ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት በርካታ ፈተናዎችን እየተጋፈጠች ትገኛለች። በአንድ በኩል ከአሸባሪው ህወሓትና ከጀሌዎቹ ጋር የሚደረገው ጦርነት፤ በሌላ በኩል ደግሞ ለዚህ አሸባሪ ቡድን እውቅና ለመስጠትና መልሰው ወደስልጣን ለማምጣት ከሚፈልጉ የውጭ ሃይሎች ጋር የሚደረግ ጦርነት ዋነኛ ግንባሮች ናቸው።
ለ27 ዓመታት በስልጣን ላይ የቆየው አሸባሪው የህወሓት ቡድን የኢኮኖሚ መዋቅሩን ሙሉ በሙሉ በመቆጣጠሩና በወቅቱም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ጭምር ይህንን የሚያስፈጽምበት የራሱን ኔትወርክ በመዘርጋቱ ቡድኑ ኢኮኖሚው ላይ የሚያደርሰው ጫና ከባድ እዲሆን አድርጎታል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስት በትግራይ ሲያካሂድ የቆየውን የህግ ማስከበር ዘመቻ ተከትሎ ፊት ለፊት ከገጠሙት የአሸባሪው ህወሓት ቡድን አባላት ጀርባ ያሉ ቡድኖች በመንግስት መዋቅር እና በንግዱ ማህበረሰብ ውስጥ በመደበቅ የኑሮ ውድነትን ለመፍጠርና በህዝብና በመንግስት መካከል አለመተማመንን በመፍጠር ህዝብን ለማሰቃየትና መንግስትን አጣብቂኝ ውስጥ ለመክተት የሄዱበት እርቀት ሰፊ ነው። በዚህ የተነሳ በአሁኑ ወቅት የኑሮ ውድነቱ በከፍተኛ ሁኔታ እየተባባሰ ይገኛል።
እንደሚታወቀው መንግስት በትግራይ የደረሰውን ሰብአዊ ቀውስ ተከትሎ ህብረተሰቡ ለከፋ ችግር እንዳይዳረግ ከፍተኛ የሰብአዊ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፤ አሁንም እያደረገ ነው። በዚህ ሂደት ውስጥ ጩኸታቸውን የሚያሰሙ የውጭ አካላት ግን ያላቸው ተሳትፎ ሲታይ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። በመሆኑም አብዛኛውን ድጋፍ እያደረገ ያለው መንግስት ነው። ይህ ደግሞ በመንግስት ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጫና ማድረጉ አይካድም።
በአንጻሩ የአሸባሪው ህወሓት ሃይሎች መንግስት ለትግራይ ህዝብ እያረገ ያለውን የሰብአዊ ድጋፍ ለማደናቀፍና በውጭ ማህበረሰብ ዘንድ መንግስት የትግራይን ህዝብ እያስራበ ነው ለማስባል የተለያዩ አሻጥሮችን ይፈጥራሉ። በሌላ በኩል ደግሞ እነሱም ራሳቸው ከህዝብ ውስጥ በመሸሸግ ከዚህ የመንግስት ድጋፍ ተካፋይ ይሆናሉ።
መንግስት ይህንን ሁሉ ሃላፊነት ወስዶ በዚህ ልክ የሚያደርገው ርብርብ በአጠቃላይ ሀገራዊ ኢኮኖሚ ላይ ጫና ማሳደሩ እንደተጠበቀ ሆኖ በውስጥ የተሰገሰጉት የአሸባሪው ህወሓት ሃይሎች ምርት በመደበቅ፤ አለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ፣ የኑሮ ውድነቱ እንዲባባስ ሲያደርጉ ይስተዋላል። ከዚህም ባሻገር በሀገሪቱ እየተከናወኑ የሚገኙ በርካታ የኮንስትራክሽን ስራዎች መኖራቸው ይታወቃል። ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባትም የሲሚንቶና የብረት ዋጋን በማናርና በመደበቅ ጭምር ኢኮኖሚያዊ አሻጥር እየፈፀሙ ይገኛሉ። ሰሞኑን በከፍተኛ ሁኔታ አላግባብ ተከማችቶ የተገኘው ብረትም ለዚህ አንድ ማሳያ ነው።
ያም ሆኖ ግን ህብረተሰቡ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን የተከሰተውን የኑሮ ውድነት መንስኤ ምን እንደሆነ በመረዳቱ በቀጥታ በመንግስት ላይ ከማማረር ይልቅ ከጎኑ በመሆን ችግሩ የሚፈታበትን መንገድ በመፈለግ እያደረገ ያለው አስተዋፅኦ የሚደነቅ ነው። በዚህም በተለይ የችግሩ ዋነኛ መንስኤ የአሸባሪው ህወሓት እና ተባባሪዎቹ ተግባር መሆኑን በመረዳቱ እና መፍትሄውም እነዚህን ሃይሎች መመከትና ሀገሪቱን ከዚህ ቡድን ነጻ ማውጣት መሆኑን በመረዳቱ ከመንግስት ጎን በመሰለፍ የበኩሉን ድጋፍ እያረገ ይገኛል።
በሌላ በኩል ደግሞ መንግስትም አሁን እየተፈጠረ ያለውን ህገወጥነት ለማስቆምና ህብረተሰቡ በዋጋ መናር እና በኑሮ ውድነት ችግር እንዳይጎዳ ለማድረግ ከፍተኛ ርብርብ እያረገ ይገኛል። ከነዚህም ውስጥ አንዱ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በፌዴራል መንግስት የሚመራና የኢኮኖሚ አሻጥሮችን በበላይነት የሚመራና የሚከታተል ግብረሃይል አቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱ ነው።
ይህ ግብረሃይል የኢኮኖሚ አሻጥሮችን በመፍጠር ያለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በሚያደርጉ፣ ሰው ሰራሽ የምርት አቅርቦት እጥረት በመፍጠር የህዝቡን የተረጋጋ ኑሮ ለማወክ ብሎም አገር ለማፍረስ በሚሰሩና በሚተባበሩ ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወሰድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ተናግረዋል።
ይህ ሃይል በተለይም በአሁኑ ወቅት በየቦታው ተሰግስገው ህዝብን ለማማረርና በመንግስት እና በህዝብ መካከል ቅራኔ ለመፍጠር የሚሯሯጡ አካላትን ለመቆጣጠርና ህብረተሰቡም ያለአግባብ በሚፈጠሩ የዋጋ ንረቶች እንዳይጎዳ ለማድረግ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። ያም ሆኖ ግን በአሻጥሩ ላይ ያሉ አካላት እጃቸው ረጅምና ለብዙ ዘመናት በዚህ ህገወጥ ተግባር ውስጥ የኖሩ ሴረኞች ናቸው። ከዚህም አልፎ መዋቅራቸውን እስከ ህብረተሰቡ ድረስ የዘረጉና በሌብነት ውስጥ ረጅም ልምድ ያካበቱ ናቸው። በዚህ የተነሳ በአንድ ግብረሃይል ብቻ ችግሩን መፍታት ከባድ ነው።
በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የገጠመንን ችግር ለመፍታት በአንድ በኩል ከመንግስት ጎን በመቆም በአሸባሪው ህወሓትና በውስጥና በውጭ አጋሮቹ የተከፈተብንን ጦርነት በድል መወጣት፣ በሌላ በኩል ደግሞ ውስጥ ሆነው ለአሸባሪው ህወሓት ድጋፍ የሚያደርጉ የውስጥ ባንዳዎችን ለመመከት በሁሉም መንፈስ ዝግጁ መሆን አስፈላጊ ነው። በመሆኑም በማንኛውም አጋጣሚ አለአግባብ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ገበያውን ለማናጋት የሚያደርጉ አካላትን፤ በአጠቃላይ ከፋፋይ አስተሳሰቦችን በህብረተበሱ ውስጥ በመንዛት ሀገርን ለማፍረስ የሚጥሩ ሃይሎችን ለመመከት ከመቼውም ጊዜ በላይ በጋራ የምቆምበት ወቅት አሁን ነው!
አዲስ ዘመን ነሐሴ 16 ቀን 2013 ዓ.ም