝን እድሜ ለማህበራዊ አገልግሎት ለማዋል ከመመኘት በቀር ባለፈው የምጸጸትበት ወይም የማዝንበት አንድም ነገር የለም››::
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሃሴ 16/2013