ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረረችበት ወቅት አንዳንድ ኢትዮጵያውያን ቀዬያቸውን ለቀው ለጊዜው ራሳቸውን መሸሸግ ወደሚያስችላቸው ስፍራ ለመሰወር ያመራሉ:: በከፋ ጠቅላይ ግዛት ኮንታም አካባቢ የሆነው ይኸው ነው:: ወይዘሮ ሚኖቴ አሰሌ ወላጆቻቸው ከተሸሸጉበት ጫካ ወደቀደመው ቀዬያቸው በመመለስ ላይ ሳሉ ጣሊያኖች ያገኟቸዋል:: ‹ከየት ወዴት ነው?› ሲሉም ይጠይቋቸዋል:: ወላጆቻቸው ግን ከጣሊያኑ ጋር በምን አፍ ያውሩ፤አስተርጓሚ ቀረበ፤ቀዬው ሰላም በመሆኑ ሰላማዊ ኖሯቸውን ለመመስረት ወደ መንደራቸው በመመለስ ላይ እንደሆኑ ለጣሊያኖቹ ይነግሯቸዋል፤ ነገር ግን ጣሊያንኖቹ የተተረጎመላቸውን ይረዱ አይረዱ ባይታወቅም የወይዘሮ ሚኖቴን ወላጆች ግን ይገድሏቸዋል::
ወይዘሮዋ፣ወላጆቻቸው የሞቱት የፈረንጅ አፍ ባለማወቃቸው ነው ብለው ደመደሙ:: ስለዚህም እርሳቸው በተራቸው አግብተው ሲወልዱ ልጆቻቸውን የፈረንጅ አፍ ለማስተምር ለራሳቸው ቃል ገቡ:: በ1939 ዓ.ም የወለዷቸው ስድስተኛ ልጃቸው ጥሩነህ፣ አስር ዓመት እስኪሞላው ድረስ በዚያው በኮንታ ወረዳ ኦፓ ቀበሌ ውስጥ ምንም ዓይነት ትምህርት ቤት ባለመኖሩ በቤታቸው የቄስ ትምህርት እንዲማር በመደረጉ ከሌሎች ወንድሞቹና የአካባቢው ልጆች ጋር በመሆን ፊደል ቆጠረ::
ፍደል ቆጠራውንም ሆነ ዳዊት መድገሙን በሚገባ ካጠናቀቀ በኋላ ግን በአካባቢው የትምህርት ቤት ባለመኖሩ ጭንቅ ሆነ፤እናት ደግሞ ‹‹ልጄ የፈረንጅ ትምህርት ካልተማረ ሞቼ እገኛለሁ›› አሉ:: የወላጆቻቸው በፈረንጅ መገደል ቁጭት ስላለባቸው ‹‹ሌላ ፈረንጅ ደግሞ መጥቶ ቋንቋ የማያውቀውን ልጄን ቢገድልብኝስ!›› አሉ:: በመሆኑም ረጅም ርቀት ሄዶም ቢሆንም የፈረንጅ ትምህርቱን እንዲማር በጽኑ ሽተው ነበርና ወደጅማ ሰደዱት – የዛሬውን የህይወት ገጽታ እንግዳችን የሆኑትን አምባሳደር ጥሩነህ ዜናን::
በከፋ ጠቅላይ ግዛት፣ኮንታ ወረዳ ስር ባለች ኦፓ ቀበሌ የተወለዱት አምባሳደር ጥሩነህ፣ ትምህርታቸውን ተወልደው እትብታቸው በተቀበረበት ስፍራ ለመማር ባለመታደላቸው ምክንያት ከኮንታ በ10 ዓመታቸው ከመቶ ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት ላይ ወዳለችው ጅማ ከተማ አቀኑ:: አምባሳደሩ፣ መኪና የሚባል ነገር ያዩትም ጅማ ከገቡ በኋላ ነው::
አባታቸው አቶ ኮቾ፣ አለመማርን አጥብቀው ይቃወማሉ:: ምንም እንኳ በወቅቱ እርሳቸው በነበሩበት ቀበሌ ምንም ዓይነት ትምህርት ቤት ባይኖርም በአባታቸው ቤት ብዙ ቄሶች ደጋግመው መለስ ቀለስ ከማለታቸውም በላይ ብዙዎቹም ቄሶች አብረዋቸው ይኖሩም ነበር:: እግረመንገዳቸውን በዚያው ቤት፣ የቤቱን ልጆች ጨምሮ በአካባቢው ያሉ ልጆችንም አብረው ያስተምራሉ:: አምባሳደርም ፊደል መቁጠር የጀመሩት ከእነዚሁ ተለቅ ተለቅ ካሉት ልጆች ጋር ነው::
የአባታቸው የስም ቅያሬው
የአሁኑ የአምባሳደር ጥሩነህ አባት ስም ግራዝማች ዜና ተክለኃይማኖት እውነተኛ ስማቸው አይደለም:: ትክክለኛው የአባታቸው ስም አቶ ኮቾ አራጆ ነበር:: አቶ ኮቾ፣ ግራዝማች የተባሉበትም ምክንያት ቤተክርስትያን በራሳቸው ገንዘብ አቋቁመው ብዙ ሰዎችን ክርስትና እንዲነሱ ስላደረጉ በወቅቱ አዲስ አበባ ያሉ ሊቀጳጳስ ለንጉሱ ነግረዋቸው የግራዝማችነት ማዕረግ እንዲሰጣቸው ተወሰነ:: ይሁንና ኮቾ የሚለው ስም መለወጥ ግድ ሆነና የአባታቸው አቶ ኮቾ ስም ወደ ዜና ተክለኃይማኖት ተቀየረ:: ዜና ከሚለው ስም ፊትለፊትም የግራዝማችነት ማዕረግ ተቀመጠ:: በቃ ይኸው ነው፤ ዛሬም ድረስ ዜና የሚለው ስም የአምባሳደሩ አባት መጠሪያ ሆኖ ዘለቀ::
ለፈረንጅ ትምህርት ወደጅማ
የዛሬው ባለታሪካችን፣ በተወለዱበት በከፋ ጠቅላይ ግዛት ውስጥ ቦንጋ አውራጃ ስንዲሁም ዋካ የሚባለው የኩሎ ኮንታ ወረዳ ቢኖርም በመቶ ኪሎ ሜትር ርቀት ያሉ ቦታዎች ናቸው:: የዚያን ያህል ርቀት ከሄደ አልቀረ ደግሞ ጅማ ሊረዳው የሚችል የአባቱ ጓደኛ በመኖሩ ወደ ጅማ ይሂድ ተብለው ወደዚያው አቀኑ::
ጅማ ለፈረንጅ ትምህርት ከሄዱ በኋላ ጊዜው ሐምሌ አካባቢ በመሆኑ የሒሳብን ስሌት ለማወቅ ሲባል የማታ ትምህርት ገቡ:: ቀደም ብለውም የእንግሊዝኛን ፊደልንና መደመር መቀነስን ተማሩ:: በዚያ ወር የቀን ተማሪ እንዳይሆኑ ትምህርት ቤት የሚከፈተው ገና መስከረም ወር ላይ ነውና ያቺን ጊዜ ላለማባከን በማታው መርሐግብር ገብተው የተባሉትን አጠኑ:: ከዚህ በኋላ ልክ መስከረም ላይ ትምህርት ቤት ሲከፈት ምንም የሚቸግራቸው ነገር ባለመኖሩ በቀጥታ ሁለተኛ ክፍል ገቡ::
ብዕደማርያም ትምህርት ቤት በልዑል ብዕደማርያም መኮንን ስም ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለመማር በትምህርት ቤቶች ከ10ኛ እስከ 11ኛ ክፍሎች ውስጥ የላቀ ውጤት ያመጡትን ተማሪዎች በመመልመል በመምህርነት ሙያ የሚመድብ ነው:: በወቅቱ በዚህ ትምህርት ቤት መማር ማለት ዩኒቨርሲቲ እንደመግባት የሚቆጠር ነው::
አምባሳደር ጥሩነህ፣ ከጅማ 11ኛ ክፍል አጠናቀው ወደአዲስ አበባ የመጡ ሲሆን፣ በዚህ ትምህርት ቤት እንዲማሩ ተደረገ:: ይሁንና ይህ ትምህርት ቤቱ የሚያስመርቀው ለመምህርነት በመሆኑ በመምህርነት ሥራ መሰማራቱ ደስ አላሰኛቸውም:: ስለዚህ ከዚህ ትምህርት ቤት 12ኛን ክፍል ከተማሩ በኋላ ወደመምህርነት ላለመሄድ ሁለት ነገሮችን የግድ ማቅረብ ይጠበቅባቸው ነበር:: የመጀመሪያ ማትሪክ ማለፍ ሲሆን፣ ሁለተኛ ደግሞ እነርሱ ስላበሏቸውና ስላስተማሯቸው 500 ብር መክፈል ነበረባቸው:: ማትሪክን በማለፋቸው የመጀመሪያውን ጉዳይ ማሳካት ቻሉ:: ነገር ግን ብሯን ከየት ያምጧት:: ስለዚህ እሷን ብር ለማግኘት ሲሉ ወጥተው ለአንድ ዓመት በመምህርነት ማገልገል ግድ ሆነባቸውና አገለገሉ:: የተቀጠሩትም በ160 ብር የወር ደመወዝ ነበር:: ይሁንና ከዚህች ደመወዝ አጠራቅመው እንኳ 500 ብሩን ለመክፈል ቀርቶ ለወር ፍጆታቸውም በቂ ባለመሆኗ በዚያው ወቅት አንድ ሌላ ሥራ የማግኘት ዕድል አጋጣማቸው::
መምህርም ባለእዳም ላለመሆን
እንደዕድል ሆነና በገንዘብ ሚኒስቴር ስር በሚገኝ አንድ ተጠሪ መስሪያ ቤት ውስጥ በአርሶ አደሩ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ ግብር ለመጣል መስሪያ ቤቱ ሰው በመፈለጉ ባወጣው ማስታወቂያ ላይ ተወዳድረው በማለፋቸው ለሥራው ወደጅማ ሄዱ:: በአዲሱ ሥራቸው የወር ደመወዛቸው 200 ብር ሲሆን፣ በቀን ደግሞ የውሎ አበል እየተባለ የሚሰጣቸው አራት ብር አለ:: በየቀኑ የሚያገኟት አራት ብር ለኑሯቸው በቂ ስትሆን፣ 200 ብሩን ደግሞ በማጠራቀም እዳቸውን ለዩኒቨርሲቲው ለመክፈል ረዳቸው:: ጅማ ተመድበው የሠሩትም ስድስት ወር ያህል ብቻ ሲሆን፣ እዳቸውን በመክፈላቸው ተመልሰው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገቡ:: መምህርም ባለእዳም ላለመሆን ታግያለሁ ሲሉ በማሸነፋቸው ተደሰቱ:: በመጨረሻም አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ኢኮኖሚክስ ትምህርት በመማራቸው የትምህርት መስካቸውን ቀየሩ::
ከዩኒቨርሲቲ ማጠናቀቅ በኋላ እናትና አባታቸውን በሞት በማጣቸው ሥራ ለመምረጥ ዕድሉ አልነበራቸውም:: በወቅቱ ሦስት እህቶችና ሰባት ወንድሞች አሏቸው:: በመሆኑም ሥራ ላለማጣት ሲሉ ፈጥነው ገንዘብ ሚኒስቴር ተቀጠሩ:: ለዚህም ምክንያታቸው ገና ከመመረቃቸው አስቀድሞ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ሳትመረቁም ቢሆን አስቀድሜ ሥራ አስጀምርችኋል በማለቱ ነበር:: ይሁንና ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱን ከተቀላቀሉ በኋላ ሥራውን አልወደዱትም::
በዚህ መሃል ሌላ ሥራ እየፈለጉ ባሉበት ሰዓት በ1960ዎቹ ካዱ በሚል ምህጻረ ቃል በሚታወቀው የጭላሎ ግብርና ልማት ግብርናን ለማዘመን በሲውድን ዓለም አቀፍ ተራድኦ ድርጅት ድጋፍ (ሲዳ) እና በኢትዮጵያ መንግሥት በጋራ የሚሠራ ፕሮጀክት ውስጥ ሥራ አገኙ፤ ሥራውም ምርምር ከመሆኑም በተጨማሪ ደመወዙም በጣም ትልቅ የሚባል ዓይነት በመሆኑ ደስተኛ ነበሩ:: በዚህ ሥራ አምስት ዓመት ያህል እንደቆዩ አብዮቱ መጣ::
አብዮቱ
ባለታሪካችን፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እያሉ ስለአብዮቱ አንዳንድ እንቅስቃሴዎችን ጀምረው ነበር:: ወደ አርሲም ከሄዱ በኋላ ሥራውንም ይኸኛውን የአብዮቱን ዓላማ ለማሟላት ምቹ ሁኔታን ስለሚፈጥርላቸው ደስተኛ ሆኑ:: ነገር ግን እንደሄዱ ለውጡ በመምጣቱ ተከፋፈሉ:: አብዮቱ ከመጣ በኋላ መጥፎ ነገሮች ይከሰቱ ጀመር:: በተለይ እርስበእርስ መጣላት፣ ከመንግሥትም ጋር መጣላት ሆነ:: እርሳቸውም በወቅቱ ማርክሲስት ሊኒንስትን ነበር አጥብቀው ይከተሉ የነበረው:: ይሁንና የእርሳቸው ፓርቲ በጣም ጥቂት ሰዎች ሲሆኑ፣ እነርሱም ምሁራን ናቸው:: መንግሥትም የእነርሱ ፓርቲ ብዙም ተጽዕኖ አያመጣም በሚል ቸል ቢለውም ሌሎቹ ፓርቲዎች ግን ተጽዕኖ ያደርስባቸዋል:: በወቅቱ ኢህአፓ ውስጥ ግባ ሲባሉ አልገባም በማለታቸው ተጽዕኖ ይፈጥሩባቸው ነበር:: በዚህ ጉዳይ አብዮታዊ እርምጃ ይወሰድበት እስከማለት ተደርሶባቸው ነበር:: በዚህ ሁኔታ አሰላ መቆየት ስላልፈለጉ ከአካባቢው ወጡ::
አዲስ አበባ ከመጡ በኋላ ግን የሥራ መለቀቂያውን ይዘው ባለመምጣታቸው የሚቀጥር ጠፋ:: አርሲ መሄድ የሚፈልግ ስለሌለ ለእርሳቸው መልቀቂያ ሰጥቶ ማሰናበት አልተቻለም:: ምክንያቱም በአርሲ ቆይታቸው በጣም ብዙ ሥራ ሠርተዋል:: በአርሲ ስንዴ በሄክታር ይገኝ የነበረው 15 ኩንታል ብቻ ነበር፤ ከተሠራው ሥራ በኋላ ግን በሄክታር 30 ኩንታል ሆነ::
ከአርሲ ከተመለሱ በኋላ ለወራት ያህል ያለሥራ ተቀመጡ:: በኋላ ላይ ግን ልክ የካዱ ዓይነት ፕሮጀክት በ1960ዎቹ መጨረሻ ላይ በዓለም ባንክ ድጋፍ የዋዱ የወላይታ ግብርና ልማት እቅድ ፕሮጀክት ሲተገበር እርሳቸው ልምዱ ስላላቸው ወደ ወላይታ ሄዱ:: ወደዚያ አካባቢ መሄዳቸው አንድም ወደ ትውልድ አካባቢያቸው ቅርብ መሆን ስለሚያስችላቸው ተደሰቱ:: አርሲ ላይ የተቋቋመው ፕሮጀክት በሲውዲኖች ሲሆን፣ ወላይታ ላይ ግን ያቋቋመው የሲውድኖቹን አይቶ በዓለም ባንክ ድጋፍ መንግሥት ነበር:: ነገር ግን ዎርልድ ባንክ ደግሞ ሰዎቹን ያመጣው ከኬንያ እንዲሁም ከእንግሊዝ ነው:: እንግሊዞች ከኬንያ የላኩት ገበሬዎችን እንጂ ኤክስፐርቶችን አይደለም:: የሲውድኖቹ ግን ትክክለኛ ኤክስፐርቶች ናቸው:: ደግሞም በሥራቸው በኩል በእርግጥም ቁርጠኞች ናቸው:: ኢትዮጵያውያኑንም የሥራ ዲስፒሊንና ሙያን በአግባቡ አስተምረዋቸዋል:: አምባሳደር፣ ወላይታ ሲሄዱ አርሲ የሠሩትን ግልባጭ ስለሆነ በሥራው አልተቸገሩም:: ግን ብዙም አልቆዩም፤ የዓለም ባንክ ድርጅት በኢትዮጵያ በነበረው የሰብዓዊ መብት ጥሰትን ምክንያት በማድረግ ይረዳ የነበረውን ገንዘብ አቆመ::
ያም ባይሆን ዋዱ የካዱን ኮርጆ የተቋቋመ በመሆኑ ቀጣይነቱ አጠራጣሪ መሆኑን እርሳቸው ያውቁ ነበር:: አርሲ ያለው ችግር ከወላይታ ጋር የሚመሳሰል አይደለም:: አርሲ ብዙ እንዲያርስ ነበር ሲያደርጉ የነበረው፤ ወላይታ ሲመጣ ደግሞ መሬት እንደልብ አይደለም፤ ስለዚህ የእርሻ ነገር ብዙ ርቀት አያስኬድም ሲሉ ነበር፤ በመሃል ግን እርሳቸውም አካባቢውን ጥለው ወጡ::
ሥራ መፍታትና የሞት አዋጅ
ከወላይታ ሥራ ለቀው ከወጡ በኋላ ለተወሰኑ ጊዜ ያለሥራ ተቀመጡ፤ በአንድ በኩል ሥራ መፍታቱ በሌላ በኩል ትገደላለህ መባሉ ሰላም የሚሰጥ ነገር አልሆነም:: እርሳቸው በአገሪቱ ካሉ በአንዱ ፓርቲ ውስጥ የነበሩ ሲሆን፣ ደርግ ደግሞ በተለያየ ነገር ውስጥ ያሉትን ወደ አንድ ብትመጡ በሚል ሐሳብ አቀረበላቸው:: ወደውጭ አገር ሄደውም ዲፕሎማሲ መማር እንደሚችሉ ስለገለጹላቸው ይህ ለአምባሳደር ትልቅ ዕድል ሆነላቸው:: ምክንያቱም እርሳቸው አንደኛ ሥራ ፈት ናቸው፤ ሁለተኛ ደግሞ ይገደል የሚል አዋጅም ወጥቶባቸው ነበርና ጉዳዩን በቸልታ አላዩትም:: ይልቁኑ ዕድሉን ቶሎ ብለው መጠቀም ፈለጉ:: በወቅቱ ከአገር መውጣቱ ለእርሳቸው ከሞት መሸሽም ጭምር በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው:: ደርግ ግን በእርሳቸው ላይ ዕርምጃ በተገኘበት ይወሰድበት መባሉን አያውቅም ነበር::እርሳቸው ሄደው ከነበረበት ጀርመን (በወቅቱ ከምሥራቅ ጀርመን) የዲፕሎማሲ ትምህርት የስድስት ወር ኮርስ ወስደው ሲመለሱ ዕርምጃ ይወሰድባቸው በሚል በሊስት ስም ዝርዝራቸው የሰፈሩ ጓደኞቻቸው ሁሉ ደርግ ገድሎ አጠናቋል::
እርሳቸው በመጀመሪያው ዙር ወደ ጀርመን ከመሄዳቸው በፊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ የተመረቁና እንደገና የዲፕሎማሲ ኮርስ የወሰዱ በመሆናቸው ተፈላጊ ሆኑ፤ በዚህም የትምህርት ዝግጅታቸው መሰረት ኢኮኖሚክስ መምሪያ ገቡ:: በዚህ መስሪያ ቤት ለሁለት ዓመት ከሠሩ በኋላ በወቅቱ በጀርመን የኢትዮጵያ አምባሳደር የኢኮኖሚ አማካሪ በመሆን እንደገና ወደ ጀርመን ተመልሰው ሄዱ:: በዚያው ወደ ስድስት ዓመት ቆዩ::
ቤተሰብ ምስረታ
ጀርመን ለሁለተኛ ጊዜ በሄዱበት ወቅት ከአንዲት የዩኒቨርሲቲ መምህርት ከሆነች ጀርመናዊት ጋር ተዋወቁ፤ በተዋወቁ በሁለት ዓመት ውስጥ ደግሞ የጋብቻ ጥያቄ አቅርበውላት የውሃ አጣጭያቸው አደረጓት:: በጀርመን አንድ ዓመት ያህል ከቆዩ በኋላ ተያይዘው ወደኢትዮጵያ መጡ:: ባለቤታቸው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ረዳት ፕሮፌሰር ሆና ፊዚካል ኬሚስትሪ ማስተማር ጀመረች፤ በቆይታቸውም ልጅ ወለዱ፤ መኖሪያ ቤትም ሠሩ:: ነገር ግን ይህ መልካም የሆነ ኑሯቸው ቀጣይ መሆን አልቻለም::
ልክ ኢህአዴግ ወደአዲስ አበባ ሲገባ እርሳቸውንና ባለቤታቸውን ወይዘሮ እንዲሁም ልጃቸውን ወደ ጀርመን ለመሸኘት ጀርመኖች ወደቤታቸው መጡ:: ይህን አካሄድ አልወደዱትም፤ ጀርመኖቹ ከቤታቸው ድረስ መጥተው ጀርመናዊት ባለቤታቸውንና እርሳቸውን ከሚወስዱ አስቀድመው ባለቤታቸውን እርሳቸው ራሳቸው መሸኘት አለብኝ ሲሉ ወሰኑ::
ይህ ሁሉ ሲሆን ባለቤታቸው ምንም አልሰሙም:: በወቅቱ ደግሞ እርሳቸው በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስር ወደውጭ የሚሄደውን የውጭ አገር ዜጋ ሁሉ በፊርማቸው እንዲወጡ የሚፈቅዱት በበላይ አለቃ ትዕዛዝ እርሳቸው ነበሩና ይህን ሥራውን ጥለው የትም መሄድ አልፈቀዱም:: ለዚህ ምክንያታቸው ደግሞ የውጭ አገር መንግሥታት ከደርግ ጋር ስምምነት ነበራቸው፤ ይኸውም ኢህአዴግ አምቦን ካለፈ የውጭ አገር ዜጎች የሆንን በቻርተር አውሮፕላን ወደየአገራችን እንድንሄድ ትፈቅድልናለህ የሚል ስምምነት ነበር:: የኢትዮጵያ መንግሥት ደግሞ በዚህ ተስማምቷል:: ይህንን ጉዳይ ደግሞ እየፈረሙ የሚያስወጡት እርሳቸው ነበሩ::
ለዚህም ነው ባለቤታቸው እንዳይረበሹ ጦርነት እየመጣ ነውና ወደአገርሽ ግቢ ማለትን ያልፈለጉት:: ልክ አምቦን አለፉ የሚል መረጃ ሲሰሙ ግን ጊዜ አልወሰዱም:: በአንድ ቀን ውስጥ ትኬት ይቆርጡና ባለቤታቸውንና ልጃቸውን ‹‹ነገ ወደጀርመን ትሄዳላችሁ›› ይሏቸዋል:: በማግስቱ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ እንደደረሱ ‹‹እባክሽ ይቅርታ አድርጊልኝ፤ ጦርነቱ እዚህ ደርሷል፤ ያልነገርኩሽ ደግሞ ትረበሽያለሽ በሚል ነው›› ብለው ሲሸኟት፤ ‹‹ይህ እንዴት ይሆናል!?›› በሚል ተጣሉ:: ‹‹እኔን አላመንከኝም ማለት ነው!?›› በሚል አኮረፉ:: በዚህም ልባቸው ተሰብሮ ወደአገራቸው ጀርመን ገቡ:: ይህ ጉዳይ ለመፋታታቸው ምክንያት ሆነ:: ከባለቤታቸው ጋር ምንም እንኳ ቢፋቱም አሁንም ድረስ ይጠያየቃሉ:: ከዛሬ ሰባት ወር በፊትም አዲስ አበባ ነበሩ:: ከልጃቸው ጋርም በየቀኑ ይደዋወላሉ::
የኢህአዴግ መግባት ለፍቺያቸው ምክንያት
ኢህአዴግ ብዙ ሰዎችን እንዲሁ ደርሶ መጠራጠር ያበዛል:: ስለሰዎችም ማጥናትን ያበዛል:: ይሁንና አምባሳደር ከእነዚህ አካላት ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነትም ስላልነበራቸው ሰዎችን የመከታተላቸውን ሥራ እምብዛም ከቁጥር አይጽፉትም ነበር፤ ነገር ግን አንዴ ክንፈ የተባለው የኢህአዴግ የደህንነት ሰው ወደእርሳቸው ስልክ ይደውልና ‹‹እየሠራህ ያለውን ሥራ እናውቃለን፤ በዚያው ቀጥል፤ ሰዎቹን የማስወጣት ሥራ ላይ እክል ቢያጋጥምህ የእኔን ስም ንገራቸው›› አለ:: እርሳቸው ግን ክንፈ ማን እንደሆነ የሚያውቁት ነገር የለም፤ እንዳጋጣሚ ሆኖ ደግሞ የኢህአዴግ መግባትን ተከትሎ በተፈጠረው ረብሻ ምክንያት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ውስጥ ያሉት ብቻቸውን ነበር:: የውጭ አገር ዜጎች ወደ አገራቸው የሚመለሱት እርሳቸው በሚፈርሙት ፊርማ ነው:: ስለዚህ እርሳቸው ከመስሪያ ቤቱ መጥፋት የለባቸውም፤ አምባሳደሮቹ ይመጣሉ ይፈርሙላቸዋል:: አንድ ቀን ግን በመስሪያ ቤቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ የተገኙት እርሳቸውና አንድ የጥበቃ ሠራተኛ ብቻ ነበሩ::
እርሳቸው ልክ ኢህአዴግ እንደገባ ያለምንም መንገላታት ከባለቤታቸው ጋር ወደ ጀርመን መሄድ ይችሉ ነበር:: ጀርመኖቹም ቢሆኑ ብዙ ለምነዋቸዋል:: እርሳቸው ግን ያስቀደሙት አገርን እንጂ ትዳርን ባለመሆኑ የተጣለባቸውን አደራና ኃላፊነት ወደጎን መተውን አልወደዱም:: የሚወዷቸውን ባለቤታቸውንና ልጃቸውን ተለይተው ከባድ የተባለውን ጊዜ ለመጋፈጥ አላቅማሙም:: ሥራ ከተባለ ሁሉም የየራሱ የሥራ ድርሻ ነበረው፤ ነገር ግን ነፍሱን በማስቀደሙ በቤቱ ተከቷል፤ እርሳቸው ግን አገሪቱ የጣለችባቸውን ኃላፊነት ለመወጣትና የውጭ አገር ዜጎች ለመውጣት ሲፈልጉ ወደውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሚመጡበት ጊዜ የሚፈርምላቸው አጥተው ቢቸገሩና በዚህ መሃል አደጋ ቢያጋጥማቸው የሚጠፋው የኢትዮጵያ ስም ነው በሚል ብቻቸውን ሆነው ከሥራ ገበታቸው ዞር ሳይሉ በቁርጠኝነት ሥራቸውን ሲተገብሩ ነበር::
በወቅቱ ዶክተሯን ባለቤታቸውን ይዘው ወደ ጀርመን ቢያቀኑ በምሥራቅና በምዕራብ ጀርመኖች መካከል ከፍተኛ የሆነ ፉክክር በመኖሩ እርሳቸውም ሆኑ ባለቤታቸው ትልቅ ስፍራ ተሰጥቷቸው በከፍተኛ ደመወዝ ሥራ መሥራት እንደሚችሉ ቢያውቁም እንዲሁም ከባለቤታቸውና ከልጃቸው ጋር የሰመረ ህይወት መምራት እንደሚችሉ ቢረዱም እሱን ግን አልመረጡም፤ ብሞትም ብቆስልም ለአገሬ ቅድሚያውን መስጠት አለብኝ በሚል በየዕለቱ የእርሳቸውን ዕርዳታ በመሻት ወደውጭ ጉዳይ ለሚመጡ ደንበኞች ተገቢውን መስተንግዶ እያደረጉ ይሸኟቸው ነበር::
በወቅቱ የነበራቸው ዕድል በጀርመን ጥሩ ኑሮ መኖር ብቻ ሳይሆን በአገራቸው ኢትዮጵያ ደርግ የኮሚኒስት ደጋፊ ነውና ያንን ክደው ወደጀርመን ቢያቀኑ ኖሮ በጣም ከፍተኛ ደመወዝ ተከፋይ ሊሆኑ እንደሚችሉም ያውቃሉ፤ ግን አላደረጉትም:: እንደዛ ማድረግ ከአገር ክህደት አይነጠልም በሚል ሥራቸው ላይ አተኮሩ:: ከፍተኛ ተኮስ በአዲስ አበባ ውስጥ እየተካሄደም ፈረንጆቹ ወደእርሳቸው መምጣታቸውን አላቋረጡምና ሥራውን ምንም ዓይነት የተኩስ እሩምታ ሳይበግረው ማከናወን ቀጠሉ::
በዚያን ወቅት ኢህአዴግ አዲስ አበባ የገባው በዕለተ ማክሰኞ ሲሆን፣ በዋዜማው ሰኞ ዕለት በአዲስ አበባ ከፍተኛ ተኩስ እንደነበር ያስታውሳሉ:: ተኩሱ ደግሞ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም ወደውጭ በሚወጡበት ጊዜ ጠባቂዎቹን ወጣ ብለው ቅኝት እንዲያደርጉ አስቀድመው ልከው ነበር:: እርሳቸው ወደውጭ እንደወጡ ጀነራል ተስፋዬ ገብረኪዳን ተሹመው ነበርና ልክ እንደተሾሙ ‹ጦርነቱ ቆሟል› ሲሉ አወጁ::
በፕሬዚዳንት መንግሥቱ የተላኩ ኃይሎች ሲመለሱ እነዚህ ኃይሎችና የጀነራል ተስፋዬ ጠባቂዎች ቤተ መንግሥቱን ያዙ:: በዚህ ሰዓት አምባሳደር ጥሩነህ ብቻቸውን ቢሯቸው ውስጥ ነበሩ:: ያለው አንድ ጥበቃ ብቻ ነው:: በወቅቱ በእርሳቸው ቢሮ የጣሊያን አምባሳደር ነበሩ:: እኚህ የጣሊያን አምባሳደር ተቀምጠው የሚመጡ ብዙ ጣሊያውያንን እያስወጡ ስለነበር በቆይታቸው እየተጨዋወቱ ነበር::
የኢህአዴግ ኃይሎች ከባባድ መሳሪያችን በመያዝ ሰተት ብለው ወደቤተ መንግሥት በሚያቀኑበት ወቅት የፕሬዚዳንት መንግሥቱ ጠባቂዎች አትዋጉ ስለተባሉም ዝም ሲሏቸው የጀነራል ተስፋዬ ግን ይከለክሏቸው ያዙ:: በዚህ መሃል ተኩስ ተጀመረ:: ለካ በወቅቱ የጣሊያን አምባሳደር የደርግ ከፍተኛ አመራሮችን በቤቱ ሸሽገው ነው ወደእርሳቸው የመጡት::
በዚህ መሃል ኢህአዴግ ከሱ ፈቃድ ውጪ አውሮፕላን እንዳይንቀሳቀሰ አዘዘ:: ፈረንጆቹ ደግሞ ለመውጣት ይችሉ ዘንድ ወደእርሳቸው እየመጡ ነበር፤ ቢፈቅዱላቸውና ቢበሩ አውሮፕላኑ ሊመታ ይችላል የሚል ስጋት ሰቅዞ ያዛቸው:: የድሮው መንግሥት ደግሞ መፍቀድ ትችላለህ ብሎ ፈቅዶላቸዋል:: አዲሶቹ ኢህአዴጎች ደግሞ አውሮፕላን እንዳይንቀሳቀስ ብለው አዘዋል:: ሊያማክሩት የሚችል አካል ባለመኖሩ ግራ ግብት አላቸው:: ስለዚህ አንድ አቋም ያዙ፤ ‹እንዲወጡ ባላደርግ ይሻለኛል› አሉ፤ ከሚሞቱ ቢሰነብቱ የሚለውን መረጡ፤ደግሞም የመጪዎቹን ትዕዛዝ መቀበሉ አማራጭ ነው ወደሚለው አዘነበሉ:: ምክንያቱም ትዕዛዙን ባይፈጽሙ ሊፈርዱባቸው የሚመጡ መሆናቸው እሙን ነው:: የድሮዎች ቢያንስ ትዕዛዝ ለመስጠት የሚችል አንድም ሰው እንኳ በአጠገባቸው የለም:: ስለዚህ ‹የመጪዎቹን ብቀበል ይሻለል፤ አውሮፕላኑ ቢመታ የሚጠለሸው የኢትዮጵያ ስም ነውና ባልፈርምላቸው ይሻላል› በሚለው ወሰኑ:: በዚህ ውሳኔ ጸንተው እያሉ አንደኛው የራሺያ አምባሳደር አትወጡም ስላሏቸው ‹እኔ ከኢህአዴግ ፈቃድ አመጣለሁ› አሏቸው፤ እርሳቸውም ቀበል አድርገው ‹ኢህአዴግ የት ነው ያለው?› ሲሉ ይጠይቋቸዋል:: ደብረዘይት መኖሩን ይነግሯቸዋል:: ይሁን እንጂ አስር ዓይነት ትዕዛዝ ቢመጣ ሐሳባቸውን እንደማይቀይሩ ይነግሯቸዋል:: ሰውዬው ለጊዜው ፎከሩ፤ ገሚሱም አንገታቸውን ይዘው ሊያንቋቸውና ሊያስፈርሟቸው ሞከሩ::
ኢህአዴግ ከገባ በኋላም በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኛ ሆነው ቆዩ:: ኢህአዴግ ውጭ አገር ኤምባሲዎችን መክፈት ቢፈልግም ሄዶ በዚያው የሚቀር ሰው ነው ያለው የሚል ስጋት ነበረበት:: ምክንያቱም አብዛኛዎቹ የደርግ ሰዎች በመሆናቸው የፓርቲም አባል ናቸው የሚል ስጋት ነበረውና ነው::
እርሳቸውን ግን አዲስ ኤምባሲ በደቡብ ኮሪያ እንዲከፍቱ ወደዚያው ላኳቸው:: ገንዘብ ይዘው ሄደው ከፈቱ፤ ወደስፍራውም አምባሳደር ሾመው ላኩ:: በቀጣይም ኢህአዴጎች ወደውጭ አገር የሚልኩ ሁነኛ ሰው ማግኘት ፈለጉ:: የተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ ነበርና እርሳቸውን ሂድ አሏቸው:: አቶ መለስ የተባበሩት መንግሥታት ለኤርትራ እውቅና ይስጥ የሚል ደብዳቤ ጻፉ:: በዚህ ጊዜ አፍሪካውያኑ በጣም ጮሁ:: ይህ የአፍሪካን መርህ የሚጻረር ነው ሲሉም ኮነኑ:: የአፍሪካ መርህ ደግሞ አፍሪካውያን ነፃ በወጡበት ጊዜ የያዙትን ድንበር አስጠብቀው ሉዓላዊነታቸውን መቀጠል አለባቸው የሚል ነው::
ከተባበሩት መንግሥታት ሰብሰበባ መልስ ተጠርተው ወደጋና ሄደው የአምባሳደሩ ተጠባባቂ ጉዳይ ፈጻሚ እንዲሆኑ ላኳቸቸው:: የአምባሳደሮች አማካሪ በመሆን በ835 ብር ለ15 ዓመታት አገልግለዋል:: በወቅቱ ከ835 ብር በላይ ተከፋዮች ተሹዋሚዎች ናቸው::
ኒዮርክም የቆየሁት በአማካሪነት ነው:: በኋላ ላይ ግን ኢህአዴግ ለሁለት ሲሰነጠቅ ከአገር ቤት ካሉት ይልቅ ውጭ አገር ያሉትን ማመን ስለጀመሩ ነው አምባሳደር መሆን የቻሉት:: በአምባሳደርነትም ያገለገሉት ምክትል ሆነው በሄዱበት እዚያው ኒዮርክ ነው:: አምባሳደር ሆነው ሦስተት ዓመት እዚያው ቆዩ:: ከኒዮርክ መልስ በጡረታ ሳሉ በተለያዩ ግብረ ሰናይ በሆኑ ድርጅቶ ውስጥ በአማሪነት መሥራት ጀመሩ::
ኮሚሽነርነት
አንደ ቀን ድንገት ስልክ ከአንድ ቢሮ ተደወለላቸው:: የተደወለው ከፓርላማ እንደሆነ ከወዲያኛው ጫፍ የሚያዋራቸው ሰው አሳወቃቸው:: በወቅቱ መኪና በማሽከርከር ላይ ነበሩና ጉዳዩን አጠር ለማድረግ በማሰብ ‹‹ምን ልታዘዝ?›› ይላሉ:: ደዋይዋ፣ ‹‹እርስዎ የሰበዓዊ መብት ዋና ኮሚሽነር አንዲሆኑ በሰዎች ተጠቁመዋልና ኮሚሽነር ለመሆን ፈቃኛነትዎን አፈ ጉባኤ ተሾመ ቶጋ እንድጠይቅዎ አዘውኝ ነው ይላሉ::
እንዲህ ሲባል ቀልድ ቢጤ ነበር የመሰላቸው፤ ለማንኛውም ግን ‹እሺ!› አሉ:: ጉዳዩ ቆየት ከማለቱ ጋር ተያይዞ እርሳቸውም ረስተውት ባለበት ጊዜ በድጋሚ ጸሐፈዋ በመደወል ‹‹ቃለመመጠየቅ ሊደረጉ ነውና እዚህ እዚህ ቦታ ይገኙ›› ይሏቸዋል:: እርሳቸውም ከተጠቆሙት መቶ ያህል ውስጥ አንዱ ናቸውና ለቃለ መጠይቅ ቀረቡ:: ከብዙ ቆይታ በኋላ ለቃለ መሃላ ወደፓርላማ ቀርበው ያለምንም ተቃውሞ ሹመቱን በመሃላ ተቀብለው ተመለሱ::
በጊዜው ኮሚሽኑን ሲረከቡት ቤቱ ባዶ ነው ማለት ያስደፍራል:: በወቅቱም የሠራተኛው ቁጥር 70 ያህል ብቻ ነበር:: 70 ሰው ደግሞ ለመቶ ሚሊዮን ያህል በጣም ጥቂት ነበር:: ቢሮ አዲስ አበባ ብቻ እንጂ በሌሎቹ የአገሪቱ ክፍል ቅርንጫፍ የሚባል የለውም:: ስለዚህም የመጀመሪያ ሥራቸው ጥናት በማካሄድ ሌሎች ክልሎች ላይም ቅርንጫፍ እንዲከፈት ማስደረግ ነው:: የሰው ቁጥርም እንዲጨመር ለምክር ቤቱ ባቀረቡት መሰረት ፈቀዱላቸው:: ይህን መሰል ሥራ እየሠሩ ባለበት የ2002 ምርጫ መጣ::
በምርጫ ወቅት ደግሞ በተሻለ መንቀሳቀስ ስለፈለጉ ሁሌ ፈረንጆች እየመጡ በመታዘብ ስም እንዳሻቸው እንዳያደርጉ በሚል ምርጫውን በኮሚሽኑ አቅም ለመታዘብ አሰቡ፤ ያለው የሰው ኃይል ግን ጥቂት በመሆኑ በየዩኒቨርሲቲው በመደወል መምህራንና ተማሪውን ታዛቢ ለማድረግ አሰልጥነው እንዲታዘቡ አደረጉ፤ ኮሚሽኑ ትልቅ ተቋም የሆነ መሰለ::
ያጠናቀሩት የምርጫ ሪፖርት በበረከት
ስምኦን መከልከሉ
አቶ በረከት የምርጫውን ሪፖርት ማሳተም የለብህም አሏቸው:: እርሳቸው ደግሞ የማያሳትሙ ከሆነ እንደሚለቁ አስታወቁ:: በዚህ ሰዓት የውጭ ጉዳይና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ ኃይለማርያም ጠርተዋቸው ቢለቁ ይሻላል ይሏቸዋል:: በዚህ ሰዓት በጣም ተናደዱ፤ አለቀሱም:: አንድ ሰው ልቀቅ ስላለ ብቻ ለምን እለቃለሁ ሲሉም አዘኑ:: ግን ደግሞ አቶ ኃይለማርያም ልቀቅ ስላሏቸው ምናልባት በደቡብነታቸው በእርሳቸው ላይ ሌላ ነገር ከሚያመጡባቸው ብለቅ ይሻላል ወደሚል ውሳኔ ላይ ደረሱ::
ነገር ግን በዚህ ሐሳብ ውስጥ እያሉ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት እንዲያውም ተጨማሪ ሥራ እንዲሠሩ ሲፈለጉ፤ ልቀቅ የመባላቸው ጉዳይ የአንድ ሰው ያውም የበረከት ሸፈጥ መሆኑን በመረዳታቸው ለመልቀቅ ያዘጋጁትን ወረቀት ቀደው ጣሉት:: በፊትም ቢሆን ለአቶ ኃይለማርያም ሲሉ ነበር ልቀቅ መባላቸውን ተቀብለው ሊለቁ የነበረው:: ይህ የአቶ በረከት ሴራ በህወታቸው ያዘኑበት ጊዜ ሆኖ ሁሌ ያስታውሱታል::
በዚያው ልክ ደስ የተሰኙበትም ጊዜ አለ፤ በሰብዓዊ መብት ኮሚሽነር ሆነው በሠሩበት ጊዜ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ሌጋል ኤይድ የሚል ሲሆን፣ ይኸውም ከየዩኒቨርሲቲዎቹ ጋር በመሆን ኮሚሽኑ ገንዘብ እየሰጠ የየዩኒቨርሲቲው የህግ ምሁሩ ደግሞ ለተከሰሰው ድሃ ግለሰብ ጥብቅና በመቆም እንዲሟገት ማድረጋቸው ነው:: እያንዳንዱን ዩኒቨርሲቲ እየዞሩ የሕግ ድጋፍ ለደሃው ተከሳሽ በጥብቅና በኩል እንዲደረግ በመጠየቃቸው በአሁኑ ወቅት እስከ መቶ ሺህ ለሚሆኑ ሰዎች በህግ ጉዳይ በማገለገል ላይ ናቸው:: በየትኛውም ፍርድ ቤት ሄደው ጠበቃ ይሆኗቸዋል:: የዚያን ያህል ሰው በጥብቅና የተሻለ ድጋፍ እንዲያገኝ በማድረጋቸው በጣም ደስተኛ ናቸው::
መልዕክት
አምባሳደር፣ ቀደም ሲል በአጼ ኃይለስላሴ ጊዜ ‹‹ዲፕሎማሲ›› በሚል ርዕስ የታተመ አነስተኛ መጽሐፍም ለንባብ አብቅተዋል:: በአሁኑ ወቅት በአብዛኛው ጊዜያውን የሚያሳልፉት በመጻፍ ነው::ከሚጽፉት መካከል አንዱ ግለ ታሪካቸውን ሲሆን፣ስለደቡብም ፖለቲካዊ ታሪክ በመጻፍ ላይ ይገኛሉ:: ቀጣዩ የመጽሑፍ ርዕሳቸውም ዲፕሎማቲክ ሂስትሪ ኦፍ ኢትዮጵያ የሚል ነው::
ራስን ሆኖ የትም መድረስ ይቻላል የሚል አቋም አላቸው፤ ባለቤታቸው ወደጀርመን ከእርሳቸው ጋር እንዲኖሩ ሲጠይቋቸው፤ ‹‹አንቺ አገር የተማረ ሰው ሞልቷል፤ እኔ ግን አገሬ ትፈልገኛለች›› ብለዋቸዋል:: ስለዚህ ወጣቱን የሚሉት ነገር ቢኖር ተደስተው መኖር የሚችሉት በአገር እንደሆነ ነው:: አገር ስትበልጽግና ሰላም ስትሆን ነው ክብር ያለው የሚለውን ወጣቱ መያዝ አለበት ይላሉ:: በሌላ አገር ሄዶ ሀብት ማፍራትም፤ ያሻንን መሸመትም እንችል ይሆናል ነገር ግን ባፈራነው ሀብት ደስታን መግዛት በጭራሽ አያቻለንም ሲሉም ምክር ይለግሳሉ፤ መከበር፣ መወደድም ሆነ መደሰት በአገርና በአገር ብቻ ነው::
አስቴር ኤልያስ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 16 ቀን 2013 ዓ.ም