በዓለም አቀፍ ደረጃ ታዋቂና በአትሌቲክስ ስፖርትም ስኬታማ የሆኑ አትሌቶች አቅማቸውን የሚያሟሹት በታዳጊና ወጣቶች ቻምፒዮናዎች ላይ ነው። ኢትዮጵውያን አትሌቶችን ጨምሮ በስፖርቱ ስማቸው የናኘ ጀግና አትሌቶችም በእነዚህ ውድድሮች አልፈዋል። እድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ለሆኑ ተተኪና ተስፋ ያላቸው አትሌቶችም አቅማቸውን ለመፈተሽ እንዲረዳቸው የዓለም አትሌቲክስ መሰል ውድድሮችን ያዘጋጃል።
እአአ ከ1986 ጀምሮ በዓለም አትሌቲክስ አዘጋጅነት የሚካሄደው ከ20 ዓመት በታች የዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮና ዘንድሮ ለ18ኛ ጊዜ በኬንያ አስተናጋጅነት በመካሄድ ላይ ይገኛል። በየሁለት ዓመቱ የሚካሄደው ይህ ቻምፒዮና ዓምና በዓለም አቀፉ ወረሽኝ ኮቪድ 19 ምክንያት ለአንድ ዓመት የተራዘመ ሲሆን፤ ከቀናት በፊት ናይሮቢ ላይ ተጀምሮ ዛሬ 4 ኛ ቀኑን አስቆጥሯል። ለ5 ቀናት በድምቀት ሲካሄድ የቆየው ይህ ቻምፒዮና ለቀጣዩ አስተናጋጅ ሃገር ኮሎምቢያ አስረክቦ ነገ የሚጠናቀቅም ይሆናል።
በተለያዩ ከተሞች እየተዘዋወረ የሚደረገው ውድድሩን የማሰናዳት እድል ዘንድሮ በስፖርቱ ስኬታማ ለሆነችው ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሀገር ኬንያ ሲሰጥ በአህጉሩ የመጀመሪያው ነው። በቻምፒዮናው አሜሪካ በውጤት የበላይ ስትሆን ኬንያ ትከተላታለች። በቀጣይ ሀገራቸውን ለማስጠራት በርካታ ታዳጊና ተተኪ አትሌቶች ስፖርቱን የሚከውኑባት ኢትዮጵያም በቀዳሚነት ከሚያጠናቅቁ ሀገራት መካከል የምትጠቀስ ናት።
ከዚህ ቻምፒዮና ኃይሌ ገብረስላሴ፣ አሰፋ መዝገቡ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ፋጡማ ሮባ፣ ጌጤ ዋሚ፣ ገብረእግዚአብሄር ገብረማርያም፣ ማርቆስ ገነቲ፣ ስለሺ ስህን፣ ጥሩነሽ ዲባባ፣ መሰረት ደፋር፣ ገንዘቤ ዲባባ፣ ዮሚፍ ቀጄልቻ፣ ሙክታር እድሪስ፣ ሰለሞን ባረጋ፣… የመሳሰሉ አትሌቶች አቅማቸውን ፈትሸው ሀገር ለማኩራት በቅተዋል። በተለያዩ ርቀቶች ክብረወሰኖችን በመስበርና ፈጣን ሰዓት በማስመዝገብም ውጤታማነታቸውን ማረጋገጥ ችለዋል።
እየተካሄደ በሚገኘው ውድድርም ኢትዮጵያ በተለያዩ የማሰልጠኛ ተቋማት፣ አካዳሚና ክለቦች የተወጣጡ ወጣት አትሌቶችን በማሳተፍ ላይ ትገኛለች። አትሌቶቹ የሚካፈሉትም ከአጭር ርቀት ማለትም ከ400 ሜትር ጀምሮ የረጅም ርቀቶች፣ በ3ሺ ሜትር መሰናክል እንዲሁም በእርምጃ በስምንት የውድድር እርቀቶች መሆኑም ታውቋል። 10 ወንድ እና 15 ሴት በአጠቃይ 25 አትሌቶችን የያዘው ቡድኑ ለአንድ ወር ያህል ሆቴል ገብቶ ልምምድ ሲያደርግ ቆይቶ በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው ሳምንት መጀመሪያ ወደ ናሮቢ ተሸኝቷል። ቡድኑ በሆቴል ቆይታውም የልምምድና የውድድር ስፖርት ትጥቆችን ያገኘ ሲሆን፤ የኮቪድ 19 እና የስፖርት አበረታች ቅመም ተጠቃሚነት ምርመራም አከናውኗል።
በዚህ ውድድር ላይ የሚካፈሉት ኢትዮጵያውያን ወጣት አትሌቶች በዓለም አደባባይ አገራቸውን በድል ለማስጠራትና ለማስተዋወቅ ከመቻላቸውም ባለፈ ለዓለም አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች ልምድ እንዲቀስሙ ትልቅ አጋጣሚ ይሆንላቸዋል። በዚህም መሰረት የውድድሩ ድምቀት የሆኑት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ውጤት ያስመዘገቡት ገና ከጅምሩ ነው። በ3ሺ ሜትር አስደናቂ ብቃት በማሳየትና ተወዳዳሪዎቹን ከፍተኛ ብልጫ በማሳየት የረታው ታደሰ ወርቁ የወርቅ ሜዳሊያውን አጥልቋል። ወጣቱ አትሌት የገባበ 7:42.09 የሆነ ሰዓት ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቧል። አትሌት አሊ አብዱልመናን ደግሞ 7:44:55 በሆነ ሰዓት ተከትሎት በመግባት ለሀገሩ የብር ሜዳሊያ አስገኝቷል።
በወንዶች 5ሺ ሜትር የፍጻሜ ውድድር አትሌት ታደሰ ወርቁ ሁለተኛ በመሆን የብር ሜዳሊያ ሲያገኝ፤ ርቀቱን ያጠናቀቀበት ሰዓትም 13:20.65 ሆኖ ተመዝግቦለታል። ሌላኛዋ ሀገሯን በ3ሺ ሜትር በብቸኝነት የወከለችው አትሌት መልክናት ውዱ 9:00.12 የሆነ የግሏን ምርጥ ሰዓት በማስመዝገብ የነሀስ ሜዳልያ ባለቤት ለመሆን ችላለች። ትናንት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የተካፈሉበት በርካታ የማጣሪያ ውድድሮች እንዲሁም በ3ሺ ሜትር የሴቶች የፍጻሜ ውድድር የተካሄደ ሲሆን፤ ዛሬ እና ነገም የተለያዩ ርቀቶች በሁለቱም ጾታ ፍጻሜያቸውን ያገኛሉ።
ኢትዮጵያ እስከአሁን በተካሄዱት 17 የዓለም ከ20 ዓመት በታች አትሌቲክስ ቻምፒዮናዎች በ37 ወርቅ፣ 32 ብር እና 29 ነሃስ በድምሩ በ98 ሜዳልያዎች ከዓለም የደረጃ ሰንጠረዥ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ይህ ደረጃ ከአፍሪካ ሀገራት ጋር ሲወዳደር ደግሞ ሀገሪቷን ከኬንያ ቀጥሎ 2ኛ ደረጃ ላይ እንድትገኝ ያደርጋታል። ከተመዘገቡት ሜዳሊያዎች መካከል 49 የሚሆኑት ሜዳልያዎች በሴት አትሌቶች የተገኙ ሲሆኑ፤ 47ቱ ደግሞ በወንድ አትሌቶች የተቆጠሩ መሆናቸው ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
እአአ በ2018 ፊንላንድ ቴምፔሬ ላይ በተካሄደው 17ኛው ቻምፒዮና ላይ የተካፈለው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን 3 ወርቅ፣ 2ብር እና 4 ነሃስ በጥቅሉ 9 ሜዳሊያዎችን በማግኘት ነበር የተመለሰው።
ብርሃን ፈይሳ
አዲስ ዘመን ነሐሴ 15/2013